ከፈተና የተዘገነ ህይወት…

የልጅነት ትዝታዎች…

ነፍስ ከማወቁ በፊት እናት አባቱ በፍቺ ተለያዩ:: ትንሹ ልጅ የወላጆቹን ፍቅር በእኩል ሊያገኝ አልታደለም:: እናት አባቱን በወጉ ሳያውቅ እንደዋዛ ከዓይኑ ራቁት::እንዲያም ሆኖ መልካም አሳዳጊ አላጣም:: ከደብሪቱ ዘገየ እጆች አረፈ:: ጠንካራዋ ደብሪቱ አክስቱ ናቸው:: የእናቱ እህት:: እሱን እንደልጅ ተቀብለው በፍቅር ፣ አቀፉት:: እናት ሊሆኑት ፣ልጅ ሊሆናቸው ፈቅደው ወሰዱት::

ቢኒያም ሰለሞን የልጅነቱ ሀ..ሁ በአክስቱ ቤት ተጀመረ:: ውሎ ሲያድር ከወላጆቹ የመነጠሉን እውነት አላጣውም:: አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉት ሴት እናቱ መሆናቸው ተነገረው:: ይህኔ የሚያሳድጉት ወይዘሮ አክስቱ እንደሆኑ አሳምሮ ገባው::

አንዳንዴ ታዲያ በወጉ የማያውቃቸው ወላጆቹ ይናፍቁታል:: የእናት ፍቅር፣ የአባት ክብር ውል እያለው ይቸገራል:: አክስቱን ደግሞ ከልብ ይወዳቸዋል:: እሳቸውም እንደዚያው:: እነዚህ ስሜቶች ለህጻኑ ቢኒያም ከፈተና በላይ ናቸው::

በወቅቱ አሳዳጊ እናቱ ልጅ አልነበራቸውም:: እሱ ለቤቱ የመጀመሪያ ሆኖ የማደግ ዕድል አግኝቷል:: ቆይቶ ግን አክስት በልጆች በረከት ተጎበኙ:: እንዲያም ሆኖ ከቢኒያም የታላቅነት መንበሩን የነጠቀ የለም:: አሁን እህት ወንድም የሚሆኑ ታናናሾችን አግኝቷል:: ቢሆንም ግን…?

የእሱና የቤተሰቦቹ ኑሮ አርሲ ከሚገኘው ‹‹አዲሌ›› እርሻ ልማት ግቢ ነው:: አክስቱ የድርጅቱ ተቀጣሪ ናቸውና ህይወታቸው ከግቢው ተቆራኝቷል:: የቢኒያም አስተዳደግ እንደ እኩዮቹ ነበር:: ማንኛውም ልጅ እንደሚያደርገው ጨዋታና ዝላይ አልቀረበትም::

አባትን በአካል …

አስረኛ ክፍል ሲደርስ ወላጅ አባቱን የማግኘት አጋጣሚ ተፈጠረ:: በአካል አግኝቶ አወጋቸው:: እንደልጅ ዳሰሱት፣ እንደአባት አቀፋቸው:: የማንነት ጥያቄው መልስ ሲያገኝ ተሰማው:: ሁለቱም እንደ አባትናልጅ ሊሆኑ ያገዳቸው የለም:: ባያሳድጉትም ልጅ የመሆን ስሜቱን አላጣም::

መሰናዶ ላይ ሲደርስ ወደ አሰላ መጓዝ ነበረበት:: በዚህ ከተማ የትምህርት ቆይታው እንዳበቃ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባው ውጤት ከእጁ ደረሰ:: ጅማ ዩኒቨርሲቲን እንደተቀላቀለ የትምህርት መስኩ ሶሾሎጂ ሆነ::

ዘለቄታው ስኬታማ ነበር:: የዓመታት ልፋቱ ዋጋ አላጣም:: ከዓላማው ጥግ ተጉዞ ያለአንዳች ስብራት ደረሰ:: ምርቃቱ ሚሊኒየሙ ላይ አርፏል:: ይህ ጊዜ ለእሱ አይረሴና ታሪካዊ ነው:: ከምርቃቱ በኋላ የመጀመሪያው የስራ ዕድል ሐረር ሂርና አካባቢ አደረሰው:: በአዲስ አዕምሮ በትኩስ ጉልበት ስራውን ሊጀምር ተዘጋጀ::

ቢኒያም አሁን ተማሪ አይደለም:: የመንግሥት ሰራተኛ የወር ደሞዝተኛ ሆኗል:: እንዲህ መሆኑ ብቻ ደስታ አልሰጠውም:: ቦታው ከከተማ መራቁ፣ ለአካባቢው እንግዳ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች ምቾቱን ይጋፉት ይዘዋል:: ውሎ አድሮ ከራሱ መከረ:: የአንድ አመት ቆይታው በቂ ነበር:: ሥራውን ሊለቅ ሲውስን አላወላወለም::

ቢኒያም ሂርናን ርቆ አባቱ ዘንድ ጥቂት ጊዜያት አሳለፈ:: ያለስራ መቀመጥን አልመረጠም:: ሰሜን ሸዋ ‹‹ሙሎ›› ከምትባል ወረዳ ተቀጥሮ ለስድስት ወራት ቆየ:: ይህ አጋጣሚ በሙያው ሌሎች ስራ ለማማረጥ ዕድል ሰጠው:: የነበረበትን ለቆ ከአንድ የውጭ ድርጅት ለመቀጠር አልዘገየም::

አዲሱ ሥራ…

ወጣቱ ተቀጣሪ ሱሉልታ ከተማ የጀመረው ስራ መልካም ሆኗል:: የስራ ባልደረቦቹ፣ ያለበት ሙያና የሚያሳልፈው ውሎ ተመችቶታል:: አሁን ከመሀል ከተማ ብዙ አልራቀም:: በየቀኑ ከስራው አዲስአበባ ይመላለሳል:: የሱሉልታ መንገድ ሁሌም እረፍት አልባ ነው:: መውጫ መግቢያ በመሆኑ በየቀኑ በርካታ መኪኖች ይገባሉ፣ ይወጣሉ::

አንዳንዴ በመንገዱ አሽከርካሪዎችና፣ እግረኞች በእኩል ይጋፋሉ:: ብዙ ጊዜ መሪ የሚጨብጡ ሾፌሮች ስሜታቸው ይለያያል:: ወደከተማ የሚገቡት ቤት ለመድረስ ይከንፋሉ፣ ከከተማ የሚወጡት ለመንገዳቸው ይፈጥናሉ:: ሱሉልታና ዙሪያ ገባው በየቀኑ ለዚህ እውነት ብርቅ አይደሉም::

ቢኒያም አሁን ሸጋ ወጣት ሆኗል:: ጥሩ ደሞዝ መልካም ህይወት አለው:: ትናንት የተራመደውን ክፉ መንገድ እያሰበ አይደለም:: ልጅነቱ በውጣውረድ ቢያልፍም ወጣትነቱ ክሶታል:: ስለ ዛሬን በትጋት ቀጥሏል:: አንድ ወጣት በእድሜው የሚያስበው ጥሩ ምኞት ሁሉ ከእሱ ዘንድ አለ:: ሁሌም ያለድካም ይሰራል፣ ለእሱ የቆመበት ቀን በየዕለቱ የአዲስ ነገር ምዕራፍ ነው::

ከቀናት በአንዱ…

ሰኔ ግም እያለ ነው:: ክረምቱ ማንዣበብ ዝናቡ ማስፈራራት ይዟል:: እረፍት አልባው የሱሉልታ መንገድ ዛሬም ጭር አላለም:: መንገደኞችን ሲሸኝና ሲቀበል አርፍዷል:: ለቢኒያም ይህ ጎዳና የየእለት ግዴታው ነው:: ማለዳ ወጥቶ ማምሻውን ይመለስበታል::

ቢኒያም እንደወትሮው ከስራው የደረሰው ማልዶ ነበር:: በዕለቱ የሚጠብቀውን ግዴታ ከውኖ በሰአቱ ሊሄድ ተዘጋጅቷል:: ሁሌም ከቤቱ ሱሉልታ፣ መልሶም አዲስአበባ የሚያደርሰው የግል ትራንስፖርት ነው:: የዛን ቀንም ከአንድ ሚኒባስ ገብቶ ለመንገዱ ተዘጋጅቷል:: ወንበሮቹ በተሳፋሪዎች እንደሞሉ አፍንጫውን ወደ አዲስአበባ መውጫ ያደረገው ታክሲ ሾፌር ቁልፉን ተጭኖ ሞተሩን አስነሳ:: ጉዞው ተጀመረ፣ ወደ አዱገነት አዲስአበባ::

ቢኒያም ዛሬን ተሻግሮ ነገ ስለሚሰራው እያቀደ ነው:: ሌሎች መንገደኞች በራስ ሀሳብ ተይዘዋል:: ዳመናው እየከበደ ፤ክረምቱ እያስፈራራ ነው::ጥቂት ቆይቶ ሊዘንብ ፣ሊጎርፍ ይችላል::ሚኒባሱ መንገዱን ይዞ ቀጥሏል::ከባድ መኪኖች ከፊት ከኋላው እያለፉት ነው::

ከደቂቃዎች በኋላ…

ከግራ ከቀኝ ሽው የሚሉት መኪኖች መንገዳቸውን ቀጥለዋል::ከነዚህ መሀል ግዙፍ የሚባሉት ሊጠጓቸው ያስፈራሉ:: አብዛኞቹ ተሳቢያቸው የሚጎተት፣ ጭነታቸው የሚከብድ ነው:: ከከባዶቹ፣ ከግዙፎቹ መኪኖች አንዱ በድንገት ወደ ሚኒባሱ ተምዘገዘገ:: አመጣጡ የሰላም አይደለም::መንገዱን በተቃራኒው ስቶ እየከነፈ ተጠጋ::

የታክሲ ሾፌሩ ጥረት አልተሳካም:: መሸሽ፣ ማምለጥ አልቻለም:: ተሳቢው ደርሶ በሙሉ ኃይል ተላተመው:: የሚኒባስ ውስጥ ነፍሶች ለአፍታ ያህል ዝም ያሉ ይመስላል:: ጥቂት ቆይቶ በከባድ ጨኸት የታጀበ የለቅሶና ጣር ድምጽ ዝምታውን ጥሶ ተ ሰማ::

እነሆ! የነበረው እንዳልነበር ሆኗል:: አሁን ኃይለኛው የግጭት ድምጽ አላፊ አግዳሚውን ስቦ በዙሪያው እያሰባሰበ ነው::የሞቱ፣ክፉኛ የቆሰሉ፣በሞትና ህይወት መሀል ያሉ ከወደቀው ታክሲው ጉያ ተንጋለው ይታያሉ:: እያንዳንዱን እውነት ማየት ልብ ይሰብራል፣ ያስደነግጣል::

ቢኒያም ሩቅ አሳቢው፣ብዙ አላሚው ወጣት:: ሙሉ አካሉ ደም ተለውሶ ራሱን ስቶ ወድቋል:: ሊረዱት የተጠጉት ሰዎች ትንፋሽ እንዳለው አውቀዋል::በቻሉት ፍጥነት ነፍሱን ለማትረፍ እየጣሩ ነው::ከአዲስ አበባ እየመጣ ነው የተባለ አምቡላንስ በታሰበው ጊዜ ፈጥኖ አልደረሰም::አሁን ሌላ መኪና ደርሶ ተ ጎጂዎች መነሳት ጀምረዋል::

ቢኒያምን ከወደቀበት አንስተው ወደመኪናው ሲያስገቡት ድንገቴ ጩኸት አሰማ::ወዲያው ደግሞ ራሱን ስቶ በዝምታ ተዋጠ::እሱ በሞትና ህይወት መሀል ነው::አሁን ቁስለኞችን የያዘው መኪና መዳረሻው ከአንድ ሆስፒታል ሆኗል::የአደጋውን ዜና የሰሙ፣ የዘመዶቻቸውን ሞት የተረዱ፣ከስፍራው ናቸው:: ግቢው በለቅሶና ከባድ ድንጋጤ ተውጧል::

‹‹እግሬን ! እግሬን››

ከሆስፒታሉ የደረሰው ቢኒያም አሁን እንደ መንቃት ብሏል::ሰውነቱን እየዳሰሰ፣እየነካካ ስሜቱን ማወቅ እየጣረ ነው::እግሩን ለማዘዝ ሲሞክር ያገኘው እውነት ደግሞ አስደንግጦታል:: ‹‹እግሬን !እግሬን›› እያለ ይጮሀል:: ስቃዩ የበዛ፣ ህመሙ የከበደ ነው:: እስከ ምሽት አራት ሰአት የቆየው የመጀመሪያ እርዳታ ከአቅም በላይ ሆኖ ወደሌላ ሆስፒታል ሊተላለፍ ግድ ብሏል::

ከሌላው ሆስፒታል..

ቢኒያም ከሆስፒታሉ ሲደርስ በቂ የሚባሉ ሀኪሞች አልነበሩም::አሁን ለሙያው አዲስ በሆኑና ተለማማጅ በሚባሉ ተማሪዎች እጅ ነው::ከእነዚህ መሀል አንደኛው የተጎዳውን እግር በፋሻ ደጋግሞ ይጠቀልላል::አሁን ጠብቆ የታሰረው እግር የደም ዝውውሩን እያቆመ ነው::ቢኒያም በመንቃትና መነሳት መሀል ሆኖ ዝብርቅርቅ ስሜት ከቦታል፣እግሩ ደንዝዟል፣አካሉ ዝሏል::

ማለዳ ቤተሰቦቹ ደርሰው መላ አካሉን ዳሰሱት:: አንድ እግሩ ስሜት አልባ ሆኖ ቀዝቅዟል:: ሁሉም በድንጋጤ ክው ብለው ለሀኪሞች አሳወቁ:: እውነትም እግሩ ቀዝቅዞ ደንዝዟል:: በወቅቱ ጠብቆ መታሰር፣ አብዝቶ መጠቅለል አልነበረበትም:: እንዲያም ሆኖ ማንም ኃላፊነቱን ሊወስድ አልደፈረም::ዕለቱን አፋጣኝ እርምጃ ሳይኖር ያለውሳኔ ሰዓታት ባከኑ::

ቢኒያም ከቆይታ በኋላ ከአንድ የአጥንት ህክምና ሆስፒታል ደረሰ::በስፍራው ያሉ ሀኪሞች ልክ እንዳዩት ደነገጡ:: የተጎዳው እግር ታስሮ ማደሩ ስህተት ነበር:: ተስፋ አልቆረጡም::ፈጥነው ቀጣዩን ህክምና ሊሞክሩት ተዘጋጁ:: ብዙ ደም የፈሰሰው ቢኒያም ለሳምንት ያህል ራሱን ስቶ ቆየ::

ፈጣኑ ውሳኔ …

ሀኪሞቹ የደከሙበት ህክምና ስኬታማ አልሆነም::የደም ዝውውር ያቆመው እግር ወደ ‹‹ጋንግሪን›› እንዳያመራ አስግቷል:: አሁን ፈጣኑ ውሳኔ ግድ የሚልበት ነው::ጥቂት ከቆየ ቢኒያም ለሞት ይደርሳል::ጠንካራው ወጣት ሀሳቡ ከሀኪሞች አልራቀም:: የእግሩን ጉዳት ካየ ወዲህ ራሱን አዘጋጅቷል:: በእግሩ መቆረጥ አምኖ በይሁንታ ወስኗል::

እነሆ! የታሰበው ሁሉ በጊዜው ተፈጸመ::አሁን ቢኒያም አንድ እግሩ ተወግዷል::ይህን እውነት እንደዋዛ ማመን ከባድ ነው:: በእሱ ዘንድ የነበረው ስሜት ግን ተቃራኒው ነበር:: እሱ አሁን ዛሬ ከሆነው ይልቅ ስለ ወደፊቱ ያስባል::ህይወት ከአካል ጉዳት ጋር አዲስ ነው::ለዚህ ደግሞ መፍትሄው በእጁ ነው::የቀሰመው ትምህርት፣ያለፈበት የስራ መንገድ ፣የተገበረው የሙያ ልምድ ለአሁኑ እውነታ አግዞታል::

ቢኒያም ከዚህ ቀድሞ በበጎ ተግባራት አልፏል:: በሙያው ብዙ አካል ጉዳተኞችን ደርሷል፤ የሚያሳቅቁ፣ የሚያበረቱ ታሪኮች ብርቁ አይደሉም::የእነሱ ስነልቦና ከእሱ ባዕድ አልነበረም:: ሁሌም ጥንካሬቸው ብርታቱ ነው:: እንዲህ መሆኑ ማንም ለአካል ጉዳት ሩቅ እንዳልሆነ አስገንዝቦታል:: ይህ እውነት የማንነቱ ጽናት ሆኖ በራሱ ሲቀልድ፣ ሲዝናና ይውላል::አሁን አካሉ እንጂ ውስጡ አልተጎዳም:: ‹‹እችላለሁ›› ይሉት ሀቅ ከደሙ ገብቶ ትርጉሙን ዘርቷል::

ህይወት በሌላ መልክ …

ቢኒያም ከጉዳቱ ማግስት ቤት ማዘወተር ይዟል::የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ብዙ አልከበዱትም::ራሱን ለእርምጃ ሲያለማምድ፣ ቁስሉን ሲያስታምም ቆይቷል:: ዋል አደር ሲል ግን ዛሬ እንደትናንት አልሆነም:: ከድብርት የገባበት፣ በዝምታ የተዋጠበት ፣ በትካዜ አንገት የደፋበት ጊዜ ተመላለሰ::

የስራ ባልደረቦቹ መልካም የሚባሉ ናቸው::ከጎኑ ሳይርቁ አስታመውታል:: ብዙ የፈጀውን የህክምና ወጪ ተጋርተውታል፣ እክስቱ፣እናት አባቱ በክፉ ቀናት አልራቁትም:: አከራዮቹ አልገፉትም::ደም ለግሰው ህይወት የሰጡትም አይረሱም:: ቢኒያም ስራው ላይ እንዲቀጥል ማገር ናቸው:: ሁለተኛ ዲግሪውን እንዲማርም ብርታት ሆነዋል::

አዲሱ አካል ጉዳተኛ በሌሎች የሚያውቃቸው ችግሮች ሲፈትኑት ቆይተዋል:: መንገዱ፣ትራንስፖርቱ፣ መውደቅ መነሳቱ አልቀረለትም:: በመንገዱ ብዙ ይገጥመዋል:: ሁኔታውን አይተው ከንፈር የሚመጡለት፣በሀዘኔታ ሳንቲም የሚጥሉለት አይጠፉም::ይህ ሁሉ በጥንካሬ አቆመው እንጂ አልጣለውም:: ሁሌም በጎ ላደረጉለት ምስጋናው ከልብ ነው::

ቢኒያም በማህበራዊ ዘርፍ የቀጠለው ትምህርት ስኬታማ ሲያደርገው አልዘገየም::በግሉ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ንግዱን ሞክሯል:: በተለያዩ የውጭና የሀገር ውስጥ ተቋማት በስራ አስኪያጅነት ሰርቷል:: አሁን ላይ በሚሰራበት ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላላቅ ስብሰባዎችን ይመራል፣ ሰፊ ስልጠናዎችን ይሰጣል:: በአማካሪነት ሙያ በእጅጉ ጎልብቷል:: ከአካል ጉዳት ጋር ላሉ ወገኖችም ያለስስት ልምዱን ያካፍላል::

ከባልንጀሮቹ ጋር የጀመራቸው ሰፋፊ ስራዎች ለሀገርና ወገን የሚጠቅሙ ናቸው::ብዙኃንን አሳትፈው ችግሮችን ይፈታሉ:: በበጎ አድራጎት ተቋማት ያሳረፈው አሻራ ዕንባ የሚያብሱ ፣መፍትሄ የሚያመነጩ ሆነዋል::ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በእርዳታ ሳይሆን በሌሎች አማራጮች ለመፍታት ያደረጋቸው ሙከራዎች በተወሰነ ፍጥነት አራምደውታል::

ለአፍታ እረፍት ይሉትን አያውቀው ወጣቱ ከአካል ጉዳቱ ተስማምቶ፣ለሌሎች አጋርነቱን ሲያሳይ ከልቡ ነው:: ቢኒያም መለስ ብሎ ትናንትን ያስታውሳል:: እሱና አደጋው የተገናኙበት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ ሁለት ዓመት በኋላ ነው::መስራት በሚችልበት አፍላ ዕድሜው ያጋጠመው ችግር ግን አሰናክሎት አልቀረም:: ክፉ ደግ ቀናት ከቀናው መንገድ አድርሰው ከስኬት ጫፍ አቁመውታል::

ትዳርና ጎጆ…

ቢኒያም እጮኛው ከነበረችው ወጣት ጋር የተለየው አካል ጉዳት ካጋጠመው ወዲህ ነበር::በወቅቱ ሁኔታው ሆድ ቢያስብሰውም ፈጣሪ ሊክሰው አልዘገየም:: በድንገት ከተግባባት ጓደኛው ጋር በአጭር ጊዜ የመሰረተው ትዳር ደስተኛ አድርጎታል፡ ፡ባለቤቱ ለእሱ መልካም አጋር ፣ ቅን አሳቢ እህትና ሚስት ናት:: ዛሬ ላይ የሁለት ቆንጆ ሴት ልጆች አባት ነው::በጥሩ ቤት እየኖረ ዘመናዊ የሚባል መኪና ያሽከረክራል::

ቢኒያም በህይወቱ ያለፈባቸው መንገዶች ሜዳማ ብቻ አልነበሩም:: ሻካራማዎቹን፣ ገደላማዎቹን መስመሮች ተራምዶባቸዋል::ሁሉም ግን ለዛሬ ማንነቱ መልካም ሆነዋል::ከአስተዳደጉ በጎና ክፉ ትዝታዎች ፣ከወጣትነቱ ደግሞ ህመምና ደስታዎችን ዘግኗል::

እሱ ከህይወቱ ክፉ አጋጣሚዎች በህክምና ስህተት የደረሰበትን እውነት ፈጽሞ አይዘነጋም:: በግዴለሽነት የሚፈጠረው ማንኛውም የህክምና ስህተት፣የስራ ላይ ጥንቃቄ ጉድለትና ሌሎችም ክፍተቶች ቢደፈኑ ይወዳል::ከጊዜ በኋላ ከሚኖር የአካል ጉዳት ህክምናው በዘለለ የስነልቦና ድጋፍና የአማካሪ ባለሙያዎች ድጋፍ በህይወት ለተረፈው ሰው ታላቅ ተስፋ ይሆናል ሲል ያምናል::

ቢኒያም ክንደ ብርቱ መንፈሰ ጠንካራ ወጣት ነው:: ዛሬ ላይ ከአካል ጉዳቱ በፊት ያደርጋቸውን የነበሩ ተግባራት ‹‹ይቅርብኝ›› ሲል ራሱን አያገልም:: ሁሉንም እንደቻለው ያደርጋል፤ ይሞክራል:: ከአጋጣሚው ብዙ ተምሯል::ስለነገ ያለው ህልም ብዙ ነው:: የጀመራቸውን የቴክኖሎጂ ውጥኖች ከሌሎች ሙያዎች አቀናጅቶ የማስፋት ዕቅዱ ሰፊ ነው:: ዛሬም ይሮጣል፣ይተጋል:: መልከ ቀናው፣ አንደበተ መልካሙ፣የእውቀት ቀንዱ ቢኒያም ሰለሞን::

መልካምሥራ አፈወርቅ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You