የዓለም አትሌቲክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከስያሜው አንስቶ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚህ የሪፎርም ስራዎቹ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ራሱ የሚመራቸውን የውድድር አይነቶች ማስፋትና የጥራት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው።
በእንግሊዛዊው የቀድሞ የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮን አትሌት ሴባስቲያን ኮ የሚመራው የዓለም አትሌቲክስ የውድድር አድማሶቹን ለማስፋት ባደረገው ጥረት ከወራት በፊት የጎዳና ላይ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ ማዘጋጀት ችሏል።
የዓለም አትሌቲክስ ሰሞኑንም አንድ አዲስ የውድድር መድረክ ይፋ አድርጓል። ይህም በአይነቱ ልዩ መሆኑ የተነገረለት የውድድር መድረክ ለአሸናፊ አትሌቶች በአጠቃላይ 10 ሚሊየን ዶላር ሽልማት የተዘጋጀለት ሲሆን ይህም በትራክና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ታሪክ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ አዲስ የዓለም ቻምፒዮና የዓለም፣ የኦሊምፒክ፣ የዳይመንድ ሊግ ቻምፒዮኖችን፣ በውድድር ዓመቱ ድንቅ አቋም ያሳዩ አትሌቶችን በአንድ ላይ የሚያፋልም የአሸናፊዎች አሸናፊ ቻምፒዮና ሲሆን በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ መሆኑ ተጠቁማል። በዚህም የተለያዩ የትራክ (መም) እና የሜዳ ተግባራት አትሌቶች በበርካታ ርቀቶች የትኛው አትሌት ምርጥና የቻምፒዮኖች ቻምፒዮን መሆኑ የሚለይበት ነው።
ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት እንደ ውድድር ዓመቱ መርኃ ግብር መዝጊያ የሚያገለግል ሲሆን ከ2026 ጀምሮ እንደሚካሄድም የዓለም አትሌቲክስ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። ያለፈውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በቡዳፔስት ያስተናገደችው ሀንጋሪም የመጀመሪያውን አዲስ ውድድር እንድታዘጋጀ ተመርጣለች።
የመጀመሪያው ውድድር በፈረንጆች ከመስከረም 11-13/2026 የሚካሄድ ሲሆን በእያንዳንዱ የውድድር አይነት አሸናፊ የሚሆነው አትሌት 150ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። ሌሎችም እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ።
የዓለም አትሌቲክስ ይህን አዲስ ውድድር የፈጠረው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቴሌቪዥን ተመልካቾችን ለማግኘትና እንደ የመጨረሻው የውድድር ዘመን ማጠናቀቂያ ወይም መዝጊያ ውድድር እንዲሆን በማሰብ ነው። የውድድሩ ፎርማት እንደ መደበኛው የዓለም ቻምፒዮና በርካታ ቀናት የማይፈጅ ዝግጅቱም ፈጣንና የተለየ እንደሚሆን ታምኖበታል። ከሦስት ባልበለጡ ቀናት የሚካሄደው ይህ ውድድር ፣ እያንዳንዳዱ ቀን በሶስት ሰአት የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ፉክክር ይታይበታል። በዚህም የአትሌቲክስ ምርጡን፣ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ሩጫዎች፣ የዱላ ቅብብል፣ ዝላይ እና ውርወራ ውድድሮችን የሚያካትት ይሆናል።
ለአትሌቲክስ አፍቃሪዎችና ለመላው ዓለም ተመልካች አጓጊ ይሆናል በተባለለት ውድድር አትሌቶች ልክ እንደመደበኛው የዓለም ቻምፒዮና አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉበት እንደሚሆን ተጠቁሟል። በእያንዳንዱ ውድድር የምርጦች ምርጥ ይለያል የተባለለት አዲስ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና የጥራት ደረጃው ከፍ ያለ እንደሚሆንም የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ መናገራቸው በመግለጫው ተቀምጧል።
የዓለም አትሌቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆን ሬድጎን አዲሱን አይነት የዓለም ቻምፒዮና ማዘጋጀት ስላስፈለገበት ምክንያት ሲያስረዱ ‹‹አዳዲስ ፈጠራዎችን ወደ አትሌቲክሱ ዓለም በማምጣትና ከተለመደው አሰራር በመውጣት ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኘት፣ በተለይም ወጣት አትሌቲክስ አፍቃሪዎችን ተደራሽ ለማድረግና ስፖርቱን ለማነቃቃት ነው›› በማለት ተናግረዋል።
ስራ አስፈፃሚው አክለውም በስቴድየምና በቤቱ ተቀምጦ በቴሌቪዥን መስኮት የአትሌቲክስ ውድድሮችን የመመልከት ባህልን ለማሳደግ እንዲህ አይነት አዳዲስ ውድድሮችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ‹‹ይህ በአጠቃላይ የስፖርቱን ገፅታ የሚቀይር እንደሚሆን እናምናለን›› ሲሉም በአዲሱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ያላቸውን ተስፋ አስረድተዋል።
የዓለም አትሌቲስ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከቤት ውጭ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና፣ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና፣ የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና በዋናነት በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂድ ሲሆን፣ ዘንድሮ ከአንድ ማይል ጀምሮ እስከ ግማሽ ማራቶን ድረስ የዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮችን ያካሂዳል። 2026 ላይ ይጀመራል የተባለው አዲስ የውድድር አይነት ደግሞ ከ አጭር ርቀት ጀምሮ የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን ብቻ የሚያካትት ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም