እንደሚታወቀው በመፅሐፍ ቅዱስ እና በቅዱስ ቁራን ውስጥ በተደጋጋሚ ስማቸው ከተጠቀሱ የዓለም ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ትሰለፋለች። ይህም የሚያሳየው ሀገሪቱ ጥንታዊ የእምነት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የፍልስፍና የሥነ-ጽሁፍ፣ የዜማ፣ የጥበብ … ወዘተ መፍለቂያ መሆኗን ነው። ሕዝቧም ከዓለም ሕዝብ ቀድሞ የሠለጠነ፣ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ነው።
ለአብነት “ኢትዮጵያ” የሚለው የሀገራችን ስም በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ 43 ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። በቅዱሱ መፅሐፍ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከተነገሩት ታሪኮች ውስጥ ለዛሬ መጣጥፌ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ፤ ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 13 ከቁጥር 23 ላይ ያለውን ታሪክ ወስጃለሁ። በዚህ ገጽ ላይ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” የሚል ሃይለ ቃል ተፅፎ እናገኛለን።
አዎ! ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው ዛሬም ድረስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን አልለወጠም። ነብር ባሕሪውን አልቀየረም። ዛሬም የሚኖረው በጫካ ነው። አመጋገቡም እንደጥንቱ አልተቀየረም። የዚህን እንስሳ የተራክቦ ሥርዓት ብንመለከት፤ ከግልገልነታቸው ጀምሮ አብረው ካደጉ በኋላ ባልና ሚስት ይሆናሉ። ልክ እንደሰው ልጆች ወልደው ተንከባክበው ያሳድጋሉ። በፍቅር ይኖራሉ።
በሕይወት እያሉ ነብር ከሚስቱ ወይም ከባሏ ውጭ አይባልግም/ አትባልግም። ከሁለት አንዱ በሞት ቢለይ፤ በሕይወት የቀረው ወይም የቀረችው በዱር፣ በገደሉ መንኖ ወይም መንና ከእንስሳ ተገሎ/ላ እስከ ሕይወት ፍሜው ወይም ፍጻሜዋ መንኩሳ/ሶ ይኖራል ወይም ትኖራለች። ዛሬም ይህ እንስሳ ፀባዩን፣ ባሕሪውን፣ አኗኗሩን፣ … ወዘተ አልቀየረም።
ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንስሳ አንሰን መልካችንን ቀይረናል። አዎ! መልካችን ተቀይሯል። ደም ግባታችን ከገጻችን ጠፍቷል። ውበታችን እረግፏል። የሚያምረው መልካችን ተጠብሷል፣ በልዟል፣ ከስሏል፣ ተበርዟል። በጥቅሉ ባሕሪያችን፣ መልካችን፣ ማንነታችን፣ ፀባያችን … ተለዋውጧል።
ኢትዮጵያዊ መልካችን ምን ነበር? ብለን ስናወሳ ከየት መጣህ? ዘርህ፣ ቋንቋህ፣ ቀለምህ፣ መልክህ … ምንድ ነው? ሳይል በፍቅርና በፈገግታ እንግዳ ተቀብሎ እግር አጥቦ፣ ቤት ያፈራውን “በሞቴ ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ” ብሎ አብልቶ፣ አጠጥቶ፣ ከሳጥን የታጠበውን አውጥቶ አልብሷ፣ አልጋውን ለእንግዳ ለቆ መሬት ላይ ተኝቶ ማስተናገድ ነበር።
በተለይ በከተሜው ልክ እንደዛሬው ለአውደ ዓመት አርዶ በፍሪጅ የሞተ ሬሳ ሥጋ ከቶ ቤት ዘግቶ ብቻ መብላት ሳይለመድ፤ የዛሬን አያድርገውና ድሮ ለአውድ ዓመት ታርዶ፣ ጠላ ተጠምቆ፣ ጠጁ ተጥሉ፣ ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ተጠርቶ፣ “ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ” ተብሎ ነበር በጋራ የሚበላው፣ የሚጠጣው። ይሁን እንጂ የሀገሬው ሕዝብ ይህን በማድረጉ ማድጋው ጎሎ፣ ማሰሮው ነጥፎ፣ ጓዳው ተራቁቶ አያውቅም ነበር። ይህ ነበር መልካችን፣ ወግ ልማዳችን።
እርስ በእርስ አንተ ትብስ አንቺ ተባብለን ተከባብረን በመኖር፤ ድንበር ጥሶ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነታችን ሊያጠፋ የመጣን ጠላት ልክ ቀፎው እንደተነካ ንብ “ግልብጥ” ብሎ ወጥቶ በተደጋጋሚ በጋራ ድል የነሳን፤ ከነኩን ወደ ኋላ የማንል፣ ክንደ ብርቱዎች፣ ልክ እንደ አንበሳ የተፈራንና የተከበርን ነበርን።
የኛ ኢትዮጵያውያን የጥንት የጧቱ መልካችን፣ ውበታችን፣ ባሕሪያችን … የታረዘን ማልበስ፣ ፍትህ የተጓደለበትን መካስ፣ ስደተኛና እንግዳ መቀበል፣ በጋራ መቆም፣ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር መኖር፣ በቃል መገኘት፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ፣ መተባበር፣ መተዛዘን፣ መፈቃቀር … ነበር። አንድነትና ፍቅራችን የሃይላችን ሚስጥር፤ የአልበገርነት ባይ መገለጫችን ነበር።
ይሁን እንጂ ይህንን የሃይላችን፣ የሰላማችን፣ የፍቅራችን፣ የአልደፈር ባይነታችን፣ የአንድነታችን… ሚስጥር የሆነውን ኢትዮጵያዊ መልካችን አጥብቀን ባለመያዛችን፤ በዚህ በሉላዊ ዓለም በእየለቱ ከሚፈጠሩ ተለዋዋጭና መጤ ባህሎች ሳቢያ በሂደት ኢትዮጵያዊ መልካችን፣ ባሕሪያችን፣ ፀባያችን ተቀይሯል፣ ተበርዟል። ደም ግባታችን ፈዝዟል ።
በዚህም አንተ ትብስ አንቺ ተባብሎ ተከባብሮ መኖር ተስኖን፤ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ከእርስ በእርስ የጦርነት አዙሪት መውጣት አቅቶናል። በእርስ በእርስ ጦርነት የአንድ እናት ልጆች እልፍ በግራ፣ እልፍ በቀኝ ወድቀዋል፤ እየወደቁም ይገኛሉ። በተለይ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ በሀገሪቱ ሰላም ጠፍቷል፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ነግሷል፣ መገዳደል በዝቷል። በጥቅሉ ምድር አኬል ዳማ ሁናለች። ወንድምን ገድሎ በወንድም እሬሳ ላይ መፎከር የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሆኗል።
ባህር አቋርጦ የመጣን እንግዳ ባህል፣ እምነቱን አክብሮ ተቀብሎ ተንከባክቦ ያኖረ ማህበረሰብ፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊ መልኩ ተቀይሮ ትናንት ለሀገራቸው ዳር ድንበር አብረው የተዋደቁ ወንድማማቾች በዘርና በቋንቋ ጎራ ለይተው አንዱ አንዱን እያፈናቀለ፣ እየገደለ፣ እያሳደደ ይገኛል።
አብዛኛው የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በንዋይ አይናቸው በመታወሩ፤ እውነተኛ የሃይማኖት አባት፣ የሀገር ሽማግሌ ጠፍቷል። በእምነቱ የጸና፣ ለቃሉ የታመነ ምዕመን ጠፍቷል። አብዛኛው ማህበረሰብ አንድ ዳቦ በልቶ ለማደር ተቸግሮ፤ ጥቂቶች “ከየት አመጡት” ብሎ ጥያቄ በሚያስነሳ መልኩ ከህንፃ ላይ ህንፃ ይደረድራሉ።
እነዚህ አካላት ከነዋይ ሌላ የሀገርና የወገን ፍቅር የላቸውም። በወገን ደምና ላብ የሚነግደው ስግብግብ ነጋዴው በዝቷል። በጥቅሉ ከ90 ከመቶ በላይ አማኝ ሕዝብ ባለበት ሀገር የሚፈጸሙ ወንጀሎች ለመስማት ይዘገንናሉ። ሰላም፣ ደስታ፣ እርቆናል በአንጻሩ የሞት፣ የረሀብ፣ የችግር፣ የጦርነት ዜና ዙሪያችን ከቦናል።
ስለምን ደስታ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ልማት፣ እድገት፣ ከኛ እራቀ? በተቃራኒው ስለምን ሞት፣ ረሀብ፣ ችግር፣ ጦርነት በሀገራችን ነገሰ? ብለን ሁላችንም እራሳችንን ቆም ብለን ብንጠይቅ እንደኔ ኢትዮጵያዊ መልካችንን በመቀየራችን ነው። በመሆኑም በፍቅር፣ በደስታ በሰላም፣ ተከባብሮ ለመኖር እና ሀገራችንን ከገባችበት የጦርነት አዙሪት ለማውጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊ መልካችን ያስፈልገናል።
ሁሉም ዜጋ አንድነትና ፍቅራችን ከሚሸረሽሩ የምዕራባውያን ባህልና ወግ እራሱን አላቆ፤ ልክ እንደ ንስር ኢትዮጵያዊ መልካችን አድሰን በከፍታው ማማ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንወጣ ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያዊ መልኩን በተግባር ሊኖረው ይገባል።
የእምነት አባቶች ደግሞ ልክ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገር ሰላም፣ ለወገን ፍቅርና አንድነት፣ ለሃይማኖት ዶግማና ቀኖና መከበር አንገታቸውን ለሰይፍ፤ ደረታቸውን ለጦር ሊሰጡ ይገባል። በጥቅሉ በሰላም ተከባብሮ ለመኖር ኢትዮጵያዊ መልካችን ይሻለናል፤ ይበጀናል!
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም