ልምድ ሊወሰድበት የሚገባው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት

ለዛሬው ዓለም ሰው “የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት” አዲሱ አይደለም። ካልሰለቸው በስተቀር ሲሰማው ውሎ ሲሰማው አድሯል፤ ኖሯልም። ድምፃዊው “ታዲያ ምን ያደርጋል · · ·” እንዳለው ሁሉ፣ የዛሬው ዓለም ሰው የሰማውን ከመስማት በስተቀር ወደ መሬት፣ ወደ ምድር አውርዶ ተግባራዊ ሲያደርገው አይታይም። ጭራሽ በተገላቢጦሹ ሲረዳውና ሲያደርገው ነው የሚስተዋለው። ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ ልተወውና ወደ ተነሳሁበት ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ ልመለስ።

ሰሞኑን ለሥራ ጉዳይ በርዕሴ ወደ ጠቀስኩት አካባቢ ሄጄ ነበር። ስሄድ የነበረኝ ስሜት ስመለስ አለመኖሩ እንጂ ድካሙ ያው ድካም ሲሆን፤ ብርታቱ ደግሞ የአካባቢው ሰላም የወለደው ጥንካሬ ነው።

ከድህረ – 1983 ጀምሮ መቼ ሰላም ሆኖ ያውቅና ነው ካልተባለ በስተቀር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ለሰሚው ግራ፣ ላገሩ ባዳ የሆኑ ክስተቶች ሲስተዋሉ መቆየታቸው ይታወቃል። ምክንያታቸውን በውል ባናውቅም አንዱ በአንዱ ጣት ሲቀሳሰር ስለመዋሉም የአደባባይ እውነት ነው።

ይህ ጣት መቀሳሰር፤ ሕዝብን እያስታከኩ (በሕዝብ ስም) ጠብ ያለሽ በዳቦ እንቅስቃሴ ከላይ በርዕሳችን የገለፅነው አካባቢ (ክልል)ንም ይመለከታል። ይመልከተው እንጂ እዛው መቀሳሰር ላይ ተቸክሎ አልቀረም። ጠመንጃውን እንደ ነከሰም ያዙኝ ልቀቁኝ አላለም። ጠረጴዛን የመሀል ዳኛ አድርጎ ክብ ሰርቶ ተቀመጠ እንጂ የያዝ፣ ልቀቅ፣ ተኩስ · · · ድቤን ሲደልቅ አልተገኘም። ግልፅ እናድርገው።

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ክልሎች ክልል ነው። እንደውም ከሌሎች ክልሎች አኳያ ሲታይ በብዙ መልኩ የተጎዳ ክልል ነው። የዛሬው ጉዳያችን እሱ አይደለም እንጂ ይህንን በብዙ መልኩ መናገር እና ማሳየት ይቻላል።

የዛሬውን እንቅስቃሴ አይተን እንደምድም ካልተባለ በስተቀር ከምር ወደ ኋላ የቀረ አካበቢ ጥቀሱ ቢባል ክልሉ አንዱ ስለ መሆኑ መጠራጠር አይቻልም። እዚህ ጋ ጉዳዩ አስቂኝ የሚሆነው ወደ ኋላ የቀረው ከሀገሪቱም ባለፈ ለሌላው ሁሉ መትረፍ እሚችሉ፣ እነ ወርቅን የመሳሰሉ ማእድናትን በውስጡ ታቅፎ መሆኑ ነው።

ይሁን እንጂ፣ ቀደም ካሉት ጊዜያት በባሰ የ83ቱ “ለውጥ” ለውጥ ከተባለ በኋላ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መከራ ሲያዩ ከቆዩት ክልሎች አንዱ ነው። የዛን የተባረከ፣ ቅን፣ አልማጅ፣ ታማኝ (ለሱዳን ጥቂት የቀራት ኩምሩህ የጣልኩትን ታብሌት አሶሳ ስደርስ አስታውሼ ተደዋውለው በማግስቱ እጄ መግባቱን መናገር ግድ ይሆናል) ሕዝብ ስም በሚያጎድፍ መልኩ ግጭቶችና ጭካኔ የታየባቸው መገዳደሎች የተካሄዱበት ክልል ነው።

ያንን ሁሉ አልፎ ግን ዛሬ እንደዚሁ ክልል የግጭት አዙሪት ውስጥ ከገቡት ክልሎች ቀድሞ ወደ ሰላም በመመለስ የልማት ሥራው ላይ አተኩሮ እየሠራ የሚገኝ ሕዝብ ነው። በወገናቸው ላይ ሲተኩሱ የነበሩትም እንደዛው። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤

ሁላችንም በቅርብ እንደምናውቀው፣ በየማህበራዊ ገፁ ሳይቀር ሲመላለስ እንደነበረው፤ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ ከአካባቢውም አልፎ ለሁላችንም አስጊ የሆኑ ሁኔታዎች ተከስተው የንፁሀን ደም ፈሶ ነበር። በአካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ ክፍፍል ተፈጥሮ ያልተፈለገ መስዋእትነት ተከፍሎ ተመልክተናል፤ የሚመለከታቸውም ነግረውናል። ያ ዛሬ የለም።

“ተጠቃሚ አልሆንኩም፣ ሥራ የለኝም፣ ተገለልኩ” በሚል ሰበባ ሰበብ ወደ ጫካ ሄዶ መልሶ ወገን ላይ መተኮስ እንደ ፋሽን ተይዞ ሲሰራበት የነበረው ክልል ዛሬ፣ እድሜ ለጠረጴዛ ውይይት ያ ሁሉ ቆሞ፤ ነገር አለሙ ሁሉ ወደ ሰላምና ልማት ተመልሷል።

ጠያይቀን ለመረዳት እንደ ሞከርነው፣ እነዚህ “ለውጡ የመጣባቸው” ፣ “ጥቅማቸው የቀረባቸው”፣ “ያኮረፉ” ወዘተ በሚሉ መጠሪያዎች የሚገለፁት ጫካ ገቦች እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች በቤንሻንጉል ጉሙዝም አንድ የሆነን ሕዝብ በማጋጨት ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሰዋል፤ ሥራ አስተጓጉለዋል፤ ምርት እንዲቀንስ አድርገዋል፤ በእነሱ ምክንያትም የተወሰኑ አካባቢዎች ከልማት ወደ ኋላ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ እድሜ ለተከታታይና እልህ አስጨራሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ይሁንና ዛሬ በክልሉ ይሄ ሁሉ የለም።

በክልሉ ያሉ ወጣቶች የተነገራቸው ሁሉ እውነት መስሏቸው ጥቂቶችን ተከትለው ወደ ጫካ በመግባት ለብዙኃኑ መከራ ሆነው የነበሩ፤ ከሕዝቡ ወጥተው መልሰው ወደ ሕዝቡ ይተኩሶ የነበሩ፤ ዛሬ እድሜ ለጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ይሁንና በልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ከራሳቸውም አልፈው ቤተሰቦቻቸውን በመጥቀም፤ ወርቅ ሳይቀር በማፈስ ላይ ናቸው።

ቀደም ሲል፣ በሀገሪቱ እዚህም እዛም እሳት በሚነድበት ወቅት በክልሉም ተመሳሳይ ችግሮች እንደነበሩ አይዘነጋም። በእነዚህ ችግሮች ምክንያትም በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ መንቀሳቀስ በአዋጅ የተከለከለ እስኪ መስል ድረስ አስቸጋሪ ነበር። ዛሬ ግራና ቀኝ ያሉት እንደሚመሰክሩት፣ እድሜ ለጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ያ ሁሉ ቀርቶ ቢያንስ በክልሉ 100 ፐርሰንት በነፃነት መንቀሳቀስ ተችሏል። ጠይቀን እንደተረዳነው ብቻም ሳይሆን፤ በጠቀስነው ሥራ ምክንያት ተዘዋውረን እንደ ተመለከትነው ያለ ምንም እንከንና ስጋት መንቀሳቀስ ይቻላል፤ ችለናልም።

እርግጥ ነው፣ ነገሮች በስመ ክልል በመታጠራቸው ምክንያት በጋራ የመሥራቱ ጉዳይ እየላላ መምጣቱ ፀሐይ የሞቀው ብቻ ሳይሆን ያቃጠለው እውነት ነው። በመሆኑም፣ አንዱ ያደረገውን ሌላኛው ባለ ማድረጉ ምክንያት፤ ወይም፣ ሳያደርግ በመቅረቱ ምክንያት ተመሳሳይ ችግሮች በተመሳሳይ ጊዜና ሁኔታ ሳይፈቱ ይቀራሉ።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ሲፈቱ፣ ያ ሌሎች ጋ አልሆነም። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራር በአጎራባች ክልሎች እየዞረ (እስከ ሱዳን የዘለቀ) ባደረገው ያልተቋረጠ ውይይት፣ ድርድርና ምክክር፤ እንዲሁም በሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ አብሮ ለመሥራት በማሰብ በደረሰባቸው ስምምነቶች ቢያንስ የራሱን ተቀናቃኞች አሳምኖ የውስጥ ሰላሙን ማስፈን የቻለ ቢሆንም፤ የክልሉ ሕዝብ ወደ አጎራባች አካባቢዎች በቀላሉ መንቀሳቀስ ግን አልተቻለውም። ይህ የሚያመለክተው እንደ ሀገር ለተሟላ ሰላም በጋራ መስራት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ነው።

በሥራ አጋጣሚ ተዘዋውረን ከተመለከትነው በተጨማሪ ከክልሉ መሪዎች እንደተረዳነው ከክልሉ ወጥተው መልሰው ክልሉን ሲያደሙ ከነበሩት ወገኖች (አብዛኞቹ ወጣቶች) ጋር በተደረገ ተደጋጋሚ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በተደረሰ መተማመን ጫካ ገብተው ወደ ወገናቸው ሲተኩሱ ከነበሩት መካከል ከ90 በመቶ በላይ ወደ ሰላም ተመልሰው፤ ተደራጅተውና ወደ ሥራ ተሰማርተው ከራሳቸውም ባለፈ ቤተሰቦቻቸውን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፤ በባህላዊ መንገድ ወርቅ ወደሚያመርቱት ጋ ሄደን የተመለከትነውም ይህንኑ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You