ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው:: የፋይናንስ ስርዓቱም በቴክኖሎጂ መመራት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል:: በአሁኑ ሰዓት በርካታ ነገሮች ወደ ዲጂታል እየተቀየሩ ነው:: የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መበራከትን ተከትሎ አብዛኛው ግብይት በዲጂታል እየተሳሰረ መጥቷል::
የዲጂታል ስርዓት መስፋፋት ደግሞ አገልግሎት አሰጣጥን በማቅለል የተጠቃሚዎችን እንግልትን በመቀነስ ፋይዳው የጎላ ነው:: በተለይ የፋይናንስ አገልግሎቶች ዲጂታል መሆናቸው ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጭምር በቀላሉ ግብይትና ክፍያ እንዲፈፅሙ በማስቻል ጊዜንም እየቆጠበ ይገኛል::
ይህም ሆኖ ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ሰዎች ትክክለኛ ማንነታቸውን ደብቀው ወንጀል በመፈፀም የተገኘውን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስለው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ወደ ፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ለማስገባት ጥረት ሲያደርጉ ይታያል::
ገንዘብ ሕግን በተከተለ መልኩ ሲቀመጥና የአወጣጥ ስርዓቱም ይህንኑ የተከተለ ሲሆን የፋይናንስ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው ማለት እንችላለን:: ከዚህ በተቃራኒው በቂ የሆነ የፋይናንስ ደህንነት መሰረተ ልማት አለመኖርና እንዲሁም ደግሞ የባንኮች የውስጥ ሰራተኞች ታማኝነት መጉደልና በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ባንኮች የፋይናንስ ደህንነታቸው ስጋት ውስጥ ሊገባ ይችላል::
ብሄራዊ ባንክ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ሪፖርት የሀገሪቱ ባንኮች በበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ስልቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል:: በዚህ ምክንያትም በሀሰተኛ ሰነዶችና በሌሎች የማጭበርበር ድርጊቶች ባንኮች በአንድ ዓመት ውስጥ 1 ቢሊዮን ብር ማጣታቸውን የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል::
ከዲጂታል ፋይናንስ ወይም ከኤሌክትሮኒክስ ፋይናንስ ጋር ተያይዞ የሚፈፀም የማጭበርበር ድርጊትን ለማቆም በዋናነት የፋይናንስ ተቋማቱ/ባንኮች የውስጣቸውንና የደንበኞቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ ጥብቅ አጥር መፍጠር አለባቸው:: ይህ ካልሆነ ግን ለአደጋ እንደሚጋለጡ የዘርፉ ምሁራን ደጋግመው ሲናገሩ ይሰማል::
የባንኮች የፋይናንስ ደህንነት የተጠበቀ ካልሆነ በቅድሚያ ራሳቸው ባንኮቹ ተጎጂ ይሆናሉ:: ከዚያ መለስ ሲል ደግሞ ደንበኞችንም ሊያጡ ይችላሉ:: በዚህ ምክንያትም አንድ ባንክ ስራ እስከማቆምም ሊደርስ ይችላል:: የባንኮች አስፈላጊ ነገር መልካም ስራቸውና ዝናቸው ነው:: አንዴ ስማቸውና ዝናቸው ከጠፋ ከገበያ ወጡ እንደማለት ነው::
ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ከትንሽ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የማጭበርበር ድርጊት ድረስ ሰነድን ጨምሮ በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የብር ማጭበርበሮችም ይፈፀሙበታል:: ይህ ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ደህንነት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችንም ያስከትላል:: ሀገሪቱን የሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ ተቋማት የሚባሉት ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው:: እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ ሀገርን እንዲያንቀሳቅሱ ደግሞ ደንበኞቻቸው የሀገሪቱ ዜጎች አንዳይከስሩና እንዳይጎዱ ጥንቃቄው የበረታ መሆን አለበት:: በማጭበርበር ምክንያት ዜጎች ሲከስሩ በሀገሪቱ ላይ የሚያመጣው ኪሳራ ከበድ ይላል::
ከአሁን በኋላ እያንዳንዱ ስልክ የያዘ ሰው ከባንኮች ጋር ግንኙነት የሚፈጥርበት ሁኔታ ተመቻችቷል:: እያንዳንዱ ሰው የባንኮች ቅርንጫፍ ሆኖ የማገልገል ተግባር የጀመረበት ወቅት ነው:: 70 ሚሊዮን የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ካሉ 70 ሚሊዮኖቹም ከባንኮች ጋር ስርዓት ጋር ተሰናስነዋል ማለት ነው::
በእርግጥ ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ጥሬ ገንዘብን ይዞ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ይበልጥ ምቹ እንደሆነ ታምኖበታል:: በኢትዮጵያም ባለፉት ሁለት ዓመታት እና ሶስት ዓመታት የገንዘብ ዝውውሩ ቴክኖሎጂን ተከትሎ ተግባራዊ እየተደረገ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው:: ጠቀሜታውም የገዘፈ ነው::
መንግስት ለገንዘብ ሕትመት በየጊዜው የሚያወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ከማስቀረት ረገድ እንዲሁም ጥሬ ገንዘብን ይዞ መንቀሳቀስ ተገቢ አለመሆኑን የሚያስረዳ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው:: ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ሀገሪቱን ከዓለማቀፍ የንግድ ስርዓት ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስራትና ኢኮኖሚውን አንድ እርምጃ የሚያሳድግ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይመሰክራሉ::
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት ለመጀመሪያ ጊዜ የጥሬ ገንዘብ በልጧል:: የፋይናንስ ስርዓቱም ወደ ዲጂታል አሰራር እየተቀየረ ነው:: የወረቀት ብር ዝውውር በእጅጉ እየቀነሰ በዲጂታል መልኩ ግብይትና ክፍያ መፈፀም እየተለመደ ነው::
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ መሰረት በ2016 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን በላይ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ገንዘብ ማንቀሳቀስ ተችሏል:: ይህ የዲጂታል ኢኮነሚ የገንዘብ ስርዓቱን ከማዘመን አንፃር ያበረከተው ፋይዳ ከፍተኛ ተብሎለታል:: የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ባሉበት ስፍራ ሆነው በቀላሉ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ መቻላቸው ጠቀሜታውን ገዘፍ ያደርገዋል::
በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ እየተደረጉ ያሉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ በመምጣት ላይ ናቸው:: ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የባንክ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን ተግባራዊ ያደረገው መመሪያ አስተዋፅኦ ተጠቃሽ ነው:: ለግለሰብ እስከ 50 ሺህ ብር ዝቅ ብሏል፣ለኩባንያዎች እስከ 1 መቶ ሺህ ብር እንዲሆን ተወስኗል::
ከዚህ በላይ ጥሬ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ከተፈለገ ግን ዲጂታል የገንዘብ አገልግሎትን መጠቀም እንደሚገባ መመሪያው ያዛል:: ይህ ደግሞ ለጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ መቀነስ አይነተኛ ሚና ተወጥቷል:: ገበያው ላይ፣ የግብይት ሂደትና ዝውወር ላይ ሁሉም ሰው በዲጂታል ገንዘብ ሲጠቀም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው::
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው በሞባይል ባንኪንግ ብቻ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር ገንዘብ ማዘዋወር ችሏል:: በተመሳሳይ ሌሎች ባንኮችም በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ መጠን እያሳደጉና አብዛኛው የገንዘብ እንቅስቃሴ በዚሁ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት እያካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል::
ታዲያ ይህን መሰል የገንዘብ ዝውውር ከዓለማቀፉ ንግድ ስርዓት ጋር የበለጠ የማቀራረብ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ:: ዲጂታል የባንክ አገልግሎት በዚህን ያህል ደረጃ እያደገ መምጣት ባንኮችና ሌሎች አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ገቢ እየጨመሩ መሆኑ ይታመናል::
በዚህ ዘመናዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ደንበኞች እያደገ መሄድ የገንዘብ እንቅስቃሴው እንዲጨምር እያደረገው ነው:: ቴክኖሎጂን አንድ የሕይወት አካል ማድረግ መቻሉ መንግስት ለብር ህትመት የሚያወጣውን ወጪ በመቀነሱና ለምዝበራዎች የሚውለውን ገንዘብ በስርዓት እንዲመራ ያደርገዋል::
የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ለተገልጋዩም ሆነ ለባንኮች እጅግ ጠቃሚ መሆኑ አነጋጋሪ ጉዳይ አይደለም:: ተገልጋዩ በቀላሉ ገንዘብ በማንቀሳቀስ እና ክፍያዎችን መክፈል እያስቻለው ነው:: ይህ አሰራር ጥቅሙ ቢያመዝንም ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን የፋይናንስ ተቋማትን ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል:: ይህን ስጋት ለመከላከልና በሳይበር ጥቃት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ደግሞ ሀገራትም ሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የሳይበር ደህንነታቸውን ማሻሻልና ማዕቀፍ ማበጀት እንደሚገባቸው ይመከራል::
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓቱ ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ተነድፎ እየተሰራ ይገኛል:: አንዳንድ ጊዜ የፋይናንስ ስርዓቱ የማጭበርበር ችግሮች ሲገጥሙት ይስተዋላል:: ባለፈው ጊዜ በንግድ ባንክ ላይ የደረሰውን ማንሳት ይቻላል:: በወቅቱ የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ አቤ ሳኖ የደረሰውን የገንዘብ ማጭበርበር ተግባር ለመቆጣጠር በፍጥነት ለመቆጣጠር ለመገናኛ ብዙሀን መግለፃቸው ይታወሳል::
ይህ ለአብነት ያነሳነው ጉዳይ ቢሆንም የፋይናንስ የማጭበርበር ተግባር በተለይም በባንክ ስርዓቱ ላይ ትልቅ እንቅፋት እየሆነ የመጣው ሕገወጥ የሀዋላ አገልግሎት የሚጠቀስ መሆኑን የባንክ ባለሙያዎች ይናገራሉ:: ከጥቁር ገበያ ተገዝቶ ወደ ዲያስፖራ አካውንት የሚቀመጥ ገንዘብ ወንጀል ሲሆን ሶስት ወንጀሎችንም አካቶ ይዟል::
አንደኛ ሀሰተኛ የመንግስት ሰነድ ማዘጋጀት በራሱ ወንጀል ነው:: ሁለተኛ ሰነድ ማዘጋጀት ማጭበርበር ነው:: ሶስተኛ ከጥቁር ገበያ ዶላሩን ገዝቶ ወደ አካውንት ማስገባት ሌላኛው ወንጀል ነው:: የእነዚህ ድምር ውጤት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን የመፍጠር አቅም አለው::
በዚህ መንገድ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ጠንካራ የሆነ የምርመራ፣ የክስና ገንዘቡን የማስመለስ ስራ ቢሰራ ሌሎችን የማስተማር እድሉ ሰፊ ነው:: በቴሌ ብር፣ በሞባይል እንዲሁም በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ገንዘብ የማጭበርበር ተግባራትን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋት የፋይናንስ ደህንነትን ማስጠበቅ ግዴታ ነው::
ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በርካታ የማጭበርበር ሙከራዎች እየታዩ መምጣታቸውን ተከትሎ ይህንን ስጋት ለማስቀረት በጥንቃቄ መስራት ይገባል:: ማጭበርበሮች ሲታዩ ማህበረሰቡ እንዲያውቀውና ጥንቃቄ እንዲያደርግ መረጃዎችን በፍጥነት ማድረስ ያስፈልጋል:: የፋይናንስ ተቋማት የሚመጣው ነገር/ማጭበርበር ከመምጣቱ በፊት ሙከራ ሲደረግ ማሳወቅ አለባቸው:: ደንበኞችም አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥማቸው ለገንዘብ ተቋማት ማሳወቅ ይገባቸዋል::
የፋይናንስ ዘርፉ በጥብቅ ስርዓት ካልተመራ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከትላል:: ባንኮችና መሰል የፋይናንስ ተቋማት ጥብቅ አጥር በገንዘብ ዝውውራቸው ላይ ማበጀት እንዳለባቸው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል:: በቅርቡ የብሄራዊ ባንክ ባወጣው ሪፖርትም በአንድ ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ብር ከባንኮች ማጭበርበር ተፈፅሟል ሲል ገልጧል:: ከባንኮችም ዶላር ሊያጭበረብሩ ሲሉ መያዛቸው ይታወቃል::
በመሆኑም ማንኛውም ተቋም ወይም ግለሰብ ዲጂታል ፋይናንስ ወይም የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ዝውውር በሚጠይቅበት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል:: የፋይናንስ ደህንነት አስተማማኝና ደህንነቱ እንዲሆንም ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግም ይጠበቅበታል::
ብሄራዊ ባንክ በስሩ የሚያስተዳድራቸውን ንግድ ባንኮችና የመንግስት ባንኮች አግባብ ያለው የደህንነት እርምጃዎች እየወሰዱ እንደሆነ፣ ጥንቃቄዎችን እያደረጉ እንደሆነ፣ ፖሊሲዎቻቸውን በአግባቡ እየተገበሩ እንደሆነ መቆጣጠርና ኦዲት የማድረግ ኃላፊነቱ ከዚህ ቀደሙ በተሻለና ዘለቄታነት ባለው መልኩ ሊወጣ ይገባል:: የፋይናንስ ተቋማትም የአሰራር ስርዓታቸውን ደህንነት ቀልጣፋነት ይበልጥ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭ ባህሪን በማየት በቀጣይነት መስራት ይጠበቅባቸዋል::
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም