በኢትዮጵያ በተለያዩ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት ለበርካታ ዓመታት በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት ፣እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ በቅርቡ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል፡፡
የአዋጁ መውጣት የሀገሪቱንና ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍና አሕጉራዊ ስምምነቶች የተረጋገጡት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እና ተግባራዊ ለማድረግ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ጉልህ የመብት ጥሰቶችን ምንነት በግልጽ መለየት እና ለእርቀ-ሰላሙም አስፈላጊ መሆኑ በመንግስት በኩል ታምኖበታል፡፡
መንግስት አዋጁን ለማውጣት የደረሰበት ውሳኔ በደል ሲፈጸምባቸው የኖሩት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለበርካታ አመታት የ‹‹ብሄራዊ እርቅ›› ያለህ እያሉ ሲያነሱ ለቆዩት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፡፡
ይህ ጉዳይ አስከ አሁንም ድረስ የሚነሳ እንደመሆኑ የመንግስት እርምጃ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማስፈን የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
በመሰረቱ ኢትዮጵያ ካሏት ባህላዊ እሴቶች አንዱ እርቀ-ሰላም ነው፡፡ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረን ጉዳይ በመመልከት በ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› በሚል የኢትዮጵያውያን ባህል ይፈታል፡፡ በዚህም መግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር ደም የተቃቡ እና በነፍስ የሚፈላለጉ ሰዎች በእርቀ-ሰላም እንዲስማሙ በማድረግ ተጨማሪ ቀውስ እንዳይከሰት ሲያደርግ ኖሯል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው እርቅ ደም ያደርቅ የሚባለው፡፡
በሀገሪቱ እርቀ-ሰላም በሚያዝበት ሽምግልና ላይ ከፍተኛ እምነት በመኖሩም ፍርድ ቤት የደረሰ የባልና ሚስት ጉዳይ በቅድሚያ በሽምግልና እንዲታይ ለማድረግ ወደ ሽማግሌዎች ይላካል፡፡ ጉዳዩ ከሽምግልና በፊት በፍርድ ቤት ውሳኔ ቢያገኝ ሊከተል የሚችለውን የሀብት መከፋፈልና የቤተሰብ መበተን እርቁ ያስቀራል፡፡
በመሰረቱ እያንዳንዱ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል፡፡ በፍርድ ቤት የሚታየው እንዳለ ሆኖ በእርቅ ማለቅ የሚችለውን በእርቅ መጨረስ የፍትህ ተደራሽነትን ያሰፋል እንጂ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ አይኖርም፡፡ ህዝብ የእርቅ ያለህ ሲል ደግሞ ጉዳዩን በእርቀ-ሰላም ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡
ዋናው ጉዳይ ለእርቁ ሲባል በሽምግልና ላይ የሚቀመጡት ሰዎች ገለልተኛ እንዲሁም ተሰሚነት እና ልምዱ የሌላቸው መሆናቸው ላይ ነው፡፡ የህግ ባለሙያዎችም የዚህ አይነት ችግር የሚያጋጥም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ገለልተኛና ልምድ ያለው ሽማግሌ ሲኖር እርቀ-ሰላም የማይፈታው ችግር የለም፡፡
የሀገሮችን ተሞክሮም ማጤኑ ይጠቅማል፡፡ ደቡብ አፍሪካ እና ርዋንዳ በብሄራዊ እርቅ በዜጎቻቸው ላይ የተፈጸመውን ግፍ ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ ፈትተው በሰላምና ልማት ጎዳና ላይ እየተጓዙ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከባህላዊ እሴቷ በተጨማሪ ከእነዚህ ሃገራት መልካም ተሞከሮ መውሰድ ይኖርባታል፡፡
አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ ‹‹ብሄራዊ እርቅ›› መደረግ አለበት ሲባል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ የባልና ሚስት ጉዳይ አይደለም፤ በሽምግልና ሊታይ አይገባውም እያሉ የእርቅን ፋይዳ ሲያኮስሱ ኖረዋል፡፡ ይህ የትም አያደርስም፡፡ ችግሩ በምንም ይሁን በምን መፍታቱ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡
የህግ ባለሙያዎች በፍርድ ቤት ከሚሰጥ ፍትህ ይልቅ በእርቀ-ሰላም የሚያልቅ ጉዳይ በጠላትነት ላለመተያየት ትልቅ አማራጭ እና የሚያስገኘው እርካታም ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዕርቀ-ሰላም የሚያልቁ ጉዳዮች የሰዎችን ግንኙነት አያሻክሩም፡፡ ሊሂቃን በፈጠሩት ችግር ምክንያት ምንም በማያውቀው የህብረተሰብ የተፈጠረው ቅሬታ ሊሽር የሚችለው በእርቀ-ሰላም ነው፡፡
የእርቀ-ሰላም ፋይዳ ይህን ያህል እስከሆነ ድረስ መንግስት የተከተለው አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል፡፡ አዋጁ ገና ያልጸደቀ እንደመሆኑም ግብአት በማከል ውጤታማ ተግባር የሚከናወንበትን መደላድል ከወዲሁ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ብሄራዊ እርቅ እንዲካሄድ አጥብቀው ሲጠይቁ የነበሩ ወገኖች፣በህዝብ ላይ የተፈጸመ በደልን ይፋ ለማውጣት እና ይቅርታ ለመጠየቅ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የእርቅ ጉዳይ ውጤታማነት የሚወሰነው አንድም ጉዳዩን በሚይዙት ሽማግሌዎች እንደመሆኑ እርቀ-ሰላሙን የሚያስፈጽሙ አካላት አሰያየም ላይም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
ዘመኑ የእርቅና የይቅርታ እንደመሆኑም ለእርቀ-ሰላም የሚከፈለው ዋጋ ሁሉ መከፈል ይኖርበታል፡፡ መንግስት የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በማውጣት ትልቁን እርምጃ ወስዷል፡፡ ባለፉት አመታት በዜጎች ላይ በደል የፈጸሙ አካላት ጥፋት መስራታቸውን ይፋ በማድረግ ይቅርታ ለመጠየቅ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
በእርቀ-ሰላሙ የሚታዩ እና የማይታዩ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መታየት የሚችሉትን ማየት መቻል በራሱ አንድ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡በተለይ ምንም በማያውቁ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው መቃቃር እንዲወገድ የእርቁ ፋይዳ ከፍተኛ እንደመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መረባረብ ይኖርበታል፡፡ እርቅ ደም ያደርቅ!