ኢትዮጵያውያን ከ99 በመቶ በላይ አማኞች ናቸው የሚል የጨረታ /Clichy / እውነት አለ። የክርስትና ፣ የእስልምና ፣ የይሁዲ ወይም የሌላ ዕምነት ተከታዮች ናቸው። ጥያቄው እኔን ጨምሮ ይሄን እምነታቸውን በተግባር ይኖሩታል የሚለው ነው። አዎ ! አብዛኛዎቹ ዕምነታቸውን በህይወታቸው ገልጠው ይኖራሉ። ቁጥሩ ቀላል የማይሆን አማኒ ግን ከዕምነቱ አስተምህሮና ቀኖና በተቃራኒው መቆሙ ጸሐይ የሞቀው የአደባባይ ሀቅ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ቁጥራችን ቀላል ያልሆነ ይሄን እምነታችንን በህይወታችን ስለማንኖረውና ስለማንገልጠው ዛሬም ሆነ ትናንት ሀገራችን ፈተና ላይ ወድቃለች። ልዩነት፣ ጥላቻና መጠራጠር መልካሙን ተቆጣጥሮታል። ሀገራችንና ሕዝባችን እረፍት አጥተዋል ። ሃይማኖታችንና ዕምነታችን ወደ ሰውነት ተራ መመለስ ተስኗቸዋል። ከራሳችንም ከአምላኩም ተጣልተናል። በዓላትን በነቂስ ወጥተን አክብረን ወደየቤታችን ስንመለስ ልዩነታችንን ፣ ጥላቻችንን፣ መጠራጠራችንና አጠቃላይ ፖለቲካችን የቱ ጋ ነበር ያቆምነው ብለን እንደ እሪያ ወደ ጥፋታችን እንመለሳለን ። የጥላቻንና የልዩነትን ፍላጻ ወደ ሚያንበለብሉት ማህበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች ጎራ እንቀላቀላለን። ውጊያውን እንመራለን።
ከገባንበት ሁለንተናዊ ቀውስ ለማገገምም ሆነ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የጣልናቸውንና የረሳናቸውን ዕምነቶች ፣ ሃይማኖቶች ባህላዊ ወረቶች እንዲያንሰራሩና መልሰው እንዲያቆጠቅጡ ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅብናል። ጎን ለጎን መንግሥት ልዩነትንና ጥላቻን የሚጎነቁሉ አስተሳሰቦችን ከስር ከስር የማስወገድ ኃላፊነት አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻልን ከገባንበት ፈተና መውጣት አይቻልም። ከፈተናዎቻችን አንዱ የግብይት ሥርዓታችን ነውና እሱን በአለፍ ገደም አይተን ወደ ዛሬው መሰናዘሪያችን ወደ ወርቃማው ሕግ እናልፋለን።
በሀገራችን የግብይት ሥርዓት ላይ የምናየው ስስት፣በአንድ ጀምበር የመክበር አባዜ፣ኪሎ መቀሸብ፣በምግብ ሸቀጦች ላይ ባአድ ነገር መጨመር፣ አመሳስሎ ማምረት፣የመጠቀሚያ ጊዜያ ቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ለገበያ ማቅረብና ሌሎች ፈተናዎች አማኝ ከሆነች ሀገር ለዛውም የሦስቱ አብርሃማዊ ዕምነቶች ማለትም የክርስትና፣የእስልምና እና የይሁዲ ዕምነቶች ቀደምት ተቀባይ ከሆነች ሀገር የሞራል ስሪት ጋር የሚጋጭ ነው።
የግብይት ሥርዓቱን አነሳን እንጂ ነገረ ስራችን ሁሉ አማኝ ያለበት ሀገር ላይ መሆኑ ግራ ያጋባል። ምን ነካን ያስብላል። በጥቂት አስርት አመታት ውስጥ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባል፣መተሳሰብ፣መተዛዘን እንዴት እንዲህ ሊዳከም ቻለ፤ፈሪአ ፈጣሪ የነበር ሕዝብ ዛሬ ምናገኘውና ተጨካከነ ብሎ መጠየቅ የአባት ነው። እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። የሚጠይቅም የሚመልስም ብርቅ ሆኗል። ከዛ ይልቅ መላመድን መርጠናል። ባላየ ባልሰማ ማለፈን በጀ ብለናል።
“አንተ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ።” የሚለውን ወርቃማ ሕግ ገሸሽ አድርገን የየራሳችንን ወርቅ ቅብ አብለጭላጭ ሕግ ያወጣን መስሏል። መጭበርበር፣ማጭበርበር፣ መወሻሸት፣መከዳዳት፣ማታለል፣መታለል፣ወዘተረፈ የዕለት ተዕለት ምሳችን የሆነ ይመስላል።አለማዊ ሕጉም አስርቱ ትዕዛዛትም ሆነ ስነ ምግባርና እሴት አባ ከና ሚላቸው እየጠፋ ነው።
እውነት ለመናገር ከዚህ የውድቀት ቁልቁለት የሚገታንና ወደ ቀደም ከፍታችን የሚመልሰን አለማዊና መንፈሳዊ ተቋም አለ ወይ ብሎ መጠየቅ በራሱ ያባባል።ያስጨንቃል። መልሱ ምንም ይሁን የዜግነት ድርሻን መወጣት ሌላው ቢቀር ከህሊና ሙግትና ክስ ያድናል።ፖሊስ አቁመን፣ዳኛ ሰይመን፣የሃይማኖት አባት ሰምተን ሰው መሆን ካቃተን እስኪ ወርቃማውን ሕግ እንሞክረው።
ላንተ ቢደረግልህ ምትወደውን ለሌሎችም አድርግ፤ባንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሰው ላይ አታድርግ። ብዙ አይነት ሕጎች አሉ። ይህኛው ሕግ ግን ወርቃማ በሚል የተቀመጠው ለአብዛኞቹ አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕጎች መሰረት በመሆኑ ነው።ወርቃማው ሕግ ውስጣችን ሰርፆ የመግባት አቅም አለው። እንደሌሎች ሕጎች ሕግ አስከባሪ ፈርተን የምንተገብረው አይደለም።
ወርቃማው ሕግ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙንት ወደ መልካምነት ይቀይራል። ሰዎችን የሚጎዳ ነገር የማናደርገው በውል ስለታሰርን ወይም ወንጀል ስለሆነ አይደለም እኛ ላይ ቢደረግ ስለማንወድ ነው። ይህ ሕግ ማህበረሰቡንም ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው። ኢፍትሐዊነትን እና የሌሎችን በደልና ቅሬታም ይቀንሳል።ይህን ወርቃማ ሕግ ለማወቅ ሕግ ት/ቤት መግባት ወይም የሕግ መጽሐፍትን መመርመር አያስፈልግም።
ልብ ብለን ካስተዋልነው በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተከትቧል። አጭር እና ግልፅ ነው።‘‘ላንተ ቢደረግልህ የምትወደውን ለሌሎችም አድርግ !!’’ይህን ታላቅ ሕግ አውቀህ በትክክል ከተገበርከው በቃ! ሀሪ ጌንስለር የጻፈውን አጣቅሼ የወርቃማውን ሕግ ጥቂት ወርቃማ ነጥቦች ላንሳልህ ይለናል ኪዳኔ መካሻ። እንዲህ ሆነ ፤አንድ ዝንጀሮ እና አሳ ከወንዝ አጠገብ ይኖሩ ነበር። ዝንጀሮው ወርቃማውን ሕግ ስለሚያከብር ሁሌም ለሱ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ለሌሎችም ያደርግ ነበር።
አንዳንዴ ግን ሕጉን የሚተገብረው በቅጡ ሳያስተውል በየዋህነት ነበር። አንድ ቀን ኃይለኛ ጎርፍ መጣና እየባሰ ሲሄድ ዝንጀሮው ተንጠላጥሎ ከወንዙ አቅራቢያ ያለው ዛፍ ላይ ወጣ። ቁልቁል ሲመለከትም የጎርፉ ውሃ ትንሿን ወንዝ ስለሞላት አሳውን ሲያንገላታው ተመለከተ። ዝንጀሮው ‘እኔ ውሃው እንዳይደርስብኝ መሸሽ ፈልጌ ዛፍ ላይ ወጥቻለሁ አይደል?ለአሳውስ? እኔ እንዲደረግልኝ የምፈልገውን ለሱም ማድረግ አለብኝ’’ ብሎ አሰበና ከዛፉ ላይ ወርዶ ከወንዙ ውስጥ አሳውን አውጥቶ የዛፉ ቅርንጫፍ ላይ አስቀመጠው።እንዳሰበው ሳይሆን ቀረና ወዲያውኑ አሳው ሞተ።
ይህ የአፍሪካውያን ብሒል ወርቃማውን ሕግ በአግባቡ መረዳትና እኛ የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች ስናደርግ በሌሎች እና በኛ መሀል ያለውን ልዩነት መረዳት እንዳለብን ይጠቁማል። ከየዋሁ ዝንጀሮ አይነት ስህተት ለመጠበቅ “እኔ ሌላው ሰው በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ብሆን ይህ የማደርገው ነገር እንዲደረግብኝ ፍቃደኛ ነኝን?” ብለን መጠየቅ አለብን።
አንድ አደገኛ ወንጀለኛ ነበር። ለብዙ ጊዜ ሀገሩን ሲያምስ ኖሮ አንድ ቀን ተያዘና ታሰረ ክስም ቀረበበት። ክሱ የቀረበበት ፍርድ ቤት ግድግዳ ላይ ‘‘ለሌሎች አንተ እንዲሆንልህ የምትወደውን አድርግላቸው።’’ የሚል ጥቅስ ተለጥፏል። ይህን የተመለከተው ወንጀለኛ፤‘‘ክቡር ዳኛ እርሶ በኔ ቦታ ቢሆኑ ወደ እስር ቤት መግባት አይፈልጉምና በወርቃማው ሕግ መሰረት እርሶ ላይ እንዲሆን የማይፈልጉትን እኔ ላይ ፈርደው ወህኒ ሊከቱኝ አይገባምና በነፃ ይልቀቁኝ’’ ሲል አመለከተ።
ዳኛው ‘‘ወርቃማውን ሕግ በትክክል ስላልተረዳከው ነው ተከሳሽ። በታላቁ ሕግ መሰረት አንተን በእስር መቅጣት እችላለሁ። ምክንያቱም እኔም እንዳንተ አደገኛ ወንጀለኛ ብሆን አሁኑኑ ወደ እስር ቤት ለመላክ ፍቃደኛ ነኝ።’’ ብለው ቀና አሉና ‘‘እንዲህ አይነት ወንጀል ከሰራሁ አደራ እንዳትለቁኝ ወደ ወህኒ ወርውሩኝ።’’ በማለት ለችሎቱ ታዳሚ አሳሰቡ።ወንጀለኛውንም ተገቢውን የእስር ቅጣት ፈረዱበት።
ወንጀለኛው ወርቃማውን ሕግ አለሳልሶ በመተርጎም በፍፁም ከሌሎች ፍላጎት ጋር የሚቃረን ነገር አታድርግ በማለት ነው ከቅጣት ለማምለጥ የሞከረው።ሆኖም ብዙ ጊዜ ሌሎች የማይፈልጉትን ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። እሳት ውስጥ እጁን የሚከት ሕፃንን መከልከል አለብን፣ያለ ሽያጭ ደረሰኝ የሚሸጥልንን ነጋዴ እምቢ ማለት አለብን፣ ሙሰኞችን ማጋለጥ፣ ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ አለብን። ይሄን የምናደርገው እኛም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ እኛ ሌላው ላይ ያደረግነው ያ ሰው የማይፈልገው ነገር እንዲደረግብን ፍቃደኛ እንሆናለን።
ወርቃማው ሕግ ሌሎችን የሚጎዳ ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች የማይፈልጉትን ነገር እንድናደርግ ስለሚፈቅድልን ነው። ሕጎች የወጡት የሰዎችን ባህሪ ለመቆጣጠር ነው። በእርስ በርስ ግንኙነታችን ውስጥ በሚከሰት የፍላጎትና የጥቅም ግጭት እራሳችንን ወይም ሌላውን ለመጥቀም ሌሎችን እንዳንጎዳ ነው ዋነኛ አላማቸው ። ሕጎችን አውቆ የራስን መብት ማስከበር ግዴታንም መወጣት በሕግ ተጠያቂ ከመሆን ያድናል።
ከየትኛውም ሕግ በላይ በማንኛውም የሕይወታችን እንቅስቃሴ ልንጠቀምበት የሚገባን አስፈላጊውና ታላቁ ሕግ ግን ይህ ወርቃማው ሕግ ነው።ለማንኛውም የሕጎች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ታላቁን ሕግ እናክብረው። ምንም ነገር ከማድረጋችንም በፊት ‘‘የማደርገው ነገር እኔ ላይ ቢደረግ እወዳለሁ?’’የሚለውን ይህን የወርቃማውን ሕግ ወርቃማ ጥያቄ እራሳችንን መጠየቁን አንዘንጋ!! እስኪ እውነታውን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ደግሞ በወፍ በረር እንቃኘው።
“ወርቃማው ሕግ” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ብዙ ሰዎች ይህን አገላለጽ የሚጠቀሙት ኢየሱስ ያስተማረውን አንድ የሥነ ምግባር ደንብ ለማመልከት ነው። ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ የሚከተለውን የሥነ ምግባር ደንብ ሰጥቶ ነበር። “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው። ”ማቴዎስ 7:12፤ ሉቃስ 6:31፤።
ወርቃማው ሕግ፣ ሌሎች እንዲይዙን በምንፈ ልግበት መንገድ እነሱን እንድንይዝ ያበረታታናል። ለምሳሌ አብዛኞቻችን ሌሎች ሰዎች አክብሮት፣ ደግነትና ፍቅር ሲያሳዩን ደስ ይለናል። በመሆኑም እኛም ለሌሎች “እንዲሁ” ልናደርግላቸው ይገባል። ወርቃማው ሕግ ከሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ጋር በተያያዘ ይሠራል። ለምሳሌ ትዳራችንን ያጠናክርልናል። ኤፌሶን 5:28, 33 ወላጆች ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው እንዲያሳድጉ ይረዳቸ ዋል። ኤፌሶን 6:4፤ በጓደኛሞች፣ በጎረቤታሞች እና በሥራ ባልደረቦች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል። ምሳሌ 3:27, 28፤ ቆላስያስ 3:13፤
ወርቃማው ሕግ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን አብዛኛውን ሃሳብ ጠቅልሎ የያዘ ነው። ኢየሱስ ስለ ወርቃማው ሕግ ሲናገር “ሕጉም (የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት) ሆነ የነቢያት ቃል (የትንቢት መጻሕፍት) የሚሉት ይህንኑ ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) በሌላ አባባል ወርቃማው ሕግ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በዋነኝነት የተገለጸውን መሠረታዊ ሃሳብ ጠቅለል አድርጎ ይዟል፤ ይህ ሃሳብ ‘ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ’ የሚለው ነው። ሮም 13:8-10፤ወርቃማው ሕግ፣ ሰጥቶ የመቀበል ጉዳይ ነው? አይደለም። ወርቃማው ሕግ ትኩረት የሚያደርገው በመስጠት ላይ ነው።
ኢየሱስ ወርቃማውን ሕግ ባስተማረበት ወቅት እየተናገረ የነበረው በጥቅሉ ሰዎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን ብቻ አይደለም፤ ከዚህም ባለፈ ጠላቶቻችንን እንኳ እንዴት ልንይዝ እንደሚገባ እየገለጸ ነበር። (ሉቃስ 6:27-31, 35) ከዚህ አንጻር ወርቃማው ሕግ ለሁሉም ሰው መልካም እንድናደርግ የሚያበረታታ ነው።
ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
1.አስተዋይ ሁኑ። ለሌሎች ሰዎች ትኩረት ስጡ። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ከባድ ሸክም እንደያዘ ስትመለከቱ፣ ጎረቤታችሁ ታምሞ ሆስፒታል እንደገባ ስትሰሙ ወይም የሥራ ባልደረባችሁ እንደከፋው ስታስተውሉ ይሆናል። ‘ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት የምትሰጡ’ ከሆነ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር መናገር ወይም ማድረግ የምትችሉበት አጋጣሚ ማግኘታችሁ አይቀርም። ፊልጵስዩስ 2:4፤
2.የሌላውን ስሜት ለመጋራት ጥረት አድርጉ። ራሳችሁን በሌሎች ቦታ ለማስቀመጥ ሞክሩ። እናንተ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ ኖሮ ምን ይሰማችሁ ነበር? (ሮም 12:15) የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ስታደርጉ እነሱን ለመርዳት መነሳሳታችሁ አይቀርም።
- እንደ ሁኔታው ማስተካከያ አድርጉ። እያንዳንዱ ሰው የተለያየ እንደሆነ አትርሱ። ሌሎች እንዲደረግላቸው የሚፈልጉት ነገር እናንተ እንዲደረግላችሁ ከምትፈልጉት የተለየ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ልታደርጉላቸው የምትችሏቸው የተለያዩ ነገሮች ቢኖሩም ይበልጥ የሚያስፈልጋቸውን ነገር መርጣችሁ አድርጉላቸው። 1 ቆሮንቶስ 10:24፤
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም