የሰሞኑ እንመካከርና አንድምታው

ከሰውም ሰው እንዳለው ሁሉ፣ ከቃልም ቃል፤ ከቃላትም ቃላት አሉ። ከእንጨት ተመርጦ ለታቦት እንደሚሆነው ሁሉ፤ ከሰውም ተመርጦ ለሹመት የመታጨቱ ጉዳይ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነው – ካስፈለገም “ሳይንሳዊ ሀቅ ነው” ማለትም ይቻላል።

ቃላት ሁሉ እኩል አይደሉምና፣ ቃልም ሆነ ቃላት በይዘትና ቅርፅ ይለያያሉና “እንምከር”ም ሆነ “እንመካከር” የራሱ የሆነ መለያ አለው። በተለይ ከአዎንታዊነቱ፣ ገንቢነቱ፣ ተግባቦታዊ ባህሪያቱ፣ አካታችና አቃፊነቱ፣ አሳታፊነቱ ወዘተ አኳያ ካየነው መመካከር ምንም አይነት እንከን ሊወጣለት የሚችል ቃል ወይም ጽንሰ ሃሳብ አይደለም።

ከ“እንገማገም” በእጅጉ የሚለየው “እንመካከር” የ“እንተጋገዝ” ፤ የ“እንረዳዳ”፤ የ“እንግባባ”፣ የ“አብሮነት” ወዘተ ማሳለጫ እንጂ ለ“ሆድና ጀርባነት” ምንም አይነት እድል አይሰጥም፤ ልዩነት ያላቸው ወገኖች ካሉም ልዩነቶቻቸውን ይዘው እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ አቅም በእንመካከር ውስጥ የለም። በመሆኑም በእንመካከር የፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊውም ሆነ ሌላው ሁሉ እዳው ገብስ ነው ማለት ነው።

ሰብአዊነት የሚንፀባረቅበት መመካከር ከመከራከር ይለያል፤ መመካከር ከመጨቃጨቅ ይርቃል፤ መመካከር ቅርበቱ ለውይይት ሲሆን፤ ማጠቃለያው አንድነት ነው። በመሆኑም በማንም ለማንም የሚመከር እንጂ በማንም የሚጠላ፤ ወደ የትም የሚገፋ አጀንዳ አይደለም፤ አይሆንምም። እንደውም “እስኪ በዚሁ እንኳን በቃ ቢለን” የሚያሰኝ እንጂ ከመመካከር ጋር ግብ ግብ ሊያስገጥም የሚችል ምንም አይነት መሠረታዊ የሆነ ምክንያት (በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ) የለም።

ማንም እንደሚያውቀው፣ “እንመካከር” በባህርይውም ሆነ አቀራረቡ የጋርዮሽ እንጂ የበላይነትና የበታችነት የለውም። በ“እንመካከር” የበታችም፣ የበላይም የለም። በ“እንመካከር” ያለው አቻዊነት ነው። እኩልነት ነው። ሃሳብ ያለው ሃሳቡን ያካፍላል፤ መረጃ ያለው መረጃውን “እነሆ” ይላል፤ ሀገራዊ ጉዳዮች ይቀድማሉና በ“እንመካከር” አጀንዳው ሀገራዊ፣ ሕዝባዊ የመሆኑ ጉዳይ ከ“እንመካከር” ባህርይ የሚመነጭ ነውና ማንንም ሊገፋ፣ ማንንም ለይቶ ሊያቅፍ የሚችልበት እድልም ሆነ አጋጣሚ የለውም።

“ኑ፣ እንመካከር” በአራቱም አቅጣጫ ቢመረመር፣ በስድስቱም ማእዘን ቢፈተሽ ከ“መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ”፣ ወይም ከ“መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” ጋር ምንም አይነት ተዛምዶም ሆነ ትውውቅ የለውም፤ “እንመካከር” ሌላኛው የ“ደህና ሁን ጠመንጃ” መጠሪያ ሲሆን፤ ከሰላምና ደህንነት፣ ፀጥታና ስጋት አልባነት፤ መተማመንና ዜግነት ወዘተ ጋር ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን አሰባሳቢ ሃሳብ የሁሉም መሪ ተዋናይ ነው።

እንደዚህ ጸሐፊ እምነት፣ “እንመካከር” የጎበጠው እሚቀናበት፣ የተወጠረው እሚላላበት፣ የጨለመው እሚበራበት፣ የከፋው እሚደሰትበት፣ አብሮነት የሚፀናና የበለጠም የሚጠብቅበት መድረክ ነው።

እንደዚህ ጸሐፊ እምነት፣ “እንመካከር” በምክክር ኮሚሽን ተመራም አልተመራ በባህርይው ሰዋዊ ነውና ሰዎች የሚሸሹት ሳይሆን የሚቀርቡት፤ የሚያጣጥሉት ሳይሆን ከእነ “ፉክክር” እና “እኔ እበልጥ”፣ “እኔ እበልጥ” በተለየ መልኩ የሚያስተናግዱት፤ በጥቅሉ ሀገርና ሕዝብ ከፍ ከፍ የሚሉበት የተከበረ የውይይት መድረክ ነው።

ተማክሮ፣ ተመካክሮ የሚያውቅ ሁሉ እንደሚያውቀው፣ “እንመካከር” ከተመካካሪዎች፣ ከተፈቃቃሪዎች ጀምሮ የሆድ የሆዳቸውን የሚጫወቱበት፤ ስር ከሰደደና ከተዛባ አስተሳሰብ የሚላቀቁበት፤ ልዩነትን ትተው ወደ አንድነትና ፍቅር የሚመጡበት፤ ከአሉባልታና የሀሰት ትርክት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፋቱበት፤ የፍቅር ሁሉ፤ የሰላም ሁሉ፤ የአንድነት ሁሉ • • • ሁሉ • • • መሠረት፤ መደላድል ነው።

ማህበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን እንደሚያስተምሩን በመመካከር ፍቅር ይደረጃል፤ ትዳር ይቀናል፤ ይሰምራልም። በመመካከር ጓደኝነት ዳር ይደርሳል። በመመካከር የነበረው እንዳልነበረ፤ ያልነበረው እንደ ነበረ ይሆናል። በመመካከር የደበዘዘው ይፈካል፤ ያደፈው ይፀዳል። በመመካከር የከፋው ይደሰታል፤ የተሸፈነና የተሸፋፈነው ይገለጣል። በመመካከር እነ “እኔ” እና “እሱ”፣“እነሱ”፤“መጤ” እና “ነባር” ተብዬ ሳይፈለጉ የመጡ፣ ባእድና ከፋፋይ እሳቤዎች ጥግ ጥጋቸውን ይይዛሉ። በመመካከር እኛነት ይነግሳል። በመሆኑም፣ በመመካከር ማትረፍ እንጂ መክሰር ብሎ ነገር የለም።

የምክክር መድረኮች በባህርያቸው የምክረ-ሃሳቦች መሰናዘሪያ እንጂ፣ ትእዛዝ ማስተላለፊያ ቀጫጭን ሽቦዎች አይደሉም። መድረኮቹ የጋራ እንጂ የማንም አይደሉምና ማንም ሊዘውራቸው ፣ እንደ ፈለገው ሊያሽከረክራቸው ከመድረኩ ጀምሮ መድረከኞቹ ሁሉ አይፈቅዱለትምና የዚህ ሰው (ወይም ቡድን) ተገቢ ቦታ እዛ ሊሆን አይችልም።

ምክክሮች ችግሮች ከመሠረታቸው ይፈቱበታል፤ እውነት የበላይነትን ያገኝበታል፤ ሀሰት ይደፈቅበታል፤ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” ባይነት ልኩን ያይበታል ተብለው ይታሰባሉና ሀገራዊና ሕዝባዊ ፋይዳቸው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።

የምክክር ሳይንስም ሆነ ፍልስፍና አበክሮ እንደሚያስረዳው፣ በመመካከር “ሰራሁለት”፣“ሰራሁላት” አይሠራም። በመመካከር “ቆይ አገኝሻለሁ”፣ “ቆይ አገኝሀለሁ” ቦታ የላቸውም። በመመካከር ሁሉም እኩል አትራፊና ሁሉም እኩል አሸናፊ እንጂ ከሳሪም ሆነ ተሸናፊ የለም። ምክክሮችና መድረኮቻቸው ለጋራ አቋም እንጂ ለግል ወይም ለፓርቲ አቋም የመገዛት ባህርይ የላቸውም። እውነቱ ይኸው ነው።

ከእስከዛሬው የሰው ልጅ እድሜና ሂደቱ መረዳት እንደተቻለው፣ የመመካከርም ሆነ ምክክር መድረኮች የ“ወጋ ወጋ በፈገግታ” አይነት ሃሳቦችም ሆኑ አስተሳሰቦች ምንም አይነት ስፍራ የላቸውም። የምክክር መድረኮች የጦር አውድማዎች አይደሉምና ጩኸትን አይፈልጉም፤ ዝናር መታጠቅን፣ ርእዮተ-አለም ጉያ ውስጥ መወሸቅን አይሹም። ፖለቲካዊ ግሳንግሶች መድረካቸው እዛው ግሳንግሱ አካባቢ እንጂ የምክክር መድረኮች ለእነሱ ፍፁም ምቹ አይደሉም።

አበውና እመው ሲያስተምሩን እንደ ኖሩት፣ “ቧልት” እና “ምክክር” ፍፁም ተቃራኒዎች ናቸው። ተሰሚነትን ለመሻት መስገብገብ፣ ታዋቂነትን ፍለጋ መክለፍለፍ፣ ከፍ ብሎ ለመታየት መንጠራራት፣ አልኩ ለማለት ያህል መዘላበድ ወዘተ የምክክር መድረኮችን የሚመጥኑ አይደሉም እና መድረኩ ከእነዚህ ሁሉ ማህበራዊ ህፀፆች የፀዳ ይሆን ዘንድ የቅን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጥልቅ ምኞት መሆኑን ከወዲሁ በደማቁ ከስሩ ማስመር ያስፈልጋል።

ምክክር የቅን ልቦች መናኸሪያ ነው። ምክክር የቁም ነገሮች መንሸራሸሪያ መድረክ ነው። ምክክር የጨዋዎች ጨዋ መድረክና ተግባር ነው። በምክክር መድረክ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ዲያቢሎስ ስለመገኘቱ የተገኘ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለምና መድረኩ ሎሬቱ “እፍ አንቺ ኩራዝ ጥፊ /መድረክ ላይ ኩስ ከምትተፊ” እንዳለው እንደማይሆን፤ ወይም ከበደ ሚካኤል “ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም/ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” እንዳሉት፤ ካለመመካከር መመካከር እንደሚሻል፤ እንደሚበጅም፤ እንደሚገባም፤ ሌላ የተሻለ ምርጫ እንደሌለም ከወዲሁ መናገር ይቻላል ብቻ ሳይሆን እጅጉን ያስፈልጋልና መልካም የምክክር መድረክ እንላለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You