ጉማ- ፍትህ የሚገኝበት፤ ቂም በቀል የሚሻርበት ስርዓት

የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የሚመራበትና የሚተዳደርበት ቱባ ባህል፣ ልምድ፣ ወግና ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው:: በኑሮ ሂደትም እነዚህ ሲጠቀምባቸውና ሕይወቱን ሲመራበት የቆየው ባህልና ልምድ በማስቀጠሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገሩ አሁንም ድረስ እንደተጠበቁ ቀጥለው አንዳንዱ አካባቢዎች እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ::

የኦሮሞ ሕዝብ የሚያጋጥሙትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ሲመራበትና ሲተዳደርበት ከቆዩ ሥርዓቶች ውስጥ የገዳ ሥርዓት በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው:: በሌላ መልኩም ግጭት ሲገጥመው የሚፈታበት የራሱ የሆነ የግጭት አፈታት ሥርዓት አበጅቶ አሁንም ድረስ እየተጠቀመበት ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ::

ማኅበረሰቡ እየተጠቀመባቸው ካሉ ቱባ ባኅሎችና በጎ ልምዶች መካከል የግጭት አፈታት ስርዓት ተጠቃሽ ነው:: ይህንን ስርዓትም ግጭቶች ሲፈጠሩ ለመፍታት እየተጠቀመበት ኖሯል፤ አሁን ድረስ እየተጠቀመበት ይገኛል:: ይህ የግጭት አፈታት ሥርዓትም የሰውን ነፍስ ያጠፋ ወይም ሰው የገደለ ሰው የሚቀጣበት ሲሆን፤ ለሟችና ለወገኖች ደግሞ ፍትሕ የሚረጋገጥበትና ፍትሕ አግኝተው ካሳ እንዲካሱ የሚያደርግበት የእርቅ ሥርዓት የጉማ ሥርዓት አንዱና ዋነኛ ባሕል ነው::

የጉማ ሥርዓት የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ እየተጠቀመበት የመጣ የእርቅ ሥርዓት ቢሆንም በጊዜ ሂደት የተለያዩ የመንግሥታትና የሥርዓት ለውጦች ወቅት በተፈጠረ ጫና የተነሳ እየደበዘዘና እየተዳከመ ቢመጣም ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ማኅበረሰቡ ስርዓቱ እንዲቀጥልና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር አድርጓል:: የጉማ ሥርዓት በማኅበረሰቡ የአኗኗር ሂደት ውስጥ የሰላምና የእርቅ መሰረት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል:: በተለያዩ ምክንያቶች በሰዎች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት እና መጎዳዳት ሲኖር ወይም ሲፈጠር ሰላምና እርቅ ለማውረድ ጉማ ሥርዓት ትልቅ ሚና ሲጫወት የቆየና አሁንም ድረስ እየተሰራበት የሚገኝ ነው::

የጉማ ማውጣት ሂደቱም በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት የሚፈጸም ሲሆን የሀገር ሽማግሌዎች በተጎዳዱ አካላት መካከል ጣልቃ በመግባት ጉዳዩ በሽምግልና በመያዝ በእርቅ እንዲፈታ መፍትሔ የሚያደርጉበት ሂደት ያለው ነው:: በዚህም ሂደት የሰው ነፍስ ያጠፋ (የቀጠፈ) ወይም የአካል ጉዳት ያደረሰ ሰው ለተበዳይ እንዲከፈል (እንዲሰጥ) የተወሰነበት ካሣ ጉማ ተብሎ ይጠራል::

ጉማ የግጭት አፈታት ሥርዓት ካሳን በመክፈል የሚያደርግ እርቅ ነው:: ይህም በዘፈቀደ የሚፈጸም ሳይሆን በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለደረሰው ጉዳት ወይም የንብረት ውድመት የሚፈጸም ራሱን የቻለ ሥርዓት አለው:: የእርቁና የጉማ ሂደቱን በሀገር ሽማግሌ የሚመራ ሲሆን ማኅበረሰቡ የተቀበለውን የአካሄድ ሥርዓት ተከትሎ የሚፈጸም ነው::

ጉማ በጊዜ ሂደት ውስጥ እያደገ መጥቶ ከፍተኛ ሀብትና ንብረት ይያዝ እንጂ መነሻው ግን በእርቁ ዕለት ለሁለቱ ወገኖች ማለትም ለገዳይና ለሟች ወገኖች ለመብል የሚከፋፈል ወይም የሚሰጥ ሥጋ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ:: ይህም የሆነበት ምክንያት ሁለቱ ወገኖች የሚፈጸሙት እርቅ ከልባቸው እንደተቀበሎት ተደርጎ ስለሚቆጠር ነው::

ጉማ ሥርዓት የሚፈጸመው የሰው ሕይወት ሲጠፋና የአካል ጉዳት ሲደርስ ብቻ ሳይሆን ንብረት ላይም ጉዳት ሲደርስ እንደየደረጃው ታይቶ ተግባራዊ ይደረጋል:: ጉማ ለመክፈል ሥርዓቱ የሚያወቁ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች በጋራ ሆነው ግድያውን የተፈጸመበት ሁኔታ ካጣሩ በኋላ የችግሩን አስከፊነት የተመለከቱ ደረጃዎችን ያወጣሉ:: እንዲሁም የተፈጸመው የአካል ጉዳት ከሆነም በተመሳሳይ ሁኔታ የማጣራት ሥራ በመስራት ጉዳቱን አይነት በየደረጃዎች የሚያስቀምጡበት ሁኔታ አለ::

ችግሩ ከተፈጸመ በኋላ በሁለቱም ወገኖች በቂምና በቀል ተነሳሰተው ሌላ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ በማሰብ ነፍስ ያጠፋው ሰው (የገዳይ ወገኖች) ለተወሰነ ጊዜ ከአካባቢው እንዲሰወሩ (እንዲርቁ) በማድረግ መረጋጋት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ:: የሰው ሕይወት ያጠፋው ሰው (ገዳዩ) ደግሞ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገባ ይደረጋል:: አልፎ አልፎም ገዳዩ ወደ ማረሚያ ቤት ያልገባ ከሆነ ግን ሩቅ ወዳሉ ዘመዶቹ ዘንድ በመሄድ የሚደበቅበት ሁኔታዎች ይኖራሉ::

የሟች ወገኖች ወዲያውኑ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ዘንድ በመሄድ ስለጠፋው የሰው ሕይወት የሟች ወገኖችን የሚማጸኑበት ሂደት ይፈጸማሉ:: ሂደቱም እንደየሁኔታ በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ የሚቆይ ሊሆን ይችላል::

የጉማ ሥርዓት የሰው ነፍስ ያጠፋ ሰው ምክንያት የሚያጣራበት ሥርዓት አለው:: ይህም በተለያዩ መንገዶች ይፈጸማል:: ሆን ብሎ አውቆና አስቦበት የሰው ነፍስ ያጠፋ እና ሳይሰብ በድንገት የሰው ነፍስ ያጠፋ በሚል ተከፋፍሎ በተለያየ መንገድ ማጣራቶች ይደረጋሉ:: በተጨማሪም የሰው ነፍስ ያጠፋ ሰው ማጥፋቱን ያመነና ያላመነ መሆኑን የሚለይበት ነው:: ገዳይ ሆንብሎ አውቆና አስቦበት የሰው ነፍስ ያጠፋ እንደሆነ ተጣርቶ ቅጣቱ በዚያው ልክ ከፍ እንዲል ተደርጎ ውሳኔ ይወሰንበታል:: ሳያስብበት በድንገት የፈጸመው እንደሆነ ደግሞ የፈጸመውን በደል ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደጥፋቱ መጠን ቅጣት ይሆናል::

በጉማ ሥርዓት የሟች ወገኖች ያጡት ወገናቸውን በማሰብ እርቁን አልቀበልም ማለት አይችሉም:: በእርቅ ሥርዓቱ ወቅት የሟች ወገኖች እርቁን ለመቀበል እምቢ በማለት ምክንያቶችን ቢደረድሩም ፍጽም ተቀባይነት አያገኙም:: ምክንያቱም እርቅ እምቢ ማለት ማህበረሰቡ በተሰማማበት የእርቅ ሥርዓት አለመመራትና አለመተዳደር ከመሆኑ ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚያስወግዝና እርግማን የሚያስከትል ድርጊት ነው:: የተበዳይ ወገን አሻፈረኝ እርቁን አልቀበልም እምቢ የሚል ከሆነ ስለሚረገም ይህ እርግማን ደግሞ የተወለደው እንዳያድግ፤ የተዘራው እንዳይበቅል ያደርጋል ተብሎ በማኅበረሰቡ ይታመናል:: በመሆኑም እርቁን መቀበል እንደ ግዴታ ተደርጎ ይቆጠራል::

በሁለቱ ወገኖች መካካል እርቅ ከተፈጸመ በኋላ የሚከፈለው ጉማ አይነትም እንዲሁ የተለያየ ሊሆን ይችላል:: በጉማ በዋናነት የገንዘብና የከብት ካሳ ይከፈላል (ይሰጣል):: ይህም ካሳ ለሟች ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን ለሟች ወገኖችም ጭምር የሚከፋፈል ነው የሚሆነው:: ምክንያቱም የሟች ወገኖች በቂም በቀል ተነሳሳተው የገዳይ ወገኖች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸሙ የሚከፈለው ካሳ ለእያንዱንዱ ሰው እንዲዳረስ የሚደረግበት ሂደትም አለ::

በዚህ የሕይወት ካሳ አወሳሰን ላይ የሀገር ሽማግሌዎች የማይተካ ሚና ቢኖራቸውም በዋናነት ግን አባገዳዎች ትልቁን ድርሻና ስልጣን አላቸው:: ይህም የሚካሄደው ሁለቱም ወገኖች የተግባቡበት የሕይወት ካሳ ክፍያ ለአባገዳና ለአባቦኩ ለውሳኔ ያቀርባሉ:: ስምምነታቸው በሚገባ ከታየ በኋላ የተለያዩ ሥርዓቶች በመፈጸም እርቁ ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚያደረጉበት ሂደቶች ይፈጸማሉ::

የእርቁ ዕለት የሰው ሕይወት ያጠፋ ሰው (ገዳይ) የፈጸመው ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነና በፈጸመው ድርጊት ማዘኑንና መጸጸቱን በተለያየ መንገድ መግለጽ ይጠበቅበታል:: ይህንንም አሮጌ፤ አዳፋ (ቆሻሻ) አሊያም የተበጣጠሱ ልብሶችን በመልበስ፣ ፊቱን ጭቃ በመቀባት እና በመሳሳሉ ሁኔታ ይገልጻል:: አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ እጅ ወደኋላ ታስሮ እንደሚቀርብ ጭምር ይነገራል::

በእርቅ ሥርዓቱ ከሚፈጸሙት ሥርዓቶች መካከል በዋነኛነት ሳይጠቀስ የማይታለፈው የመሀላ ሥርዓት ይፈጸማል:: መሀላውም ሥርዓቱ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በበዳይና ተበዳይ መካከል ዳግም ጸብ እንዳይከሰትና እርቁን ለማጽናት በማሰብ ነው:: በመሀላው ደግሞ እንዲህ አይነት ነገር አልፈጸምም ከፈጸምኩ ደግሞ ይህ ይሁንብኝ ይደረግብኝ አይነት የሚሉ ሀሳቦችን የያዘ ነው:: እንዲህ አይነት ከባድ መሀላዎች ያሉ ስለሆነ መሀላው ካልተፈጸም የተናገረው ነገር እንደሚፈጸምበት ይቆጠራል:: መሀላው ከተፈጸመ በኋላ ሁለቱ ወገኖች መሀላውን በማሰብ ዳግም ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርግ ሲሆን፤ የሟች ወገኖች ይህ መሀላ ችላ ብለው መልሰው ወደ ቂም በቀል እንዳይገቡ ያደርጋል ተብሎም ይታመናል::

ከዚህ ቀጥሎም የጉማ አከፋፋል ጊዜና ሁኔታ ይስወናል:: የሰው ነፍስ ያጠፋው ሰው (ገዳዩ)፤ የተወሰነበትን የሕይወት ካሳ ለመክፈል በራሱ ካለው ንብረት ላይ መክፈል ቢችልም እንኳን ከራሱ ንብረት ላይ ብቻ እንዲከፍል አይፈቀድለትም:: ምክንያቱ ያጠፋው ነፍስ መመለስ ባይቻል እንኳን ጥፋተኛነቱን አውቆ ከልቡ እንዲሰማውና እንዲጸጽት የሚያደርጉ አካሄዶች መከተል ይጠበቅበታል::

በመሆኑም የሰው ሕይወት የቀጠፈው ሰው (ገዳይ)፤ በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ወጥቶ ወርዶ እና ለፍቶ ወገኖቹንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ስለጉዳዩ በመንገር ጉዳዩን እንዲያወቁ እያደረገ እንዳለም ይደረጋል:: በልመና ሂደቱም የሰው ሕይወት የቀጠፈው ሰው (ገዳይ)፤ ሁለት እጆቹ በስንሰለት ታስረው ከወገኖቹ ጋር በመሆን በገበያ ቦታዎች እና ሰዎች በተሰበሱበት ቦታ ሁሉ በመዞር ‹‹የሰው ሕይወት በእጄ ላይ ጠፍቶ ነው›› እባካችሁን እያለ ሰዎችን በመማጸን ይለምናል:: ይህ የሚሆንበት ምክንያትም የሰው ሕይወት ያጠፋው ሰው በድርጊቱ አብዝቶ እንዲጸጸትና እንዲቆጨው ለማድረግ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ለሌሎች እሱን ለሚመለከቱት ሰዎች የሰው ነፍስ ማጥፋት ኃጢያት መሆኑና ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ለማስገንዘብ በማሰብ ነው::

በገዳ ሥርዓት ከጦርነት ውጭ ያለአግባብ የሰው ሕይወት ያጠፋ ሰው ጉማ ካላወጣ ከማኅበራዊ ሕይወት እንዲያገለግል ይደረጋል፤ ስለዚህ በኦሮሞ ሥርዓት ጉማ መክፍል ግዴታ ነው:: የሚከፍለው ካሳ የጠፋው የሰው ሕይወት ዋጋ የሚተካ ተብሎ ሳይሆን በሁለቱ ወገኖች መካከል እርቅን እንዲኖር በማድረግ የተሰራው ኃጢያት ማስተሳሰሪያ እና የቀድሞ ዝምድና ወደነበረበት ይመልሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው::

ከእርቅ በኋላም በሁለቱም ወገኖች በዳይና ተበዳይ መካከል የዝምድና ሁኔታ ተጣርቶ ዝምድና ከሌላቸውና መጋባት የሚችሉ ከሆነ አንዱ ከሌላ ጋር በጋብቻ እንዲተሳሰር የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል:: ይህ የሚሆንበት ዋንኛ ምክንያትም በሁለቱ ወገኖች መሀል ያለው ጥላቻ በማራቅ ጥብቅ የሆነ ዝምድና በመፍጠር ትስስር እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ነው::

በተጨማሪም በጉማ እርቅ ሥርዓት የተወሰነ ካሳ ቢከፍል፤ ጉማ የሚሰጠው ለጠፋው ሕይወት ዋጋ ለመስጠት እንጂ፤ የሚከፈለው ካሳ የሚገኘው ሀብት ተፈልጎ አይደለም::

ይህ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የኦሮሞ ሕዝብ የግጭት አፈታት ሥርዓት ያለው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ነው:: ሥርዓቱ አሁን ላይ እንደሚታየው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም:: በመሆኑም ጠቀሜታው እንደማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ከፍተኛ በመሆኑ ሌላው ማኅበረሰብ ሊጠቀምበት የሚችል እንዲሆንና ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ በደንብ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያመላክታል::

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You