ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማዕድን ሀብቷ ተወዳዳሪ ሊያደርጓት የሚችሉ በርካታ የማዕድን ሃብቶች እንዳሏት በተለያዩ ጊዜያት የተጠኑ የሥነ-ምድር ጥናቶችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። የማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ ከዚህ ሀብት በሚፈለገው ልኩ ተጠቃሚ ሳትሆን ኖራለች።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የአስር ዓመት እቅድ ትኩረት ከሰጣቸው የምጣኔ ሀብት ምሰሶዎች መካከል ይህን የማዕድን ዘርፍ አርጎ እያሰራ ይገኛል። ይህን ተከትሎም ዘርፉ ከዓመት ዓመት የአፈጻጸም መሻሻል እያሳየ ይገኛል። እንዲያም ሆኖ ግን ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ ለሀገር እድገት ሚናውን እየተወጣ አለመሆኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኘ ይናገራሉ።
ሚኒስትሩ ሰሞኑን የተቋማቸውን የዘጠኝ ወር የስራ አፈጸጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ዘርፉ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛሬም በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ነው ያመለከቱት።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ እንደ ሀገር የማዕድን ዘርፍ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፤ ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብአቶችና የማዕድን ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካትና በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በተከናወኑ ተግባራት የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው። እነዚህ ጅምሮች በቀጣይ ዓመታት ኢትዮጵያ በያዘችው የማደግ ሕልምና ጥረት ላይ ዘርፉ የላቀ አስተዋፅዖ ሊያበረክት እንደሚችል ማሳያዎች ናቸው።
በዚህ ረገድ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የማዕድን የወጪ ንግድን ለማነቃቃት በስፋትና በጥራት በማምረት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ማሳደግ አንዱ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኩባንያዎች አማካኝነት ሁለት ነጥብ 414 ቶን እንዲሁም በባህላዊ መንገድ ዜሮ ነጥብ 609 ቶን በአጠቃላይ ሶስት ነጥብ 023 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ተችሏል። በዚህም 274 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ተችሏል፤ ይህም አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 12 ነጥብ 6 በመቶ እንዲሁም በገቢ 83 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት ነው።
የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትን ለማሻሻልም አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የፀጥታና ተያያዥ ችግሮች በቅርበት በመፍታት የተለያዩ ውጤቶች መገኘታቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ በዚህም ለመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።
እንደ አጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ነጥብ 42 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ተመርቷል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ22 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነው። ይህም በገበያ ላይ ተከስቶ የነበረውን የሲሚንቶ አቅርቦት ዕጥረት በተወሰነ መልኩ ለማረጋጋት አስተዋጽኦ አበርክቷል።
አንደ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገሪቱ ከሚገቡ ምርቶች መካከል አንዱ ብረት ነው። የማዕድን ሚኒስቴር ይህን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን ብረት በሀገር ውስጥ በማልማት ለመጠቀም የሚያስችሉ የብረት ማዕድን ፍለጋና ክምችት ግምት ስራዎችን በራስ አቅምና በውጭ ባለሀብቶች አማካኝነት እያስጠና ይገኛል።
አሁን ላይ የብረት ፋብሪካዎች እያጋጠማቸው ያለውን የግብዓት እጥረት በጊዜያዊነት ለማቃለል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን ቁርጥራጭ ብረቶችን ከተለያዩ ተቋማት እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በኢንዱስትሪዎች ዜሮ ነጥብ 25 ሚትሪክ ቶን ብረት ማምረት ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከወርቅ ውጭ ባሉ የወጪ ንግድ ማዕድናት 69 ነጥብ 79 ቶን ታንታለም ኦር፤ 11 ሺ 176.4 ቶን ሊትየም፤ 19 ነጥብ 894 ቶን ጥሬ እና እሴት የተጨመረበት ኦፓል፤ 79 ነጥብ 55 ቶን ጌጣጌጥ እንዲሁም 32 ሺ 141 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ 13 ነጥብ 335 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ተችሏል። በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 289 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ68 በመቶ ብልጫ ያሳያል።
ተኪ ማዕድናትን በተመለከተ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በዋናነት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚያስገቡትን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለመተካት የድንጋይ ከሰል ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ስራ በማስቆም አቅርቦትን ለመጨመር የሚስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለድንጋይ ክሰል ተጠቃሚ የሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀረበው የምርት መጠን መሰረት ከአጠቃላይ ፍጆታቸው 64 ከመቶ ለመሸፈን ተችሏል።
በቀጣይ በጀት ዓመት ሁለት ፋብሪካዎች የታጠበ ድንጋይ ከሰል የሚያመርቱ ይሆናል። የቀሩት ኩባንያዎች የቅድመ ምርት ዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በገቡት ውል መሰረት ስራዎችን መስራት ያልቻሉ ኩባንያዎች ላይ ውል እስከ ማቋረጥ የደረሱ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሎች ለ378 የድንጋይ ከሰል አምራቾች ፈቃድ የተሰጠ ሊሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 40 ባለፈቃዶች ብቻ በሥራ ላይ ይገኛሉ ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ ፈቃዶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ በአግባቡ በማስተዳደርና ጥራቱን የጠበቀ የድንጋይ ክሰል በሚመረትበት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት ማስተካከያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአፈር አሲዳማነት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ለእዚህም 192 ሺ ኩንታል ላይምስቶን ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። አሁን በአሲድ የተጠቃውን መሬት በግብርና ኖራ ለማከም ከተዘጋጀው የ3 ዓመት መሪ ዕቅድ በመነሳት 100 ሺ ሄክታር መሬት ለማከም የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ከግብርና ሚኒስቴርና ከክልሎች ጋር በጋራ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው ያመለከቱት።
ከወርቅ ውጭ ለዓለም ገበያ ከሚቀርቡ ማዕድናት ሀገራችን በተለይም በውጭ ምንዛሬ ረገድ ማግኘት የሚገባትን ታገኝ ዘንድ የጌጣጌጥ ማዕድናት የመላኪያ መነሻ ዋጋ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉንም ገልጸዋል። በዚህም የመላኪያ መነሻ ዋጋና ደረጃ ከወጣ በኋላ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንደገለጹት፤ ከታህሳስ በፊት የአንድ ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓል አማካይ ዋጋ 29 የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከታህሳስ ጀምሮ ባሉት ወራት የአንድ ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓል አማካይ ዋጋ 308 የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህም የአንድ ኪሎ ግራም አማካይ ዋጋ ከአስር እጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ያሳያል።
የአንድ ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረበት ኦፓል እማካይ ዋጋ 547 የአሜሪካ ዶላር እንደነበረ አስታውሰው፣ ከታህሳስ ጀምሮ ባሉት ወራት የአንድ ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረበት ኦፓል አማካይ ዋጋ ሁለት ሺ 922 የአሜሪካ ዶላር ሆኗል ብለዋል። ይህም የአንድ ኪሎ ግራም አማካይ ዋጋ ከአምስት እጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በ2016 ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከተላከው ጥሬ ኦፓል ውስጥ 17 ሺ 154 ኪ ግራም የሚሆነው የመላኪያ መነሻ ዋጋና ደረጃ ከመውጣቱ በፊት የተላከ ሲሆን፣ በዚህም 0 ነጥብ 49 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። የመላኪያ መነሻ ዋጋና ደረጃ ከወጣ በኋላ ሁለት ሺ 349 ነጥብ 85 ኪሎ ግራም ለውጭ ገበያ በመላክ 0 ነጥብ 7237 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። ይህ የሚያሳየው የመላኪያ መነሻ ዋጋና ደረጃ መውጣቱ ለውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ነው።
በሌላ በኩል በተለያዩ የውጭ ሀገራት በመገኘት የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት፤ በዘርፉ ለመሰማራት ያሉ ምቹና አስቻይ ሁኔታዎችን የማስረዳት ስረዎች ተከናውነዋል ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በዚህም በዘጠኝ ወራት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም ላላቸው የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አንድ የምርት ሁለት የፕሮሰሲንግና አራት የምርመራ ፈቃዶች መሰጠታቸውን ተናግረዋል። ለውጭ ባለሃብቶችም ሁለት የምርት፣ አንድ የፕሮሰሲንግና ሁለት የምርመራ ፈቃዶች በመስጠት 4 ነጥብ 82 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ሊመዘገብ ችሏል ብለዋል።
ሚኒስትሩ የማዕድን ሀብት ብክነትን ለመቆጣጠር፤ በአግባቡና በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲሁም አጠቃለይ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ማኅበረሰቡ በእኔነት ስሜት እንዲመለከት ማድረግ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በዘጠኝ ወራት ከ154 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በባህላዊ ማዕድን ስራ ላይ የሚፈጠረው የስራ ዕድል ስፋት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የቴክኒክ ሥልጠናዎች እንዲሁም የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኩባንያዎች የውል ግዴታቸውን እንዲወጡ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በማከናወን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 22 ነጥብ 18 ሚሊየን ብር ለማኅበረሰብ ልማት ማሰራጨት ተችሏል። የማዕድን ልማት የሚካሄድባቸው ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ ኩባንያዎች በሚገቡት የውል ግዴታ መሰረት 12 ሄክታር የማዕድን ልማት የተካሄደባቸው ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ተችሏል።
ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች ድጋፍ ከማድረግ አኳያ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአፋር የአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለ400 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ፣ በክልሉ ለሚገኙ አምስት አባወራዎች የመኖሪያ ቤት እና በጦርነት ለተጎዳ አንድ ትምህርት ቤት ማደሻ የ600 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉንም አስታውቀዋል።
ይህ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ በማዕድን ሀብት ተጠቃሚነት ረገድ ኢትዮጵያ ካሏት የማዕድን ሀብቶች አንጻር እያገኘች ያለው ሲታይ ብዙ እንደሚቀር ግልጽ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከማዕድን ጋር ያለን ታሪካዊ ቁርኝትና የማልማት ልምምድ በርካታ መቶ ዓመታትን የተሻገረ ቢሆንም ረዥም ታሪኩና ሰፊ ልምምዱን የሚመጥን ስራ ተከናውኗል ለማለት አያስደፍርም ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ዘርፉ በአንድ ወገን ለረጅም ጊዜ ሲመራበት የቆየው ስትራቴጂ ችግሮች፤ የፖሊሲ አለመኖር እንዲሁም ሜጋ ፕሮጀክቶችን መከታተል የሚያስችል አደረጃጀት አለመፈጠሩ ከቀዳሚ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ ይላሉ። በተመሳሳይም በክልል የማዕድን ዘርፉን የሚመሩ ተቋማትን አደረጃጀት ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም የማስፈፀም አቅምን ለማሳደግና በተሻለ ሁኔታ ለመምራት በማዕድን አዋጁ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አስተያየትና ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለሚመለከተው አካል መቅረቡንም አስታውቀዋል።
በብዙ ቦታዎች የተፈጥሮ ሃብትን እንደ ፀጋ ሳይሆን እንደ ግጭት መንስኤ ተደርገው ከመታየታቸው ጋር በተያያዘ ማዕድናቱን በሚፈለገው ልክ ማልማት እንዳልተቻለም ነው ያመለከቱት። በዚህ የተነሳም ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማግኘት ሳይቻል መቅረቱን ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሕገ ወጥ የማዕድናት ግብይትና የኮንትሮባንድ ንግድ፤ እንዲሁም በማዕድን ማምረቻ አካባቢዎች ያሉት የፀጥታ ችግሮች በዘርፉ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ሕገወጦችን የመቆጣጠርና ሕጋዊ እርምጃዎች የመውሰድ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለቀጣይም ጊዚያትም በተቋቋመው ብሔራዊ ማዕድን ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ አማካኝነት በዘርፉ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት በዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል።
የማዕድን ዘርፍ በባህሪው የረጅም ጊዜ ጥናት፤ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት፡ ከፍተኛ ቴክኖሎጂና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንደሚጠይቅ ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ምክንያትም ካለው እምቅ አቅም አንፃር የሚገባውን ያህል ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል። ለማዕድን ኢንዱስትሪዎች ለጥሬ ዕቃ፤ ለማሽነሪና ለመለዋወጫ የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መኖር ዛሬም ለዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የዘርፉን የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የሁለቱ ተጠሪ ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩትና የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት እንስቲትዩት በጥናት ላይ በመመስረት የማዕድን ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ይህም ሆኖ ዘርፉ ካሉበት ተግዳሮቶች አንጻር የተከናወኑት ተግባራት ገና በጅምር ላይ ያሉ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
በአንጻሩ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት የሚሰሩት ስራ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የወከሏቸው ሕዝቦች ክልሎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም