እንደ ሀገር የስራ ባህል ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። መንግስት የስራ ባህልን በተለይም ደግሞ የስራ ፈጠራ እንዲጎለበት ለማድረግ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አቋቁሟል። በዚህ ሳቢያም በየተዋረድ የስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ተቋቁመው እየተሰራበት ነው። በርካታ አምራች ኃይል ዜጋ ባለባት ሀገር ውስጥ የስራ ፈጠራ ባህል ማሳደግ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ ነው። የዛሬው የተጠየቅ አምዳችን የከፋ ዞን የስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ በስራ ዕድል ፈጠራ ምን አቅዶ ምን ሰራ? የስራ ዕድል ፈጠራ ልምድና ተሞክሮው ምን ይመስላል? በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መምሪያው እያከናወነ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ከመምሪያው ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ኃይሌ ጋር ቆይታ አደርጓል፡፡
መልካም ምንባብ!
አዲስ ዘመን፡- መምሪያው ባለፉት ወራት ምን አቅዶ ምን ሰራ?
አቶ ሚሊዮን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም አዲሱ ክልል መመስረትን ተከትሎ የስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ እና ስራና ክህሎት ዘርፍ ተብለው በአንድ መምሪያ ተዋቅረዋል። በዚህም መምሪያችን እንዲያከናውናቸው ከመንግስት የተሰጡት በርካታ ተግባራት አሉት።
ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ስራ አጥ ዜጎችን እንለያለን ብለን አቅድን ነበር። ከዚህ አኳያ በገጠር ወደ 32ሺ በከተማ ደግሞ 12 ሺ በላይ ስራ ፈላጊ ዜጎችን ለመለየት አቅደን በገጠር 36 ሺህ በከተማ ደግሞ ከ7 ሺ በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን መለየት ችለናል።
አንድ የስራ እድል ፈጠራ መምሪያ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አብይ መነሻው ስራ የሚፈልገውን ዜጋ ክህሎት እና በአካባቢው የሚገኘው የተፈጥሮ ጸጋ ነው። ይህን እሳቤ መሰረት በማድረግና ያሉ ጸጋዎችን በመያዝ ወጣቶችን ወደ ስራ እያሰማራን እንገኛለን። እስካሁን 17ሺህ 250 ወጣቶችን በገጠር እና ከአራት ሺ በላይ ወጣቶችን ደግሞ በከተማ በቋሚነት ወደ ስራ አስገብተናል።
በጊዜያዊ የስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ወጣቶች ጥቂት ጥሪት መቋጠር እንዲችሉ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ኑሯቸውን በዘላቂነት የሚመሩበት መስክ ባለመሆኑ በርካታ ወጣቶችን በቋሚነት ስራ የሚያገኙበትን ሁኔታዎች እያመቻቸን ነው። በቋሚነት ስራ ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙት በገጠር የመሬት ባለቤትነት የተደረጉት ናቸው ። በዚህም በበጀት ዓመቱ በ6 ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ የተለያዩ የግብርና ፓኬጆች እዲሰሩ ለማድረግ አቅደን1700 ሄክታር መሬት ለወጣቶች አስተላልፈናል። በዚህም በርካታ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ምርቶቻውን ለገበያ በማቅረብ የገበያ ዋጋ መረጋጋት ላይ የራሳቸውን አስተዋጾ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በጨታ ወረዳ በስንዴ፤ በለውዝ፤ በሰሊጥ፤ በጤፍ፤ ኮባ እና በበቆሎ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ምርት ተገኝቷል። የደጋ መሬቶችን ወደ እርሻ አስገብተን ወጣቶች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እያመረቱ ያሉበት ሁኔታ አለ። በጊምቦና በሺሾ ወረዳ ላይ እንዲሁ ወደ አምስት የሰፈራ ቦታዎችን በመፍጠር ለስራ ፈላጊ ወጣቶች የስራ አድል ፈጥረናል።
ጨታ፤ ሺሾ ቀበሌዎች ለወጣቶች በሰጠነው መሬት ተጨማሪ ቀበሌ የተፈጠረበት እና በጣም ውጤታማ መሆን የቻልንበት ነው። በዞናችን በሚገኙ በአምስት ወረዳዎች ሞይሽ ከሚባል መንግስታዊ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በንብ ማነብ ስራ ላይ ወጣቶች እንዲሳተፉ አድርገናል። ጊምቦ፤ ጓታ፤ ሺሾወንዴ ፣ በጨታ እና ሌሎች ወረዳዎች ላይ ወጣቶችን አደራጅተን በማር ምርት ላይ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ችለናል።
በተለይም ከለውጡ ወዲህ በክልላችን ብሎም በዞናችን የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራነው። በዚህም ከ2012 ዓ.ም ከ13 ሺ በላይ ሄክታር መሬት ወደ እርሻ ገብቷል። ለውጡን እንዲመጣ ካደረጉ አንዱ ምክንያት የስራ አጥ ቁጥር መብዛት ነው። በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት እንደዞን ማድረግ የምንችለው ሁሉ እያደረግን ሲሆን የተለያዩ የስራ እድል ፈጠራ ፓኬጆችን በማዘጋጀት ወጣቱ ተጠቃሚ እየሆነ ነው።
ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መጀመሪያ እንደዞን በእጃችን ያሉን ሀብቶችን ምንድን ናቸው? የሚለውን በማጥናት የልየታ ስራ አከናወን። በጥናቱ መሰረትም በዞናችን ለእርሻ መዋል የሚችል መሬት መኖሩን አረጋገጥን። በመቀጠልም ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የገጠር መሬት እንዲያገኙ አመቻችን ። በዚህም ወጣቱ በቀየው የመሬት ባለ ንብረት መሆን ችሏል። ወጣቱም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሰጠነው መሬት ላይ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት በመቻሉ የኑሮ ውድነቱን ይስተዋል የነበረውን የገበያ አለመረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ማስተካከል አስችሎናል።
በከተማም የተለያዩ ፓኬጆችን ቀርጸን የከተማ ግብርና ስራዎችን እያከናወን ሲሆን በተለይም በጠባብ መሬት ላይ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን በመለየት በርካታ ተግባራትን እያከናወን ነው። በዚህም በከተሞች በጫጩት እርባታ፤ በንብ ማነብ፤ የእንቁላል ዶሮዎች እርባታ፤ የወተት ከብቶች እርባታ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው።
አሁን ላይ ወጣቶችን ከመንግስት ተቀጣሪነት ስሜት በመውጣት የራሰቸውን ስራ መፍጠር እንዲችሉ ተደርጓል። በመሆኑም ወጣቶች የመንግስትን ተቀጣሪነት ስሜት ወጥተው የፋይናንስ እና የቦታ ድጋፍ እንዲመቻችላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
የወጣቶችን ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ መስጠት ተገቢ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ በገጠርና በከተማ ለሚገኙ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ከ24 ሚሊየን ብር በብድር ተሰጥቷል። ከዚህ ቀደም የተሰራጨውንም ብድር በማስመለስ ለሌሎች እንዲሰጥ በርካታ ስራዎችን ሰርተን፤ ብድር የማስመለስ ስራንም ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው።
አሁንም ከወጣቶች የስራ አድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ከዞኑ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ጋር በየሶስት ወሩ በመነጋር እየተገመገመ፤ አዳዲስ አቅጣጫዎችን እና አሰራሮችን በመቀየስ ወጣቱን የስራ ባለቤት ለማድረግ እሰራን እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዞኑ ያለውን ጸጋ በማደራጀት ወደ ስራ ከማስገባት አንጻር ያላችሁ ተሞክሮ ምን ይመስላል?
አቶ ሚሊዮን፡– በርካታ ኢንተርፕራይዞች አሉ። አሁን ባለው ሁኔታ የተሸጋገሩ የመንግስትን ድጋፍ ማለትም የፋይናንስ እና የቦታ ድጋፍ አግኝተው የራሳቸውን ሀብት የፈጠሩ ኢንተርፕራይዞች አሉ። አሁን የሃይቲ ዳቦና እንጀራ ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ 135 ስራ አጥ ወጣቶችን በስሩ ቀጥሮ ማስተዳር ችሏል። የዛሬ ሶስት ዓመት ሁለት መቶ ሺ ብር ብድር የተጀመረ ነበር። አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ያንቀሳቅሳል። ይህ ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች ተሞክሮ የተወሰደበት ነው። በከተማችን ውስጥ ምርቱን በ11 ቦታዎች ላይ ያቀርባል፡፡
በገጠር ስናይ በሰፈራ ያስገባናቸው ወጣቶች ዛሬ ለመንግስት ደጋፊ እየሆኑ እና ወደ ኢንዱስትሪም በመሸጋገር ላይ ይገኛሉ። በአንድ ዓመትና በሁለት ዓመት ውስጥ መኪና መግዛት የቻሉ፤ ኢንዱስትሪ መገንባት የቻሉ፤ በአካባቢያቸው ላይ ወፍጮ መትከል የቻሉና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት የቻሉ ናቸው፡፡
ዞኑ ካለው እምቅ አቅም አንጻር በርካታ ያልሰራንባቸው ስራዎች አሉ። የስራ ባህል ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት በውይይት እና በመነጋገር ለመፍታት ስራዎች ተሰርተዋል። አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ተቀጣሪ የመሆን ፍላጎት እና በማህበረሰቡም ውስጥ ተጽእኖ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። ከዚህም አንጻር ይህንን ተግዳሮት አልፈነዋል ብለን እናምናለን፡፡
በቅርቡ ለ270 ወጣቶች ጋር ቦንጋ ላይ ውይይት አድርገናል። ዶክተሮች፤ በርካታ ዲግሪ እና ዲፕሎማ ያላቸው ወጣቶች ጋር ተወያይተናል። ያሉንን ጸጋዎች አማትረው እንዲለዩ እና ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ተገንዝበው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ እና በኛም በኩል የሚያስፈልጋቸውን ግብዓትና ተሞክሮዎች ሰጥተን ወደ ስራ እንዲገቡ እያደረግን ነው።
አሁን ላይ በዞናችን ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ተመራቂ ወጣቶች አሉ። እነዚህ ወጣቶች አስከ ሰኔ 30 በሚፈልጉት የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የ90 ቀን እቅድ በማውጣት እየሰራን ነው። አሁንም ያሉንን ሀብቶች እና ጸጋዎች ከለየን በኋላ የስራ እድል ፈጠራ አመራሮች እና የወረዳ አስተዳዳሪዎችን እንዲሁም የመንግስት ተጠሪዎችን አወያይተናል። በዚህም ያሉትን ተመራቂ ወጣቶች ስራ ሳናስይዝ ሌሎች እንዳይጨመሩ የሚል መግባባት ላይ ደርሰናል።
በዞኑ በርካታ ልምድ የሚወሰድባቸው ኢንተርፕራይዞች አሉ። በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ላይ ስራ ፈላጊ ዜጎችን ስራ ለማስያዝ አቅደን እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ከፋ የሚታወቀው በቡና ልማት ነው። በዚህ ላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን ለማሰማራት ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡– በገጠር ላይ በቡና ልማት ዘርፍ ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው። ነገር ግን ተመራቂ ተማሪዎችን ቡና ላይ እያስገባን አይደለም። ምክንያቱም በቡና ላይ ጥቅም ለማግኘት በትንሹ ከሶስት ዓመት በላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል። አሁን ላይ የእኛ ወጣቶች ጥያቄ ደግሞ ዳቦ ለማግኘት ነው። በመሆኑም እኛ የምንቀርጻቸው ፓኬጆች በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉት ላይ ነው። ለምሳሌ ቡና ወጣቶችን ብናደራጅ ለሶስት ዓመት ቡናው ላይ ወጭ ሊያወጡ ይችላሉ እንጂ ከቡናው የሚያገኙት ነገር የለም። ይህ ደግሞ አሁን ላይ ወጣቶች ለሚጠይቁት የዳቦ ጥያቄ መልስ መስጠት አይችልም። በመሆኑም ከአጭር ግዜ እቅድ አንጻር ወጣቶችን በቡና ግብርና እንዲሰማሩ ከማድረግ ይልቅ ቡናን ፕሮሰስ ማድረግ ላይ ቢሰማሩ የዳቦ ጥያቄያቸውን መመለስ ይቻላል በሚል ቡና ፕሮሰሲንግ ላይ ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህን ለማድረግ መምሪያው ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የተግባር ስልጠናዎች ሰጥቷል።
ነገር ግን ቡና ተከላ ላይ ተመራቂ ወጣቶችን ብናስገባ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ስራ አጥ እንደተባሉ ነው የሚቆዩት። ይህ ሲባል ቡና እንደ ከፋ አስፈላጊ መሆኑን ለመካድ አይደለም። ስለዚህ በአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚሰጡ ስራዎችን ነው የምንሰራው። ነገር ግን ለወጣቱ አሁን ላይ የሚደርስለት ነገር ያስፈልገዋል የሚለውን እንድትገነዘቡልን እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ቡና ልማቱ ለማስገባት ምን እየተሰራችሁ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡– ከዚህ ቀደም ተደራጅተው የነበሩ እና ጥሩ ውጤት ማምጣት የቻሉ ወጣቶች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን የማስፋፋትና ሀብት የማፍራት ፍላጎቶች አሉ። ያለውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደፊት የምንሰራቸው ስራዎች አሉ። ነገር ግን መምሪያው የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው የእለት ጉርሳቸውን ማሟላት ያልቻሉ ወጣቶችን በማደራጀት ላይ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- መሬት አላቂ ሃብት ነው። በመሆኑም ሁሌ ወጣቶችን እያደራጁ መሬት መስጠት አይቻልም። ስለሆነም የስራ እድል ተፈጥሮላቸው የተለወጡ ኢንተርፕራይዞች ለሌሎች የስራ አጥ ወጣቶች ስራ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡– ለዚህ መፍትሄው ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ነው። ለምሳሌ አንድ እና ሁለት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩ ስራ አጥ ወጣቶችን በእጅጉ ሊቀንሱ ይችላሉ። በመሆኑም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራን ነው።
ለምሳሌ በበጀት ዓመቱ በዞናችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንፈጥራለን ብለን አቅደን በስድስት ወራት ውስጥ እቅዳችንን ማሳካት ችለናል። እንጨት መሰንጠቂያ፤ አዳዲስ ዲዛይን የሚሰሩ የልብስ መስፊያ መሳሪያዎችን እና የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች አስገብተናል። እነዚህ የተወሰኑ ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት ይችላሉ። በእነዚህ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።
ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ በዞኑ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችም አሉ። የውሽ ውሽ የሻይ ቅጠል ማምረቻ ጨምሮ በርካታ የቡና ኢንዱስትሪዎች አሉ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የተማረ የሰው ኃይል ሲፈልጉ የሚጠይቁት የዞኑን የስራ እድል ፈጠራ መመሪያን ነው። እኛ ደግሞ ቀደም ብለን በዞኑ ያለውን የሰው ኃይል ዳታ ስለምንይዝ ኢንዱስትሪዎች ሰራተኛ በጠየቁን ጊዜ እናቀርባለን ። በዚህም የሰው ኃይል የገበያ ትስስርን በመፍጠር ስራ ፈላጊ ወጣቶችን እና ቀጣሪ ድርጅቶችን በቀላሉ እናገናኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በኢንተርፕራይዝ ለስራ ዕድል ፈጠራው የብድር አቅርቦቱ ምን ይመስላል?
አቶ ሚሊዮን፡– ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ያለው ነገር ሲታይ ሰፊ ችግር አለበት። እስካሁን ባለው ሁኔታ ለወጣቶች ብድር ሲያቀርብ የነበረው አሁን ላይ ወደ ባንክ ያደገው ኦሞ ባንክ ነው። አሁን ያለውን የብድር ፍላጎት ከማሳካት አንጻር በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል። በዚህም ሳቢያ በየጊዜው ቅሬታዎች እየተነሱ ነው። ይሁን እንጂ የብድር አማራጩን ሳይዘጋ በጋራ እየሰራን ነው። ብድር ለኢንተርፕራይዞች ቅድሚያ ከመስጠት አንጻር ኦሞ ባንክ አካባቢ ያለውን ችግር በኮሚቴ እየተገመገመ ለማስተካከል እየተሞከረ ነው፡፡
እስካሁን ያሉት ኢንተፕራይዞች በኦሞ በኩል የተሻገሩ ስለሆኑ ባለ ውለታ ነው። ምክንያቱም የሚጠይቀው የውል ስምምነት የኢንተርፕራይዙን የነዋሪነት ዋስትና የሚወስድ ነው። ይህን ግን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርግን አልተጠቀምንበትም። በተለይም ከተሞች አካባቢ ላይ ሌሎች አማራጮችን መፍጠር አለብን በሚል ‹‹አንድ መስመር›› የሚል ፕሮጀክት አለ። በዚህም በተለይም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ የሚታወቅ ሲሆን ሌሎች በሴቶች ብቻ የተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞችን በተለየ ሁኔታ የሚደግፍ ፕሮግራም ነው። ይህም ከዳሽን፤ ከአዋሽ፤ ከህብረትና ከአቢሲኒያ ባንኮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ኢመደበኛ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መደበኛ ኢንተርፕራይዝነት ማምጣት እየተቻለ ነው። ለምሳሌ እንደ ጀበና ቡና እና መሰል ኢመደበኛ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መደበኛ ኢንተርፕራይዝነት ማምጣት ተችሏል፡፡
ለመነሻ የሚሆን እስከ 30 ሺ ብር ድረስ ብድር ይሰጣል። ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እስከ 150 ሺ ብር፤ ለመካከለኛ እስከ 300 ሺ ድረስ እያለ እስከ መጨረሻው ጣራው 700 ሺ ብር የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። ለአዳዲስ ስራ ዕድል ፈጠራ ብድር የሚያመቻቹ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር በጋራ እየሰሩ ነው። ስለዚህ ኢንተርፕራይዞችን ለማሳደግ አንድ አቅጣጫ ላይ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አማራጮችን በማየት ላይ የተመሰረተ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀማችሁ ኢንተርፕራይዞችን የብድር አቅርቦት ጥያቄ መልስ መስጠት እየተቻለ ነው ለማለት ያስደፍራል? የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ምን ይመስላል?
አቶ ሚሊዮን፡– ይህ ማለት የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ጥያቄ መልስ መስጠት ተችሏል ማለት አይቻልም። እናም አሁንም ከፍተኛ ስራ መስራትን የሚጠይቅ ነው። የኢንተርፕራይዞችን የደረጃ ሽግግር ጤናማ እንዲሆን መምሪያው በእቅድ በማካተት ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና በማብቃት ችግሩን በመፍታት ሽግግራቸው ጤናማ እንዲሆንና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ የማሸጋገር ስራዎች እየተሰሩ ነው። ከታች አንድ ጀማሪ ኢንተርፕራይዝ የሚገባ ከሆነ በሚገባው ልክ ከነበረው ቦታ ማስለቀቅ መቻል ይጠይቃል። ለምሳሌ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሲገባ በሚገባው የተማሪ ቁጥር ልክ ከአንደኛ ተማሪ ወደ ሁለተኛ ክፍል መሸጋገር አለበት። ነገር ግን ቦታውን ይዞ የሚቀመጥ ከሆነ ትክክል አይደለም። የተለያየ መልክ ያለው ድጋፍ በየደረጃው ባሉ ኢንተርፕራይዞች ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል። ዛሬ ላይ ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ በርካታ ኢንተርፕራይዞች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ኢንተርፕራይዞች ለማደራጀት የሚውለው ሀብት አላቂ እንደመሆኑ መጠን በጥናት ላይ የተደገፈ የማደራጀት ስራ ለማከናወን ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡– ሀብት አላቂ ነው። በተለይ ደግሞ ከሚያልቁት ሀብቶች የተፈጥሮ ሀብት አንዱ ነው። ለምሳሌ የወጣቱን የመሬት ፍላጎት ሁልጊዜ መሬት እየተሰጠ መመለስ አይቻልም። በጠባብ መሬት ላይ እንዴት ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል በግለሰብ ደረጃ ብቻም ሳይሆን በቡድን መጥተው የሚለወጡበትን ፓኬጆች ቀርጾ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ እየተሰራ ነው። ለአብነትም የንብ ማነብ ስራ በተወሰነ ካሬ ሜትር ላይ በርካታ ወጣቶችን በማደራጀት ብዙ የማር ምርት መሰብሰብ ይቻላል። ለዚህም የክልሉ የአየርና የስነ ምህዳር ሁኔታ እጅግ በጣም ምቹ ነው።
ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር በጥናት ላይ በመመስረት ማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት መጠቀም ተገቢ ነው። ለምሳሌ አንድ ሄክታር ሁለት ሄክታር እያሉ ከመስራት ይልቅ እንደ ሜካናይዜሽን ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን ያስችላል። አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየመጣ ካለው የስራ ፈላጊ ዜጋ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ሀብት በቀጣይ እየተነበዩና እተዘጋጁ መሄድ አስፈላጊ ነው። ከቢሮው አቅም አኳያ ሲታይ እንኳን የእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታን እየተሰራበት ያለው ከመንግስት በተገኘ 10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ሸዶችን በመስራት 400 ለሚደርሱ ወጣቶችን የስራ እድል መፍጠር አስችሏል። ነገር ግን በእርሻ መስክ ቢሆን 400 ወጣቶችን ማቀፍ የቻለው ሸድ ለአንድ ወጣት አይበቃም። ስለዚህ የኢንተርፕራይዝ ፓኬጆቹ በጠባብ ቦታ ላይ ምን ያህል ውጤታማ ስራ መስራት ይቻላል የሚለው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንተርፕራይዞች የሚያፈሩትን ሀብት በትክክል ማስተዳደር እንዲችሉ መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው ስልጠና እና መሰል የአቅም ማጎልበቻ ስራዎች ከመስራት አንጻር ምን እየሰራ ነገር አለ? በቀጣይስ ምን ታስቧል?
አቶ ሚሊዮን፡- ክህሎታቸውን ለማጎልበት ሁለት አይነት ስልጠና ይሰጣል። አንደኛው የቢዝነስ ማሳደጊያ ሲስተም ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በዚህም የሚያገኙትን ገንዘብና የሚያስተዳድሩትን ሀብት በሚፈለገው መንገድ በመምራት እንዴት ውጤታማ እንደሚሆኑ የሚስገነዝብ ነው። ይህን ስልጠና መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በመተባበር በጋራ የሚሰጥ ነው። ሁለተኛው አሁን እየተፈጠረ ያለው ስራ ዕድል ከአዲሱ የስራ ዕድል ፈጠራ እሳቤዎች አንዱ ‹‹ክህሎት መር›› የሆነ የስራ ዕድል ነው። 11 የሚሆኑ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል እሳቤ አለ። ይህ ስልጠና የሚሰጠው በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች ነው። ለምሳሌ ስልጠናው ለሁሉም ኢንትፕራይዞች ይሰጣል። ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በተሰማሩበት የስራ ዘርፍን መሰረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ዘርፎቹን የተመለከተ የስራ ዕድል ፈጠራ ክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና እንደ አስፈላጊነቱ ይሰጣል። በዞኑ 6 የሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አሉ። በእነዚህ ኮሌጆች በየዞኑና በየከተማ አስተዳደሩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።
አዲስ ዘመን፡- ስራዎች ሲሰሩ ፈተናዎች አሉና ከፋይናንስ እጥረቱ በተጨማሪ ምን ምን ፈተናዎች ገጠሟችሁ?
አቶ ሚሊዮን፡– በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች አሉ። ችግሮችን መሻገር የሚቻለው ስራ ሲሰራ ነው። ስለዚህ ወጣቶችን ወደ ስራ ከማስገባት አንጻር የአመለካከት ችግር አለ። ለምሳሌ ስራ የማማረጥ ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት ልጁን ከአስተማሪው ማህበረሰብ ጀምሮ ቅጥርን ከመጠበቅ ይልቅ ተደራጅተው የራሳቸውን ስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች አሉ። በዞኑ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማህበር ተደራጅተው ምርት በማምረት ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ኢንተርፕራይዞች አሉ። ነገር ግን ይህን አይነት ዕድል አልፈልግም በሎ የመንግስት ቅጥር በመፈለግ ከሶስት ዓመት በላይ የቤተሰብ ጥገኛ የሆነ ዜጋ አለ። በአጠቃላይ የተገኘውን የስራ ዕድል ከመጠቀም ይልቅ የማማረጥ ስራ የዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ ችግር ነው፡፡
በሌላ በኩል ስራ ዕድል የመፍጠር የመንግስት ድርሻ ብቻ አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ አለ። ተምሮ የተመረቀውን ልጄን ስራ ማስያዝ ያለበት መንግስት ነው የሚል የተዛባ አመለካከት አለ። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ መለወጥ መቻል አለብን። መንግስት መሬት ከሰጠ የእርሻ በሬ አባት፤ ወንድም አጎት መስጠት አለበት። እነዚህን ችግሮች ተከታትሎ ከመቅረፍና ወደ ውጤት ከማሸጋገር አንጻር ከቢሮው ጀምሮ የአመራር ቁርጠኝነት ውስንንት አለ። በስራ ዕድል ፈጠራ አመለካከት የታነጸ የሰው ኃይል እጥረት ሰፊ ችግር ነው።
ሌላው ችግር ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸው ለገበያ የሚያቀርቡበት እንደ መንገድ ያሉ የመሰረተ ልማት አማራጮች መጥፋት ነው። ለምሳሌ ሕይወት እንዲቆይ ተብሎ ወደ ስራ የገባ ሰው ስራ ሰርቶ ምርቱን ወደ ገበያ የሚያቀርብበት መንገድ ያስፈልገዋል። የጤና ተቋም፤ ትምህርት ቤትና መሰል መሰረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ። ይህን ከማድረግ አንጻር ክልሉ አዲስ ከመሆኑ አንጻር መሰረተ ልማቶችን በተጠየቀው ፍጥነት ለማድረስ የአቅም ውስንነት አለበት፡፡
ለአብነት መጥቀስ ቢቻል ሺሾወንዴ ወረዳ ላይ በወጣቶች ሰፈራ ብቻ አምስት ቀበሌዎች ተፈጥረዋል። በእነዚህ ቀበሌዎች ትምህርት፤ ጤና ጣቢያ፤ መንገድ የለም። በቀበሌዎቹ እናቶች ምጥ ሲያዙ ወደ ጤና ጣቢያ በቃሬዛ የሚወስዱበት ሁኔታ አለ። እነዚህን ችግሮች በቀጣይ በጋራ መፍታትን ይሻል።
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት የፋይናንስ አማራጮችን ከማስፋት አንጻር ምን አይነት አሰራሮችን እየተከተላችሁ ነው?
አቶ ሚሊዮን፤– ለምሳሌ ልማት ባንክ፤ ደቡብ ካፒታል የሊዝ ማሽን ውል በመግባት እያቀረቡ ነው። 20 በመቶ በማስቆጠብ 80 በመቶ ብድር የሚመቻችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ‹‹ኮላተራል›› ተደርጎ የሚሰጠው ማሽን ነው። በእነዚህ እና መሰል ችግሮች የፋይናንስ ችግሮችን እየፈታን ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሊዝ ማሽን ለኢንተርፕራዞች ፋይናንስ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። በደቡብ ካፒታል ደግሞ ዳቦ ማሽኖችን ለኢንተርፕራይዞች ማሰራጨት ተችሏል። ኦሞ ባንክ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተሰራጩ ብድሮችን የማስመለስ ስራ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንተርፕራይዞች ከሚፈተኑባቸው ቸግሮች መካከል የተሰራጩ ብድሮችን መመለስ ነውና ይህን ችግር ከመሻገር አንጻር ቢሮው እንዴት እየሰራ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡- የተሰራጩ ብድሮችን ማስመለስና መመለስ ከፍተኛ ፈተና አጋጥሟል። ውይይት ተደርጎ ብድሮች በጊዜ ገዳባቸው እንደሚለሱ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህ ሳቢያም በ15 ቀን ውስጥ ብቻ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የተሰራጨ ብድር ማስመለስ ተችሏል። ብድር ሲወሰድ ውል አለ፤ በውሉ መሰረት ብድር መመለስ ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ የብድር አስመላሽ ግብረ ኃይል በማቋቋም በዘመቻ መልክ ይሰራል። ባለፈው በጀት ዓመት 32 ሚሊዮን የተሰራጨ ብድር ማስመለስ ተችሏል። በዚህ ዓመት በገጠርና በከተማ 26 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰራጭቷል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ሚሊዮን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
በመልካም አስተዳደርና ምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም