የማንበብ ባህል እንዲዳብር …

ሥነ ጽሑፍና ንባብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ብቻም ሳይሆኑ አብሮ የሚያድድጉና የሚሞቱ የሰው ልጅ የፈጠራ ተግባራት እንደሆኑ ይታመናል:: የንባብ ባህል ሲዳብር የሀገራት ሥነ-ጽሑፍም አብሮ እና ተደጋግፎ ያድጋል:: የንባብ ባህልና ሥነ-ጽሑፉ የሚያድግ ከሆነ ደግሞ የሀገራት የሥልጣኔ ደረጃ እና የትውልድ ግንባታም በዛው ልክ ተያይዞ እንዲያድግ ይረዳል:: ወቅቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን የሀገራት የንባብና የሥነ-ጽሑፍ እድገት ፈታኝ ወቅትን እያሳለፈ ይገኛል::

በዳበረ የንባብ ባህል እና የሥነ-ጽሑፍ እድገት በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የበለጸጉ ሀገራት መሆኑ ደግሞ የሚያስገርም ነገር ነው:: ሀገራቱ ምንም በሳይንስና በቴክኖሎጂ የረቁቁ ቢሆንም የንባብ ባህላቸውን እና የሥነ-ጽሑፍ እድገታቸውን ሊገታው አልቻለም:: በደህነት እና በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ግን የሚታየው ከዚህ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን::

ቴክኖሎጂው በሀገራቱ የንባብ ባህልና ሥነ- ጽሑፍ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን በመፍጠር ላይ ይገኛል:: ይህ እንደ ኢትዮጵያ በሥነ-ጽሑፍ ታሪካቸው በቀዳሚነት ለሚጠቀሱ ሀገራት ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል:: ብዙ ሊነበቡ የሚችሉና ሀገርን አንድ ርምጃ ማስኬድ የሚችሉ የሃይማኖታዊ፣ የሳይንስ፣ የሥነ-ፈለግ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሌሎች የጥንት እውቀቶችን የያዙ ለቁጥር የሚታክቱ መጽሐፍትን የያዘች ሀገር አንባቢ ትውልድን መፍጠር አለመቻሏ ትልቅ ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል::

የኅብረተሰቡ የማንበብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ በመምጣቱ የሚመራመር፣ የሚጽፍ፣ እና ለነገሮች ምክንያታዊና ሙያዊ ትንታኔን መስጠት የሚችሉ ሰዎችን ማፍራት ላይ ክፍተቶች እየተፈጠረ ይገኛል:: አሁንም በየቤተ-መጽሐፍቱ እና የሃይማኖት ተቋማቱ ትውድን መቀየርና ሀገርን ማሳደግ የሚችሉ ብዙ እውቀቶችን የያዙ መጽሐፍትን ጥቅም ላይ ለማዋል የኅብረተሰቡን የንባብ ባህል በትልቁ መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ነው:: ይህም ሲባል፣ የማንበብ ባህል የሚያሸንፍበት፣ ለንባብ ዋጋ የሚሰጥበት፣ የሚከበርበትን እና የሚበረታታበትን አካባቢ መፍጠር ላይ መሥራት ያስፈልጋል::

ይህ አይነቱ አካባቢም እንዲፈጠር የሚመለከታቸው አካላት ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: ለዚህም ከቤተሰብ በመጀመር፣ በትምህርት ቤት በማስፋት መሠረት ጥሎ የንባቡን ባህል ለማሳደግ ህጻናት ላይ መሥራት ነገሩን በፍጥነት ውጤታማ ማድረግ ይችላል:: ትምህርት ቤት ላይ እና ቤተሰብ ላይ የሚሠራው ሥራ ቤት ሲሠራ ጠንካራ መሠረት እንደመጣል ይቆጠራል:: የሚወጣው የቤቱ መሠረት ጠንካራ ከሆነ ጥሩ አገልግሎት መስጠት የሚችል ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ ህጻናት አእምሮ ላይ የሚሠራው ነገር ጥሩ የሆነን አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይችላል::

እዚህ ላይ ከትምህርት ቤትና ከወላጆች የሚጠበቀው ሥራና ኃላፊነት ትልቅ ሥፍራን የሚይዝ ይሆናል:: ወላጆች ልጆቻቸው ማንበብን እንዲለማመዱ በእውቀታቸው ልክ መጽሐፍትን ገዝቶ በማቅረብ የወላጅነት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: ንባብ ላይ የሚሠራው ሥራ ትውልድን የሚያንጽ ከመሆኑም በተጨማሪ የሀገር ግንባታን የሚያቃልል ይሆናል::

ንባብን የሚያነቃቁ፣ የሚያበረታቱ እና የሚጋብዙ ሁኔታዎችን በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት መፍጠር ሌላው ማሳደጊያና ማዳበርያ መንገድ ነው:: ይህ ጉዳይ በተለይ ለመገናኛ ብዙኃን አበክረውና ጠንክሮ ሊሠሩበት የሚገባው ቀዳሚው አጀንዳቸው መሆን ይገባዋል:: ለዚህ ባህል መዳበር ሌሎችም የሚዲያ ተቋማት ትምህርት ወስደው ሊሠሩ የሚገባው የኤፌም አዲስ 97 ነጥብ 1 “ለተሻለ ነገ እናንብብ” በሚል ሃሳብ የተካሄደው የአንድ መቶ ቀናት የንባብ ዘመቻ ይጠቀሳል:: በዚህ የንባብ ዘመቻ ብዙ ሙሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሚዳያ ባለሙያዎች እና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተጋብዘው ያነበቧቸውን የምንጊዜም ምርጥ መጽሐፍትን ለአድማጭ ተመልካቾች ማድረስና የንባብ ልምድና ተሞክሮአቸውን አካፍለውበታል::

በዚህም የተነሳ የማህበረሰቡ የማንበብ ፍላጎት መነቃቃትን በማሳየት እና ለማንበብ ፍላጎትን የሚያሳይ ማህበረሰብን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል:: የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮ ጣቢያውን 24 ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልንም ሲያከብር፤ ይሄንኑ ከግምት ውስጥ አሰገብቶ የመጽሐፍ አውደ ሪዕይን አዘጋጀቶ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች መጽሐፍት ገዝተው እንዲያነቡና የንባብ ባህልን እንዲያሳድጉ ማበረታታት ችሏል::

ተቋሙ የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑና ተጽእኖ ፈጣሪነቱም እንዳለ ሆኖ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እና ኅብረተሰቡ ለንባብ እንዲነቃቃና ባህሉ እንዲያደርግ በአርአያነቱ ይጠቀሳል:: በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ የህትመት፣ የብሮድካስትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ንባብን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር ሚደረገውን ጥረት በቋሚነት መደገፍና ሰፊ ሽፋን በመስጠት መሥራት ይጠበቅባቸዋል::

ኢቢሲ በቀጣይ ዓመትም የቴሌቪዥን ጣቢያውን 60ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ሲያከብር 6 ሺ መጽሐፍትን አሰባስቦ ለሕዝብ ቤተ መጽሐፍት በስጦታ መልክ ለማበርከት አስቧል:: ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር የንባብ ባህል እንዲዳብር “መጽሐፍትን ቤተኛ” እናድርግ የሚለውን መልዕክትን ለመደገፍና መጽሐፍትን አሰባስቦ በመስጠት ኅብረተሰቡ ለንባብ የሚሰጠውን ትኩረት ለማሳደግም ታስቦ ነው::

የንባብ ባህልን ለማዳበርና ለማሳደግ ተቋማት ከኢቢሲ ተሞክሮ በመውሰድ የተለያዩ አውደ ርዕይዎችን በማዘጋጀት እና ሌሎች ማነቃቅያ መንገዶችን በመጠቀም ሠራተኞቻቸው ብሎም ህብረተሰቡ ንባብን ባህሉ እንዲያደርግ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል:: ማንባብ ለሀገር እና ለትውልድ የሚኖረውን ሚና በሚገባ የማስገንዘብ ሥራን ማስፋትና ባህሉን መገንባት ትልቁ ቦታ ሊሰጠው ይገባል:: ቤተ መጽሐፍትን በሁሉም ቦታ ማስፋት እና በቀላሉ የሚነበብበትን ሁኔታ መፍጠር ሰው ለመጽሐፍት ቅርብ እንዲሆንና ንባብን እንዲለማመድ የሚያግዝ ነጥብ ነው::

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰዎች የሚፈልጉትን መጽሐፍት በያሉበት በቀላል ሁኔታ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር:: ወጣቶችን በንባብ በማሳተፍ እና እንደየፍላጎታቸውና እውቀታቸው እንዲያነቡ መንገዱን ምቹ ማድረግ ጠንካራ የንባብ ባህልን መገንባት ይችላል::

ኅብረተሰብን የሚያሳትፉ ትምህርታዊ ሁነቶችን በማዘጋጀት ታዋቂ ደራሲዎች እና የተለያየ መጸሕፍትን በመጋበዝ የንባብ ልምድና ተሞክሮአቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ:: አንባቢ ማህበረሰብን ለመገንባት በግልም ይሁን፣ በቡድን ወደ ንባብ የሚስብና ፈጠራ የተሞላበትን መንገድ በመጠቀም አብሮ ማንበብ፣ ሃሳብ መለዋወጥ እና መወያየ መድኮችን መፍጠር ያስፈልጋል::

አለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You