ሳይቃጠል በቅጠል

የእንግሊዘኛው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ በዚያ ሰሞን ዕትሙ አንድ አስደንጋጭ ዘገባ ይዞ ወጥቷል። የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮን ጠቅሶ ባስነበበን በዚህ አስደንጋጭ መርዶ አራት መኪና ከእነ ተሳቢው ተመሳስሎ የተሰራ የአፈር ማዳበሪያ መያዙን አርድቶናል። ለፕላስቲክና ለጎማ ምርት ግብዓት የሚሆን የተፈጨ ነጭና ሰማያዊ ላስቲክ ማዳበሪያ ነው ተብሎ ወደ ክልሉ ገብቶ ተይዟል። ይህ ግብዓት ላይ ላዩን ላየው የአፈር ማዳበሪያ ስለሚመስል ነው እንግዲህ ማዳበሪያ ነው ተብሎ ተመሳስሎ የቀረበው። ይህ የተደረሰበትና የተያዘው ብቻ ነው። ምን አልባት ያልተያዘውና ያልተደረሰበት ከዚህ በላይ ሊሆን ይችላል።

ይህ ሕገወጥነት የስንቱን አርሶ አደር መሬት በዚህ ባዕድ ኬሚካል በክሎ ምን አልባትም ለዓመታት መሬቱን ጦም እንደሚያሳድረው፤ ማዳበሪያ ተጠቅሞ ምርት ሊያፍስ ተስፋ ሰንቆ የነበረን አርሶ አደር ተስፋ እንደሚነጥቀው፤ ቤተሰቡንና ልጆቹን ለርሀብ ለእርዛት እንደሚዳርግ ባሰብሁ ጊዜ ለነገ ፈራሁ። ሳይቀጠል በቅጠል ብለን ተረባርበን ነገ ዛሬ ሳንል ካላስቆምነው መዘዙ ዘርፈ ብዙና የከፋ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፈር ማዳበሪያ ግብይት ላይ የሚስተዋለው ሕገ ወጥ ንግድ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ስለሆነ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ ።

ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ሲድህ ሲድህ በማንደራደርበት በሀገራችን የአይን ብሌን ማዳበሪያ ላይ ደርሷል። የሕልውናችን መሠረት፣ የግብርናችን የጀርባ አጥንት የሆነው ማዳበሪያ ላይ እጁን አስገብቷል። መቼም አይደፈርም። አይነካም። አይሞከርም። ብለን በምንተማመነው የማዳበሪያ ግብይትና ስርጭት እጁን ማስገባት ከቻለ ነገ ተቋሞቻችንና መዋቅሮቻችንን እንደማይቆጣጠር ምን ዋስትና አለን። ከጨረታ፣ ከግዥ፣ ከማጓጓዝ እስከ ስርጭት በየደረጃው ባለ የመንግስት መዋቅር ይሳለጣል ብለን በምናምነው የማዳበሪያ ግብይት ካች አምና አምና እና ዘንድሮ ጥቂት ሕገ ወጦች ሲራኮቱበት ታዝበናል።

ከሁለት ሳምንት በፊት 250 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከስኳር ጋር ተከዝኖ መገኘቱ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ምን ያህል እጀ ረጅም እንደሆነ ያሳያል። ስድ የተለቀቀው ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ከሕዝባችን 85 በመቶ የሚሆነው ዜጋችን ኑሮውን በመሠረተበት፤ ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ በሆነው ግብርና አንገት ላይ ሸምቀቆውን እያስገ ነው። በጊዜ አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ በመሠረታዊው የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ እንዳደረገው ሸምቀቆውን ስቦ ያንቀዋል። ይህን አደረገ ማለት በ126 ሚሊየን ሕዝብ እና በሀገር ጉሮሮ ላይ ቆመ ማለት ነው። አሁን ባለን የግብይት ስርዓት የማዳበሪያ አቅርቦት በምንም ታምር ከመንግስት እጅ ሊወጣ አይገባም የሚባለው ለዚህ ነው።

በተለይ ከአለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ያለ አፈር ማዳበሪያ ግብርና የሚታሰብ አይደለም። መሬቱ ማዳበሪያ ለምዷል። ገበሬው መሬቱ ባልጓል። ያለማዳበሪያ በጀ አይልም ይለዋል። ይህን የተረዱ የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናዮች ገበሬው መሬቱ ጦም ከሚያድር የተጠየቀውን እንደሚከፍል እርግጠኛ ስለሆኑ በግብይት ሰንሰለቱ ሰርገው በመግባት ከሙሰኛ አመራር፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኛና ስነ ምግባር ከጎደላቸው ከሕብረት ስራ ማህበራት አመራሮች ጋር በመመሳጠር፤ እንዲሁም አምና ተከስቶ የነበረውን የአቅርቦት መዘግየትና መስተጓጎል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም መንግስት በከፍተኛ ድጎማ ለገበሬው ያቀረበውን ማዳበሪያ በሁለትና በሶስት እጥፍ እስከ መቸብቸብ ደርሰው ነበር።

ያለው ውስን ማዳበሪያ በወቅቱ እንዳይከፋፈል በማድረግና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ቀውስ ፈጥረዋል። ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ሀገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሬ አቅም ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋ የገዛችውን ማዳበሪያ እንደ ዘይቱና ሲሚንቶው ለመቆጣጠር ዕንቅስቃሴ መጀመሩን ታዝበናል። ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ከ2 ሺህ 300 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የክልሉ ሕብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ መስፍን ረጋሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል።

በዚህም ከ2 ሺህ 330 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መያዙን፤ በድርጊቱ የተሳተፉ 30 ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም አመልከክተዋል። በክልሉ በዘርፉ የሚፈፀመው ሕገ -ወጥነት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ያስከተለ ሲሆን፤ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያ በኩንታል እስከ 11 ሺህ ብር ለመግዛት መገደዳቸውን ይታወሳል፡፡ ዘንድሮም እንደአምናው የከፋ ባይሆንም የአፈር ማዳበሪያ ደብቀው በመከዘን የተያዙና በሕገ ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ መያዛቸው ተዘግቧል። የአፈር ማዳበሪያ ከተነሳ አይቀር አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ።

የአፍሪካ አገሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ሆነው እ.ኤ.አ. በ2006 የአቡጃ ዲክላሬሽን የተባለ አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ አገሮቹ ማዳበሪያን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ነው የሚል ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ ምርትና አቅርቦቱን ለማሳደግ ቃል ተገባብተው ነበር፡፡ አፍሪካ የማዳበሪያ ማምረቻ ጥሬ ዕቃ ያላት በመሆኗ ምርቱን በማሳደግ ከሌሎች ጥገኝነት መላቀቅ አለባት የሚል ዕቅድ በወቅቱ የያዙ ሲሆን፣ ድንበር ሳይገድበው የማዳበሪያ ንግድ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲደረግም ወስነው ነበር። በአቡጃ ዲክላሬሽን መሠረት እ.ኤ.አ. እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በአኅጉሩ የማዳበሪያ አጠቃቀምን ከ22 ኪሎ ግራም በሔክታር ወደ 50 ኪሎ ግራም ለማሳደግ ግብ ተይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በአንድ ሔክታር የምትጠቀመውን የማዳበሪያ መጠን ወደ 88 ኪሎ ግራም ማድረስ መቻሏንና የአቡጃ ዲክላሬሽን ግብን ከማንም አገር በተሻለ ማሳካቷን ተናግረው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም የኢትዮጵያ የማዳበሪያ የግብይት ሰንሰለት እንደ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በብዙ ችግሮች የተተበተበ ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝና የፖታሽ ማዕድን ክምችት በሰፊው ቢኖራትም እስካሁን ራሷን አልቻለችም፡፡ አገሪቱ በሌላ የውጭ ምንዛሪ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማዳበሪያ ከውጭ ለመግዛት ታውላለች፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ “Freedom from Hunger” በተባለ ፕሮጀክት አማካይነት ማዳበሪያን የለመደው የኢትዮጵያ መሬት፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ፍጆታውን እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በ1970ዎቹ ወደ 3,500 ቶን ማዳበሪያ ነበር የሚገባው፡፡ በ1980ዎቹ መጠኑ ወደ 34 ሺሕ ቶን ሲያድግ፣ ይህ መጠን በ1990ዎቹ 140 ሺሕ ቶን መድረሱ፣ ከዚያም እ.ኤ.አ. በ2012 የአገሪቱ ዓመታዊ የማዳበሪያ ፍጆታ 650 ሺሕ ቶን መድረሱ ይነገራል። በዚሁ ጊዜም አገሪቱ ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣው ወደ 350 ሚሊዮን ዶላር አድጎ ነበር፡፡ከፍ ብሎ እንደተመለከተው አሁን ግን ለማዳበሪያ ግዥ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ እየዋለ ነው።

ወደ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ስንመለስ፤ ከዓመት ዓመት ክንዱ እየፈረጠመ የመጣው ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ነገ የሕልውናችንና የሰላማችን ስጋት መሆኑ አይቀርምና መንግስት ነገ ዛሬ ሳይል ስርዓት ሊያሲዘው እና በግብይት ስርዓቱ የሕግ የበላይነትትን ሊያረጋግጥ ይገባል። ካልሆነ እንደ ጣሊያኑ የሲሲሊ ማፍያ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት መሆኑ አይቀርም። መንግስት መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን፣ ነዳጅንና ማዳበሪያን በብዙ ቢሊየኖች እየደጎመ በሌለ የውጭ ምንዛሬው ቅድሚያ ሰጥቶ እያስገባ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ግን አመድ አፋሽ እያደረገው እና ከሕዝብ ጋር እያቃቃረረው ስለሆነ አበው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግስት ከዳተኝነት አባዜ ወጥቶ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱን በፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ታግዞ ሊያስተከክለው ይገባል።

የግብይት ስርዓታችን ጤናማ ቢሆን ኑሮ የዋጋ ግሽበቱም ሆነ የኑሮ ውድነቱ እዚህ ደረጃ ባልደረሰ። የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት የተለየ የሚያደርገውም እሴት በማይጨምሩ ሕገ ወጦች የታነቀ መሆኑ ነው። ይህ ማለት ግን የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ አለማቀፉ የዋጋ ግሽበትና የዩክሬን በራሽያ መወረር ለዋጋ ግሽበቱም ሆነ እሱን ተከትሎ ለመጣው የኑሮ ውድነት አስተዋጾ የለውም ማለት አይደለም። ዝቅ ብዬ ዋቢ ያደረግሁት አስደንጋጭ ጥናት እንደሚያትተው ደላላው ወይም የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናይ በሀገራችን ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ድርሻ አለው። መንግስት ይሄን አጉራ ዘለል የግብይት ስርዓት ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ሳይባባስ አደብ ቢያስገዛ የዋጋ ግሽበቱን 60 በመቶ የመቀነስ ዕድል አለው ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አንድ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ ምግብ ውድ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏንና ከዓለም 8ተኛ ደረጃ፤ ከዚምባቡዌ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት ሃገር እንደሆነች አርድቶናል። አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 49.1 በመቶ ሲሆን የምግብ የዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ወደ 23 በመቶ እንደወረደ እየተነገረ ቢሆንም ገበያው ላይ የመጣው ለውጥ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህም ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን በአማራና ደቡብ ክልል ያለው የዋጋ ግሽበት ከሃገራዊ ምጣኔው ከፍ ያለ ነው፡፡

ከተቀረው ዓለም የሀገራችንን የኑሮ ውድነት ለየት የሚያደርገው ማለትም ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ ከማሳ እስከ ገበያ መሰግሰጋቸው፤ መንግስትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ አለመውሰድ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል ይላል ጥናቱ፡፡ በዚህም ምክንያት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ከፍ ብሎ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት ዛሬ በሀገራችን ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ያህሉ የተከሰተው በስግብግብ ነጋዴዎች እና በደላሎች አማካኝነት መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል።

በሕግና በስርዓት ሊስተካከል በሚችል የግብይት ሰንሰለት ሸማቹ ምን ያህል ፍዳውን እያየ መሆኑንም ቁልጭ አርጎ አሳይቶናል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከስንት ውትወታ በኋላ ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ መመሪያ አዘጋጀሁ ቢለንም ስራ ላይ ባለመዋሉ የሀገሪቱ የግብይት ሰንሰለት የደላላ መፈንጫ እንደሆነ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚካሄደው የግብይት ስርዓት አገሪቱ በየዓመቱ እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ እያጣች መሆኑን፤ በዓለም ታዋቂ ከሆነው የምጣኔ ሀብታዊ መፅሄት “ዘ-ኢኮኖሚስት” ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና በአህጉራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ችግሮች፣ መንስኤዎቻቸውና መፍትሄዎቹ ዙሪያ በመከረ ጉባኤ ላይ መመልከቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያረጋግጣል። በኢትዮጵያ ከሚካሄደው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ግብይት ስርዓት ውስ40 በመቶ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚገቡ ምርቶች የተያዘ ነው። በዚህም አገሪቱ ከግብይቱ ስርዓቱ ማግኘት የነበረባትን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በየዓመቱ ታጣለች። ይህ ገቢ ለ72 ሺ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር አገራዊ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ መጠን ያግዝ ነበር ተብሏል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ 45 በመቶ የትንባሆ ምርቶች፣ 48 በመቶ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንዲሁም 30 በመቶ መድሃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ገበያውን የሚያውኩት ቀዳሚ ሸቀጦች ናቸው። በዚሁ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት አማካኝነት ወደ አገር የሚገቡ ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችም የህብረተሰቡን ጤና ስጋት ላይ የሚጥሉ መሆናቸውንም ጥናቱ አመልክቷል።

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You