በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል-በማዕድን ልማት እየታየ ያለው ለውጥ

ከሰሩበት የማዕድን ዘርፍ አክባሪ ነው። የሰሩትን ያከብራል፤ ያስከብራልም። ትልቅ የልማት አቅም በመሆን ማገልገልም ይችላል፡፡ ማእድንን ማልማት ከተቻለ ሀገር የማእድን ውጤቶችን ከውጭ ከምታስመጣ ይልቅ በሀገር ውስጥ የማእድን ምርቶች መጠቀም፣ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብም ይበልጥ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች፡፡

በአንጻሩ በማእድኑ ካልተሰራበት ደግሞ ጠንቅ እስከመሆን ሊደርስ ይችላል፡፡ ጠላቶችን ከሩቅ ይጋብዛል። ማእድኑን በሕገወጥ መንገድ ለመጠቀም ሲሉ በሚመጡ የውጭ ኃይሎች በሚፈጠር ችግር የማእድን ሀብቱ የሚዘረፍ ከመሆኑ በተጨማሪ የሀገር ደህንነት ፈተና እስከመሆንም የሚደርስበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ማእድኑ በውጭ ኃይሎችና ሕገወጦች ቁጥጥር ስር እየዋለ መሄዱን ተከትሎ ባለ ማእድኖቹ ለበይ ተመልካችነት ይዳረጋሉ።

ባለ ማእድኖቹ ባለ ማእድን ላልሆኑቱ ጠባቂ፤ ውሎ አድሮም አስረካቢ ይሆናሉ። ለዚህም ነው ቱጃሩ ሮክ ፌለር የአፍሪካ ወርቅ በአግባቡ ተጠብቆ ይቆየን ዘንድ ራሳቸውን በትንሽ ሳንቲም (“እርዳታ እየሰጠን እንዳይሰሩ በማድረግ…” ማለቱ ነው) ማስጠበቅ አለብን ብሎ በተናገረው ታሪካዊ ስህተት ፈፅሞ በታሪክ ተወቃሽ ለመሆን የበቃው።

ዘላለም-አለሟን ተፈጥሮ የለገሰቻትን አንጡራ ሀብት እየተበዘበዘች ያለችው አፍሪካ ስለ መበዝበዟ ራሱ በዝባዡም የሚክደው አይደለም። ይህንን ከማረጋገጥ አኳያ፣ “በዓለም ላይ ካለው ወርቅ ግማሽ ያህሉ፤ ከአጠቃላይ በዓለም ላይ ካሉት ማእድናት አንድ ሶስተኛው የሚገኘው በአፍሪካ ነው” የሚለው የራሳቸው የፈረንጆቹ ጥናት ትክክል ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፤ ለዚህም በ2019 ብቻ 406ቢሊዮን ዶላር ያወጣ አንድ ቢሊዮን ቶን ማዕድን ከአህጉሪቱ ለገበያ ቀርቦ የነበረ መሆኑ በቂ ማሳያ ነው።

አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንዳመላከተው፤ ከአጠቃላይ የዓለም ማእድናት 30 በመቶ፤ ከዓለም ዘይት/ነዳጅ 12 በመቶ፤ ከዓለም የተፈጥሮ ጋስ ክምችት 8 በመቶ የሚሆነው ያለው በአፍሪካ ነው።

ከዓለም የማዕድን ክምችት (global mineral reserves) አኳያ ስትመዘን አንደኛ የሆነችው አፍሪካ፤ ይህን ከፍተኛ የማእድን ክምችቷን በአይነት ስንመለከትም 92% ፕሎቲኒየም፤ 56% ኮባልት፣ 54% ከብረት ጋር ውሁድ ሆኖ የሚገኝ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር (manganese) እና 36% ክሮሚየም ይይዛሉ። ማእድናቱ በአውሮፓውያን እጅጉን የሚፈለጉ ሲሆን፣ በተለይ አረንጓዴ ቴክኖሎጂን ለማምረት ያላቸው አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ከተፈላጊነታቸው አንፃር ተወዳዳሪ የላቸውም።

በተለይ የአህጉሪቱ ማእድናት ተቋም (Africa Mining IQ) ደርሼበታለሁ እንዳለው መረጃ፣ አህጉሪቱ በማዕድን ሀብቷ ምክንያት ሁሌም በውጪ ኩባንያዎች ትጎበኛለች፤ ኩባንያዎቹ ብዛታቸውና የተሰማሩበት ዘርፍ ሲታይም “776 የወርቅ፣ 180 የድንጋይ ከሰል፣ 108 ዩራኒየም ፣ 151 የአልማዝ , 113 የፕላቲኒየም እንዲሁም 89 የብረት ነክ ፕሮጀክቶች›› ተብለው ሰፍረዋል፡፡ በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 776 ፕሮጀክቶች ከብዛት አኳያ የመሪነቱን ስፍራ ይዘው እናገኛቸዋለን።

ስለ አጠቃላይ አፍሪካ ለመነሻ ያህል ይህን ካልን፣ ኢትዮጵያም ከፍተኛ የማዕድን መጠን ካላቸው የአህጉሪቱ ቀዳሚ አገራት ተርታ ስለ መገኘቷ ይገለጻል። ይህ የማእድን ሀብት ግን በተለያዩ ምክንያቶች እንዳለማ፣ አለመልማት ብቻም ሳይሆን በቅጡ እንዳልተጠናም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ባለፈው ዓመት (2023/5/19) አል ዐይን የተባለ ድረ-ገፅ ሚዲያ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ጉታ ለገሰን ዋቢ አድርጎ እንደ ዘገበው፣ ከሀገሪቱ የማእድን ሀብት እስካሁን ማወቅ የተቻለው “ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው፤ ሀገሪቱ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የማዕድን ሀብቷን ማወቅ” አልቻለችም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ “የማዕድን ሀብት ፍለጋና ጥናት ጉዞው ደካማ መሆን፤ ፍለጋው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፉ፣ የፍለጋ ስራው ሽፋን አነስተኛ መሆኑ ሲሆን፣ የሚካሄደው ልማትም ቢሆን ስራው ባህላዊ መንገዶችን ተከትሎ መካሄዱ ነው።

የስነ-ምድር መረጃዎችን የማግኘት ችግርን ለመፍታት በጂኦሎጅካል ኢንስቲትዩት፣ በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ‹‹ኦርየን አፕላይድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› በተባለ ተቋም መካከል የፍለጋ ስምምነት መፈረሙን ዳይሬክተሩ አስታውሰው፣ ይህ ኦርየን አፕላይድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተባለው የአሜሪካ ተቋም በዋናነት በሳተላይት የተደገፈ የስነ-ምድር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል። ስምምነቱ ማእድኑን በተለምዶ ከመፈለግ የሳተላይት ምስሎችን እየተጠቀሙ የት እንዳለ በአጭር ጊዜ መጠቆም ከተቻለ የፍለጋ ጊዜያችንን ያሳጥርልናል ይላሉ። ተዘጋጅተን ሀብቱን ቶሎ የማግኘት ፍላጎት ስላለን ለዚህ ግብዓት ይሆነናል ብለን ነው የተፈራረምነው” ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪ እና የትምህርት ቤቱ ዲን ምንያህል ተፈሪ (ዶ/ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከርሰ ምድሯ ከሦስት የአለት ዓይነቶች የተዋቀረ ነው፤ እነርሱም ኢግኒየስ፣ ሴድ መንታሪ እና ሜታሞርፊክ ይባላሉ። ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ዓይነቶች እንደሚገኙባት ይታመናል:: በሀገሪቱ በርካታ የማዕድን ዓይነቶች እንደሚኖሩ ፍንጮች እንደሚያመላክቱ ጠቅሰው፣ የት ቦታ፣ በምን ያህል መጠን ምን አለ የሚሉ ነገሮች በጥናት በውል ተለይተው እንዳልተቀመጡ ዶ/ር ምንያህል ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ በማእድን ሀብታቸው በእጅጉ ከሚታወቁ ክልሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ ነው፤፤ በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በፓርላማ ቆይታቸው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብትሄዱና ብትመለከቱ ወርቅ ሞልቷል፤ በሰፌድ • • • ያሉለት ክልል እንደ መሆኑ መጠን አካባቢው በማእድን በኩል ሁሉ በእጁ፤ ሁሉ በደጁ ነው።

በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባደረግነው ቆይታ የክልሉን የማእድን ልማት ስራ አስመልክቶ ያገኘነው መረጃም ይህንኑ አመላክቶናል፡፡ የክልሉ የማእድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል አህመድ በጽሕፈት ቤታቸው በተገኘንበት ወቅት በሰጡን ማብራሪያ እንዳሉትም፣ ክልሉ በማእድን ሀብት የበለፀገ ነው።

የቢሮ ኃላፊው እንደተናገሩት፤ ከአምስትና ስድስት ዓመት (ከለውጡ) በፊት የነበረው የማእድን አስተዳደርና አጠቃቀም ሁኔታ ከአሁኑ ጋር እጅጉን ይለያያል። ከለውጡ በፊት ክልሉ ማእድንን የመምራትም ሆነ ማስተዳደር መብት አልነበረውም። በተወሰኑ ሰዎች ነበር የሚዘወተረው።

የአጠቃቀም ፖሊሲም ሆነ መመሪያና ደንብ የማውጣትና ባወጣው የሕግ ማእቀፍ መሰረት የማስተዳደር ሙሉ ኃላፊነትን ክልሉ ያገኘው ከለውጡ በኋላ መሆኑን አስታውቀው፣ አሁን ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ችሎ፣ በራሱ እቅድ እየተመራ የማእድን ሀብቱን እያስተዳደረ፤ ለዜጎችም የስራ እድልን እየፈጠረ እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ ይገኛል። ለብሄራዊ ባንክም ከድሮው በተሻለ መጠን ገቢ እያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዛሬ በክልሉ የተለያዩ ማእድናት በክልሉ አመራር ሙሉ አስተዳዳሪነት እየለሙ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ኳርትስ፣ ግራናይት፣ እምነበረድ እና ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩባቸው ካሉና ባለ ሀብቶች እያለሟቸው ከሚገኙት ማእድናት መካከል ናቸው ብለዋል።

‹‹በክልሉ የተደረሰባቸው፣ የታወቁና ያልተደረሰባቸው፣ ገና በጥናት ይደረስባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ጋር ተዳምሮ በርካታ ማእድናት አሉ። ክልሉ በማእድን የበለፀገ ነው›› የሚሉት የማእድን ልማት ቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹የሰላም እጦት የፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ እነሱን በመቋቋም በዘርፉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ከእነዚህ ስራዎች መካከልም አንዱና ተጠቃሹ በወርቅ ማእድኑ ዘርፍ የተሰራው መሆኑንም ገልፀዋል። ወርቅ አምራቾችን በተለያዩ ደረጃዎች በመመደብ እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ካሚል፣ በግለሰብ ደረጃ በተበታተነ መልኩ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ወጣቶች በማደራጀትና ማህበር እንዲመሰርቱ በማድረግ በባህላዊ መንገድ በወርቅ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ተደርገዋል ይላሉ። በዚህ አሰራርም ከፍተኛ ለውጥና ውጤት ተገኝቶበታል ነው ያሉት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ባለ ሀብቱ በዘርፉ እንዲሰማራ በማድረግ በኩልም እየተሰራ ሲሆን፣ ባለ ሀብቱ ብቻውን እንዲሰራ ከማድረግ ይልቅ የ70/30 አሰራርን በመዘርጋት ወጣቱን እንዲያሳትፍ፣ ማሽነሪዎችና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች ከባለሀብቱ ወጣቱ በጉልበቱና ባለው እውቀት ድርሻ እንዲኖረው በማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማእድን ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው የሚሉት የቢሮ ኃላፊው ይህም እያደገ በመምጣት ላይ መሆኑንም ይናገራሉ። በ2014 ዓ•ም ሁለት ኩንታል ከ100 ግራም የነበረው ከክልሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት፤ በ2015 ዓ•ም ወደ 4 ኩንታል ከ800 ግራም አድጓል ሲሉ ገልጸዋል። ይህ የመጣው ለውጡን ተከትሎ ክልሉ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ማእድናት ላይ የማስተዳደር መብትን በመጎናፀፉ መሆኑን አመልክተው፣ የሰላም ችግር ባይኖር ኖሮ ከዚህም በላይ መስራት ይቻል እንደነበርም አስታውቀዋል።

ከማእድን ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በተመለከተም ዋናውና ቁልፉ ችግር፣ ትልቁ ፈተና የጥቁር ገበያ ጉዳይ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው አመልክተዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በርካታ ኪሎ ግራም ወርቅ በጥቁር ገበያው በኩል ይወጣል። ጥቁር ገበያው ከመንግስት በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ልዩነት ስላለው ወርቅ አምራቾቹ ወደዛ የመሄድ አዝማሚያ ያሳያሉ። ይህ በከፍተኛ ደረጃ ችግር እየሆነ ነው። በተለይ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የማዘዋወር ፍቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ይህንን ስራ እየሰሩ መሆናቸው ነው፡፡

አቶ ካሚል በክልሉ በጥቁር ገበያው ተሰማርተው ከተገኙ 10 ሕገወጦች መካከል 8ቱ የማዘዋወር ፍቃድ ያላቸው ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህን ችግር በክልል ደረጃ ለመቆጣጠርና ስርአት ለማስያዝ እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ከማገድ ጀምሮ ማስጠንቀቂያ መስጠት ድረስ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

በማእድን ልማቱ ዘርፍ ሊቀረፉ የሚገባቸው ሌሎች ችግሮች እንዳሉም ጠቁመው፣ በክልሉ ማእድንን ለማልማት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመኖር እንድ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እስከ 30 ሜትር ድረስ በባህላዊ አሰራር እየተቆፈረ ማእድን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

ማእድን አምራቾቹ ለማጠቢያ የሚጠቀሙበት ኬሚካል (የሜርኩሪ ዝርያ) በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑንም ጠቅሰው፣ ዘርፉ በተሟላ እውቀት አለመመራቱና የመሳሰሉት ችግሮች የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት በፌዴራል ደረጃ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የማእድን አጠቃቀም መመራት ያለበት ምን ጊዜም በሕግና በሕግ ብቻ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚሁ ከማእድን ልማትና ምርት ጋር በተያያዘ አምቡዱሪዩ ወረዳ፣ ሆዴ ቀበሌ ወደሚገኘው ወርቅ ማምረቻ በመሄድ የአብዱልባስጥ ወርቅ አዘዋዋሪ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አልበይድ ሆጀሌን በፅህፈት ቤታቸው አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸውም ዘርፉ አዋጭ እንደሆነ፤ ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠረ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ በሚያገኙት ገንዘብ ማህበራቸውን ከማጠናከርም አልፈው ለወደፊት የቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችል መናፈሻ (የአምቡዱሪዩ ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ድርጅት መናፈሻ) እየገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለመናፈሻው አገልግሎት የሚውሉ የዱር እንስሳትንም እያላመዱ ስለ መሆናቸው ገልጸው፤ በክልሉ የከተማ ልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አንዳንድ ችግሮች፣ ለምሳሌ ማጠቢያ ማሽን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማቅረብ የሚያግዛቸው አካል ካለ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ቀደም ሲል በተሳሳተ ግንዛቤ ወደ ጫካ በመግባትና ከጸረ ሰላም ቡድኖች ጋር በመቀላቀል የራሱን ሕዝብ ሲጎዳ እንደነበረ የሚናገረው ወጣት በሽር አሸሪፍ፤ በክልሉ መንግስት የተደረገውን የሰላም ጥሪ በመቀበል፤ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሶ በመደራጀት በስፍራው በባህላዊ ወርቅ ማንጠር ስራ ላይ መሰማራቱን ነግሮናል፡፡ የክልሉ መንግስት እነሱን በዚህ መልኩ በማደራጀት ወደ ስራው እንዲገቡ በማድረጉ ደስተኛ መሆኑን አመልክቶ፣ ዛሬ ከራሱም አልፎ ለቤተሰቦቹ ሳይቀር ቤት በመስራት ከስራው በሚገባ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝ አስታወቋል።

ግርማ መንግሥቴ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You