በብዙ ስኬት የታጀበው የግብርናው ዘርፍ

ኢትዮጵያ ግብርናን ከፈጠሩ ሀገሮች አንዷ ነች። ይህ ብቻም አይደል በወቅቱ ለግብርና ሥራ መዋል ይችላሉ የተባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንም ትጠቀም እንደነበር በርካታ መዛግብት ይናገራሉ። ይህም ሆኖ ዘርፉ የዕድሜውን ያህል ባለማደጉና በተለመደው ባህላዊ አስተራረስ ዘዴ እንዲቀጥል በመደረጉ ጉዞው የኋሊት እንዲሆን ተገድዷል። ይባሱኑ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች መነቃቃት ከማበርከት ይልቅ በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የህዝብ ቁጥር መመገብ አቅቶት ሀገሪቱ በድርቅና በረሃብ የምትፈተንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የሀገሪቱ ስምም ከርሃብ ጋር እንዲነሳ አስገድዷል ።

ከችግሩ ለመውጣት በኢህአዴግ ዘመን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀይሶ ለ27 ዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል። በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ቢታዩም ኢህአዴግ ስልጣን እስኪለቅ ድረስ በሴፍትኔትና መሰል ስርዓቶች ድጋፍ የሚደረግለት የህዝብ ቁጥር 13 ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው ።

የለውጥ ሀይሉ /በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱና ዋነኛው የግብርናው ዘርፍ ነው። በተለይም የኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርዓትን በማላመድ የተበጣጠሱ መሬቶች በቅንጅት እንዲታረሱ ተደርጓል። በዚህም አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል።

ቀደም ሲል በብጣሽ መሬት ላይ በተናጥል ሲዳክር የነበረው አርሶ አደር ከአዋሳኝ መሬቶች ጋር በቅንጅት እና በትብብር ወደሚያመርትበት ስርዓት ገብቷል። ትራክተር እና ውሃ መሳቢያ ሞርተር የመሳሰሉ ዘመናዊ የግብርና መሳርያዎችን በጋራ በመጠቀም አርሶ አደሩ ከባህላዊ አስተራረስ ዘዴ እንዲላቀቅ በመደረጉ እንደሀገርም ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ።

ለአብነትም ጤፍ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ የሚመገበው እና አብዛኛውን የእርሻ መሬት የሚሸፍን ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ይሄ ነው የሚባል የምርት ዕድገት ሳያሳይ ቆይቷል። የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም።

ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በኩታ ገጠም ማረስ በመቻሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል። በቅርብ ዓመታት ውስጥም 1ቢሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከጤፍ ባሻገር ባለፉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱ በአዲስ የልማት ጎዳና እንድትራመድ ካደረጓት የግብርና እንቅስቃሴ አንዱ የስንዴ ልማት ነው። ቀደም ሲል በጥቂት መጠን፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፤ በክረምት ብቻ ይመረት የነበረውን የስንዴ ልማት ወደ በጋም በማሸጋገር የስንዴ ምርትን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም ላይ ተደርሷል።

የስንዴ ምርት በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በሄክታር ሁለት ቶን ይገኝ የነበረው የስንዴ ምርትም ወደ አራት ቶን ማሳደግ ተችሏል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2016 ምርት ዘመን ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሠራም ነው።

ሀገሪቱ አሁን ላይ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች። በ2015 ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው። ሀገሪቱ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች። በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከትውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች። ሆኖም በሀገሪቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። ከሩዝ አኳያ አምና ከስምንት ሚልዮን ኩንታል ያልበለጠ ነበር የተመረተው ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ብቻ 38ሚልዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል።

በተለይ በአማራ ፎገራና በጅማ እንዲሁም በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው።

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል። 500ሺ የነበረው ዓመታዊ ምርትን ወደ 800ሺ ማሳደግ ተችሏል። በዚህም 700ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ገቢ ወደ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ችሏል። የሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለሀገሪቱ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የማምጣት አቅም ላይ ደርሷል።

ከዚህ በሻገርም በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል። በማር፤ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽዖ፣ በጓሮ አትክልትና በፍራፍሬ ምርት ላይ የጎላ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ዜጎች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ብሎም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏል።

የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቱ የግብርና ዘርፉን ዕድገት እያፋጠነው ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ የፖሊሲ ድጋፎች በግብዓት፣ በኤክስቴንሽን ሥራዎች፣ በፋይናንስ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት ድጋፍ በመደረጉ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። በዚህም በወተት ዘርፍ አምና ከተመረተው ሁለት ቢልዮን ሊትር ተጨማሪ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ማምረት ተችሏል። እንቁላልን ብንመለከት ባለፉት ዘጠኝ ወራት አምና ከተመረተው ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢልዮን ተጨማሪ ማምረት ተችሏል ።

ቀይ ስጋን ስንመለከት አምና ከነበረው ወደ ሁለት መቶ ሺህ ቶን ተጨማሪ የስጋ ምርት ተገኝቷል። ማርን እንደዚሁ ስንመለከት አምና ዘጠኝ ወር ተመርቶ ከነበረው ተጨማሪ 110 ሺህ ቶን በላይ ምርት ተመርቷል። ይህም ግብርናው እየሄደበት ያለውን ግስጋሴ የሚያመላክት ነው።

በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ያለው መሻሻል ስንዴን፤ሩዝንና አቦካቶን የመሳሰሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም እንዲቀርብ ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ በውጭ ታዛቢዎች ጭምር የተመሰከረለትና ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ እምርታ እያሳየች መምጣቷን ያሳየ ነው። ለዚህም ጥር 19 ቀን 2016 በጣሊያን ሮም ከተማ የአግሪኮላ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችበት ሁኔታ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

የአግሪኮላ ሜዳሊያ ድህነትን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትና እና የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ለሠሩ ታዋቂ ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ትልቁ የፋኦ ሽልማት ነው። በወቅቱም የፋኦ ዳይሬክተር ጄኔራል ኪዩ ዶንግዩን እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሽልማት የበቁት በኢትዮጵያ የገጠር እና የምጣኔ ሃብት ልማት ሥራዎቻቸው እና የአረንጓዴ አሻራ የግል ጥረታቸው ነው ብለዋል።

ዳይሬክተር ጄኔራሉ በወቅቱ እንደገለጹትም ባለፉት 5 ዓመታት አስቸጋሪ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ባሉበት ሁኔታ በጠቅላይ ሚንስትሩ “ውጤታማ፣ ተጠያቂነት ያለው እና የተረጋጋ አመራር” የኢትዮጵያን አስደናቂ ዕድገት ተመልክተናል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት 5 ዓመታት በኢትዮጵያ የእርሻ መሬት በ50 በመቶ እንዲጨምር መደረጉን እና ይህም በተለይ የስንዴ እና የሩዝ ምርት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማስቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ሲረከቡ ኢትዮጵያ የውስጥ ፍላጎቷን ለማሟላት ስንዴ ከውጪ ስታስገባ መቆየቷን እና አሁን ግን አገሪቱ ፍላጎቷን አሟልታ ከእአአ 2023 ጀምሮ ስንዴ ለውጭ ገበያ መላክ መጀመሯንም ገልጸዋል። የፋኦ ሽልማትም ሆነ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችውን እምርታ ዕውቅና በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 120 ሚሊዮን የሚጠጋውን ህዝብ የሚመግብ ዘርፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 96 ሚሊዮን ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ኑሮው ቀጥታ ከግብርና ስራ ጋር የተያያዘ ነው። ከውጭ ምንዛሬ አንጻርም ብንመለከተው አብዛኛው ድርሻ የሚገኘው ከዚሁ ዘርፍ ነው።

ይህንኑ ሃቅ በመገንዘብ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል። የሀገሪቱን መልክዓ ምድርና የአየር ጻባይን መሰረት ያደረጉ ስራዎች በመሰራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪኳ አምርታቸው የማታቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችላለች።

ይኸው የተጀመረው ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርም ግብርናውን በፋይናንስ፤በቴክኖሎጂና በአሰራር የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው እየቀጠሉ ነው ። እነዚህም ድጋፎች ኢትዮጵያ ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ወደ ሜካናይዜሽን የምታደርገውን ጥረት የሚያግዙ ናቸው።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚመለክተው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሁለት ሚሊዮን 532 ሺህ 454 የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች እና 852 ሺህ 683 ለቅድመ ምርት የሚያገለግሉ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ወደ ሃገር እንዲገቡ ተደርጓል።

ሁለት ሚሊዮን 210 ሺህ 327 ዘመናዊ የእህል ማከማቻ ፣ ሶስት ሺህ 675 ትራክተር ፣ 652 ሺህ 92 የመርጫ መሳሪያዎች ፣ 196 ሺህ 916 የውሃ ፓምፖች ፣ 217 ሺህ 58 መውቂያዎች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል። በተጨማሪም የተለያዩ ኮምባይሮች ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያዎች፣ ማበጠሪያ እና መፈልፈያዎች አርሶ አደሩ ጋር ደርሰዋል።

መለዋወጫዎቹ ከገቡም በኋላ የግብርና መካናይዜሽን ማሽነሪዎችን የአጠቃቀም ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማዘጋጀት በተለይም አፋር እና በሱማሌ ክልሎች ላይ የተለያዩ የአጠቃቀም ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ግብርና ሚኒስቴር ገልጿል። በተጨማሪም በተለያዩ ከተሞች ለ238 ሞዴል አርሶ አደሮች ስልጠናው ተደራሽ ተደርጓል። ማሽነሪዎችን ከማስገባት ጎን ለጎን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ዘጠኝ ማዕከላትን በማቋቋም የማጠናከር ስራ ተከናውኗል ።

ግብርና ሚኒስቴር እንደሚለውም በአሁኑ ወቀት በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የግብርና መካናይዜሽን ግብአቶች ከገቡ በኋላ በትንሹ እስከ አስር ዓመት ማገልገል እንዲችሉ ማድረግ ላይ ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ከማሳደግ ባሻገር የግብርና ሜካይዜሽን ቴክኖሎጂ ኦፕሬሽን እና ጥገና ባለሙያዎችን በማሰልጠንም የሙያ ደረጃ እንዲሻሻል እየተሰራ ነው ።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በሞጆ አካባቢ በ50ሺ ዶላር የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እየተከናወነ ነው፤ ይህ ፋብሪካ ወደ ማምረት ደረጃ ሲሸጋር ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚጠጋ ትራክተር ባለቤት ትሆናለች። ይህ ሲሆን ደግሞ ኢትዮጵያ በግርብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ አርሶ አደሩ ሙሉለሙሉ በትራክር የማረስ ዕድል ይኖረዋል።

ግብርናውን በሜካናይዜሽን ከማጠናከር ጎን ለጎን የአርሶ አደሩ አቅም መገንባት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ጉዳዮች ወሳኝ ሲሆኑ አንዱ ብድር ሲሆን ሌላው ደግሞ የመድን ዋስትና ነው። አርሶ አደሩ ብድር ሲመቻችለት ትራክተር ይከራያል፣ መሬት ይኮናተራል፣ ማዳበሪያ ይገዛል። የግብርና ስራውንም ያለስጋት እንዲያከናውን የመድን ዋስትና ሊረጋገጥለት ይገባል።

መንግስት አርሶ አደሩ የብድር ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረጋቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው። ቀደም ሲል አዲስ አበባ ላይ ያሉት ባንኮች ለሪልስቴት ብቻ የሚያበድሩ ናቸው። የሚያበድሩት ገንዘብ ገንዘቡ ገጠር ገብቶ ግብርናውን ለሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች ሲውል አይስተዋልም ነበር። አሁን ባንኮች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩት ጉዞ የሚበረታታ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለ18 ዓመታት ያህል ሲሰራበት የቆየው የገጠር መሬት አዋጅ ተሻሽሏል። የተሻሽለው አዋጅ አርሶ አደሩ መሬቱን አሲዞ መበደር መብት የሚሰጥና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው። በአጠቃላይ እንደሀገር ግብርናው ለማዘመንና ከምግብ ዋስትና አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው። ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You