30 ዓመታትን የተጓዘው የቤጂንግ ስምምነት

የሃገር ካስማ የሆኑትን ሴቶች ልናነሳ ስንወድ ከእናታችን ሄዋን ብንጀምር ቅር የሚሰኝ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ባለ ድንቅ ጥበቡ ፈጣሪ ከአዳም ጎን ሄዋንን ሲሰራ ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ ስላልወደደ ነበር። የምድር ሚዛን ተጠብቆ እንዲቆይ ሴትነት እኩሌታውን የሕዝብ ክፍል ይዞ ይኖራል።

ሴትነትን ስናነሳ እህት፤ ልጅ፤ ሚስት ከሚለው በላይ እናትነት በብዙሃኑ ልብ ላይ ገዝፎ ይታያል። ምድር ላይ እናቱን የማይወድ ፍጡር አለ ቢባል እናትነት ደመነፍሳዊነት መሆኑን የዘነጋ ነው።

እስከዛሬ በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሰሩ ስራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ታላቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ሴቶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል። የዚህን ችግር መጠን ለማሳየት በተለያዩ ዓለማቀፍ ጥናቶች የተደገፉ አሀዛዊ መረጃዎች እንመልከት።

በሴቶች እና በወንዶች ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት ስንመለከት፤ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ ከወንዶች በ23 በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። የሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልናም ዝቅተኛ ነው። በፓርላማ ውስጥም መቀመጫ ማግኘት የቻሉት 24 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው። ሴቶች በተለያዩ መልኩ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ከሰላሳ ዓመታት በፊት የተቀበለችውን ስምምነት በመተግበር ላይ መሆኗን ትናገራለች።

ይህም የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ሲሆን ኢትዮጵያም የድርጊት መርሀ ግብሩ እ.ኤ.አ በ1995 ከወጣ ጀምሮ ይህንን ሰነድ በመቀበልና ሀገራዊ የድርጊት መርሀ ግብርም በማዘጋጀት ስትተገብር ቆይታለች።

በኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው። ከእነዚህ ጥረቶች መካከልም በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረገውና ኢትዮጵያ የተቀበለችው የቤጂንግ ስምምነት ወደ ተግባር መተርጎም አንዱ ነው።

የቤጂንግ ስምምነት 12 የትኩረት መስኮች ያሉት ሲሆን፣ በዋናነትም ሴቶች ከጤና፣ ከትምህርትና ሥልጠና፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ከአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ከሰላም፣ ከሚዲያ ተሳትፎ፣ ከድህነት ቅነሳና ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ነው።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪ ሆኖ የሚመራው የቤጂንግ ስምምነት፣ የአፈጻጸም ሪፖርት በየዓምስት ዓመቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚቀርብበት ነው። ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የተደረጉ ጥረቶችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ባካተተ መልኩ ስድስተኛውን ዙር አገራዊ ሪፖርት ለመላክ የቅድመ ዝግጅት ሥራን አጠናቃለች።

ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር 30ኛ ዓመት አገር አቀፍ ሪፖርት ከየተቋማቱ ለተውጣጡ ስትሪንግና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ይፋ በተደረገበት ወቅት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀረፁና በትግበራ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉር አቀፍ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች። ከእነዚህ መካከል የቤጂንግ መግለጫና መርሐ ግብር በዋነኛነት ይጠቀሳል።

ሚኒስትሯ አክለውም በያዝነው በጀት ዓመት የቤጂንግ 30ኛ ዓመት በማስመልከት ኢትዮጵያዊ ሀገር አቀፍ ግምገማና የሪፖርት ዝግጅትን ያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው የሪፖርቱን ጥራትና ተአማኒነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግስት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሴት አደረጃጀቶች እና የሪፖርት ዝግጅቱ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃግብር በማዘጋጀት ሪፖርቱ እንዲዳብር መደረጉን ገልፀዋል።

በመድረኩም ሀገራዊ ግምገማውንና ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ የሪፖርቱን ይዘት በመመልከት በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የአስተባባሪና ቴክኒክ ኮሚቴዎች፣ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ከሴክተራቸው አንፃር ተሰርተው በረቂቁ ያልተካተቱ ስራዎች ላይ ግብዓት ተሰጥቶበት በመጨረሻም ሀገራዊ ሪፖርቱ ይፋ ተደርጓል።

የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር የሪፖርት ዝግጅት ኮሚቴ አስተባባሪና አማካሪ ማርታ ነመራ እንዳሉት፣ ስድስተኛው አገር አቀፍ የቤጂንግ ሪፖርት ከፍ ያለ ሥራ የተሠራበትና አብዛኛዎቹ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተሳተፉበት ነው።

እንደ አማካሪዋ፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የሥራ አጥነት ክፍተት ለማጥበብና እኩል የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠራው ሥራ፣ የሥራ ዕድሉ በፊት ከነበረው የሥርዓተ ፆታ ክፍተት አንፃር መሻሻሎችን አሳይቷል።

ለዚህ ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም 41 በመቶ በሴቶች መሸፈኑ የሚጠቀስ ነው። ሆኖም የሥራ ዕድል ፈጠራው ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር አሁንም ክፍተት አለው። ካለፉት ዓመታት ከነበረው 31 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ግን፣ ትልቅ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ ከተፈጠሩ ሥራዎች 35 በመቶ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሲሆን፣ በውጭ አገር ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ደግሞ 98.6 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነውበታል።

በፆታ የተለዩ በሚመስሉ ሥራዎች ዙሪያ ያለውን ባህል ለመቀየር የተሠራው ሥራ ብዙ መሻሻሎች ታይተውበታል ያሉት ማርታ፣ ለአብነትም በትራንስፖርቱ ዘርፍ በወንዶች ብቻ ተወስኖ የነበረውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በማሽከርከር ሥራ ሴቶች ተሳታፊ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል። በዘርፉ ውስጥ 460 ሴቶች እየተሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችም ሌላው ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለሴቶች የፈጠሩ ስለመሆናቸው የተናገሩት አማካሪዋ፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተቀጠሩት 23 ሺሕ ሠራተኞች መካከል 80 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን፣ ይህም ሴቶች ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች በመሳተፍ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ማገዙን አክለዋል።

በሴክተር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሥራ ዕድል ፈጠራ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እየተሠራ መሆኑን በማስታወስም፣ በግብርና ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ ለ2.7 ሚሊዮን ሴቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

የሴቶችን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሴቶችን ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተተገበሩ፣ ሴቶች ወደ ቢዝነስ እንዲመጡና የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ኑሮዋቸውን እንዲደጉሙ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

እንደ አማካሪዋ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ የሥርዓተ ፆታ ክፍተት ከሚታይባቸው መስኮች አንዱ መደበኛ የባንክ አጠቃቀም ነበር። በአሁኑ ወቅት 39.7 በመቶ ሴቶች መደበኛ ባንክ አካውንት አላቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎችም፣ የሴቶችን የቤት ውስጥ ጫና በመቀነስና ሴቶች ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል።

እንደ አማካሪዋ፣ በሴቶች ላይ ያለውን ድህነት ከመቀነስ አኳያ በተሠራው ሥራ ለውጥ ስለመምጣቱ፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የድህነት ምጣኔም እየጠበበ መምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በትምህርትና በጤና ዙሪያ ሴቶችን ማዕከል አድርገው እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ከባለፉት አምስት ዓመታት በተሻለ ለውጥ እያመጡ መሆኑን፣ የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ በአምስት ዓመቱ 41.5 በመቶ መድረሱንና ይህ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካም ስኬት መሆኑን አክለዋል።

የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር በ12 የተለያዩ የትኩረት ነጥቦች መሰረት ሀገራት በየአምስት ዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲገመግሙ የሚጠይቅ ሲሆን ኢትዮጵያም የቤጂንግ+5 ግምገማ እ.ኤ.አ በ1999፣ ቤጂንግ+10 በ2004፣ ቤጂንግ+15 በ2009፣ ቤጂንግ+20 በ2014 እንዲሁም ቤጂንግ+25 ደግሞ በ2019 በማከናወን ለሚመለከታቸው አካላት አቅርባለች።

ይህን የድርጊት መርሃ ግብር ተከተሎ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሀገር የዜጎቿን ቁጥር እኩሌታ የሚይዙትን ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እያደረገች መሆኑን በመድረኩ ተነስተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የተሻለ አፈፃፀም ላይ ብትገኘም የተለያዩ ጉድለቶች ስለመኖራቸው ተናግረዋል።

የፀጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ቀርቶ ደህነታቸውን ማስጠበቅ አለመቻሉም፤ በዚህ ሁኔታ ያሉ ሴቶችና ሕፃናት የትምህርት የጤናና የመሳሰሉትን ማኅበራዊ አገልገሎቶች ለማግኘት እንደሚሳናቸው አብራርተዋል።

ሴቶች ተጠቃሚነታቸው እያደገ ሲሄድ ከፍ ወዳሉ የባንክ ስርአቶች የመግባት ሁኔታቸው የተቀዛቀዘ መሆኑን፤ በሪፖርቱ እንደተቀመጠው በአሁኑ ወቅት 39.7 በመቶ ሴቶች መደበኛ ባንክ አካውንት እንዳላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በትንንሽ የፋይናንስ ሰርዓት የሚሳተፉት በርካታ መሆናቸው ተግለፇል። ሴቶችም ከፍ ወዳሉ ደረጃዎች ከመሳብ በላይ በትንንሽ ሰራዎች መገደባቸውንም እንደ አንድ ተግዳሮት ከመድረኩ ተነስቷል።

አሁንም በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች መኖራቸው በመድረኩ የተነሳ ሲሆን የእናቶችንንና የሕፃናትን የጤና አገልግሎት ሽፋን በማሳደግ ሴቶች በደህንነት የሚኖሩባት ሀገር አንድትሆን ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ከተሳታፊዎቸ ተነስቷል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተለያዩ ችግሮች ባሉባት ሀገር ውስጥ ስኬት ያስመዘገበው የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር በ12 ዘርፎች የሚታይ ለወጥ አስመዝግቧል። በዚህም በተጨባጭ ሴቶች በሀገራቸው ተገቢውን አገልግሎት አግኝተው የተሰካ ህይወት እንዲኖሩ ቀሪ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።

እኛም በተግባር የተገለፀ ሴቶችን በተለያዩ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ማኅበረሰብ እየፈጠርን የጋራ ሀገራችንን በጋራ እናሳድግ እንላለን፤ አበቃን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You