የኃይል አቅርቦትን ያሻሻለው ሀገራዊ ንቅናቄ

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት ነው፡፡ በቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሌለው ሀገር ስለአምራች ዘርፍ እድገት ሊያስብ አይችልም፡፡

ዛሬ በአምራች ዘርፍ እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀሱት ሀገራት ለኃይል ልማት ከፍተኛ ትኩረት የሰጡ በቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን እውን ማድረግ የቻሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አስተማማኝና ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአምራች ኢንዱስትሪው እድገት የጀርባ አጥንት ነው።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሃገር ብትሆንም፣ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እንዳታገኝና ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲነገርለት የቆየው መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ሽግግር እስካሁን ድረስ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ከሀገሪቱ የአምራች ዘርፍ ማነቆዎች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት እጥረት ነው፡፡ ይህ ችግር አምራቾች ባሰቡት ልክ እንዳያመርቱ በማድረግ በምርት መጠን፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ የኃይል እጥረቱ አምራቾቹ ማሽኖቻቸውን ብቻም ሳይሆን የሰው ኃይላቸውንም በበቂ መጠን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡

በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ስላላቸው ሚና ይፋ ባደረገው ጥናት፤ ምንም እንኳ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለየ ማበረታቻና ድጋፍ ፓኬጆች አዘጋጅቶ ወደ ስራ የገባ ቢሆንም፤ አብዛኛው የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብት የመጀመሪያ ምርጫው አምራች ኢንዱስትሪው ሳይሆን የንግድ፣ ሪል እስቴትና የአገልግሎት ዘርፎች እንደሆኑ አመልክቶ ነበር፡፡

ለዚህ ደግሞ ጥናቱ በምክንያትነት የጠቀሳቸው ቀድመው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች የኃይል እጥረትን ጨምሮ በብዙ ችግሮችና ማነቆዎች ምክንያት ውጤታማ ባለመሆናቸው ወደ ዘርፉ መግባት ለሚፈልግ ባለሀብት ጥሩ አርአያ መሆን አለመቻላቸውን እና በንግድና አገልግሎት ዘርፎች የሚገኘው ትርፍ በጣም የተጋነነና ሳቢ መሆኑን ነው፡፡

የሀገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥ ማቸውን የኃይል እጥረት ለማቃለልና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። የውሃን ጨምሮ የነፋስ፣ የእንፋሎትና የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ተገንብተዋል፤ የኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትና አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዝ ስምምነት ባለፈው ዓመት ተፈራርመው እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትና አቅርቦትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪው በስፋት ገብተው በዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የኤክስፖርት ምርትና ገቢን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን እድል እንደሚፈጥር እንዲሁም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና የኃይል አቅርቦት ከመቋረጡ አስቀድሞ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተገልጾም ነበር፡፡ በእነዚህ ጥረቶች የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ ከአገሪቱ አቅምና ከችግሩ ስፋት አንፃር ግን መፍትሄዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚጋጥማቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር በማቃለል ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ መንግሥትም ሆነ አምራቾች ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ንቅናቄው የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር የሚያቀላጥፍ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በኃይል አቅርቦት ረገድ ይስተዋሉ የነበሩ የቅንጅት ጉድለቶችን ለማረም የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል፡፡

‹‹የኃይል አቅርቦትና የአምራች ዘርፍ ስራ ከፍተኛ ትስስር አላቸው፡፡ ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ለኃይል ዘርፍ ልማትም ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አምራች ኢንዱስትሪው ምርት ለማምረት ያስችላል፤ የአምራች ኢንዱስትሪው ምርቶች ደግሞ ለኃይል ምርትና ስርጭት ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ስለሆነም ምርት ማምረት ያለኃይል አቅርቦት እንዲሁም ኃይል ማምረትና ማቅረብ ደግሞ ያለኢንዱስትሪ ምርቶች ሊታሰቡ አይችሉም›› በማለት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት ተግባር ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡

ኢንጂነር አሸብር እንደሚሉት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዲጀምሩ እንዲሁም ነባሮቹም የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር በማድረግ ተጨማሪ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ንቅናቄው የኃይል አቅርቦት ፍላጎቶች በባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ምላሽ እንዲያገኙ እድል ፈጥሯል፡፡

የኃይል አቅርቦትና ስርጭት ተግባር ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ መሆኑ ኃይል ለማምረትና ለአምራቾች ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ኢንጂነር አሸብር ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ኃይል 96 በመቶ የሚሆነው ከውሃ የሚመነጭ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከፀሐይ፣ ከእንፋሎትና ከነፋስ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችልም ከፍተኛ አቅም አላት፡፡ ከሀገሪቱ አቅም እና የመልማት ፍላጎት አንፃር በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የዘርፉ ልማት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

‹‹ የኃይል ማመንጫዎች እድሜያቸው ሲጨምር እድሳት ይፈልጋሉ፤ ካልታደሱ ውጤታማነታቸው ይቀንሳል፡፡ ግንባታቸውም እድሳታቸውም ከፍተኛ ወጭ አለው፡፡ እስካሁን የተሰሩት ስራዎች ወጭ የተሸፈነው መንግሥት በመደበው ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የአገልግሎት ክፍያ በቂ ስላልሆነ ታሪፉን ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ታሪፉን ማሻሻል የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት ያሻሽላል፤ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ያበረታታል›› ይላሉ፡፡

ከታሪፍ ማሻሻያው በተጨማሪ በመንግሥትና የግል አጋርነት አሰራር (Public-Private Partnership) የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማት ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚገባም ኢንጂነር አሸብር ይመክራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፣ ንቅናቄው ለአምራች ኢንዱስትሪው ካስገኛቸው አወንታዊ አበርክቶዎች መካከል አንዱ በኃይል አቅርቦት ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተቀናጀ አሰራር ለማቃለል የሚቻልበትን እድል መፍጠሩ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የንቅናቄው ትግበራ በኃይል አቅርቦት ረገድ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት ይገልፃሉ፡፡

አቶ ሽፈራው እንደሚሉት፣ አገልግሎቱ በልዩ ትኩረት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ዋናዎቹ ለአምራች ዘርፉ ጥራት ያለውና አስተማማኝ የሆነ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ለአዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለኢንዱስትሪ ደንበኞች ቅድሚያ የሚሰጥ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ደንበኞች ልዩ ትኩረት የሚያገኙበት አሰራር በቴክኖሎጂ እንዲታገዝም ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የደንበኞች ግንኙነት ስርዓት እንዲሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ደንበኞች የተለየ የጥሪ መስመር (904) ተዘጋጅቷል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ8200 በላይ ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በ96 ትልልቅ ከተሞችና የኢንዱስትሪ ማዕከላት በሆኑ አካባቢዎች የኃይል መሰረተ ልማቶችን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የኃይል አቅርቦቱ በብዙ አካባቢዎች ተደራሽ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎች በጥቂት አካባቢዎች ብቻ ተከማችተው እንዳይገኙ አዎንታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትም እየተሻሻለ ነው፡፡ የአምራቾችና የአገልግሎቱ ስራዎች የተሳሰሩ ናቸው፡፡ አምራቾች ለምርት ስራዎቻቸው ኃይል እንደሚፈልጉ ሁሉ አገልግሎቱም ስራዎቹን ለማከናወን ከኢንዱስትሪ ደንበኞች የሚጠቀማቸው ብዙ ግብዓቶች (ኬብሎች፣ ትራንስፎርመሮች…) አሉ›› በማለት የኃይል አቅርቦትንና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል ስለሚከናወኑ ተግባራት ያብራራሉ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኃይል አቅርቦት ከአምራች ዘርፉ ተወዳዳሪነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለአምራች ዘርፉ እድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የኃይል ልማትና ስርጭት ወሳኝ ናቸው›› የሚሉት አቶ ታረቀኝ፣ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የተመረተውን ኃይል ወደ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማድረስ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መፍጠር በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን ይገልፃሉ፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መጠናከር ሌሎቹን የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያሳድግ ግብዓት ነው፡፡ ለአብነት ያህል የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ውጤታማነት ለማሻሻል ደግሞ የዘርፉን የስራ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ግብዓቶችን (መሳሪያዎችን) በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት የሚያመርት አምራች ዘርፍ ያስፈልጋል፡፡ አምራች ዘርፉ ከሚጠናከርባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ግብዓቶችን ማሟላት እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ነው፡፡

የኃይል አቅርቦት ከግብዓቶቹ መካከል ወሳኝ ሚና አለው፡፡ አማራጭ ኃይልን በመጠቀም ለኢንዱስትሪዎች ያልተቆራረጠ ኃይል ማቅረብ ይገባል፡፡ የአባይ ግድብ የኃይል አቅርቦት ችግሩን በመፍታት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

አንዳንድ ሀገራት የድንጋይ ከሰል ሀብታቸውን አጋዥ አድርገው በመጠቀማቸው ምርቶቻቸውን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ስለሆነም ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ የድንጋይ ከሰል አማራጮችን ማጤንና መጠቀምን ችላ ማለት አያስፈልግም፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩ መፍትሄ ካገኘ አምራቾች በአቅማቸው ልክ ማምረት የሚችሉበት እድል ይፈጠራል፡፡

የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት የሚመጣጠኑ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉን ችግሮች መፍታት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የዘርፉ አጠቃላይ አሰራር የሚመራባቸውን አስፈላጊ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ይገባል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You