ስለ ሀገር – እንመካከር

ምንጊዜም በግል ከወጠኑት ሃሳብ ይልቅ በጋራ የመከሩበት ጉዳይ ሚዛን ደፍቶ ይገኛል፡፡ ይህ እውነት ከግለሰቦች አልፎ ወደ ሀገርና ሕዝብ በተሻገረ ጊዜም ትርጉሙ ከበድ ያለ ነው፡፡ ‹‹አንድ ሰው አይፈርድም አንድ እንጨት አይነድም›› እንዲሉ ከግላዊነት በላይ የአብሮነት ተግባር ፍሬው ያማረ፣ ውጤቱ የሰመረ ይሆናል፡፡

አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በትኩረት እየመከረች ነው። ይህ ምክሯ በሕዝቦቿ የማንነት ህልውና ላይ የተመሰረተ ጽኑ አለት ሆኖ ተገንብቷል፡፡ እንዲህ መሆኑ ‹‹እያንዳንዱ – ለእያንዳንዱ ሁሉም ለብዙኃኑ›› እንዲያገባው ሆኖ የተዋቀረ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነት ጥብቅ ሰንሰለት በዋዛ እንዳይላላ፣ እንዳይፈታ ሆኖ ተጋምዷል፡፡

ሀገራዊ ምክክሮች ሲካሄዱ የተለያዩ ዓላማዎችን ከግብ ለማድረስ ሲባል ነው፡፡ እነዚህ ምክክሮች ደግሞ የአጭር ጊዜ ግብን ለማሳካትና መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት ጭምር የሚካሄዱ ናቸው፡፡ የአጭር ጊዜ ግብን ለማሳካት የሚካሄደው ምክክር ዋንኛ ዓላማ ቀውስን ለመከላከልና በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ነው፡፡ ይህ የምክክር አይነት በተወሰነ ጥረት፣በአጭር ጊዜና በጥቂት ኃይሎች ብቻ ችግሮችን ለመፍታት የሚካሄድ ነው፡፡

ይህ አይነቱ ሂደት ጥቂት ተልዕኮችን ብቻ በመያዝ አነስተኛ በሚባል ቆይታ የአጭር ጊዜ ሂደት ይኖረዋል። በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትም ውስን ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ምክክሩን ለማቅለል የሚያግዙ ናቸው። እንዲህ አይነቱ የምክክር ይዘት ሰፊ መሰረት ያለው እንዲሆን አይጠበቅም። በርካታ የአካታችነት ቅርንጫፎች እንዲኖረውም አያስገድድም፡፡

መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ግን በባህሪው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወሰድ እንደመሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉበት የሚጋብዝ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም የተለያዩ አመለካከቶች እንደሚንጸባረቁ ይጠበቃል፡፡ ምክክሩ በአንድ ሀገር በግልጽ በሚስተዋሉ መሠረታዊ ልዩነቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ በየጊዜው እነዚህን ችግሮች ለማጥበብና ለመፍታት አበክሮ ይሰራል፡፡ በዚህ የምክክር ሂደት የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነቶችን ዳግም ለመወሰን አልያም አዲስ የሚባል ውል ለማጠናከር መሰረት ይጣላል፡፡ ልዩነቶች ባሉበት አካባቢ ከኃይል አማራጭ ይልቅ ሰላማዊ አንድነት እንዲጠናከር ይሰራል። ሀገር ወደ አዲስና ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ እንድትሻገር የማድረግ ኃይልም አለው፡፡

ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች እንደሚጠቁሙት፤ ሀገራዊ ምክክር ማለት አዲስና ያልተለመደ ክስተት አይደለም፡፡ መረጃዎች እንደሚነግሩን የመጀመሪያው ሀገራዊ ምክክር መነሻ እ.ኤ.አ በ1989 በምሥራቅና መካከለኛው አውሮፓ ሰፍኖ ከነበረው የኮሚኒዝም ሥርዓት መንኮታኮት ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ አጋጣሚ በዘመኑ በየሀገራቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ክፍተት ለመድፈን የሚያስችል ምክንያትን ፈጠረ። በዚህ ወቅት ፖላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ምሥራቅ ጀርመንና ቡልጋሪያ በችግሮቻቸው ዙሪያ ለመምከር በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጡ፡፡

ተከታዩ ምክክር የታየው በአፍሪካና አፍሪካውያን ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንደ እኤአ በ1990ዎቹ ገደማ ሥልጣን በያዙ መሪዎችና በዜጎቻቸው መካከል እየተፈጠረ የመጣው ልዩነት በርካታ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራትን ወደምክክር ጉባኤ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ጊዜ በደቡብ አሜሪካ አሳታፊ አስተዳደርን ለመመስረት ሲባል መግባባት ላይ የተደረሰበት ሀገራዊ ምክክር እንደቦሊቪያና ኮሎምቢያ የመሰሉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ ያስቻለ ነው፡፡

በቅርቡ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ከአረብ ሀገራት ጋር ተያይዞ የተነሳው ትኩሳት በሌሎች ሀገራት ዘንድ ለመስፋፋት ኃይሉ የተጠናከረ ነበር፡፡ ይህ ችግር ስሩን ሰዶ ከመዛመቱ በፊት በሞሮኮ፣ሊቢያ፣ቱኒዚያና ግብጽ ምክክር ሊካሄድ ግድ ብሏል፡፡ ሱዳን ሊባኖስና ዮርዳኖስ፣ የመንና ባህሬንም ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ ስኬትና ውድቀቶቻቸውን ለመለየት ችለዋል፡፡

ዛሬ ሀገራችን በጽኑ እየተፈተነችበት ላለው የሰላም እጦት ሕዝቦቿ በእኩል መክረው፣ መፍትሔ ሊሹላት ይገባል፡፡ ሰላም ከሌለ የሁሉም ዜጎች ህልም ከቶውንም እውን መሆን አይችልም፡፡ ሰርቶ ማደር ውሎ መግባት፣ አይታሰብም፡፡ ሌት ተቀን እንቅልፍ የሚነሳን የሰላማችን ስብራት በወጉ ተጠግኖ ጤናው ይረጋገጥ ዘንድ በአንድ እሳቤ የመከረ፣ በጋራ ክንድ የተጣመረ አንድነት ዕውን ሊሆን ግድ ይላል፡፡

በሀገራችን የሚካሄደው ምክክር በኅብረተሰቡ፣ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ በማድረግ ለዘመናት በችግር ሲጓዝ የቆየውን ውስጣዊ ቀውስ በውይይትና በሰላም ለመፍታት የሚያስችል ነው። በዚህ ሂደት የፖለቲካ ባህል ዳብሮ ምቹ የዴሞክራሲዊ ሥርዓት እንዲገነባ ፣ ወቅታዊ ችግሮች ለዘለቄታው ተፈተው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል፡፡

በኢትዮጵያ መካሄድ የጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሕዝብና ትውልድ ወደተሻለ ምዕራፍ እንዲሻገሩ የማድረግ ኃይል አለው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሀል የሃሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩና ከጦርነትና ግጭቶች ማግስት የፖለቲካ ክፍተት ሲያጋጥም ሰላምና መግባባት እንዲፈጠር አልሞ የሚሠራ ነው፡፡

በአንድ ሀገር ብሔራዊ ምክክር ሲኖር በማህበረሱ መሀል የሚከሰቱ ከባድ ያለመግባባት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይቻላል፡፡ እንዲህ መሆኑ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የመተማመን ስሜት እንዲፈጠር ያግዛል፡፡ ምክክርን ባህል በማድረግና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማጠናከር ልዩነቶችን በዘለቄታዊነት ለመፍታት ለሚደረገው ጥረትም ዓይነተኛ መፍትሔ ይሆናል፡፡

የሀገራዊ ምክክር መኖር በፖለቲካ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚ ያደገና የተለወጠ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት ይጥላል፡፡ ይህ የምክክር ሂደት የራስን ችግር በራስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በተለየ ቅርበት መፍትሔ ለመስጠትም የሚያግዝ ነው፡፡

የሀገራዊው ምክክር ኮሚሽኑ የኮሚሽነር ምክር ቤቱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት አጀንዳዎች ተለይተው በተለያዩ አካላት ወሳኝ የሚባሉ ውይይቶች እንዲካሄዱ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን በሕግ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ፈተናዎች መሀል ተራምዷል፡፡

ኮሚሽኑ በእስከዛሬ ቆይታውም በአስር ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከአንድ ሺ በላይ ወረዳዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ነበረው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በምክክር የምዕራፍ ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮችን በማስመረጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን በትኩረት ቀጥሏል፡፡

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት በነበረው ምክክር የወረዳ ማህበራት፣ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ተወካዮች፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ሕዝቡን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ወገኖችም በሚያቀርቧቸው ይዘቶች ላይ ሰፊ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

አሁን ላይ በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሁሉ በግልም ይሁን በጋራ አጀንዳውን ወደ ኮሚሽኑ የማምጣት መብት አለው። ምክክሩ ግልጽና ሁሉን አካታች ይሆን ዘንድም በስፋት እየተሠራበት ነው፡፡

ሀገር ካስማዋ ጸንቶ ሕዝቦቿ በኑሯቸው እንዲታመኑ ሰላም ይሉት ወሳኝ ጉዳይ ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ልዩነቶች ተፈተው፣ ግጭትና ጦርነት ይቆም ዘንድ መካሪ፣ ዘካሪ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም ዓለም በልዩነት ፣ በሃሳብ ተነጣጥሎ መኖር አዲስ የሚባል አይደለም፡፡ ጉዳዩ በአጭሩ ካልተቋጨ ግን የዚህ መንገድ መጨረሻው ገደል እንደሚሆን መገመቱ ቀላል ነው፡፡

ልዩነቱ ሰፍቶ ግጭት የሚፈጥር ፣ጦርነት የሚያጭር በሆነ ጊዜ ችግሩ በምክክር እንዲፈታ የሚያስማማ፣ የሚያቀራርብ አካል ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ሀገራችን በመልከ ብዙ ችግሮች እየተፈተነች ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነት፣ የፍላጎት መለያየትን አስከትሎ ፣የመብትና የይገባኛል ጥያቄዎች ጤናማ መስመራቸውን ከሳቱ ቆይተዋል ፡፡

ነፍጥ አንግበው፣ ጫካ መሽገው፣ ከመንግሥት ጋር ፊትና ጀርባ የሆኑ ወገኖች ዛሬ ስለሀገርና ሕዝብ ሰላም ሲባል ልዩነታቸውን በመነጋገር፣ በመወያየት እንዲፈቱት ይጠበቃል፡፡ ለዚህ እውነት የብረት ድልድይ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሁሉም ወገን የሚደርሰውን የአጀንዳ ጭብጥ በማሰባሰብ ወደሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

አሁን በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የአጀንዳ ግብአት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ቀሪ ክልሎች በመድረስ ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ይጠበቃል። ከሀገራዊ ምክክሩ የሚገኙ ቱርፋቶችን ለመካፈል ‹‹ሁሉም ወገን ለሁሉም›› የራሱን አሻራ ሊያኖርም ግድ ይለዋል፡፡ የዚህ እውነታ መልክ አንድም የሰላም፣ ሌላም ደግሞ የሀገር ጉዳይ ነውና ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You