በቆዳ ኢንዱስትሪ አራት አስርት ዓመታትን የተሻገሩ ባለራዕይ

የኢትዮጵያ የቆዳ ምርት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል:: ሀገሪቱ ከአመታት በፊት ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ጥሬ ቆዳ ነበር:: በዚህም ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ከቡና ቀጥሎ ጥሬ ቆዳ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ይጠቀሳል:: ሀገሪቱ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ ጥሬ ቆዳ ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ማድረጓም ይታወሳል:: ይህን ተክትሎም የቆዳ ፋብሪካዎች ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ በሆኑ የተለያዩ ችግሮች የተነሳ የቆዳ ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ ይታይበታል:: እንዲያም ሆኖ ጥቂት የማይባሉ የዘርፉ ተዋናዮች በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ሥራ ተሰማርተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ::

ከእነዚህም የቆዳ ኢንዱስትሪዎች መካከል ዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪ አንዱ ነው:: አብዛኛውን የዕድሜ ዘመናቸውን በቆዳው ዘርፍ እንዳሳለፉ የሚናገሩት የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ ይግዛው አሰፋ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ ከሚገኙ 28 የቆዳ ፋብሪካዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪን ጨምሮ አስር የሚደርሱ ፋብሪካዎች ብቻ በሥራ ላይ ይገኛሉ:: ዴቪምፔክስ ባህርዳር ቆዳ ፋብሪካ ቆዳን በጥሬው ከማምረት ባለፈ የቆዳ ውጤቶችንም ያመርታል::

ጎንደር ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ይግዛው፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎንደር ከተማ የተከታተሉ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት አግኝተዋል:: የስራውን አለም ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቢሆንም፣ የተሻለ ሥራ ፍለጋ በሚል በ1971 ዓ.ም የቆዳ ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለው በዚያው መቅረታቸውን ይናገራሉ:: ሞጆ ቆዳ ፋብሪካን ጨምሮ በሶስት የመንግሥት ቆዳ ፋብሪካዎች ከተራ ሰራተኛነት አንስቶ እስከ ሥራ አስኪያጅነት ደረጃ በመስራት ከ40 ዓመታት በላይ በዘርፉ አገልግለዋል::

‹‹ዕድሜዬን በቆዳ ሥራ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት›› የሚሉት አቶ ይግዛው፤ የቆዳ ፋብሪካ አቋቁመው ያለቀለት ቆዳን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከመጀመራቸው አስቀድሞ በተለያዩ የመንግሥት ቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ መሥራት መቻላቸው ብዙ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ ቆዳ በአጠቃላይ ያለውን ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ውዳቂና ተረፈ ምርት ተብሎ የሚጣለው ቆዳ ሳይቀር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ጉልህ አበርክቶ እንዳለው በሚገባ ተረድተዋል:: ለዚህም ብለው ዛሬም ድረስ ዘርፉን በስስት እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ:: ለዘርፉ ካላቸው ስስትና ቁጭት የተነሳ ከመንግሥት ቤት በተሰናበቱ ማግስት ሌላ ሥራ ልሥራ ሳይሉ በግላቸው የቆዳ ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለዋል::

በወቅቱ በራስ አቅም በከፊል የለፋ ቆዳን ማዘጋጀት ቀላል ባይሆንም ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት፣ ቁጭትና ተነሳሽነት መሥራት ችለው ዛሬ ላይ ደርሰዋል:: ‹‹ዘርፉን በሚገባ መረዳት በመቻሌ በግሌ መሥራት አልከበደኝም›› የሚሉት አቶ ይግዛው፤ ሲጀምሩ በከፊል የለፋ ቆዳን በትንሽ ካፒታልና በአነስተኛ የማምረት አቅም በመጀመር ገበያ ውስጥ መግባት ችለዋል::

እንዲህ እንዲህ እያሉ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ያለቀለት ቆዳን ጨምሮ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት የሚያስችል አቅም በመገንባት ባለሁለት ፋብሪካዎች ለመሆን በቅተዋል:: የቆዳ ኢንዱስትሪውን ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው የተቀላቀሉት አቶ ይግዛው፤ ዕድሜያቸውን ሙሉ ያሳለፉበት የቆዳ ኢንዱስትሪ በእጅጉ እንደሚያሳሳቸው ይናገራሉ::

በዘርፉ ቆይታቸውም በርካታ ሀገራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፤ በተለያዩ የንግድ ትርዒቶች ላይ የመሳተፍ እድልም አጋጥሟቸዋል፤ ከዚህ ሁሉም ብዙ እንደተማሩ ይናገራሉ:: ኢትዮጵያ ገና በሚገባ ያልተጠቀመችበት ከፍተኛ መጠን ያለው የእንስሳት ሀብት እንዳላት ጠቅሰው፤ በስጋውም ሆነ በቆዳው ዘርፍ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች ይናገራሉ::

በቆዳው ዘርፍ ከዓለም ሀገሮች ጋር ስትወዳደር የኢትዮጵያ ቆዳ በተፈጥሮ የተለየ ጸጋ የተሰጠውና ልዩ ባህሪ ያለው መሆኑን መረዳታቸውን ይናገራሉ:: በተለይም ለፋሽን ኢንዱስትሪው ማለትም ለጓንት፣ ለጃኬት፣ ለጫማና ለልዩ ልዩ የቆዳ ውጤቶች የተመቸ ባህሪ እንዳለው ይገልጸሉ::

እሳቸው ኢንዱስትሪውን በተቀላቀሉበት ዘመን የኢትዮጵያ የቆዳው ኢንዱስትሪ በቴክኖሎጂ እንዳላደገ አስታውሰው፣ በዚህ የተነሳም ቆዳ በጥሬው ሲላክ እንደነበር ገልጸዋል:: ከምርቱ ዋናውን ጥቅም የሚያገኙት የውጭ ገዢዎች እንደነበሩም አመልክተው፣ ኢትዮጵያ በሀብቷ ተጠቃሚ እንዳልነበረችና አሁንም በሚፈለገው ልክ ዘርፉ ውጤታማ አለመሆኑን አንስተዋል::

እሳቸው ከመንግሥት ቆዳ ፋብሪካ የለቀቁትና በግላቸው የቆዳ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉት በዚህ ተቆጭተው መሆኑን አመልክተዋል:: በአሁኑ ወቅትም ባህርዳር በሚገኙ ሁለት ፋብሪካዎች ያለቀለት ቆዳ እንዲሁም የቆዳ ውጤት የሆኑ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የእጅ ጓንቶችን እያመረቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውንና ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል::

ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤት የሆነውን የእጅ ጓንት በጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪ ሁለት ፋብሪካዎች የሚገኙት ባህርዳር ከተማ ነው:: ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያትም በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተፈላጊና ልዩ ባህሪ ያለው ቆዳ በስፋት የሚገኘው በደጋማው አካባቢ ነው ሲሉ አቶ ይግዛው አብራርተዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ሃይላንድ ሌዘር የሚባለውና ከፍተኛ ጥራት ያለው ቆዳ የሚገኘው ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ እና ወለጋ በመሆኑ ከእነዚህ አካባቢዎች ጥሬ ቆዳውን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል::

ለፋብሪካዎቹ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ጥሬ ቆዳ በባህርዳር ከተማ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ማግኘት እንደሚቻልም ገልጸዋል:: በእነዚሁ አካባቢዎች የሚገኙ ቆዳ ሰብሳቢዎች ከድርጅቱ ጋር ተሳስረው ጥሬ ቆዳውን እንደሚያቀርቡም አስረድተዋል:: ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የቆዳ ጓንቶችና ለቆዳ ጓንት መስሪያ ምቹ የሆነውን ያለቀለት ቆዳ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል::

ፋብሪካው የተቋቋመው ያለቀለት ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶችን ለማምረትና ለውጭ ገበያ ለመላክ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ይግዛው፤ ይህንኑ ህልማቸውን ዕውን ማድረግ እንደቻሉ ነው የገለጹት:: በተለይም የእጅ ጓንቶቹ እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዋነኛ የገበያ መዳረሻቸውም ስውዲን መሆኗን ተናግረዋል:: የባህርዳር ታነሪ የቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ ከጓንት በተጨማሪም የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለው ጠቅሰው፣ በቀጣይም ጃኬት፣ ቦርሳ፣ ቀበቶና መሰል የቆዳ ውጤቶችን ለማምረት ማቀዱን አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የጓንት ምርቶች በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ጥራትን ለሚጠይቀው ለጓንት ምርት ተስማሚ የሆነ ቆዳ በማምረት እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ ጓንት በማምረት የሚታወቅ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን ማሳደግ ችሏል:: በመሆኑም ዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪ በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያ ሥራዎችን አጠናቅቋል:: በሚያመርታቸው ጥራት ያላቸው ቆዳዎችም ትላልቅ የሚባሉ የውጭ ገበያዎችን መቀላቀል ችሏል::

በተለይም ከፍተኛ የሆነ የጥራት ደረጃን የሚጠይቁ እንደ ጃፓን ያሉ ገበያዎችን መቀላቀል የቻለ ሲሆን፣ ጃፓን ለሚገኘው ጎልፍ ክለብ ያለቀለትን እና ጓንት ለማምረት ዝግጁ የሆነውን ቆዳ እያቀረበ ይገኛል:: ታይላንድና ጣሊያንም ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎቹ ናቸው::

ከጥሬ ቆዳ ጀምሮ እሴት የተጨመረባቸውን ጓንቶች እያመረተ ያለው ዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪ በቀን ከ600 እስከ 700 ጥንድ ጓንቶችን የማምረት አቅም አለው:: እነዚህን ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚደርሱ ምርቶች ለውጭ ገበያ ይቀርባል:: ይህም ሲባል፤ 80 በመቶ ጓንት ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ ሲሆን፤ 20 በመቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል::

ካለቀለት ቆዳም እንዲሁ 70 በመቶ ያህሉን ወደ ውጭ ገበያ ሲልክ 30 በመቶውን ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል:: ፋብሪካው ጃኬትና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን ለማምረት የሚያስችል ሙሉ አቅም ያለው እንደሆነና በቅርቡም ወደ ምርት እንደሚገባ አቶ ይግዛው አጫውተውናል::

ፋብሪካው ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን ማምረት በሚጀምርበት ወቅትም ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ ይግዛው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ለ250 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አመልከተዋል:: ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል እና ረዘም ያለ የእሴት ሰንሰለት ያለው መሆኑን አብራርተው፣ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደለውም አስታውቀዋል:: ከዘርፉ በአግባቡ ተጠቃሚ መሆን እንዲቻል መንግሥትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሙሉ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም አምልክተዋል::

አቶ ይግዛው ከሥራ ዕድል ፈጠራ በተጨማሪም ማህበራዊ ኃላፊነትን እየተወጡም ይገኛሉ:: ፋብሪካው በሚገኝበት አካባቢ የተለያዩ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ መሰረተ ልማቶችን ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ ህጻናትን እንደሚያሳድጉና እንደሚያስተምሩም ገልጸዋል:: መንግሥት ለሚያደርገው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ::

ድርጅታቸው በጥራት በሚያመርታቸውንና ወደ ውጭ ገበያ በሚልካቸው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርቶች ምክንያት ያለፈው ዓመትን ጨምሮ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተከታታይ ጊዜ ተሸላሚ እንደነበሩም አቶ ይግዛው አጫውተውናል::

በአሁኑ ወቅት ከጥሬ ቆዳ አንስቶ እስካለቀለት የቆዳ ውጤቶች እያመረተ ያለው ዴቪምፔክስ ባህርዳር ታነሪ፣ ለእዚህ ደረጃ የደረሰው ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውለት እንዳልሆነም ገልጸዋል:: በዘርፉ በተለይ የጥሬ ቆዳ እጥረትና የግብዓት አቅርቦት ችግር ዘርፉን እየጎዳው እንደሆነ ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ከጥሬ ቆዳ ጋር ተያይዞ ከእንስሳት አረባብ ጀምሮ እንዲሁም በእርድ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችና ቆዳ ሰብሳቢው በሚፈጥረው ችግር ቆዳ ፋብሪካ እየደረሰ ያለው ቆዳ ጥራቱን የጠበቀ አይደለም:: በእነዚህና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በርካታ ፋብሪካዎች እስከመዘጋት የደረሱበት ሁኔታም ይታያል::

ቆዳ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ የዘርፉ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉም ጠቁመዋል:: የተጎዳ ቆዳ በኬሚካል ታክሞ መዳን አይችልም ያሉት አቶ ይግዛው፣ ይህ ችግር የቆዳን የጥራት ደረጃ በማውረድ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንዳደረገውም ጠቁመዋል:: ‹‹ችግሩን ለመፍታት በቆዳ ሥራ ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያኖች በሙሉ በጥንቃቄ ተናበው ሊሰሩ ይገባል›› ያሉት አቶ ይግዛው፤ ማህበረሰቡም አጠቃላይ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባም ያስገነዘቡት:: በተለይም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል::

ባለፉት ጊዜያት መንግሥት የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የኤክስቴንሽን ሥራ ይሠራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ይግዛው፤ ገጠር ቀበሌዎች ድረስ በመውረድ እንስሳው በሕይወት እያለ፣ በእርድ ወቅትና ከታረደ በኋላ ለቆዳው ሊደረግ በሚገባው ጥንቃቄ ላይ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበት እንደነበር አስታውሰዋል::

አሁንም ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፣ ፋብሪካዎች በግብአትነት በዋናነት ከሚጠቀሙት ቆዳ በተጨማሪ ጨው፣ ኖራ አሁን አሁን ደግሞ መጠነኛ የሆነ ኬሚካል በሀገር ውስጥ እያገኘ እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል:: ከዘርፉ ግብአት 60 በመቶ ያህሉ ከውጭ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እንዲሁ ሌላው የዘርፉ ችግር መሆኑን አመልክተዋል::

በዚህ የተነሳም አሁን ላይ ቆዳ ፋብሪካዎች ከማምረት አቅማቸው በታች እያመረቱ እንደሆነ ገልጸው፣ ያሉትን ችግሮች በመጋፈጥ በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊና ልዩ የሆነውን የኢትዮጵያ ቆዳ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

በተለይም ከጥሬ ቆዳ ይልቅ ያለቀለት ቆዳ በመላክ እንዲሁም እሴት በመጨመር የቆዳ ውጤቶችን ወደ ውጭ ገበያ መላክ እጅግ አዋጭ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ይግዛው፣ እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቁት::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You