ሰኔና አርሶ አደሩ …

ለኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም ያለው የሰኔ ወር እነሆ ገባ። የግንቦቱ የጸሀይና የሙቀት ይህን ተከትሎ የሚከሰት አቧራማ ወቅት እያበቃ የክረምቱ ወቅት ለመግባት መንደርደር የሚጀምርበት ነው። እናም ዝናብ፣ ጭቃ፣ ብርድ፣ ጉም የመሳሰሉት ይህን ወር ይዘው ብቅ ይላሉ። የበጋው ወቅት አለባበስ ፣ አመጋገብ፣ አዋዋል ፣ወዘተ በዚህ ወር መቀየር ይጀምራል።

ሰኔ ለአርሶ አደሩ / ለግብርና ሥራው/፣ ሰኔ ለተማሪው፣ ሰኔ ለበጀት መዝጊያው… ወዘተ ልዩ ትርጉም አለው። አርሶ አደሩ ለመኸር እርሻ ያዘጋጀውን ማሳ በዘር መሸፈን የሚጀምርበት፣ ለሌላ ማሳን በዘር የመሸፈን ሥራ የሚያዘጋጅበት፣ ግብዓት ዝግጁ የሚያደርግበት ወቅት ነው።

በትምህርቱ ዘርፍም ሰኔ ልዩ ትርጉም አለው። የዓመቱ ትምህርት ማጠቃለያ ወቅት ነው። ተማሪው የዓመቱን ትምህርት አጠናቆ ፈተና የሚቀመጥበትና አላፊ ወዳቂው የሚለይበት መሆኑ ይታወቃል። ከፊት ለፊቱ ወደ ሚመጣው ረጅሙ የእረፍት ጊዜ ለመግባት የሚንደረደርበትም ነው።

ለመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም ልዩ ትርጉም እንዳለው ይታወቃል። መሥሪያ ቤቶቹ ከዓመቱ ሥራቸው የቀረ ካለ ሌት ተቀንም ብለው ቢሆን ለማጠናቀቅ የሚረባረቡበት በዚሁ ወር ነው። በተለይ ከበጀት አኳያ ለዓመቱ ከተመደበ በጀት የቀረ ገንዘብ ካለ ያንን ገንዘብ ያንንም ያንንም በመግዛት ተመላሽ እንዳይሆን በማድረግ ቀን ተሌት የሚደክሙበት ወቅት ሆኖ ነው የኖረው። ከዓመታት በፊት የተፈጠረው የማእከል ግዥ ሥርዓት ያመጣው ለውጥ ካለ እንጃ የተኖረው በዚሁ መልኩ ነው። አሁንም በአንዳንድ ተቋማት ግዥ ተበራክቶ የሚታይበት ይስተዋላል፤ ይህ ሁኔታ ችግሩ አሁንም እንዳለ ያመለክታል።

ይህ ጽሁፍ ተማሪውንም፣ መንግሥታዊ ተቋማትንም አርሶ አደሩንም ነካ ነካ አደረገ እንጂ ጉዳዩ ከአርሶ አደሩ ጋር ነው። ይህ ወር የክረምት ወቅት የሚገባበት፣ ለሀገራችን አርሶ አደር ደግሞ ልዩ ስፍራ ያለው ነው። አርሶ አደሩ በሰኔ ዋዛ ፈዛዛ አያውቅም። ሲሰነጥቅ፣ ሲከሰክስ፣ ሲያለሰልስ የቆየውን ማሳ ለዘር ዝግጁ የሚያደግበትና በዘርም የሚሸፍንበት ታላቅ ወሩ ነው። ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል አንዲሉ ሰከፍ ገበሬ ካልሆነ በቀር በዚህ ዋዛ ፈዛዛ ላይ ጊዜውን የሚያጠፋ አርሶ አደር የለም።

የኢትዮጵያ አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን ይህ ወር ከሕይወታቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያውቃሉ። ከዚህ ወር ያመለጠ የግብርና ሥራ ዋጋ እንደሚያስክፍል በሚገባ ያውቃሉ፤ ለዚያውም ትልቅ ዋጋ። አበው ‹‹አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም›› ማለታቸውም ለእዚሁ ነው።

የዚህ ዘመኑ የሀገራችን አርሶ አደር እንደ ከዚህ ቀደሙ አይደለም፤ የመኸር አዝመራውን በታህሳስና ጥር ሰብስቦ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ አይደለም። በበጋውም ባተሌ መሆን ከጀመረ ቆይቷል። የመስኖ እርሻው፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃው እየተስፋፉና እየገሎበቱ መምጣት፣ የበልግ እርሻው መስፋፋ እንደ ቀድሞው አያስቀመጡትም።

እናም ባተሌ ሆኖ እንደቆየ ሁሉ አሁንም ባተሌነቱን ይበልጥ ወደሚያጠናክረው ሰኔ ነው የገባው። በዚህ ሁሉ ሥራ ውስጥ ቆይቷልና የሰኔ ወር ለእሱ ምኑም አይደለም አይባልም፤ ሰኔ ዱሮ ቀረ ሊባል አይችልም።

እንደሚታወቀው የሀገራችን የእርሻ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል። በየአመቱ የሚገኘውም የግብርና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ለእዚህም በመኸር እርሻ ከሚመረተው ስንዴ በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተመረተ ያለበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

በየዓመቱ የማሳ መጠን ይጨምራል፤ የኩታ ገጠም ማሳ ሄክታር መጨመሩን ቀጥሏል፤ አሲዳማ መሬት ማከም አለ። በዚህ ላይ አንድም ማሳ ጦም ማደር የለበትም በሚል እየተሠራ ነው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ረግረግ መሬት ሳይቀር በሰብል መሸፈን ተጀምሯል።

ከአንድ ማሳ በዓመት ከአንዴ በላይ ወደ ማምረት ተገብቷል። የአንድ ሰብል አዝመራ አንስቶ ሌላ ሰብል መዝራት ተለምዷል። የበልግ አዝመራ ተሰብስቦ የመኸር እርሻ ሥራ ይቀጥላል። የመኸር አዝመራ ተሰብስቦ የበጋ መስኖ ስንዴ እና አትክልት ልማት ይቀጥላል። በዚህ ላይ እንደ አቮካዶ ያሉ ቋሚ ፍራፍሬ ተክሎችን መንከባከብ አለ። አረንጓዴ ዐሻራ አለ።

በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ

ያለበት ሁኔታ የመጣው በእዚህ ሁሉ ርብርብ ውስጥ እንደመሆኑ፣ ይህ አይነቱ የግብርና ሥራ በአርሶ አደሩ በአጠቃላይም በግብርናው ዘርፍ ላይ ትልቅ የባህል ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ ነው።

ይህ አይነቱ አጠቃላይ ርብርብ አሁን ደግሞ በተለይ በእዚህ የመኸር እርሻ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በዚህ ወቅት ማሳ ይዘጋጃል፤ እንዲለስልስ፤ በዘር እንዲሸፈን ይደረጋል፤ ማረምና መኮትኮት የሚፈልጉትም ይታረማሉ ፤ ይኮተኮታሉ። የአረንዴ ዐሻራ ሥራዎች ደግሞ ሌሎች ግዙፍ ሥራዎች ናቸው።

በሀገራችን የእርሻ ሥራ የሚካሄድባቸው ወቅቶች ጨምረዋል። አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን የግብርና ባለሙያውና ሌሎች ተዋንያኖች ዓመቱን ሙሉ ባተሌ የሚሆኑበት ዘመን ላይ ተደርሷል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው፤ ያ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን የመኸር እርሻ በሀገራችን ግብርና ምርት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እንደመሆኑ ለእዚህ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።

ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩም ነውና በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ አርሶ አደር ሰኔ ግብቷል ተነስ ታጠቅ የሚባል ባይሆንም ምን ያህል ከፍተኛ ሥራ በዘርፉ የሚሠራበት ወቅት መሆኑን በማስገንዘብ እሱን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይበልጥ ማንቃት ግን ይገባል። አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም ብሎ አርሶ አደሩን ማንቃትም ይጠቅማል፤ የትኛውም አርሶ አደር በምንም አይነት መልኩ በእዚህ የግብርና ሥራ በከፍተኛ ርብርብ ሊካሄድ በሚገባው ወቅት ከግብርና ሥራው ሊረቅ አይገባውም።

ይህ የክረምቱን ዝናብ በመጠቀም የሚካሄድ የግብርና ሥራ ዝናቡን በሚገባ ለመጠቀም ዝግጁ ሆኖ መገኘትን የግድ ይላል። የዝናቡን ፋይዳ አስመልክቶ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ለአርሶ አደሩ የሚነገረው አይደለም፤ ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የሚኖሩ ለውጦች መኖራቸው ግን የአርሶ አደሩን የዳበረ ልምድ እየረበሹት እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህ እንዳይሆን የሜትሮሎጂ እና የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎችን እየተከታተሉ የግብርና ሥራውን እንዲሠራ ምክር መለገስ ሥራውን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል።

የማሳን እርጥበት መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች አስቀድሞ እንዲከናወኑ፣ ማሳን በዘር የመሸፈኑም ሥራ የግብርና ሚኒስቴርና የሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩትን መረጃዎች ተከትለው እንዲፈጸሙ ማድረግ ይገባል። ተባይ መከላከልም ሌላው ዝግጁነት ተረጋግጦ የሚጠበቅበት ተግባር ነው።

የመስኖ እርሻ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የመስኖ እርሻን ለማስተዳደር ብዙም ችግር አይገጥምም። የመኸር እርሻ ግን በዝናብ መቋረጥ፣ ዝናብ ፈሩን ተከትሎ ባለመጣሉ ፣ ወዘተ፣ ሳቢያ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያርፍበት ይችላል። በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት የምክር አገልግሎቶች ያስፈልጋሉ የሚመለከታቸው አካላትም ይህን ምክራቸውን ለአርሶ አደሩና ለዘርፉ ባለደርሻዎች መለገስ ይጠበቅባቸዋል።

በዝናብ እጥረትና በመሳሰሉት ሳቢያ ቡቃያው የሚያሳስብ ደረጃ ላይ ከደረሰ ወይም ከዝናብ መቋረጥ ጋር ተያይዞ ተባይ በቡቃያ ላይ ጉዳት ካደረሰ ማሳ እስከ መገልበጥ የሚደርስ ሥራ ውስጥ ሊገባም ስለሚችል ከወዲሁ ዝግጁ መሆን ይገባል።

የዚህ ዘመን ሰኔ ለኢትዮጵያውያን የቀደሙትን ዘመናት አይነቱ ሰኔ አይደለም፤ አርሶ አደሩ ከበሬዎቹ በተጨማሪ ተደራጅቶም ይሁን ተከራይቶ በትራክተር እርሻውን ሊያካሂድ የሚችልበት እድል ሰፋ ያለበት ነው። በተለይ በኩታ ገጠም እርሻ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን ቀለል የሚያደርግ ቴክኖሎጂም በአጠገባቸው እንዳለ ይታወቃል።

እነዚህን ማሽነሪዎች ዝግጁ ማድረግ፣ ማሽነሪዎቹ በእጃቸው ካለ አካላት ብቻ ሳይሆን ከግብርናው ዘርፍ ተዋንያንም ይጠበቃል። ማሽኖቹን ልክ በአዝመራ ስብሰባ ጊዜ በተቀናጀ መልኩ ሰብል ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች በማሠማራት አዝመራ እንደሚሰበሰብ ሁሉ፣ በዘር ወቅትም ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ማሽነሪዎቹን አሰባስቦ በማንቀሳቀስ ማሳ በወቅቱ በዘር እንዲሽፍን ማድረግም ይገባል። በተለይ በመንግሥት ትኩረት የተሰጣቸው እንደ ስንዴና ሩዝ ያሉት ሰብሎች ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ብቻ እንዲዘሩና ተገቢው እንክብካቤም እንዲደረግላቸው ማድረግ ላይም መሥራት ይገባል።

ኃይሉ ሣህድንግል

አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You