ዓለምን ወደ አንድ መንደር ለማምጣት ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ሀገራት ዓላማቸውን እውን ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ የመመልከቱ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአንዱ ተገርመን ሳናበቃ እንዳሻቸው ይፈራረቃሉ፡፡ በአህጉራችን አፍሪካ ግን ወደ ዓለም አስተሳሰብ ለመጠጋት ያሉ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው ብሎ ለመናገር ያዳግታል፡፡ ጅምሮች እንኳን ቢኖሩ ቀጣይነታቸው አጠያያቂ ሆኗል፡፡
በእርግጥ ለችግሩ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ የስልጣኔ እና የኋላቀርነቱ ችግር ተደራርቦ ካመጣው ባልተናነሰ የምዕራባዊያንም ሆነ የሌሎች ሀገራት ቀጥተኛም ሆነ የእጅ አዙር ጫናዎች ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ፣ በአንዱ ችግር አንዱ እንዲደረብ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በኢኮኖሚ ብዙ እድገት እንዳይመዘገብ ጎታች ምክንያት ሆኗል፡፡ በግብርናውም ይሁን በሌሎችም ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎች ራስን ከመቻል ይልቅ ተመጽዋችነትን ምርጫ እንዲሆን አስገድዷል።
በአህጉሪቱ ከስልጣኔ ይልቅ ኋላቀርነት ገዝፎ ይታያል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ ከመማር ይልቅ ትምህርት ቤቶችን ማውደም ቀሏል፡፡ ውይይትና ንግግርን ከማስቀደም ይልቅ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደአማራጭ ይወሰዳል። የአህጉሪቷ ሕዝብ እንደዚህ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ቆም ብሎ ‹‹ ግን ለምን?›› የሚለውን ጥያቄ የማንሳት ሞራል እንዳይኖረው በተለያዩ ትርክቶች ተተብትቧልና እንዴት ይህን ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል?
በሀገራችንም ቢሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም ወጥቶ የመግባቱ ነገር ፈተና ሲገጥመው ታዝበናል፡፡ ለአብነት የትምህርቱን ዘርፍ አንስተን ብናይ ብዙ ፈተናዎችን እንደገጠመው መጥቀስ ይቻላል። ከሁለት ዓመታት በፊት እንኳን በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያ ምን ያህል ትምህርት ቤቶች እንደወደሙ እና በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ እንዳስገደዳቸው የሚዘነጋ ክስተት አይደለም፡፡
ሁሉም ሀገራት ኢትዮጵያን ይወዳሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን ከማድረግ ባሻገር የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም አበክረው የመሥራታቸው ነገር አዲስ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ የገዛ ልጆቿን በገንዘብ እና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በማማለል እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት ዛሬ የተፈጠረ ወይም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደውም የብዙ ዓመታት ልምድ የተካበተበት ጭምር መሆኑን የታሪክ ምስክር ነው፡፡ እዚህ ጋር ያለው ልዩነት የሀገራቱ መለያየት ብቻ ሲሆን፤ በዓላማ ግን አምሳያ ናቸው፡፡
የሰላም ዋጋው ብዙ ብቻ ሳይሆን በምንም ሊተመን የሚችል እንዳልሆነ ነጋሪ አያሻም፡፡ እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ፍጻሜያቸው የሚያምረው የሰላም አየር ምድሪቱን ሲያውድ እና ሲሞላ ብቻ ነው፡፡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራቱ ነገር የሚሰምረው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የዛሬ ፍሬዎች አድገው እና አብበው ሀገራቸውን የሚጠቅሙት ሰላም ኖሮ ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲያቀኑ ብቻ ነው፡፡
ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን እና እርቅን በመስበክ፤ ተከታዮቻቸው እነዚህን መልካም ተግባራት በተግባር እንዲያውሉ እና ከሁሉም ጋር በፍቅር እንዲኖሩ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ በዘር እና በሃይማኖት አክራሪነት ተጠልፈው ወይም ተከልለው፤ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ካለው ፈተና በተጨማሪ ሌላ ፈተና ሲፈጥሩባት ይስተዋላል፡፡
የተለያዩ ሃይማኖቶች አምልኳቸውን ለመፈጸም፣ አማኞቻቸውን ለመገሰጽ፣ ለማስተማርም ሆነ ስለ ሀገር ሰላም ለመጸለይ እንኳን ሰላም አስፈላጊ መሆኑን መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ያለ ቢሆንም፤ ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ማስገንዘብ ያሻል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የሰሜኑ ጦርነት፤ የጦርነትን አክሳሪነት ለመረዳት የታሪክ መዛግብት ሳናገላብጥ በዘመኑ የታሪክ ተካፋይ በመሆናችን ብቻ ብዙ ትምህርት እንድናገኝ ዕድል ሰጥቶናል፡፡ በዚህም የጦርነት ትርፉ ሞት፣አካል ጎዳተኝነት፣ ርሃብ፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ መፈናቀል፣ ከትምህርት መገለል፣የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ውድመት፣ ሰብአዊ እና የጤና እርዳታዎችን ለማግኘት መቸገር እና የመሳሰሉትን ችግሮች እንጂ ሌላ ያስገኘው አንዳችም ጥቅም አልነበረውም፡፡
‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ዛሬም ቢሆን እዚህም እዛም በሚታየው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዳግም የሀገር ሀብት እንዳይባክን፣ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ አካል እንዳይጎድል እና እንዳይፈናቀል ለማድረግ ነፍጥ ከማንገብ ይልቅ ቁጭ ብሎ ለምክክር ዝግጁ መሆን ብልህነት እንደሆነ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ ላይ ቁጭ ብሎ ለመነጋገር እና ለመወያየት ያሉት ጅምሮችም የሚበረታቱ ናቸው፡፡ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካኝነት ሰላም እንዲሰፍን ንግግር እና ውይይት እንዲጎለብት ‹‹ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ›› በሚል ሃሳብ ለውይይት ለመቀመጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ትልቅ ተስፋን የሚሰጡ ናቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ምክክሩ ለይስሙላ ሳይሆን አንዳች የሚያመጣው ለውጥ አለ ብሎ በማመን መንግሥት እንደ መንግሥት፣ ሲቪል ማህበራት፣መገናኛ ብዙኃን የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሑራን እና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ምናልባትም በዚህ መንገድ ችግሮችን ተነጋግሮ፣ ፈትቶ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ከተቻለ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም ምሳሌ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ በጦርነት፣በድርቅ በረሃብ፣ በድንቁርና በመሳሰሉት ነገሮች ስሟ ቀድሞ ለሚጠራው አፍሪካ የሚሰጠው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ስለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ ያነገቡ ታጣቂዎች በጠብ መንጃ ከማመን ይልቅ በውይይት እና በንግግር ብዙ ችግር እንደሚፈታ አውቀውና ተረድተው ከንግግር በዘለለ በተግባር የታገዘ የሰላም አብሳሪ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በጦርነት የሚፈታ ችግር እንደሌለ በማመን እና በማሳመን ስለ ሀገር ሰላም ሲሉ የድርሻቸውን የሚወጡበት ጊዜ አሁን እና ዛሬ ነው። ብዙ ተከታይ ያሏቸው ጋዜጠኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች የጦር ወሬን በማባባስ እና በማቀጣጠል ‹‹በለው፤ በለው›› ብሎ ወደ እሳቱ ከመገፋፋት ይልቅ ሁሉም ራሱን ገዝቶ ለሰላም በር እንዲከፍት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ጊዜው ዛሬ ነውና እድሉን መጠቀም ብልህነት ይሆናል፡፡
በምስጋና
አዲስ ዘመን ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም