“ሐረር ዳግም እየተወለደች ነው” – አቶ ኦርዲን በድሪ – የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር

የሠላም ከተማዋን ሐረር በጉያው አቅፎ በያዘው የሐረሪ ክልል የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ክልሉ በልማትም ሆነ በመልካም አስተዳደር ዘርፍ እመርታን እያሳየ ከመሆኑም ባሻገር ታሪካዊቷን ሐረር ከተማ በቱሪስቶች ተመራጭ ለማድረግም የሚሠሩ ሥራዎችም ዓይነ ግቡ ናቸው፡፡

የፍቅር እና የአብሮነት ከተማ የሆነችውም ሐረርም ከ1ሺ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ቢሆንም የእድሜዋን ያህል ሳታድግ ዘመናትን ተሻግራለች። ዛሬ ግን በመሠረተ ልማት ዘርፍ እና ተያያዥ ልማቶች እያሳየችው ያለው እመርታ ከተማዋ ዳግም የተወለደች ያህል የሚያስቆጥር ነው። ይህንንም በክልሉ የሥራ ስምሪት አድርጎ የነበረው የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ ልማቱን ለመመልከት ችሏል፡፡

በተለይ ከለውጡ ወዲህ የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ በክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦድሪን በድሪ መሪነት የጋዜጠኞች ቡድን ልማቱን ተዘዋውሮ ለመመልከት ችሏል።

በአጠቃላይ በአዲስ ጎዳና የሚገኘው የሐረሪ ክልል ከለውጡ በኋላ ባስመዘገባቸው ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር የተደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፤ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሐረሪ ክልል የተለያዩ ብሔር፤ ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ ሙዚየሞች ተገንብተዋል፤ በመገንባት ላይ ያሉም አሉ። እነኝህ ሙዚየሞች የሐረርን የሠላም ከተማነት እሴት ከማጉላት አንጻር የሚኖራቸውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ኦርዲን በድሪ፡- እንደመንግሥት ከልላችንን ብሎም ሀገራችንን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው። ከዚህ አኳያ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር የሀገራችንን ብልጽግና እውን ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን። በማኅበራዊ ዘርፉም በጥናት ላይ ተመርኩዘን የክልሉን ማኅበራዊ የልማት ሥራዎች ለማጠናከር በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው።

በክልላችን ቋሚ ሀብት እንዲፈራ ወይም እንዲፈጠር ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ ጠንክረን እየሠራን ነው። ይህን ለማድረግ በተለይ በመንግሥት በጀት የሚሠሩ የጀመርናቸው የለውጥ ሥራዎች አሉ። አንዱ የለውጥ አቅጣጫ የመንግሥትን በጀት ቋሚ ሀብትን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ ሥራ ላይ ማዋል ነው። ይህን እውን እንዲሆን ከዘንድሮ አጠቃላይ የመንግሥት በጀት 58 በመቶውን ለካፒታል በጀት መድበናል። 42 በመቶውን ብቻ ለሥራ ማስኬጃ እና ለደሞዝ ተጠቅመናል።

58 በመቶው የመንግሥት በጀት ቋሚ ሀብት መፍጠር ለሚያስችሉ ለመንገድ ሥራ፣ ለውሃ፣ ለመብራት እና ለሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲውሉ እያደረግን ነው። ይህ በጀት ለማኅበራዊ ሥራዎች ማለትም ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ተቋማት ግንባታዎች እና ለመሳሰሉት ቋሚ ሀብቶች ግንባታም የሚውል ነው።

ይህ አይነት አሠራር ቋሚ ሀብትን በማፍራት ለነገው ትውልድ የተሻለ ሕይወት ከመፍጠር አኳያ በጣም ጠቃሚ እና ተመራጭ ነው። ቀጣዩ ትውልድ መሠረታዊ ፍላጎቶች የተሟሉ እንዲሆኑ ለማስቻል ዛሬ ያለን ሀብት ለዛሬ ሳይሆን ለነገ ትውልድ የሚለውን አሠራር እንደመርሕ ወስደን እየሠራን ነው። በቀጣይም አሁን የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በማኅበራዊ ዘርፉ በተለይም ከባሕል እሴት ግንባታ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወንን ነው። እንደሚታወቀው ከባሕል ጋር ተያይዞ የነበረው እይታ የነጠላ ትርክት እይታ ነበር። ታሪካችንም የነጠላ ትርክትን መነሻ ያደረገ ነበር። ይህ ደግሞ ለአብሮነት፣ ለአንድነት እና ለትብብር የማያመች እና ለተለያዩ ችግሮች እንድንጋለጥ የሚያደርግ ነው።

ያለፈው አካሄድ የእኔ ብቻ ባሕል ተብሎ ለልዩነት እና ለመከፋፋል መነሻ የሚሆን ትርክትን የፈጠረ ስለነበር ከዚያ ትርክት እና ከዚያ እሳቤ ለመውጣት እንደ ክልል ጥረት አድርገናል። አሁን ላይ ከነጠላ ትርክት እና ከነጠላ እይታ ወጥተን ወደ ወል ትርክት እና ወደ ወል እይታ እየገባን ነው። የጋራ የሚያደርጉ እና የሚያስተሳስሩ ባሕሎች የበለጠ ለማጎልበት ልንሠራ ይገባል፡፡

ይህን መነሻ ባደረገ መልኩ የሌሎች ክልሎችን የባሕል ማዕክል እና የእንግዳ ማረፊያ በክልላችን እየገነባን ነው። ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በክልላችን በተለያዩ ቦታዎች የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ባሕል ሊያሳዩ የሚችሉ የባሕል እቃዎችን፣ አልባሳትን እና በሙዚየሞችን የማደራጀት ሥራዎች ሠርተናል። ከዚያ ባለፈ በተቻለ መጠን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የባሕል ቤቶች እንዲገነቡ አድርገናል። አሁን ላይ የሐረሪ እና የኦሮሞ የባሕል ማዕከላት ተገንብተው ሥራ ላይ ሲሆኑ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች ደግሞ የባሕል ማዕከሎቻቸውን ለመገንባት በሂደት ላይ ናቸው።

የሌሎችን ብሔር እና ብሔረሰቦች የባሕል ማዕከል በክልላችን ለመገንባት ለምን አስፈለገ? ከተባለ ምክንያቱም አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን ለማጠ ናከር ጠቃሚ በመሆኑ ነው። የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሳቤ መጎልበት ደግሞ ለዘላቂ ሠላም በጣም አስፈላጊ ነው።

በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት የመተባበር እና መደጋገፍ እሴት ለሐረር ሕዝብ የመጀመሪያው አይደለም። ሐረር የሠላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመቻቻል ከተማ ናት። ይህን ደግሞ እንዳይሸረሸር የመጠብቅ እና የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ የማድረግ ሥራዎችን ደግሞ አሁን ጀምረናል።

አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ማድረጋችን እኛን በጣም ጠቅሞናል። ትልቁ የፈጠረልን ጥቅም ምንድን ነው? ከተባለ፤ ቀደም ብሎ ሐረር የምትታወቅበትን፤ ሁላችንም በጋራ አብረን የምንኖርባት፣ የምንለማባት፣ የምናድግባት የሠላም ከተማ ናት የሚለውን እሳቤ በእጅጉ ማጎልበት የቻለ ነው። ባሕልን ለሠላም፤ ባሕልን ለአብሮነት፣ ባሕልን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከመጠቀም አኳያ ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የጀጎል ግንብን መልሶ ማልማት አንድ ትልቅ ከተማ ማልማት ነውና የመልሶ ማልማት ሀሳቡ እንዴት መጣ? ወጪውን እንዴት መሸፈን ተቻለ? እድሳቱ ለቱሪስት ፍሰቱ የሚኖረውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ኦርዲን፡- እንደሚታወቀው የሐረር ጀጎል በዩኔስኮ የተመዘገበ የዓለም አቀፍ ቅርስ ነው። ጀጎል ሲባል አጥሩ ብቻ አይደለም። በአጥሩ ውስጥ የሚኖሩ ቤቶችን፣ በቤቶች ውስጥ ያሉ ያኗኗር ዘይቤዎችን እና ባሕሎች እንዲሁም የሰዎች መስተጋብር ሁሉ እንደ ጀጎል ይታሰባል። የጀጎል ቅርስነትም ይህን ሁሉ የያዘ ነው።

ጀጎልን መልሶ ለማልማት በርካታ መነሻ ምክንያቶች አሉ። ጀጎል ከአንድ ሺህ አመት በላይ ታሪክ ያለው ነው። በጊዜ ሂደት የተነሳ በተለይም ከ20 ዓመት በፊት በነበረው ሁኔታ ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ቅርሱም ከፍተኛ ስጋት ተጋርጦበት ነበር። ይህ በቅርሱ ላይ የተደቀነው የመበላሸት ስጋት ደግሞ በእኛ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮብናል። ቅድመ አያቶቻችን ይህን ቅርስ ሠርተዋል ለዛሬው ትውልድ አበርክተዋል። ጀጎል ላይ የተፈጠረው ስጋት በእኛ ዘመን መፈጠር የለበትም የሚል ውይይት አደረግን፤ በውይይቱም ሀሳቦች ጎልብተው ወጡ። እኛ ያንን የመሰለ ቅርስ መሥራት ባንችል ለምንድን ነው መንከባከብ እና መጠበቅ ያቃተን? የሚል ከፍተኛ ቁጭት ተፈጠረ። ይህ ቅርሱን ለማደስ አንዱ መነሻ ወይም ገፊ ምክንያት ነው።

ስለዚህ ጀጎልን መጠበቅ እና መንከባከብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ሲባል አንድ አካል ብቻውን የሚሠራው ሳይሆን ሁሉም ሰው በቻለው ልክ መሆን አለበት። ከዚህ አንጻር ጀጎልን እንደገና በማልማቱ ሂደት ሁሉም የማኅበረሰባችን ክፍል የተሳተፈበት ነበር። በመልሶ ማልማቱ የተገኘው ስኬት የጋራ ስኬት ነው።

ይህን ሥራ ለመጀመር እንደአመራር ማን ይሥራው? እንዴት ይሠራ? እና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ ከፍተኛ ውይይቶችን አድርገናል። ይህን ለማድረግ መጀመሪያ የጋራ መግባባት ላይ ደረስን። ቀጥሎም አመራሩ ይህን ለማድረግ ቁርጠኝነት ነበረው። በዚህም ቀድሞ የነበረውን ስጋት መቀነስ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሥራ መሥራት እንድንችል አድርጎናል።

ከእድሳቱ በፊት በጀጎል እና ዙሪያው ከፍተኛ የሆነ የፅዳት ችግር ነበር። በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት ይፈጸም ነበር። ለቱሪስትም ፈጽሞ ምቹ አልነበረም። ለነዋሪዎቹም በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንዳንድ አካባቢዎች አይደለም ለመቀመጥ እና ለማለፍ እንኳን አስቸጋሪ ነበር።

አሁን ላይ ግን ጀጎልን ስንመለከት ሁሉም ነገሩ ተለውጧል። ለማመን የሚከብድ መሻሻሎች ታይተውበታል። አስደማሚ እና በአድናቆት እጅን በጉንጭ የሚያስጭኑ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ይህን የመሰለ ዕፁብ ድንቅ ሥራ ስንሠራ ምንም አይነት ገንዘብ ከመንግሥት በጀት አልተጠቀምንም። እያንዳንዱ ተቋም ከተመደበለት መደበኛ በጀት ቀንሶ እንዲሠራ ነው ያደረግነው። የክልላችን ዲያስፖራዎች ጨምሮ በሀገር ውስጥ ያለው ማኅበረሰባችን በስፋት ተሳትፎበታል። ወጪ ቆጣቢ በሆነ አካሄድ የጀጎል ገጽታ መመለስ ያስቻለ ሥራ ማከናወን ችለናል።

አሁን ላይ ጀጎል ከተደቀነበት ስጋት ወጥቶ ዙሪያው አልምተን አረንጓዴ አድርገነዋል። የቱሪስት ፍሰቱም ከዚህ ቀደም ከነበረበት ድባቴ ወጥቶ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

አዲስ ዘመን ፡- ከማኅበረሰቡ አኗኗር ዘይቤ አኳያ ቤቶችን እንዴት አጣጥሞ ማደስ ተቻለ?

አቶ ኦርዲን፡- ብዙ ከተሞች የራሳቸው ባሕሪ አላቸው። በአውሮፓ እና በእስያ ላይ የከተሞች ትልቁ ፈተና ቅርስ ይዘቱ ሳይለቅ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ እንዴት ማስተላለፍ ይቻላል የሚለው ነው። በሌላ በኩል የነዋሪዎችን የመዘመን ፍላጎት ግምት ውስጥ አስገብቶ ቅርሶችን ማደስ ሌላኛው ፈተና ነው።

ዘላቂነት ያለው ሥራ ለማከናወን ሁለቱን አጣጥሞ እና ሚዛኑን ጠብቆ መሥራት ያስፈልጋል። ማኅበረሰቡ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ይፈልጋል። ቅርስ እንጠብቅ ሲባል ደግሞ ይህን ማድረግ አይቻልም። ማኅበረሰቡ በጣም ዘመናዊ የሆኑ መንገዶችን ይፈልጋል። ቅርስ ሲኖር ደግሞ ይህን ማድረግ ከባድ ነው። ስለሆነም ከተማን ለማደስ የማኅበረሰቡን የመዘመን ፍላጎት እና የቅርሱን ይዘት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ገብተን ነበር።

በጀጎል ውስጥ ማኅበረሰቡ የማይኖር ከሆነ ቅርሱ ትርጉም የለውም። ሐረር ጀጎል ሕያዊቷ ሙዚየም (THE LIVING MUSEUM) የሚለውን እና የእኛን ዐቢይ መለያ ወይም ብራንድ ቦታ ያሳጣዋል። ስለዚህ ማኅበረሰቡ በጀጎል ውስጥ መኖር አለበት። በዚያ ለሚኖረው የማኅበረሰቡ ደግሞ መሠረታዊ ፍላጎቶችም ሊሟሉለት ይገባል።

አሁን የተሠራው የመልሶ ማልማት ሥራ ከዚህ በፊት ከጀጎል የወጣውን ማኅበረሰብ ይመልሳል የሚል እሳቤ አለን። ከእድሳቱ በፊት አካባቢው በጣም የቆሸሸ እና ለኑሮ የሚመች ስላልነበር ሰዎች በጀጎል መኖር አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን በጣም ምቹ ሆኗል። በመሆኑም ቢያንስ እዚያ ያለው ሰው እዚያው ይቆያል የሚል ግምት አለን ።

አዲስ ዘመን ፡- የጀጎልን እድሳት ጨምሮ በሐረር ከተማ እየተከናወኑ ባሉት የኮሪደር ልማቶች ሐረርን እንደገና ተወለደችም/ ተሞሸረችም የሚሉ አሉ። እርስዎ በየትኛው ይስማማሉ?

አቶ ኦርዲን፡- ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረን ሁኔታ ስንመለከት ሐረር የሥልጣኔ ማዕከል ነበረች። ጀጎል ላይ አሁን የምናያቸው አስደማሚ ቤቶች፣ መንገዶች እና አጥሮች በአብዛኛው ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የተሠሩ ናቸው። የቤቶቹ አሠራር፤ በግንቡ ውስጥ ያሉ ቤቶች ይዘት ስትመለከት በዚያ ጊዜ የነበረውን ሥልጣኔ ለማድነቅ ትገደዳለህ። የአጥሮቹ አቀማመጥ፣ ኪነ ሕንጻው እና የመሬት አጠቃቀም ስትመለከት እጅግ ማራኪ ናቸው ።

ሐረር በሥልጣኔው ቀዳሚ ነበረች። ለበርካታ ዓመታት ሐረር የምሥራቅ አፍሪካ የንግድ ማዕከልም ነበረች። የዓለም አቀፍ ንግድ ተካሂደውባታል። የራሷ የሆነ የመገበያያ ሳንቲሞች ወይም ገንዘብ ነበሯት። በኢትዮጵያ የራሳቸው መገበያያ ሳንቲም የነበራቸው አክሱም እና ሐረር ብቻ ነበሩ።

ነገር ግን በጊዜ ሂደት ሐረር የነበራትን ታላቅነት በተለያዩ ምክንያቶች እያጣች ሄዳለች። አሁን ደግሞ እንደገና እሱን የማደስ ሥራ ጀምረናል ። አሁን ላይ ጊዜው ለሐረር ህዳሴዋ ነው ብዬ አስባለሁ። ሐረር ዳግም እየተወለደች ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሐረር ሆስፒታል ጥንታዊ ሆስፒታል ነው። በቀደመው ጊዜ የውጭ ሀገራት ዜጎች ጭምር የሕክምና አገልግሎት ያገኙበት የነበረ ነው። አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው የጤና ዘርፍ ልማት ሜዲካል ቱሪዝምን ከማሳደግ አንጻር የሚኖረውን አስተዋፅዖ እንዴት ያዩታል?

አቶ ኦርዲን፡- በሐረር ረጅም ዓመታት የቆዩ፤ በሀገራችንም ቀደምት እና አንጋፋ የሚባሉት ብዙ ተቋማት አሉ። ከእነዚህ መካከል የሐረር ሆስፒታሎች፣ እድሜ ጠገብ ትምህርት ቤቶች፣ ፖስታ ቤት እና የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሽ ናቸው። አሁን እየተከናወነ ያለው “ከአጅፕ እስከ ደከር” ያለው የኮሪደር ልማት ሐሳቡ የመጣው እና የተጀመረው ባለፈው ዓመት ነው። ይህ ፕሮጀክት “የስማርት ሲቲ” መገለጫዎችን መነሻ ያደረገ ነው። መንገዶቹ 30 ሜትር ሰፋት ያላቸው ናቸው ። የሳይክል እና የእግረኛ መንግድ አጣምረው ይዘዋል። “ስማርት ሲቲ” ሲባል በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ሊያሳልጥ የሚችል ማለት ነው።

“ከአጅፕ እስከ ደከር” ያለው መንገድ ብቻ ሳይሆን የኮሪደር ልማትም እያከናወን ነው። ኮሪደር ስንል ደግሞ ዝም ብሎ ኮሪደር አይደለም። የተመረጠ የጤና ኮሪደር እንጂ። የጤና ኮሪደሩ ሲባል የመንግሥትንም ሆነ የግል የጤና ተቋማትን የሚያገናኝ ነው። በዚህ ቦታ የጤና ኮሪደርን እንዲሆን የመረጥንበት ዋና ምክንያት እየተሠራ ባለው ልማት ዙሪያ በርካታ የጤና ተቋማት ስለሚገኙ እነሱን ለማገናኘት በማሰብ ነው።

ልማቱ በሚካሄድበት አካባቢ የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ሀይቤድ ድንገተኛ ማዕከል፣ የፌስቱላ ሆስፒታል፣ የክልላችን የጤና ቢሮ፣ የክልላችን “ሪጅናል ላብራቶሪ” እና ብዛት ያላቸው የግል የጤና ተቋማት መገኛ ነው። ፕሮጀክቱን የጤና ኮሪደር ያልነው አንደኛ አሁን ያሉትን የጤና ተቋማት አስበን ነው። ሁለተኛ ቀጣይ በዚህ አካባቢ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጥ ከሆነ የሚሰጠው ፈቃድ በጤናው ዘርፍ ላይ ብቻ ነው ።

በአንድ አካባቢ የጤና ኮሪደሮችን መፍጠራችን አንደኛ ሕዝባችን ላይ እና ታች ሳይል፤ ሳይቸገር፤ የትራንስፖርት ወጭ ሳያወጣ አንድ አካባቢ ላይ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ስለሚያስችል ነው። ሁለተኛው በጤና ተቋማት መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እና ትብብር ለመፍጠር ታስቦ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሐረር ትልቁ አቅም ቱሪዝም ነው። በቱሪዝም ሐረር በዓለም ሀብትነት የተመዘገቡ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት። በሚዳሰስ ቅርስ የጀጎል ግንብ አለን። በማይዳሰስ ደግሞ ሸዋልኢድ አለን። ከዚህ በተጨማሪ ሐረር ከፍተኛ የሆነ የሜዲካል ቱሪዝም አላት።

እንደሚታወቀው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሐረር በምስራቅ ኢትዮጵያ እንደማዕከል ስታገለግል የነበረች ከተማ ነች። በዚህም ለጤና አገልግሎት ከውስጥም ከውጭም በርካታ ሰዎች ይመጣሉ። አሁን ላይ ከሱማሌ ላንድ በርካታ ሰዎች ለሕክምና ወደ ሐረር ይመጣሉ። ስለዚህ የጤና ኮሪደር ልማቱ ለሜዲካል ቱሪዝሙ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት ከቻልን የሜዲካል ቱሪዝሙን እውን ማድረግ እንችላለን። ይህ የረጅም ጊዜ ራዕያችን ነው። አሁን እያደረግነው ያለው የጤና ኮሪደር ልማት ለዚህ እርሾ የሚሆን ነው ።

አዲስ ዘመን ፡- የሐረር ከተማን የውሃ ችግር ለማቃለል የሚያግዙ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ሲጠናቀቁ የማኅበረሰቡን የውሃ ችግር እንደሚቀረፍ ይታመናል። ይሁን እንጂ የመብራት መቆራረጥ ለዘርፉ ፈተና ሲሆን ይታያል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ታቅዷል?

አቶ ኦርዲን፡- የሐረር የውሃ ችግር ያደረ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ይህን ችግር ለመፍታት በርካታ ጥረት ተደርጓል። ግን አሁንም መፍትሔ አላገኘም። አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ሲባባስ ይታያል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሻሻሎችን ያሳያል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሐረር ላይ የመጠጥ ውሃ ችግር አለ። ለዚህም ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ።

አንደኛው ውሃው ከድሬዳዋ አካባቢ ከ72 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚመጣ መሆኑ ነው። ከ72 ኪሎ ሜትር ላይ ተነስቶ ሐረር እስኪገባ ባለው ሂደት ከውሃው ምንጭ እና በሐረር ከተማ መካከል የሚገኙ ሌሎች ከተሞች ውሃ ይወስዳሉ። ለምሳሌ ደንገጎ፣ አዴሌ፣ ለሀሮሚያ እና ለአወዳይ ውሃ የሚወስዱት ለሐረር ከተማ የውሃ አገልግሎት እንዲውል በሚል በሐረሪ ክልል ሙሉ ወጭ ከተገነባው የውሃ መስመር ነው። ሐረር ውሃ የምታገኘው ይህን ሁሉ ቦታ ካዳረሰ በኋላ ነው።

አሁን በተጠቀሱት ከተሞች ያለው የሕዝብ ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው። በመሆኑም በዚያ አካባቢ ጥቅም ላይ የሚውለው ውሀ እየጨመረ ነው። ይህ ደግሞ ሐረር መድረስ የነበረበትን ውሃ በእጅጉ ይቀንሰዋል። ለሐረር የውሀ እጥረት አንዱ ችግር ይህ ነው።

ሁለተኛው ችግር ደግሞ እጅግ ተደጋጋሚ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ነው። ከ72 ኪሎ ሜትር ወደ ሐረር የሚመጣው ውሃ ምንጩ ከጥልቅ ጉድጓድ የተገኘ ነው። የጉድጓዱ ጥልቀት አንድ ሺህ ሜትር ከፍታ ያለው ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ወደላይ በከፍተኛ ጉልበት ወደላይ ተገፍቶ የመጣው ውሃ እንደገና ተመልሶ ወደነበረበት ምንጭ ይመለሳል። ጉዳቱ ውሃው መመለስ ብቻ አይደለም። ውሃው ሲመለስ ብዙ ማሽኖችን ያበላሻል። እንደገና የተበላሸውን እቃ ለመተካት ደግሞ ሌላ ወጭ ይጠይቃል። በዚህ ሂደት በርካታ “ፓምፖች” ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። በመሆኑም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እጅግ በጣም! ከባድ ችግር ሆኖ ይገኛል። በኃይል መቆራረጥ ሳቢያ ማኅበረሰቡ ከሁለት ሳምንት እስከ ሁለት ወር ድረስ ውሃ የማያገኝበት ጊዜ ይኖራል። በቃ! መብራት ከሌለ ውሃ የለም።

ሦስተኛው ችግር ደግሞ ውሃ የሚገኝባቸው ጉድጓዶች ጥልቅ በመሆናቸው ውሃው መቼ እንደሚያልቅ አለመታወቁ ነው። ለምሳሌ ሰባት ጉድጓድ ቢኖረን በአንድ ዓመት ሁለቱ ጉድጓድ ሊደርቅ ይችላል። የጉድጓድ ውሃ መቼ ያልቃል? የሚለውን በምንም መልኩ ማወቅ አይቻልም።

እንደመንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ እቅዶችን በማቀድ የተለያየ ተግባራትን እያከናወን ነው። በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ከተካተቱ ፕሮጀክቶች መካከል ኤረር በሚባለው አካባቢ ተጨማሪ ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈር የሐረርን የውሃ ችግር ለማቃለል ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረ ፕሮጀክት አለ። ይህም የኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ይባላል።

የኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስኬታማ ሆኖ ሲጠናቀቅ አሁን ካለው የውሃ ምርት በእጥፍ ይጨምራል። የኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አሁን ላይ ሥራው ተጠናቋል። ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም መጀመሪያ ሥራ ይጀምራል። ይህም አሁን ያለውን የሐረር ከተማ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት በእጥፍ ጨምሯል። ይህ ለክልላችን መንግሥት እና ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሚፈጥር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ድሬዳዋ የሚገኙትን የውሃ ጉድጓዶችንም የማደስ እና ምርታማነቱን የመጨመር ሥራ እንሠራለን ።

የኤረር እና የድሬዳዋ ፕሮጀክቶች የሐረርን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጊዜያዊነት የሚቀርፍ እንጂ በዘላቂነት መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም። በመሆኑም የሐረርን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው አሁን በክልላችን በፌዴራል መንግሥት ኤረር ላይ በሚሠራው ግድብ ነው። ግድቡ የኤረር ግድብ የሚባል ሲሆን በርካታ ጥቅሞችን እንዲሰጥ ታቅዶ የሚሠራ ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ ለሚቀጥሉት ለ50 እና 60 ዓመታት የሐረርን የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ የሚያስችል ነው። ግድቡ ከመጠጥ ውሃ አገልግሎት በተጨማሪ ለመስኖ ሥራ እና ለመዝናኛነት የሚውል ነው።

የዚህ ፕሮጀክት ጥናት እና የዲዛይን ሥራ ተጠናቋል። በቀጣይ የግንባታ ሥራው ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን ፡- በግብርናው ዘርፍ ለአርሶ አደሩ የቀጥታ ትስስር በመፍጠር እና ሸማቹም ባልተጋነነ ዋጋ እንዲገዛ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ኦርዲን ፡- እንደ ሐረሪ ክልል ዋነኛው እምቅ ሀብታችን ቱሪዝም ነው። ይሁን እንጂ ገጠር ላይ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው። በግብርና ውስጥ ደግሞ ለሌማት ትሩፋት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው። የሌማት ትሩፋት ሥራው በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡

በክልላችን የወተት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል እና የማር መንደሮች ብለን መንደሮችን እየመሠረትን ነው። ከሌማት ትሩፋት ጋር በተያያዘ የመንደር ምሥረታው ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። አሁን ላይ ወደ 21 የሚጠጉ የወተት፤ 14 የሚሆኑ የዶሮ መንደሮችን መሥርተናል። ይህን የመሰለ ሥራችንን በሚፈለገው ልክ ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎች ይጠብቁናል።

ሌላው ከግብርና ጋር በተያያዘ እንደክልል በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጀመረው “የግሪን ሌጋሲ” ሥራ ነው። ግሪን ሌጋሲ እንደ ሀገር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ12 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለናል። ለ2016 ክረምት ደግሞ 2 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ አዘጋጅተናል።

በዚህ ዓመት ከምንተክላቸው ችግኞች 70 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ ዕፅዋትን ነው። ቀሪ 30 በመቶው ደግሞ የደን ዛፎች ናቸው። ስለዚህ በምግብ ራስን ለመቻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው። የኑሮው ውድነቱን በማቃለል እና በሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

እንደክልል የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ስንጀምር በኢኮኖሚ ደከም ያሉ ቦታዎችን እና የማኅበረሰብ ክፍሎችን ነው የመረጥነው። ይህ ደግሞ ድህነትን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው።

ከግብርናው ጋር በተያዘ ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ ጥረቶች ይደረጋሉ። ከተማው ላይ በብዛት ሕዝቡ ምን ምርት ይፈልጋል? የሚለውን በማጥናት ገጠር ላይ እያመረትን ነው። አርሶ አደሩ ምርቱን ካመረተ በኋላ በቀጥታ በሸማቹ እና በአምራቹ መካከል ምንም አካል ሳይገባ ከተማ ላይ ወስዶ ለሸማቹ እንዲያቀርብ እያደረግን ነው። በዚህም አሁን ላይ ቀድሞ የነበረውን የዋጋ ንረት በእጅጉ ማሻሻል ተችሏል። ነገር ግን አሁንም ይቀረናል።

አዲስ ዘመን፡- አርሶአደሩ ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለሸማቹ ለማቅረብ መንገዶች ወሳኝነት አላቸው። ከዚህ አንጻር በክልላችን አርሶአደሩን ከከተማው የሚያገናኙ የመንገዶች ግንባታ ምን ይመስላል?

አቶ ኦርዲን፡- እውነቱን ለመናገር ሐረር ላይ ብዙም የመንገድ ችግር የለም። ሐረሪ ክልል ላይ ቀበሌ ከቀበሌ በመንገዶች ተገናኝቷል በሚባልበት ደረጃ መንገዶች ተሠርተዋል። ከራሳችን ክልል አልፈን ከሌሎች ክልሎች ጋር ለመገናኘት መንገዶችን እየሠራን ነው። አሁን ላይ የአስፋልት ሥራ ገጠር ላይ ጀምረናል። በቀጣይ ደረጃውን የማሳደግ ሥራ እንሠራለን።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ለመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ሠርቶ አስረክቧል? ትውልድ ለሚቀርጹ መምህራን የመኖሪያ ቤት ሠርቶ መስጠቱ የክልሉን የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር የሚኖረውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ኦርዲን፡- የከተሞች አንዱ ትልቁ ጥያቄ መኖሪያ ቤት ችግር ነው። ከተሞች ባደጉ ቁጥር ሁልጊዜ ተጨማሪ የመኖሪያ ቤቶች ያስፈልጋሉ። ስለሆነም በከተሞች ላይ በመኖሪያ ቤት አማራጮች ላይ በጥናት የታገዙ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ከዚህ አንጻር በሐረሪ ክልል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል። ለነዋሪዎችም ተላልፈው ተሰጥተዋል። ነገር ግን እንደመምህራን አይነት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰባችን ክፍሎች አሉ። መምህራን ያለባቸውን ኃላፊነት እና የኑሮ ጫና ስትመለከት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የመምህርነት ሙያ ትልቅ ሙያ ነው፤ ሊከበር ይገባል። ምክንያቱም ያለመምህር ምንም የለም። ስለሆነም መምህር ላይ ሥራን መሥራት ያስፈልጋል። መምህራን ተቸግረው የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ አይቻልም።

በመሆኑም መምህራን ያለባቸውን የኑሮ ጫና ማቃለል ያስፈልጋል። ከዚህ በመነሳት ለመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ገንብተን በዕጣ አስተላልፈናል። በክልሉ ለመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ገንብተን ስንሰጥ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ለመምህራን ቤት መስጠቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። መምህራን ተረጋግተው የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እና ትውልድን የማነጽ ሥራቸውን እንዲሠሩ ያስችላቸዋል።

በሐረር ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረት አለ። በቀጣይ ይህን ችግር ለመፍታት እንሠራለን። የውሃን ችግር ለመቅረፍ እንዳደረግነው የሐረርን ቤት ችግር ለመቅረፍ የአጭር እና የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ጊዜ እቅዶችን አቅድን እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን ፡- የሐረሪ ቤት አሠራር እና በውስጡ የሚከናወኑ ኩነቶች ለምሑራን እና ለሴቶች የሚሰጠው ክብር እንዲሁም ሌሎች የባሕሉ መገለጫዎቹ ኢትዮጵያውያን በመደበኛ ትምህርት ቢማሩት ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ ይነገራል። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ ኦርዲን፡- የሐረሪ ቤት ራሱን የቻለ ብዙ ታሪክ ያለው ነው። ቤት ውስጥ ከገባህ በኋላ በቤቱ የሚከናወን እያንዳንዱ ነገር ትርጉም ያለው ነው። በሐረሪ ቤት የሚገኙ አምስት መቀመጫ መደቦች አሉ። መደቦች በደረጃ የተሠሩ ናቸው። እያንዳንዱ መደብ የየራሱ ትርጉም አለው። የተማረ ከላይ መደብ ይቀመጣል፣ ያልተማረ መሬት ላይ ይቀመጣል። የተማረ ከላይ መደብ ሲቀመጥ ያልተማረ ደግሞ ከታች ተቀምጦ ሻይ እንዲቀዳ ይደረጋል። ይህ የሚያሳየው ከድሮ ጀምሮ የሐረሪ ሕዝብ ለትምህርት የሚሰጠውን ትልቅ ዋጋ ነው።

በሐረሪ ባሕል ቤት እቃዎች አደራደር በምክንያት ነው። በመሆኑም በሐረሪዎች ቤት መብራት ቢጠፋ እንኳን የፈለከውን እቃ ሳትደናገር ታገኛለህ። የሐረሪ ሰዎች የትም ቦታ ቢሄዱ የሐረሪን ባሕል የሚያሳይ ቤት ይገነባሉ።

የሐረሪን ሕዝብ ባህል እና ታሪክ የሚዘክሩ ክንውኖች አስተማሪ እና ጠቃሚ በመሆናቸው ለትውልዱ በትምህርት ካሪኩለም አካቶ ማስተማር ያስፈልጋል። ይህን በቀጣይ የምናየው እና የምንሠራበት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ኦርዲን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You