«ስደትን በግብርና መግታት ይቻላል»  – አርሶ አደር ወንድሙ ደስታ

ላቤ በአንገቴና በጀርቫዬ ይወርዳል ሳይሆን፤ ይንቆረቆራል ነው ሊባል የሚችለው፡፡ ምንም እንኳን አካባቢው በደን የተከበበና አረንጓዴ ቢሆንም ነፋሻማ የአየር ፀባይ የለውም፤ ይልቁንም በወበቅ ላብበላብ የሚያደርግ የአየርፀባይ ነው ያለው፡፡ ፀሐይም ሆኖ፤ ዝናብም ዘንቦ የአካባቢው ሙቀቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ አካባቢውን አረንጓዴው በረሃ ብሎ መጥራት ሳይቀል አይቀርም ፡፡

በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች አረንጓዴ ነገር ማየት በሚናፍቅበ፤ ገበሬዎች ለከብቶቻቸው የሳር ግጦሽ አጥተው መኖ በሚቸገሩበትና ውሃ ለማጠጣት ሩቅ መንገድ ለመሄድ በሚገደዱበት፣ ሰዎችም በዛፍ ጥላ ስር ለመጠለል አካባቢ ሲመርጡ በሚስተዋልበት በዚህ በግንቦት ወር በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግን ከእግረኛ እና ከመኪና መንገድ በስተቀር አፈር አይታይም፡፡

ለከብቶች የሚሆነው የሳር ግጦሽ ስፍራ ሳሩን በእግር ለመርገጥ ያሳሳል፡፡ የአካባቢው የመኖሪያ መንደሮች አጥር በአረንጓዴ ተክል የተከበበ ነው። ከመኖሪያና ከእርሻ ማሣ ውጪ የሚገኘውም ቦታ ቢሆን ደን የለበሰ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የእርሻ ማሳውም በበቆሎ ተሸፍኗል፡፡ ቡና አብቃይ አካባቢ በመሆኑም የቡና ተክሉና ለቡና ጥላ የተተከሉት እንደ ዋንዛ፣ ግራር፣ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎች፣ የቅመማ ቅመም ልማቱ ሌላው የአካባቢው መስህቦች ናቸው፡፡ የአካባቢውን አረንጓዴነትና ለምነት በቃላት ከምገልጽላችሁ፤ ዓይኔም አይቶ ካደነቀው በላይ ነው፡፡

ተፈጥሮ ለዚህ አካባቢ አድልታለች፡፡ ከአመት አመት አረንጓዴ፣ የዝናብ እጥረት የማያውቀው አካባቢ ነው፡፡ የአካባቢው አረንጓዴነትና የአየር ፀባዩ ከጋምቤላ ክልል ጋር ተቀራራቢ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ጋምቤላ ክልል አረንጓዴው በረሃ የሚል ስያሜ ወጥቶለታል፡፡ አጎራባች በመሆናቸው ይሆን ተመሳሳይ መልክአምድር እንዲጋሩ ያደረጋቸው? ምንም እንኳን ተቀራራቢ የአየር ፀባይ ቢኖራቸውም የጋምቤላ ክልል የአየር ሙቀት መጠን ከፍ እንደሚልና አንዳንድ ሙቀቱ ከአቅማቸው በላይ የሚሆንባቸው የክልሉ ነዋሪዎችም ነፋሻ አየር ፍለጋ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቆይታ እንደሚያደርጉ ነው የሰማሁት፡፡

ሁሌም እርጥብ ሳር የማይለያቸው እንስሳት ውሃ ይጠማቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የሚግጡት ሣር ከውሃ ጋር የተቀላቀለ ነው፡፡ ገበሬውም ቢሆን መሬቱን አርሶ ለሰብል ልማት ዝግጁ ለማድረግ ብዙ ጉልበቱን አያደክምም፡፡ እንዲህ ባለው የተፈጥሮ ፀጋ በታደለ አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ በእንስሳት፣ በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና ልማት ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ ምርታማ በሆነ አካባቢ የሚኖር ደግሞ በኢኮኖሚ ያደገ፣ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚበቃ ቱሩፋት የሚያስገኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

አካባቢውን እየቃኘሁ፤ በተፈጥሮ እየተደ መምኩ፤ በአእምሮዬ የተለያዩ ሃሳቦች ተመላለሱ፡፡ እንዲህ በተፈጥሮ ፀጋ ውስጥ የሚኖር ገበሬ በሀብቱ ተጠቅሞ እራሱንም ሀገሩንም በኢኮኖሚ ለማሳደግ ምን ያህል እየተጋ ይሆን? የሚል ሃሳብ ነበር ወደ አእምሮዬ የመጣው፡፡ የሳር ቤት የነበረው ገበሬ የቆርቆሮ ክዳን ያለው ቤት ገንብቶ መኖሪያውን መቀየሩን እንደ አንድ ለውጥ ልናነሳ እንችል ይሆናል፡፡ ምናልባትም ልጆቹን ማስተማሩ ሌላው ለውጥ ነው፡፡ ግን ለውጦቹ መሠረታዊ የሚባሉ ናቸው ወይ? ሲባል አሁንም ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ገበሬው ከእለት ፍጆታ ውጪ የሚያወጣው ምርት እያመረተ አለመሆኑን አኗኗሩ ማሳያ ነው፡፡ ክረምት ከበጋ ማምረት የሚለው የሥራ ባህል አልተቀየረም፡፡ ወቅቱን የጠበቀና በሚፈለገው ልክ የግብአት አቅርቦት አለመኖር፣ የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላታቸው የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ሌላው ገበሬው የሚያነሳቸው ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍና አርሶ አደሩ ክረምትን ጠብቆ ከማምረት እንዲላቀቅ፣ በውስን ሰብል ልማት ላይ ብቻ እንዳያተኩር ተጨማሪ ምርቶችንም እንዲያመርት ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም ችግሮቹን ለመሻገር ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ላይም መሥራት ይጠበቃል፡፡ በተፈጥሮ ፀጋ የታደልን ሆነን ሳለን ዘመናዊ አርሶ አደር አለመፍጠራችን ቁጭት ያሳድራል፡፡

አሁንም ገበሬው ከቀደመው የአስተራረስ ዘዴው አልተላቀቀም ዛሬም ድረስ የእሱን ድካም ሊቀንስ የሚችል ነገር አልተፈጠረምⵆ ማልዶ ከተኛበት ተነስቶ ሲሰራ ነው የሚውለው፡፡ በዓል፣ ሰርግ፣ ሽምግልና ከሌለበት ፀአዳ ልብስ ለብሶ አይታይም፡፡ የእጁንም አፈር አይታጠብም፡፡ እርሻ ባይኖርበት የጓሮ አትክልቱን ይኮተኩታል፡፡ ከብቶቹን ያሰማራል፡፡ ለአጭር መንገድ የታክሲ ሰልፍ የለመደ የከተማ ሰው የገጠሩ ማህበረሰብ በየቀኑ በእግሩ የሚሄጓዘውን ኪሎ ሜትር ቢያውቀው በጣም አስገራሚ ነው፡፡ የገጠሩ ማህበረሰብ ሥራው ሁሉ በእንቅስቃሴ የተሞላ ነው፡፡

የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር እንዲህ በሃሳቤ እያወጣሁና እያወረድኩ፤ ቁጭትም እያደረብኝ፤ አንድ ሰፊ የሣር ግጦሽ ባለው መስክ ላይ ከብቶቻቸውን አሰማርተው በርቀት ላይ ሆነው የሚጠብቁ ሰው አየሁ፡፡ ጠጋ ብዬ ሰላምታ ሰጠኋቸው፡፡ እርሳቸውም ደንገጥ ብለው በአክብሮት ለሰላምታዬ ምላሽ ሰጡኝ፡፡ ፈገግታቸውና አቀባበላቸው ልብ ይሞላል፡፡ በስም እንድንተዋወቅም ጠየኳቸው ወንድሙ ደስታ ብለው ተዋወቁኝ፡፡ የሚኖሩበት አካባቢም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጊምቦ ወረዳ ሀማኒ ቀበሌ እንደሚባል ነገሩኝ፡፡

አቶ ወንድሙ ለመግባባት ቀለል ያሉና ጨዋታ የሚያውቁ ሰው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ አቶ ወንዱሙ የትውልድ ዘመናቸውን በትክክል አያውቁትም፡፡ 60 አመት እንደሚሆናቸው ነው የገመቱት፡፡ ቀጠን ማለታቸው ይሁን፣ በቁመትም አጠር ብለው መታየታቸው የ60 አመት የእድሜ ባለፀጋ አይመስሉም፡፡ ቀልጠፍ ያሉ ናቸው፡፡ በልጅነታቸው የትምህርት እድል አግኝተው ቢማሩም ከአራተኛ ክፍል በላይ መግፋት ግን አልቻሉም፡፡ በወቅቱ የትምህርትን ጥቅም ተገንዝቦ በትምህርታቸው እንዲገፉ የሚያበረታታቸው ሰው በማጣታቸው ከአራተኛ ክፍል በላይ መዝለቅ ሳይችሉ መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡ በልጅነት ጊዜያቸው ከትምህርትቸው ይልቅ ከብት በመጠበቅና (በእረኝነት) ኋላም እድሜያቸው እየጎረመሰ ሲመጣ ወላጆቻቸውን የግብርና ስራ ሲያግዟቸው እንደነበር ነው ያጫወቱኝ። እርሳቸውም የቤተሰባቸውን ሥራ ተከትለው ነው ዛሬም ድረስ ግብርናውን መተዳደሪያቸው ያደረጉት።

አቶ ወንድሙ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በውትድርና ሙያ ውስጥ እንደነበሩም አጫውተውኛል፡፡ ኢትዮጵያ በወታደራዊ የደርግ ሥርዓት አገዛዝ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከመንግሥት የእናት ሀገር ጥሪ ቀርቦላቸው ግዳጃቸውን ለመወጣት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘምተዋል፡፡ በወቅቱ ጥሪውን መቀበል ግዴታ ስለነበር ሁሉም ከየአካባቢው የሰው ኃይል ይልካል፡፡ እርሳቸውም የዚህ አጋጣሚ ተካፋይ በመሆን አሰብ ላይ ዘምተዋል። እሳቸው ከዘመቱ አንድ አመት ተኩል በኋላ ግን የደርግ መንግሥት ተሸንፎ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠርና የቀድሞ ሰራዊት ሲበተን እርሳቸውም ወደአካባቢያቸው ተመለሱ፡፡

“…ለአጭር ጊዜም ቢሆን የጦርነትን አስከፊነት አይቻለሁ፡፡ የሰው ህይወት የሚቀጥፍ የሀገር ሀብትን የሚጎዳና ወደኋላም የሚያስቀር መሆኑን ተገንዝቤያለሁ” ይላሉ፡፡

ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ሠራዊቱ ላይ የደረሰውን ጉዳትና በየአካባቢው የነበረው ማህበረሰብ ለስደት ሲዳረግ የነበረውን አስከፊ ሁኔታ አስታውሰዋለሁ የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ በጉዞ ላይ ብዙዎች በረሀብና በውሃ ጥም ተንገላትተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችም ሞተዋል፡፡ እርሳቸውም ወደ ጅቡቲ ተሰደው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ተንገላተው ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም አይረሱትም ፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያን ስለገጠማት የእርስ በእርስ ጦርነት ሁኔታ እንደተናገሩት፤ ጦርነት ያደረሰው ጉዳትና አስከፊነት ካለፈው ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት ፣ የሚሰራ የሰው ኃይል ያላት በሀብት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ዜጎች ተስማምተው በጋራ ሆነው ለሀገራቸው እድገት ሊተጉ እንጂ ለውድቀት መነሳት የለባቸውም ይላሉ፡፡ የውጭ ጠላት ሲመጣ በጋራ መክቶ ለመመለስ መነሳት እንጂ ለእርስ በእርስ ጦርነት ጦር መዞ መነሳት አይገባም። ካሉ በኋላ አሁን ላይ በሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን ለመፍታት በመንግሥት በኩል የተጀመረውን ጥረትም ይደግፋሉ፡፡ አለመግባባቶች በውይይትና በመነጋገር መፈታት አለበት ይላሉ፡፡ መንግሥት ሰላም እንዲሰፍን የጀመረውን በምክክር የመፍታት ጥረት እንዲቀጥል የሁሉም ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ስለአካባቢያቸው

ስለ አርሶአደሩ የለውጥ ሁኔታ የተሰማኝን ስሜት ስለ አካባቢያቸው፣ ስለሥራቸው፣ ስለቤተሰባቸው፣ አንስተንም ተጨዋወትን። እርሳቸው እንዳሉት፤ የአካባቢው መሬት ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ ቡና፣ እንሰት፣ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና አትክልት፣ ሁሉንም የሰብል አይነቶች ያመርታል። የአካባቢው የአየር ፀባይ ለሰብል ልማት የተመቸ ነው፡፡ ዝናብ የማይዘንብባቸው ጊዜያቶች ጥቂት ወቅቶች ብቻ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በአካባቢያቸው ሸካ የሚባል ወንዝ በመኖሩ በመስኖ ማልማት ይቻላል፡፡ በተለይም በመስኖ እንደ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቀይስር፣ ካሮት፣ ሽንኩርት፣ የመሳሰሉ አትክልቶች፣ ፍራፍሬም ማልማት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው ላይ የመስኖ ልማት ባለመታወቁ ወንዙ ለመስኖ ጥቅም መዋል የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ አሁን ላይ ገበሬው ጥቅሙን እየተገነዘበ በመምጣቱ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለማበት ይገኛል፡፡

ስለሥራቸው ደግሞ እንዲህ አጫውተውኛል። የሚተዳደሩት በግብርና ሥራ ነው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት መሬታቸው ሰፊ አይደለም፡፡ አንድ ሄክታር መሬት ነው ያላቸው፡፡ አንድ ጥማድ በሚሆነው መሬት ላይ የቡና ተክል ያለማሉ፡፡ በቀሪው ላይ ደግሞ በቆሎ፣ ሙዝ፣ ጎን ለጎን ደግሞ እንሰት በተጨማሪ ያለማሉ፡፡ በአንድ ጥማድ መሬት ላይ ከሚያለሙት ቡና በአመት አምስት ኩንታል ያገኛሉ፡፡ በቆሎም በአመት እስከ ስድስት ኩንታል የሚሆን ምርት ይሰበስባሉ፡፡ ከሙዝ ምርት ደግሞ ለገበያ አቅርበው ወደ ስድስት ሺ ብር ገቢ ያገኛሉ፡፡ የእንሰት ምርቱ ደግሞ ለቤት ቀለብ ይውላል፡፡

 

ስለአርሶአደሩ የለውጥ ሁኔታ የተሰማኝን ስሜት በተመለከተም አቶ ወንድሙ፤ በእርሳቸው በኩል ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ላለማምጣታቸው ምክንያት ነው ብለው የነገሩኝ፤ በቂ የሆነ የእርሻ መሬት አለመኖር ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ከተለመደው የግብርና አሰራር ውስጥ አለመውጣት ያመጣው ችግር እንደሆነ ያምናሉ፡፡

አካባቢው ለም ቢሆንና መሬትም ቢኖር አጠቃቀሙን ማወቅ ካልተቻለ ተጠቃሚ መሆን አይቻልም የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ ‹‹በግሌ የምለው አጠቃቀሙን አላወቅንበትም፡፡ ሰው ለም መሬት በመያዝ ለችግር እጋለጣለሁ ብሎ አላሰበም፡፡ ግን ካላለሙ ለችግር መጋለጥ ይኖራል›› ሲሉ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት ከወንዝ ጠልፎ በመስኖ መጠቀም፣ ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ መጠቀም በአካባቢው የተለመደ የግብርና ሥራ አይደለም፡፡ ምርታማ ለመሆን ዘመኑ የሚጠይቀውን የግብርና ሥራ መከተል እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ የተገኘው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡

የመስኖ ልማቱ ሥራ የተጀመረውም ሆነ ጥቅሙ የታወቀው ከአራትና አምስት አመታት ወዲህ ነው፡፡ ግብርናውን ለማዘመንም በትምህርት አለመታገዝም ሌላው ክፍተት ነው፡፡ የትምህርቱን አስፈላጊነትም ሲያስረዱ፤ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ሥራ ቢሰራ ለአካባቢው የአየር ፀባይና የመሬት ሁኔታ ተስማሚ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሰብልና ሌሎችንም ለይቶ በማምረት ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድል ይፈጠር ነበር።

ይህ ባለመሆኑ ግብርናው ከኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ ሳይላቀቅ ዘመን መሻገሩን ይገልጻሉ፡፡ ገበሬው ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ባለመሥራቱ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ላይ እድሜውን እንዲያሳልፍ መገደዱን ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢያልፉም ለተተኪው ትውልድ ግን ተስፋ ሰጪ የሆነ ነገር መኖሩን መታዘባቸውንና እያዩ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ በእርሳቸው እድሜ ያላዩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ወንዝ ጠልፎ በመስኖ ማልማት፣ በግብርና ባለሙያዎች የተለያየ እገዛ ማድረግ መጀመሩ፣ ግብርናውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡ ወደፊት የመሬት አጠቃቀም ላይ ያለው የእውቀት ማነስም በትምህርት እየዳበረ ሲሄድ በአነስተኛ መሬት የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበት ዘዴ ሊኖር እንደሚችልም ያላቸውን ተስፋ ነው የተናገሩት፡፡ የግብርናው ሥራ ዘምኖ ምርታማነት ቢያድግ የገጠሩ ማህበረሰብ ከከተማ ኑሮ ባልተናነሰ ሊኖር ይችላል ይላሉ፡፡ ዛሬ ከተማ ፍለጋ ገጠሩን ለቀው የሚሄዱ ሁሉ በአካባቢያቸው ላይ የተሻለ ኑሮ መኖር ከቻሉ አካባቢያቸውን ለቀው ለመሄድ እንደማይነሳሱ ነው ያስረዱት፡፡

ስለአካባቢያቸውም እንደተናገሩት፤ አካባቢው በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ መሆኑ ለሰው ልጅ ጤና ተስማሚ ነው፡፡ በግላቸው አካባቢያቸው የመንፈስ እርካታ ይሰጣቸዋል፡፡ በንጹህ አየር ላይ ሆነው ነው የግብርና ሥራቸውን የሚያከናውኑት። ለከብቶቻቸውም መኖ አይቸገሩም፡፡ ሰው ባለው መደሰት አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡ የሚያስፈልገው የሥራ ተነሳሽነት ብቻ ነው ይላሉ። መሬቱም የሚሰራ እጅ እየጠበቀ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ሁሉንም አይነት ምርት ማምረት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል፣ ምርት ካለ ደግሞ ሸጦና ለውጦ የከተማው ማህበረሰብ እንደሚኖረው አይነት ኖሮ መኖር እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

በአካባቢያቸው የመብራት አገልግሎት የሚቀረው ቢሆንም አንዳንዶች አካባቢዎች ላይ አገልግሎቱ በመኖሩ ወደፊት ይሟላል የሚል ተስፋ አላቸው። በተለይም የከተማ ኑሮ ፍለጋ አካባቢያቸውን ለቀው ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሄዱ ወጣቶች በአካባቢያቸው ላይ ሰርተው ለመለወጥ ጥረት ቢያደርጉ ከከተማ ለማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ወደአካባቢያቸው ማምጣት እንደሚችሉ አቶ ወንድሙ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ለውጥ በሰው ልጅ እጅ ላይ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወደኋላ የቀረውን የግብርና ሥራ በማሻሻልና በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ መቻል አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡ ግብርናውን ለማዘመን እርሳቸው ካሳለፉት የግብርና ሥራ የተለያዩ እድሎች መኖራቸውንና ወጣቱ ይሄንን እድል ተጠቅሞ እራሱንና ሀገሩን ማሳደግ እንዳለበትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከተማም ቢሆን በቀላሉ የሚኖርበት፣ የኑሮ ውጣ ውረድ የሌለበት እንዳልሆነ ወጣቱ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

ስለገበሬው ሁኔታ

ገበሬው የአመት ጉርሱና ልብሱ የግብርናው ሥራ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ገንዘብ የለውም የሚለው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ እውነት ገበሬው ገንዘብ የለውም? አቶ ወንድሙ፤ ገበሬው ደሀ አይደለም ይላሉ፡፡ ተቀጥረውም ይሁን በተለያየ መንገድ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡፡ ገበሬው ደግሞ ሀብቱ ያለው ጎተራ ውስጥ ነው፡፡ ከጎተራው አውጥቶ ወደብር ይለውጣል፡፡ በእርሳቸው እምነት በግብርና የሥራ ወቅት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ያልሰራ ሰው ብቻ ነው ብር የሚያጣው፡፡ በተለይ ገበሬ ጠንክሮ ከሰራ መንግሥትም የሚያስፈልጉትን የግብርና ግብአቶች በወቅቱ ካቀረበ፣ የተለያዩ የሰብል በሽታዎች ሲያጋጥሙም ፈጥኖ መከላከል ከተቻለና ምርታማነት ካደገ እንደገበሬ ሀብታም የለም ነው የምለው ሲሉም አንስተዋል፡፡

ስለትዳራቸው

አቶ ወንድሙ ስለባለቤታቸውና የትዳራቸው ሁኔታ እንደነገሩኝ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ አዛለች ማሞ ይባላሉ፡፡ በትዳር ከ30 አመት በላይ አብረው ኖረዋል።

“… አምስት ልጆች የወለደችልኝ ባለቤቴ ናት፡፡ እወዳታለሁ፡፡ አከብራታለሁ፡፡ እርስዋም እንደኔው እንደሆነች ነው የሚሰማኝ፡፡ ኑሮአችንም እንደአቅማችን እንደቤታችን ነው፡፡ በመካከላችን መጥፎ ነገር ተፈጥሮ ከቤት ወጥታ የሄደችበት ጊዜ የለም፡፡ እርስዋ የቤቱን ሥራ እኔ ደግሞ የግብርናውን ስራ እየተወጣን በፍቅር አብረን እየኖርን ነው፡፡ እንደውም ልጆቼ ትዳራቸው እንደ እኔና ባለቤቴ እንዲሆንላቸው ነው የምመኘው” ፡፡

መቼም እንኳን ሰውና ሰው እግርና እግርም ይጋጫል ይባላል፡፡ ግጭት መኖሩ አይቀርም፡፡ አምሽቶና ጎንጨት ብሎ ቤት መግባት የአባወራ ወግ ተደርጎም ስለሚወሰድ እዚህ ላይም አቶ ወንድሙ፤ ብዙ ጊዜ በመካከላቸው ግጭት የሚነሳው ከልጆች ጥፋት ጋር በተያያዘ እንደሆነና ግጭቱም ለኑሮ መሆኑን ነው የነገሩኝ፡፡ ባለቤታቸው ከቤት ሥራ በተጨማሪ በግብርና ሥራ አረም በማረም፣ በመጎልጎል እንደሚያግዟቸው፣ በጋራ እንደሚሰሩና ለፀብ ጊዜ እንደሌላቸው ነው ያጫወቱኝ፡፡

በገጠር ሴቶች የሥራ ጫና እንዳለባቸው፣ ወንዱ ደግሞ መጠጥ ጎንጨት ብሎ የሚገባ ሽምግልና እውላለሁ እያለ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ሥራ እንደማያግዝ ስለሚነገረውም አቶ ወንድሙ የሚባለው ነገር እርሳቸውን እንደማይገልጽ ነው የነገሩኝ፡፡ በጋራ ሆነው በኑሮአቸው ለውጥ ለማምጣት እንጂ ባለቤታቸው ብቻ እንዲወጡ የሚያሳድሩት ጫና አለመኖሩን ነው ያስረዱት። በመጠጥ በኩል ያላቸውንም ልምድ ሲናገሩ፤ ሰክረው ቤተሰባቸውን ለሚያውኩ አንዳንዶች ያዝናሉ፡፡ ሁሉ ነገር ልክ አለው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም በመጠኑ አካባቢ ላይ የሚገኙ የባህል መጠጦችን አልፎ አልፎ ይጠቀማሉ፡፡ በባህሪያቸው አለኝ ብለው ማባከን፣ ተቸግረውም መታየት አይፈልጉም፡፡ ሁሉን ነገር በልክ የሚለውን ነው የሚመርጡት፡፡

ስለልጆቻቸው የአስተዳደግ ሁኔታ

አቶ ወንድሙ፤ አምስት ልጆች አሏቸው፡፡ ልጆቻቸውንም ያስተምራሉ፡፡ 12ኛ፣ 10ኛ፣ 9ኛ፣ 6ኛ ክፍል የደረሱ ናቸው፡፡ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል የደረሱት ጥሩ ውጤት ባለማምጣታቸው ካሉበት ክፍል በላይ መግፋት አልቻሉም፡፡ ልጆቻቸው በትምህርታቸው ውጤታማ ላለመሆናቸው ልጆቹ ብቻ ሊወቀሱ አይገባም ይላሉ፡፡ በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ስለትምህርታቸው ክትትል በማድረግም ሆነ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳላሟሉላቸውና የእርሳቸውም ድጋፍ እንዳነሳቸው ይገልጻሉ፡፡ የአቅም ማነስ ክፍተት እንደሆነም ይገነዘባሉ፡፡

በግብርና ሥራ የልጆች እገዛ እንዴት እንደሆነም ጠይቄያቸው፤ ‹‹ልጆችን እንዳሳደግሻቸው ነው፡፡ ሥራ እያሳየሽና እየመራሻቸው ከሆነ ይከተሉሻል። እኔም በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ተገቢውን ድጋፍ ባላደርግላቸውም በግብርናው ላይ ችሎታ እንዲኖራቸው፣ ቤተሰብንም ማገዝ እንዳለባቸው የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ። በሥራ ያግዙኛል›› በማለት ምላሽ ሰጥተውኛል። ሁሉት ልጆቻቸውን ኩለው በመዳር ለጎጆ አብቅተዋል፡፡ የልጅ ልጆችም ለማየት በቅተዋል። ልጆች እራሳቸውን እንዲችሉ ወላጅ ይጨነቃል የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ ለራሱና ለሀገር የሚጠቅም ዜጋ ማፍራት የወላጅ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ያምናሉ፡፡

ስለኑሮአቸው ሁኔታ

የገጠሩ ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት፣ የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት እጥረቶች እንዳሉበት ያስታውሳሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ላምባ፣ ኩራዝ ነበር ለቤታቸው መብራት የሚጠቀሙት፡፡ ዛሬ በየቤቱ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲዳረስ በመንግሥት በኩል ጥረት ተደርጎ አንዳንድ አካባቢዎች ተጠቃሚ መሆን ቢጀምሩም የሚቀሩ አካባቢዎች እንዳሉ ያስታውሳሉ። በተለይም የገጠሩን ማህበረሰብ በጣም ተጠቃሚ እያደረገ ያለው በፀሐይ ኃይል የሚሰራው የመብራት አገልግሎት የብዙዎችን የኃይል አቅርቦት ችግር እየፈታ እንደሆነና እርሳቸውም አንዱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ጥቅሙና አስፈላጊነቱ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል። በዚህ አጋጣሚም መንግሥት ተደራሽነቱ ላይ አጠንክሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም የቀድሞ ኑሮቸውን አሁን ላይ ከሚኖሩት ጋር በማነጻጸር ልዩነት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው ግብርና በጀመሩበት ዘመን የግብርና ሥራቸው በእውቀት ታግዞ ቢሆን በኑሮቸው ለውጥ ያመጡ እንደነበር፣ ያም ሆኖ ግን ከቀድሞ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡ ‹‹እድሜዬ በገፋ ጊዜ የመጣው ለውጥ ጥሩ እድል ነው ብዬ ነው የማስበው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት አካባቢያቸው ላይ በቆርቆሮ የተሰራ ቤት አልነበረም፡፡ የግብርና ሥራውም ቢሆን አልተስፋፋም፡፡ ዛሬ ልማቱ ተስፋፍቷል፡፡ እኔ የቀደመውንም የአሁኑንም ልዩነቱን ስለማውቅ የተሻለው የትኛው እንደሆነ ለመናገር እችላለሁ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ግን ያለፈውን ስለማያውቅ ችግሩ ላይገባው ይችላል። ከእኛ ግን በታሪክ መማር ስለሚችል አሁንም ለተሻለ ነገር መነሳት አለበት ብዬ ነው የማምነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

በግላቸው ለልጆቻቸውም ለአካባቢያቸው ልጆች ያሳለፉትን ጊዜ ያጫውቷቸዋል፡፡ በቀን ሥራ በሰአት በአንድ ብርና ባነሰ ዋጋ እየተከፈላቸው ኑሮን ለማሸነፍ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ሁሉ እንደሚነግሯቸውና እነርሱ ግን ከእርሳቸው በተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ጠንክረው እንዲሰሩ፣ በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ፣ የወጣትነት ጊዜያቸውን በከንቱ እንዳ ያሳልፉ ምክራቸውን እንደሚለግሷቸው ነው የገለጹት፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You