መንግሥት ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻል እንዲሁም በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገባውን የምግብ ፍጆታ ለማስቀረት በያዘው አቅጣጫ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው። በዚህም ከመኸርና ከበልግ እርሻ የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ በተጨማሪ እየተካሄደ ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገራዊ የስንዴ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የሰብል ልማቱ አርብቶ-አደሩ በብዛት በሚኖርባቸው ክልሎች ጭምር እየተስፋፋ ይገኛል። በእነዚህ ክልሎች የስንዴና የሩዝ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በስፋት እየተሠራበት ሲሆን፣ ይህም የአርብቶ አደሮችን ሕይወት መቀየር የሚያስችል ተግባር እየሆነ መምጣት ጀምሯል።
ሕይወቱን በአርብቶ አደርነት እና በንግድ ሥራ የሚመራው የሶማሌ ክልል ሕዝብም የዚህ አንድ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል። በክልሉ የመስኖ ልማትን አዲስ የሥራ ባሕል በማድረግ ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ ነው።
ይህንን ሰሞኑን በክልሉ ተገኝተን ባደረግነው የመስክ ጉብኝት ተመልክተናል። በክልሉ ሸበሌ ዞን የምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ይገኛል። ከዞኑ 10 ወረዳዎች ሰባቱ ከዋቤ ሸበሌ ወንዝ ጋር ኩታ ገጠም ናቸው። ከሰባቱ ወረዳዎች መካከልም የበረሃኖ ወረዳ አንዷ ናት። ወረዳዋ ለግብርና ሥራ ምቹ የሆነ ሜዳማና ለም አፈር አላት። ለዘመናት አጠገቧ ከሚገማሸረው ዋቤ ሸበሌ ወንዝ ጋር ተኮራርፋ ነው የኖረችው ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ለመስኖ ልማት የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የበረሃኖ ሜዳማና ለም መሬት ከዋቤ ሸበሌ ወንዝ ጋር ተስማምተው መኖር ጀምረዋል። ይህ ለጥ ያለና በዓይን ለማዳረስ የሚታክተው መሬት ዛሬ በልምላሜ ፈክቶ አዲስ የተፈጥሮ ገጽታን ተላብሷል። ከጓሮ አትክልት እስከ ተለያዩ አዝርዕቶች ይመረቱበታል።
ሌላው የሚገርመው ደግሞ ለመስኖ ልማት በተገነባው ቦይ ውስጥ የሚፈሰው ውሃ ብቻ አለመሆኑ ነው። ውሃውን ተከትሎ የሚመጣ ሌላም ሲሳይ አለ፤ ዓሣ። ይህ ዓሣ ለአካባቢው ሌላ በረከት ሆኗል። ዓሣው በተለይም በእርሻ ማሳው ላይ በጉልበት ሠራተኝነት ተቀጥረው ሕይወታቸውን ለሚመሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ምግባቸው መሆን ችሏል።
እነዚህ ሠራተኞች ብዙም ሳይደክሙና ሳይታክቱ እንደዋዛ መንጠቋቸውን ወርውረው ዓሣ ሲያወጡ ለተመለከተ ሕይወት በምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ምን ያህል ቀላል መሆን መጀመሯን መረዳት አይቸገርም። የሌማት ትሩፋት ትክክለኛ ትርጉምንም በተግባር ይረዳል።
አቶ አብዱልሐኪም እስማኤል በሶያል ኅብረት ሥራ ማኅበር ተደራጅተው በኢንቨስትመንት በወሰዱት 50 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ዘርተው ሲንከባከቡ ያገኘናቸው ባለሃብት ናቸው። በቀድሞው መንግሥት ይደረግባቸው በነበረው ጫና ምክንያት ኑሯቸውን በስደት አውሮፓ ውስጥ ያሳልፉ እንደነበር ይገልጻሉ።
ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በክልሉ የተገኘውን ሠላም እያጣጣሙ ሠርቶ የመኖር ተስፋ ሰንቀው በመስኖ ልማት ተሠማርተዋል። በአካባቢው በኢንቨስትመንት ከተረከቡት ሃምሳ ሄክታር እርሻ ግማሹ ላይ የዘሩት ሩዝ ቡቃያ ማሳውን አረንጓዴ ማልበስ ጀምሯል። የተቀረውንም ሄክታር ማሳ ለተመሳሳይ ዓላማ አዘጋጅተውታል።
አቶ አብዱላሂ የአካባቢው መስተዳድር ከዚህም በላይ ሰፊ መሬት ቢሰጣቸው የማልማት አቅም እንዳላቸው ይናገራሉ። በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ሲያስቡም ትርፍን ብቻ አስበው አይደለም። አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታ ውጭ ሌላም ሕይወቱን የሚመራበት ፀጋ እንዳለው ለማሳየትና አርዓያ ለመሆንም ጭምር እንደሆነ ይገልጻሉ።
በዋቤ በሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ያሉ አርብቶ አደሮች ነገ ሶማሌ ክልልን በሩዝ ምርት ተጠቃሽ በሚያደርጉበት በዚህ ሥራ እርሳቸው ፋናወጊ መሆናቸው እንደሚያኮራቸውም ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የሸበሌ ወንዝን ጠልፎ ለመስኖ ሥራ ዝግጁ ማድረጉ እሳቸው እና ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች በመስኖ ልማት እንዲሠማሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ፕሮጀክቱ የትራክተር፣ የምርጥ ዘር፣ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ አገልግሎት መስጠቱ ለሥራው የበለጠ ተነሳሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከለውጡ ወዲህ ሶማሌ ክልል ሠላም ማግኘቷ እርሳቸውና መሰል ጓደኞቻቸው ከስደት ተመልሰው በልማት ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ አርጓቸዋል።
‹‹ሶማሌ ክልል በየትኛውም ዘመነ-መንግሥት ሠላም አግኝታ አታውቅም›› የሚሉት አቶ አብዱልሐኪም፤ ሠላም የምናቅደውን ሁሉ ሠርተን ውጤታማ ለመሆን፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት ለመንቀሳቀስ፣ በአጠቃላይ ለሀገር ልማትና እድገት መሠረት እንደሆነ ያስረዳሉ። አሁን በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሠላም የሶማሌ ሕዝብን በእጅጉ ጠቅሟል፤ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ የሠላም ተጠቃሚ እንዲሆንም እያንዳንዱ ሰው ከመንግሥት ጎን መቆም ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹በክልሉ ሠላም በመስፈኑ በስደት እንኖር የነበርን የአካባቢው ተወላጆች ወደ ሀገራችን እየገባን በልማት ሥራ እንድንሳተፍ በር ከፍቶልናል፤ ሌሎችም እኛን ተመልክተው ወደ ሀገራቸው እየገቡ በልማት ሥራ ላይ እንደሚሳተፉ እጠብቃለሁ። እንዲህ አይነት ዘመን ያሳየኝን አላህን አመሰግናለሁ፤ መንግሥትም ለክልሉ ሠላም መጠበቅ ስላደረገው ሁሉ አመሰግናለሁ›› ይላሉ ፡፡
ሌላው በፕሮጀክቱ መሬት ወስዶ ሲሠራ ያገኘነው የአልኬሄራት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው። እርሱም ሩዝ በማልማት ላይ ይገኛል። የማኅበሩ ተወካይ ወጣት መሐመድ ኑር ሼክ እንደነገረን፤ ማኅበሩ ከፕሮጀክቱ ላይ 25 ሄክታር መሬት ተረክቦ የተለያዩ ሰብሎች እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።
አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩዝ ዘርቷል። ሩዝ ማምረት እንደሚቻል በምርምር ማዕከሉ ከተረጋገጠ በኋላ ማኅበሩ ሳያቅማማ በተሠጠው 25 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ዘርቷል። በአሁኑ ሰዓትም ሩዙ በቡቃያ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሩዝ በሦስት ወር ውስጥ የሚደርስ ሰብል መሆኑን ጠቅሶ፣ ሰብሉ ሲደርስ ቶሎ ሰብስቦ ለሌላ ሥራ ለማዋልም ይጠቅማል ሲል ይገልጻል። በሶማሌ ክልል ሩዝን አዘውትሮ ለምግብነት መጠቀም የተለመደ ነው ያለው ወጣት መሐመድ፣ ወደፊት ሩዙን እዚሁ ማምረት ከተቻለ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አውጥቶ ምርቱን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይቀራል ብሏል። የአካባቢው አርሶ አደርም ቀስ በቀስ ሩዝ ማምረትን እየለመደ እንዲሄድ የሚያስችል መሆኑን ጠቁሟል።
ኢንጂነር አብዱዋሂድ ሙሂዲን የምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ማናጀር እንዳስረዱት፤ መንግሥት ወረዳዋ ለመስኖ ልማት ያላትን ተመራጭነት በማጥናት ‹‹የምዕራብ ጎዴ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን›› ገንብቶ እ.አ.አ በ2024 ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርጓል። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ሰባት ሺ 600 ሄክታር ይሸፍናል፤ በአሁኑ ሰዓት ግን እየለማ ያለው ሁለት ሺ ሄክታር ብቻ ነው።
የመስኖ ፕሮጀክቱ ወደ አገልግሎት ከገባ ጊዜ ጀምሮ የበጋ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ ይለሙበታል፤ ሽንኩርት እንዲሁም ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉና የአርብቶ አደሩን ፍላጎት የሚያሟሉ የሣር አይነቶችም ተተክለውበታል።
በፕሮጀክቱ ድጋፍ ሰጪነትና በባለሃብቶች ተሳትፎ ለመጀመሪያ ጊዜ በ800 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ የማምረት እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ለዚህ ይረዳ ዘንድ አስቀድሞ ምርምሮች ተደርገው አበረታች ውጤቶች ታይቷል።
የጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ከክልሉ የግብርና ምርምር ማዕከል በሚደረግለት ድጋፍ በዚያው በፕሮጀክቱ ውስጥ የራሱን የምርምር ጣቢያ አቋቁሟል። ስለሆነም ውጤታማነቱ በሙከራ ሳይረጋገጥ የሚዘራ ወይም የሚተከል ነገር አይኖርም።
አብዛኛዎቹ የበርሃኖ ወረዳ ነዋሪዎች የአርብቶ አደርነት ሕይወትን የሚመሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር አብዱዋሂድ፣ የመስኖ ፕሮጀክት ሥራው ከጀመረ በኋላ ግን በቆሎ፣ ሰሊጥና ሽንኩርት እያመረቱ ከእርሻ ሕይወት ጋርም እየተለማመዱ መምጣታቸውን ይገልጻሉ። በቀጣይም የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ሩዝ የማምረት ልምድ እንዲያዳብሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
የምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ለአካባቢው ነዋሪ እንደ ሽንኩርት እና ቲማቲም የመሳሰሉ ምርቶች ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች ይመጡለት እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በፕሮጀክቱ የሚመረቱ ምርቶችን እስከ አዲስ አበባ ድረስ ለገበያ በማቅረብ አዲስ ታሪክ እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በክልሉ አስከ ቀጣይ የመኽር ወቅት ድረስ በሦስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ የማምረት አቅድ እንደተያዘ የገለጹት ኢንጂነር አብዱዋሂድ፣ ከዚህ ውስጥ በበርሃኖ ወረዳ ብቻ 800 ሄክታር መሬት በሩዝ ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። አሁን ላይ 400 ሄክታር፤ ከቀጣይ ሶስት ወር በኋላ ሌላ 400 ሄክታር መሬት በሩዝ ዘር ለመሸፈን ታስቧል ብለዋል።
እሳቸው አንዳብራሩት፤ በምዕራብ ጎዴ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ250 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ተዘርቶ መብቀል ጀምሯል። ቀሪው 150 ሄክታር ደግሞ በወረዳው የተለያየ አካባቢ ባሉ አርሶ አደሮች እየተሸፈነ ይገኛል።
የመሬት አሰጣጥ ሥርዓቱን በተመለከተም በመስኖ ልማቱ መሥራት የሚፈልጉ አካላት መጀመሪያ ከተደራጁና የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ከመጡ ባላቸው አቅም ልክ መሬት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። በቀጣይም ውጤታማነታቸው እየተለካ ተጨማሪ አቅርቦት ይደረግላቸዋል ብለዋል። እንደ አሳቸው ገለጻ፤ የሚፈልጉትን መሬት ለማግኘት መጀመሪያ በትንሽ መሬት ላይ ሠርቶ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ይህን አሠራር መከተል ያስፈለገበት ምክንያት መሬቱ ጦሙን እንዳያድር ስለሚፈለግ ነው።
ለግብርና ሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማለትም ምርጥ ዘር፣ ትራክተር፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ከፕሮጀክቱ ያገኛሉ፤ ሙያዊ ድጋፍና ክትትልም ይደረግላቸዋል። ከእነርሱ የሚጠበቀው የሰው ኃይል አሟልቶ ወደ ሥራ መግባት ብቻ ይሆናል።
የመስኖ ልማቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዲስ የሥራ ባሕል ከመሆን አልፎ፤ በመስኖ ሥራ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶችንም በሰፊው እየጋበዘ ይገኛል። ከእርሻ ዝግጅት እስከ ምርት መሰብሰብ ባለው የሥራ ሂደት ለክልሉና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመጡ በርካታ ሰዎችም የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የክልሉን የግብርና ሥራ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ለማምረት ወደ ሥራ ተገብቷል። በክልሉ ካሉት 11 ዞኖች ውስጥ ለሩዝ ምርት ተመራጭ ናቸው ተብለው የተለዩት የሸበሌ እና የሲቲ ዞኖች ናቸው። እነዚህ ዞኖች ከፍተኛ የውሃ አቅምና ለም መሬትን አስተሳስረው የያዙ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፣ የሩዝ ምርትን ለማምረት አመቺነት እንዳላቸው አስታውቀዋል። አርብቶ አደሩ ከፊል አርሶ አደር በመሆን የአካባቢውን ፀጋዎች ተጠቅሞ በሚያመርተው ምርት በምግብ ራስን የመቻል መርሐ ግብሩ እውን ለማድረግ እየተጋ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፤ እንደ ሀገርም በሩዝ ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ አምና ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ የሩዝም ምርት መገኘቱን አስታውሰው፣ ዘንድሮ 38 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል ብለዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም