ዛሬ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ላይ ነን:: ሞፈር፣ ቀንበር እና ሌሎች የግብርና ዕቃዎች ‹‹ኋላቀር›› ዕቃዎች ናቸው:: የሚገርመው ግን ዛሬም በእነዚህ መገልያዎች ነው የምንገለገለው:: በአንድ ወቅት ከጓደኞቼ ጋር ብሔራዊ ሙዚየም ገብተን ሞፈር ስናይ ፈገግ ማለታችን አልረቀም ነበር:: ምናልባት ለፈረንጆቹ ካልሆነ በስተቀር ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሞፈር ሙዚየም የሚገኝ ዕቃ ሳይሆን ከአዲስ አበባ 20 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ሲጠቀሙበት የሚያገኘው ነው:: ዛሬም በአገልግሎት ላይ ያለ ዕቃ ነው:: ትዝብቱን ለሌላ ቀን እንተወውና የገበሬውን የሥልጣኔ አስጀማሪነት ግን ልብ እንበል!
እነዚያን ዕቃዎች ከእንጨት ገጣጥሞ መሥራት የሥልጣኔ መጀመሪያ ነው:: ዓለም አሁን የደረሰችበት ላይ የደረሰችው ከዚህ በመነሳት ነው:: እነዚህ ነገሮች ሁሌም ሰኔ በመጣ ቁጥር ትዝ ይሉናል::
እነሆ ዛሬ ሰኔ አንድ ብለን የክረምቱን ወራት የመጀመሪያ ወር ተቀብለናል:: በኢትዮጵያ የወቅቶች ምደባ የክረምት ወር የሚጀምረው በሰኔ ነው:: ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ማለት ነው:: በገበሬው ዓውድ ደግሞ የሳምንቱ የመጀመሪያው የሥራ ቀን ሰኞ ነው:: ስለዚህ የሰኔ የመጀመሪያው የሥራ ቀን ሰኞ ይሆናል:: የክረምት ወቅት ደግሞ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው:: ክረምት ማለት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚያችን ዋልታና ማገር የሆነው የግብርና ሥራ የሚሠራበት ነው::
በመሬት መራቆት እና በሕዝብ ብዛት የእርሻ መሬት እየተወደደ ነው:: ትልልቅ አባቶች የአሁን ወጣቶችን እያዩ ይገረማሉ:: የሚገረሙበት ምክንያት፤ ቀደም ሲል ለእርሻ የማይውለውን መሬት ለእርሻ ሲያውሉ አይተው ነው:: ቀደም ሲል በነበረው ዘመን የሚታረሰውና የማይታረሰው እኩል ነበር፤ እንዲያውም የማይታረሰው ሊበልጥም ይችላል:: አሁን ግን እንደዚያ ብሎ ነገር የለም፤ የእግር መርገጫ የምታክል ሳትቀር ገበሬዎች እየፈቀፈቁ ያርሷታል::
‹‹ይህ ለምን ሆነ?›› ከተባለ፤ ችግር ነው ያስተማራቸው:: ወጣቱ ገበሬ የእርሻ ማሳ ሲጠበው የፈጠረው መላ ነው:: አባት ገበሬ መሬት ለልጁ አካፍሎ ሲጠበው ችግር ያመጣለት ዘዴ ነው:: ቀደም ባሉት ዘመናት ከመኖሪያ ቤት አቅራቢያ ላይታረስ ይችል ነበር፤ አሁን ግን እስከ ቤቱ አጠገብ ድረስ ይታረሳል:: እንደመሬቱ ባህሪ የሚስማማውን እህል ይዘራል ማለት ነው:: ይህ ለምን ሆነ ከተባለ ችግር የወለደው መላ ነው::
በነገራችን ላይ ‹‹የሥልጣኔ ምንጩ ችግር ነው›› ነው የሚባለው:: የሰው ልጅ ዋሻ ውስጥ ይኖር ከነበረበት ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬው ረቂቅ ዓለም ድረስ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን አሳይቷል:: እነዚህን ሥራዎች የፈጠራቸው ችግር ነው:: ግዑዝ አካላትን አፋጭቶ እሳት ከመፍጠር እስከ ኤሌክትሪክ ድረስ፣ በእንስሳት ጀርባ ከመሄድ በሰማይ የሚበር አውሮፕላን እስከ መፈልሰፍ የደረሰው ችግር እያስተማረው ነው::
አንዲት የቅርብ ምሳሌ ብቻ እንውሰድ:: ኮቪድ-19 በዓለም ብሎም በሀገራችን ሲከሰት ከፍተኛ ጭንቀት ነበር:: ቫይረሱ በእጅ ንክኪ እንደሚተላለፍ ሲታወቅ በእጅ መነካካት አስፈሪ ሆነ:: ይህ ችግር ቀደም ሲል በእጅ እየከፈትን እንታጠብ የነበረውን ልማድ የሚያስቀር ዘዴ ወለደ:: ይህን ዘዴ ለብዙ ዓመታት አላሰብነውም ነበር:: ግን ችግር ብልሃትን ይወልዳል ስለሚባል ሲጨንቀን ያንን ዘዴ ፈጠርን:: እርግጥ ነው ሁሉም ሰው እንዲህ አይነት ዘዴ ይመጣለታል ማለት አይደለም፤ ጥበብና ማስተዋልን ይጠይቃል::
ይህ የገበሬው ዘዴ አሁን ወደ ከተማ እየመጣ ነው:: ከተማ ውስጥ በበሬ ወይም በትራክተር የሚታረስ ሰፊ መሬት ቢኖር ጥሩ ነበር፤ ግን የለም! እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም ልክ እንደ ገበሬው ችግሩን የምንወጣበት ዘዴ እንፈልጋለን ማለት ነው:: የመገልገያ ዕቃዎች ውስጥ አፈር እያደረግን በየግድግዳውና አጥሩ ላይ እንሰቅላለን ማለት ነው:: ከገበሬው ማሳ እንደሚታረሰው በኩንታል የሚታፈስ ምርት ባናመርትም የዕለት ምግብ ማምረት ይቻላል ማለት ነው::
መንግሥት በየጊዜው ‹‹የከተማ ግብርና›› ሲል እንሰማለን:: መበረታታት ያለበት ነው፤ ነገር ግን አንድ ልብ ማለት ያለበት ነገር አለ:: በቤትና በጓሮ ውስጥ በመገልገያ ዕቃዎች ላይ የሚተከል አትክልት ችግር ፈቺ አይደለም:: በሄክታር የሚቆጠር ሰፋፊ መሬት በፀጥታ ችግር ምክንያት ከእርሻ ውጭ ነው:: በዋናው ጦርነትም ሆነ በአካባቢያዊ ሽፍቶች የተፈናቀሉ ብዙ ገበሬዎች አሉ:: እነዚህ ገበሬዎች ወደ ከተማ እየተሰደዱ ለልመና ተዳርገዋል:: አርሶ የሚያበላው ወገን እየተፈናቀለ በጣሳ እና በፕላስቲክ የሚተከል ጎመን ችግርን አይቀርፍም::
በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግሩ የሚቀረፈው በተለመደው በበሬም ሆነ በዘመናዊው ትራክተር በሚታረሰው እንጂ ግድግዳ ላይ በሚንጠለጠል የውሃ ፕላስቲክ አይደለም:: ስለዚህ መንግሥት ለዋናው አምራች ገበሬ ከፍተኛውን ትኩረት መስጠት አለበት::
እንደሚታወቀው ገበሬው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው የግብርና መሠረት ነው:: ስለዚህ ሁኔታዎች ተመቻችተውለት ቶሎ ወደ እርሻው መመለስ አለበት::
ይህ እስከሚሆን ግን የገበሬውን ሥልጣኔ፣ የችግር ጊዜ ብልሃት እንኮርጅ:: ገበሬው በሰፊው ይረስ፣ የከተማ ነዋሪው ደግሞ ያለችውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም በትንሹም ቢሆን ራሱን ይቻል:: እንደዚያ ከሆነ ችግርን በጋራ መጋፈጥ ይቻላል ማለት ነው:: ገበሬው ለልመና ከተዳረገ፣ የከተማው ነዋሪ በገበሬው ላይ ጥገኛ ሆኖ ከቀረ፤ ተያይዞ መውደቅ ይሆናል ማለት ነው::
ቀደም ሲል እንዳልነው ችግር ነው ብልሃትን የሚያስተምረው:: ለምሳሌ ቤታችን ሰፊ ሲሆን እና ጠባብ ሲሆን የቤት ውስጥ ዕቃ አቀማመጣችን ይለያያል:: ቤታችን ሰፊ ከሆነ፤ እያንዳንዱ ዕቃ ራሱን ችሎ ይቀመጣል:: ጠባብ ሲሆን ግን አንዱን በአንዱ ላይ እያነባበርን እናስቀምጣለን:: በሥርዓት በሥርዓት እንደረድራቸዋለን:: ለዕቃዎቹ አቀማመጥም ምቹ ይሆናል ማለት ነው:: በሰፊ ቤት ውስጥ ግን በቂ ቦታ ስላለ በሥርዓት ከመደርደር ይልቅ ያገኘንበት እንጥለዋለን::
የእርሻ ቦታዎችም ልክ እንደዚሁ ነው:: ሰፊ የእርሻ ማሳ በነበረበት ጊዜ የአረምና ድንጋይ መጣያ ይበዛል:: የእርሻ ማሳው ጠባብ ሲሆን ግን እርከን ይሠራሉ፤ ድንጋዩ በሥርዓት ይደረደራል፤ አረምና ሌሎች ነገሮችም በሥርዓት ተለቅመው አንድ ቦታ ብቻ ይቀመጣሉ::
ክረምት በመጣ ቁጥር ግብርና ነክ ጉዳዮች አጀንዳ ይሆናሉ:: በዚያው ልክ ግን የከተማ ግብርናም አጀንዳ መሆን አለበት:: ከተሜው የገበሬውን ብልጠት መጠቀም አለበት:: የእግር መረገጫ የምታክል መሬትን ጥቅም ላይ ማዋል መለመድ አለበት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም