ውይይት የትኛውንም ችግር የሚፈታ ቁልፍ የተግባቦት አማራጭ ነው:: ከሀይልና ከሰጣ ገባ በበለጠ ለትውልዱ ሰላምን፣ ለሕዝቡ ደግሞ መረጋጋትን የሚሰጥ የበላጭና የአዋጪ ምክረ ሀሳብ መገኛ ነው:: በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በእርስ በርስ ግንኙነት በኩልም የነበረውን አጥርቶ ያለውን የሚያቀና ነገን አሻቅቦ በማየት ረገድም ሀገርን ከማጥ የሚያወጣ የመፍትሄ አቅጣጫም ነው:: የመጣንበት የፖለቲካና የእርስ በርስ ግፊያ ግን ይሄን በሁለንተናው የሰመረ የእርቅና የምክክር እውነታን እንድናይ እድል አልሰጠንም::
የመጣንበት የፉክክር ፖለቲካ እድፎቻችንን ሳናጠራ እንደቆሸሽን ወደነገ እንድንሄድ ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያዊነትን እየሰጠን አይደለም:: ተወያይተን የምንስማማባቸው ልዩነቶቻችን ወደመገፋፋት እየወሰዱን በጠላትነት እንድንተያይ ከማድረግ ባለፈ ያብሮነትን ሰርጥ እየቀደዱልን አይደለም:: በአንድ ታሪክ በቅለን፣ በአንድ ቀለም ደምቀን በአንድ ስም እየተጠራን ለብዙሀነት በማይበጅ አቅም በሌለው ከለላ ስር መሸሸጋችን ለምን? የሚል ጥያቄን ከማስነሳቱ ባለፈ ትዝብት ላይ የሚጥለን ነው::
ውቅያኖስ በወንዞች የሚጠራ ነው:: ውቅያኖስ ያማረውና የገዘፈው፣ የጠለቀውና ያስፈራው ከዚም ከዛም መንጭተው ባጠጡት ወንዞችና ምንጮች ነው:: ልክ ከዛም ከዚም መንጭተው ትልቁን ውቅያኖስ እንደሚያጠጡ ገባር ወንዞች ሀገርም እንዲሁ ናት:: እኔና እናንተ ከዚም ከዛም ተነስተን፣ በተለያየ ባህል፣ በተለያየ ስርዐት፣ በተለያያ ቋንቋና ወግ ኢትዮጵያን ያገዘፍን ገባሮቿ ነን:: ከዚህ ውስጥ አንዳችን ብንጎል ሀገራችን ትወይባለች:: አንዳችን መሄጃ አጥተን አቅጣጫ ብንስት፣ ከሙላታችን ብንጎድል ሀገር የሚሏት የጋራ ስማችን ትጠይማለች::
የሀገር ስንካሌ የታሪክ ሽርፈት፣ የሉአላዊነት መደፈር ነው:: ሀገራችን ጸንታ እንድትቆም እኛ ጸንተን መቆም አለብን:: የእኛ ጸንቶ መቆም ደግሞ ሰላምን መሰረት ባደረገ የእርቅና የተግባቦት መድረክ በኩል የሚገለጥ ነው:: ዛሬ ላይ ተነጋግረንና ተወያይተን ሰላም ማውረድ ያልቻልንባቸው ጉዳዮች ፋፍተውና በልጽገው ነገ ላይ ሌላ ቁርሾ እንደሚወልዱ የሚታወቅ ነው:: “ሳይቃጠል በቅጠል “ እንዲሉ ያለፈውን በይቅርታ የአሁኑን ደግሞ በእርቅ ፈትቶ ሰላማዊ ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሀገር ለመቀጠል አንዱና ብቸኛው አማራጫችን ሆኖ ከፊት የሚመጣ ነው::
በወቅቱ ያልተገቱ በትላንት ስም የሚጠሩ ፖለቲካዊና ዘር ተኮር እሳቤዎች ዛሬ ላይ በብርቱ ሸርፈውናል:: የሽርፈታችንን መጠን ለማወቅ የነበርንበትን የኢትጵያዊነት ሞገስ ካለንበት አሁናዊ የአብሮነት ሁኔታ ጋር ማስተያየት በቂ ነው:: ባልገቡን፣ ባልተረዳናቸው፣ በማን፣ ለምንና እንዴት እንደተረጩ በማናውቃቸው መርዞች፣ ማን፣ መቼና በምን ዓላማ እንደለኮሳቸው በማናውቃቸው እሳቶች ብዙ ቦታ ላይ ጠውልገናል::
ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ያለው የትላንት ሰደድ እሳት ነው:: ነገ ላይ አንካሳ ትውልድ ላለመፍጠር ዛሬ ላይ ስለፍቅር መሸነፍ አለብን:: ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለወንድማማችነት ስንል በይቅርታ መተቃቀፍ ግዴታችን ይሆናል:: ስለሀገር፣ ስለሕዝብ፣ ስለአብሮነት ስንል ውይይት መር ንቅናቄ ያስፈልገናል::
በእልህ፣ ባለመተማመን፣ በራስ ወዳድነት እኛው በእኛ ተሸርፈናል:: ባለመደማመጥ፣ ባለመነጋገር እኛው ለእኛ ቁርሾ አስቀምጠናል:: በኃይል፣ በትዕቢት፣ በይዋጣልን እኛው በእኛ ተዋርደናል:: በማንአለብኝነት፣ ባለመከባበር፣ በበቀል፣ በጥላቻ ለማንም የማትበጅ ሀገር እየፈጠርን ነው:: እኚህ ለማንም የማይበጁ አክሳሪና አድካሚ ልምምዶች በውይይት እንዲሽሩ፣ በምክክር እንዲታቀሙ እንደብሄራዊ ምክክር ያሉ ሁሉን አቃፊ የሰላም መድረኮች ያስፈልጉናል::
ብሄራዊ ምክክር በሀሳብ ደልቦ ኢትዮጵያዊነትን በማስቀጠል መርህ ውስጥ ከሁላችን ለሁላችን በሆነ የእርቅ ሀሳብ በኩል መሀከላችን ይገኛል:: እርቅ ደም ያድርቅ፣ ከፉክክር ወደምክክር ስንል የነበረው ሀገር የማዳን እንቅስቃሴ ከቃል ባለፈ በዚህ መድረክ በኩል በተግባር የሚገለጥ ነው:: የተግባሩ ባለቤት ደግሞ እኛ ሁላችንም ነን:: ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት መንደርደሪያ የሚሆነውን ዝግጅት ሲያደርግ ሰንብቶ በአንቂና አብቂ አጀንዳዎች ወደሕዝብ ወርዶ፣ ገለልተኛና አሳታፊ በሆነ ውይይት ስለሀገር ሊያወጋ በራፉን ከፍቷል::
ከአዲስ አበባ ጀምሮ መላውን የሀገራችን ክፍል የሚያደርሰው ይሄ የሰላምና የአብሮነት ተልዕኮ በሀሳብ ነቅቶ በሀሳብ የሚያንቀላፋ የሁላችን የተስፋ ምስራቅ ነው:: በዚህ ምስራቅ በኩል የእርቅና የአብሮነት፣ የሰላምና ፍቅር፣ የኢትዮጵያዊነትና የወንድማማችነት ጸሀይ እንዲፈነጥቅልን አቅንተን የተስፋችንን ውጋጋን የምንጠብቅ ብዙዎች ነን። ተወያይተንና ተመካክረን ከጦርነት ወደሰላም፣ ከዘረኝነት ወደኢትዮጵያዊነት፣ ከጥላቻ ወደፍቅር ለመሸጋገር በጽኑ መሻት ስር ነን ::
ውይይት ሀገር የምትታከምበት ሆስፒታል ነው:: እኛ ደግሞ ስፔሻሊስቶች ነን:: በቀደመው ጊዜ በማይሆን መርዛማ መድሃኒት ሀገራችንን አሳምመናታል:: ሕዝባችንን ባልተገባ መንገድ ዋጋ አስከፍለናል:: ትውልዱ ሀገር አልባ እንዲሆን ከየት ነህ? ምንድነህ? በሚል አጉል ፈሊጥ አኮራምተነዋል:: እኚህ ሁሉ ህመመሞች ሕክምና ያስፈልጋቸዋል::
ሕክምናቸው ደግሞ በሀሳብ የዳበረ ምክክርና ውይይት ነው:: አሁን ባለው የውይይት መድረክ ለሀገራችን ባለተስፋዎች ነን:: ከሕመሟ የምታገግምበትን ሁነኛ መድሀኒት ሰጥተን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከበሽታዋ የምትፈወስበትን መላ መፍጠር ግዴታችን ብቻ ሳይሆን ለራሳችን የምንውለው ውለታ ጭምር ነው::
አሁን ባለው ሀገራዊ ውጥንቅጥ ብሄራዊ ምክክር ብሄራዊ ድላችን ነው:: እንደሰጋር በቅሎ ተደናብረን ያደናበርናቸው ብዙ ናቸው:: በኃይል ፖለቲካ፣ ባለመግባባት፣ በመበላለጥ እሽቅድምድም፣ ሰላም በታጣበት የበላይነት ግፊያ ከማጡ ወደድጡ እያደረግን ያለነው ጉዞ ዛሬ ላይ ዋጋ ቢስ አድርጎን በብዙ ክስረት ውስጥ አስቀምጦናል::
ያለፈውን እንተወውና ስለመጪው እናውራ ካልን ግን እንደመፍትሄ ከፊት የሚመጣው የሀሳብ መዋጮ ነው:: ሀሳብ አዋጥተን በበረታና አቃፊ በሆነ የተግባቦት መንፈስ ስር ነገን መሳል ሀገር ከማሻገር እኩል ትውልዱን መታደግ ጭምር ነው:: አሁን ባለው ፖለቲካዊ ትኩሳት፣ የብሄር ግጭት፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች እንዲሁም ግፊያና ጦርነቶች እንደሀገር ለመቀጠል አንድ የመጨረሻ እድል ቢኖረን ውይይት ብቻ ነው::
ከውይይት ውጪ ዓለም ነውሯን የምትሽርበት ሌላ እድል አልተሰጣትም:: ከመነጋገር ሌላ የሰው ልጅ ራሱን ነጻ የሚያወጣበት መተማመኛ የለውም:: ዘመናዊነትና ስልጣኔ እንኳን ሀሳብ የሚሉትን የልዕለሰብ ዳና ተንተርሰው ነፍስ የዘሩ ናቸው::እንደአለመታደል ሆኖ ሰላም ለማምጣት ከውይይት ውጪ ያለውን ሁሉንም አይነት ሙከራ አድርገናል:: ሰላም ግን አላመጣንም::
ሰላም ማምጣት አይደለም በባሰና በከፋ ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ ወድቀናል:: አብዛኞቹ ታሪኮቻችን እንዳለመታደል ሆኖ በሚል የመግቢያ ሀረጎች የሚጀምሩ ናቸው:: ማነው እድለ ቢስ ያደረገን? ማነው ሰላምን በገሎ መሞት ውስጥ እንድንሻ የፈረደብን? ለሁላችንም ግልጽ የሆነ አንድ እውነት ቢኖር ጀብደኝነት ነው:: ጀብድ ሰላም ውስጥ እንጂ ጦርነት ውስጥ የለም:: ከእንግዲህ ባለው ታሪካችን፣ ከእንግዲህ በሚፈጠረው ትውልድ ልብ ውስጥ፣ ከእንግዲህ በምትጸነሰው ሀገራችን በኩል ሰላም በውይይት በኩል ያለ እና የሚኖር እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል::
እስኪ ካለመታደል ወደመታደል እንመለስ:: እንደአለመታደል ሆኖ ብሎ ወሬ መጀመር ያለፈ ታሪካችን ሆኖ እንዲቀር ጦርነትን በሰላም፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ዘረኝነትን በወንድማማችነት፣ ጭካኔን በርህራሄ፣ እንቢተኝነትን በእሺታ፣ ክፋትን በደግነት፣ መለያየትን በአብሮነት፣ ጥበትን በስፋት፣ እኔነትን በብዙሀነት፣ ጭቅጭቅን በውይይት ድል እንሳው:: ያኔ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል:: የእኛ የአቅጣጫ ዝንፈት ነው ሁሉንም ከነበረበት የጣለው:: እኛ ስንስተካከልና ስንቃና ሁሉም ነገር ወደተፈጥሮው እንዲመለስ ሆኖ የተበጀ ነው::
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ትላንትና ተገዳድለናል፣ ዛሬም እየተገዳደልን ነው:: ትላንትና በጦርነት ውስጥ ነበርን ዛሬም እንደዛው ሞቶ በመግደል ውስጥ ነን:: ትላንት ኢትዮጵያዊ ነበርን ዛሬ ብሄርተኞች ሆነናል:: አምና ወንድማማቾች ነበርን ዘንድሮ ጎጠኞች ወጥቶናል.. ለምን? መልሱ መነጋገር አልቻልንም የሚል ነው:: የሚያዋጣና ሁላችንንም ሚዛን ላይ አስቀምጦ በእኩል የሚዳኝ፣ የሚክስ፣ የሚያስታርቅ፣ የሚያስተቃቅፍ፣ ጉልበት የሚስም፣ ተረከዝ የሚይዝ፣ ልብ የሚያስገዛ፣ ድሮነትን የሚመልስ፣ የሚያደምጥ፣ በቃ የሚል የመንፈስ ከፍታ ስለሰላም ግዴታችን ነው:: ይሄ የሚሆነው ደግሞ በውይይትና በሀገራዊ ምክክር በኩል ብቻ ነው::
ብሄራዊ የምክክር መድረክ የሀገራችን ነባርና ወቅታዊ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት መድረክ ነው:: በሌላ መንገድ ካየነው ደግሞ የሀገርና ሕዝብ የትውልድም የማገገሚያና ጥንተ ወዛችንን የምንመለስበት የክትትል ክፍላችን ነው:: ሀገራችንን እንደበሽተኛ ብንወስዳት አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንደ ጽኑ ታማሚ ልንቆጥረው እንችላለን:: ብሄራዊ ምክክርን ደግሞ እንደጤና ጣቢያ፣ እንደሀኪም፣ እንደጽኑ ህሙማን ክፍል ልንወስደው እንችላለን:: በሌላ ስም እንግለጸው ካልን ደግሞ ሀገር የምትታከምበት፣ ትውልድ የሚሽርበት፣ የጋራ ትርክቶች የሚዳብሩበት መድረክ ይሆናል::
ሀገር የደም ስር ናት:: የእኛ አብሮነት ለሀገራችን ውበትና ድምቀት የማይሻር ሚና እንዳለው ቢታወቅም መለያየታችንም የዚያኑ ያክል ጉዳት የሚያደርስ ነው:: ባለፍንባቸው ጊዜአቶች ዋጋ ለማስከፈል አቅም በሌላቸው ትናንሽ የልዩነት አጀንዳዎች ትልቅ ዋጋ ከፍለናል:: አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ካለፈው ባለመማር ዋጋ ለመክፈል የይዋጣልን ፉከራ ላይ እንገኛለን:: ልዩነትን በውይይት እየፈታ በእርቅና በጋራ መርህ ለሰላም በሰላም መራመድ ነው ካለንበት አረንቋ የሚያወጣን::
ስልጣኔ ከሀሳብ መንጭቶ የሚፈስ ተደራሽነቱንም ሀገርና ሕዝብ ያደረገ የብዙሀን ውህደት ውጤት ነው:: ዓለም የሰለጠነበት የውይይትና የምክክር ፖለቲካ፣ ስልጣኔ የሰመረበት ከሕዝብ ለሕዝብ መርህ እኛ ጋ ሲደርስ ለምን እንደሚፈርስ ባላውቅም ማንንም ተጠያቂ ባለማድረግ ወደራሳችን እና ወደፖለቲካው ጣት የሚቀስር ነኝ:: ከታወቀን መልካም ካልታወቀን ግን በኃይል አሰላለፍ ሸራፋና ገባጣ ትውልድ እያፈራን ነው:: እንነጋገር፣ እንወያይ፣ እንተቃቀፍ::
በጠበበ ፖለቲካ ውስጥ የገዘፈች ሀገር የለችም:: ሀሳብና ማሰብን መርሁ ላላደረገ አእምሮ ታሪክና ትውልድ ምኑም ናቸው:: አሸናፊ በሌለው በወንድማማቾች ግፊያ ፖለቲካ ስር ያሸለብን እንቅልፋሞች ነበርን፣ ዛሬም ከእንቅልፋችን አልባነንም:: ያለፈው ሳያስተምረን በአዲስ ቡዳኔ በእኔ እበልጥ ሽኩቻ ገሎ ለመሞት አልሸነፍ ባይነታችንን እያሳየን ነው:: እንነጋገር የምንለው ከዚህ ሽርፈት ለመጠገን፣ ኃይል ከለበሰ ድባቴአችን ለመንቃት ነው:: ስለሀገር መነጋገር፣ ስለሰላም መወያየት ስለአብሮነት ቀጣይ እጣ ፈንታችን ሆኖ እጃችን ላይ የወደቀ፣ ፖለቲካችን ላይ ያሸለበ ጉዳይ ነው::
የሀገራችን አሁናዊ የፖለቲካ ችግር፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ እዚም እዛ የሚሰሙ ግጭቶች በውይይት ካልሆነ በምንም እንዳይፈቱ ሆነው የጠበቁ ናቸው:: እዛና እዚህ ሆኖ መሳብ ቋጠሮውን ማጥበቅ ካልሆነ በስተቀር ምንም ሊሆን አይችልም:: አልተጠጋገንም፣ ለመጠጋጋትም አልሞከርንም:: እንደእውነቱ እዛና እዚህ ቆመን በእልህ ቋጠሮ አጥባቂዎች እንጂ ተጠጋግተን ቋጠሮውን ለማመላላት ስንሞክር አንታይም::
ቋጠሮው ከትላንት ወደዛሬ በመጡ ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ የዘር እሳቤዎች፣ የብቻ ትርክት፣ የእኔ እበልጥ እኔ ፉክክር እንዳይላላ ሆኖ የጠበቀ ነው:: አሁን ላይ የምናደርጋቸው ውይይት የሌለባቸው የትኛውም እንቅስቃዎች ቋጠሮውን ይበልጥ ከማጥበቅ ባለፈ ፋይዳ የሌላቸው ሆነው የተገለጡ ናቸው:: በመሆኑም ተጠጋግቶ መነጋገር ቋጠሮውን የሚያላላ፣ መፍትሄ የሚያመጣ፣ ሰላም የሚያወርድ እውነታ ነው:: ቸር ሰንብቱ::
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም