በጎረቤት ሃገር ኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘውና ኢትን የተባለው ስፍራ ከኢትዮጵያዊዋ በቆጂ ጋር የሚመሳሰል ነው። ‹‹የቻምፒዮናዎች ቤት›› በሚል ቅጽል የሚታወቀው ይህ ስፍራ ለአትሌቲክስ ስፖርት የተመቸ የአየር ንብረት እና መልክዓ ምድር ያለው ሲሆን፤ በርካታ ውጤታማ አትሌቶችንም አፍርቷል። ከግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው አዲዳስን ጨምሮ በርካታ የሥልጠና ማዕከላትና ካምፖች የተገነቡበት እንዲሁም ለስፖርቱ የተመቹ መሠረተ ልማት የተሟላበት አካባቢ ነው። ይህም ከሌላ ሃገራት ለልምምድ ወደስፍራው የሚያቀኑ አትሌቶችን ጨምሮ ለበርካቶች ሳቢ እንዲሆን አስችሎታል። በአፍሪካ እምብዛም ያልተስፋፋው የስፖርት ቱሪዝም ሃሳብ በእርግጥም እየተሠራበት ያለ የኬንያውያን መመኪያ የሆነ ስፍራ ነው።
በአርሲ ዞን መገኛዋን ያደረገችው የኢትዮጵያዊዋ በቆጂም ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቲኪ ገላና፣ መስታወት ቱፋ፣ ትዕግስት ቱፋ፣ ለሜቻ ግርማ፣… የመሳሳሉት የኦሊምፒክ፣ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች ወጥተውባታል። የቦታ አቀማመጡ፣ የአየር ሁኔታው፣ ከዓመት ዓመት የሚዘልቀው የአካባቢው ልምላሜ፣ ሩጫን ባሕሉ ያደረገ የማኅበረሰቡ አኗኗር፣… ዛሬም ድረስ እየተተካኩ ላሉ አትሌቶች መፈጠር ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ካገኘቻቸው 58 ሜዳሊያዎች መካከል 18 የሚሆኑት ሜዳሊያዎች(10የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሐስ) ከዚህ ስፍራ በተገኙ አትሌቶች የተሰበሰቡ በመሆናቸውም ‹‹የሯጮቹ ምድር›› የሚል ቅጽልን አግኝቷል።
በተፈጥሮ ሃብት የታደለውና የአትሌቶች ምንጭ ከሆነው ከዚህ ስፍራ በርካታ የውጪ ዜጋ አትሌቶች ከበረከቱ ሊካፈሉ የሚመኙት፤ የአትሌቲክስ ወዳጆችም ሊጎበኙት የሚሹት ቢሆንም መሠረተ ልማት ማግኘት ያልተሟላለት በመሆኑ ምቹ አይደለም። ታዳጊ አትሌቶችም በተፈጥሮው ታግዘው በጥረታቸው ያለሙበት ለመድረስ ከመፍጨርጨር ባለፈ፤ መም ለመጠቀም ወደሌላ ስፍራ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። ከብቸኛው የበቆጂ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ባለፈ፤ አትሌቶችን ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ የኮሮኮንች መሮጫዎችም ሆነ የልምምድ ስፍራዎች የሉትም። ስታዲየሙም ከደረጃ በታች ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በዓመት አንዴ ከሚያካሂደው ውድድር ባለፈ ስፍራው የሚነሳበት አጋጣሚም የለም። ይገነባል የተባለው የበቆጂ ሙዚየምም ከሃሳብ ወርዶ እውን ሳይሆን ዓመታት ተቆጥረዋል። ለጎብኚዎች የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የማረፊያ ስፍራዎችና ሌሎች አገልግሎቶችም እጅግ ደካማ የሚባሉ ናቸው።
ይህ ሁኔታ ከጎረቤት ሃገር የኬንያዋ ኤልዶሬት ኢትን ጋር በቆጂን ለማነጻጸር አዳጋች ያደርገዋል። ለችግሩ በምክንያትነት የባለሃብቶች ተሳትፎ አናሳነት ቢነሳም ከስኬት ማማ ላይ የሚገኙ አንጋፋ አትሌቶች ውለታቸውን አለመመለስ ግን ጉልህ ድርሻ የሚሰጠው ነው። የበቆጂ ከተማ ከንቲባ ብርሃኔ ነገሰ፤ ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ የሆነውን ስፍራ በመላው ዓለም የታወቀ የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ ቢቻልም በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ሥራ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። በመሆኑም የስፍራው ተወላጅ የሆኑ አትሌቶች ላሉበት ደረጃ የበቁበትን የትውልድ ስፍራ ዞር ብለው ሊመለከቱ ይገባል። ‹‹ያኔ እነደራርቱ የሮጡበት ሜዳ አሁንም እንዳለ ነው ያለው›› የሚሉት ከንቲባዋ በየጊዜው በተሻለ ይሠራበታል ተብሎ ቃል ቢገባም በመንግሥት አቅም ብቻ ማሳካት አልተቻለም። ከበቆጂ የወጡ ትልልቅ አትሌቶች ውድድሩን ተከትሎም ግብዣ ሲደረግላቸውም ባልታወቀ ምክንያት አይገኙም። ነገር ግን በቀጣይ ሊሳተፉበት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች የሚመቻች ሲሆን፤ ባለሃብቶችም እምቅ በሆነ የቱሪዝም ሃብት በካበተው በዚህ ስፍራ ላይ በመሥራት ሃገርን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ከበቆጂ የወጡ አትሌቶች የስፖርት ቱሪዝምን በማበረታታት ረገድ በተለይ ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚገልጹት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ናቸው። ያፈራቸው ምድርና ያሳደጋቸው ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ፣ ቦታውን ማሳወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለእነዚህ አትሌቶች ግብዣ ቢቀርብላቸውም ሊገኙ አልቻሉም። ሆቴሎችን በመገንባትም ሆነ በሌሎች ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ረገድ ከአትሌቶች ባለፈ ከባለሃብቶች፣ መንግሥት እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁም አሳስበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም