ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተለያዩ ምዕራፎችን አልፎ አጀንዳ ወደ ማሰባሰብ ምዕራፍ ገብቷል። ባለፈው ሳምንትም በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ሁሉም ባድርሻ አካላት የተሳተፉበትን የምክክር ምዕራፍ አካሂዷል፤ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በይፋ ተጀምሮ ሲካሄድ የቆየ የምክክር ምዕራፍ ባለፈው ማክሰኞ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ይህ አጀንዳ የሚሰባሰብበት፣ የሚደራጅበትና የሚንሸራሸርበት ወሳኝ ምዕራፍ በየክልሎቹ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ይቀጥላል።
ይህ ኢትዮጵያውያን፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ የእምነት ተቋማት፣ ባህላዊ መሪዎች፣ ወዘተ. በጉጉት ሲጠብቁት የኖሩት ታላቅ መድረክ፣ በስኬት እንዲከናወን የመድረኩ ተሳታፊዎች ዋና ዋና ሀሳቦችን በማንሳት በንቃት አንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ባቀረበው ጥሪ መሰረት፣ ንቁ ተሳትፎ የተደረገበት መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጧል።
በአዲስ አበባ ደረጃ አጀንዳዎች መለየታቸውን ምክክሩን ግማሽ መንገድ ያስጓዘ ሲል ገልጾታል። በሌሎች ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚካሄደው ተመሳሳይ መድረክ ይሄው ይጠበቃል።
ይህን በቀላሉ የማይገኝ ታሪካዊ እድል ተጠቅሞ የሀገሪቱን ስር የሰደዱ የዘመናት ችግሮች አንዲፈቱ የሚያስችል አሻራ ማኖር በራሱ ትልቅ እድል እንደመሆኑ ተሳታፊዎች በንቃት በመሳተፍ ያሳዩት ተነሳሽነት አድናቆት ሊቸረው ይገባል። በቀጣይም በእዚሁ መልኩ እንዲፈጸም አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የጦርነት፣ ግጭትና እኔ አውቅልሃለሁ አካሄድ ክፉኛ ተጠናውቷት ለቆየች ሀገር ዋና ዋና ችግሮች መፈታት ተኪ የሌለው አማራጭ ነው በሚል በእጅጉ ታምኖበት እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ የዚህ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ ደረጃ በይፋ በተጀመረበት ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ሀገራዊ ምክክሩ የሀገሪቱን ዋና ዋና ችግሮች እንደሚፈታ አስገንዝበዋል። በመድረኩ የተገኘውን እድል ሳናበላሽ መጠቀም እንዳለብንም ነው ያስታወቁት።
ለሀገሪቱ መሰረታዊ ችግር ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሄ እንደማያስገኙ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊ ማስከተላቸው ነው ብለዋል። ቢዘገይም የተሸነፈው ለማሸነፍ ይታገላል፤ ያሸነፈውም ድሉን ለመጠበቅ ይዋጋል። ምክክር ግን ሁሉንም ወገን አሸናፊ ያደርጋል ሲሉም አስታውቀዋል።
በእርግጥም ከምክክር ውጪ ያሉትን አማራጮች በሚገባ ለኖረችው ለዚህች ሀገር ስር የሰደዱ ችግሮች መፍትሄው ምክክር ነው። ከምክክር ውጪ ያሉትን ጦርነቶች፣ አብዮት፣ መፍንቅለ መንግስት፣ ግጭት፣ ወዘተ፣ ለተገበረ፣ ሲተገብር ለኖረ፣ ታሪኩን ላዳመጠና ላነበበ ደግሞ ምክክር ወሳኝ መፍትሄ መሆኑን ለመገንዘብ ይቸገራል ተብሎ አይታሰብም።
መመካከር የጨዋነት መገለጫም ነው። ያለመነጋገር፣ መናጨት የሚያስከትለውን ዳፋ በሚገባ እንዲያውቁት ለተደረጉት ኢትዮጵያውያን፣ በዚህ ላይ ብዙ የቆየም ትኩስም ታሪክ ላላቸው ለእነዚሁ ኢትዮጵያውያን ይህን የጨዋ መንገድ መምረጥ ጨዋነትም ነው እላለሁ፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ አማራጭም አይኖርም።
የጦርነት፣ የአብዮት፣ የመፈንቅለ መንግስት ታሪካቸው ሰፊ የሆነው ኢትዮጵያውያን በምክክር አልባዎቹ ዘመናት በእጅጉ ፈተና አይተዋል። አትዮጵያ ውስጥ በመንግስታት የተፈጸሙ ግፎችን፣ በደሎችን ተከተሎ መንግስትን ጥሎ አዲስ መንግስት ለማምጣት በሚል የከሸፉም ያልከሸፈም መፈንቅለ መንግስታት ተካሂደዋል።
ያልከሸፈውን መፈንቅለ መንግስት ብንጠቅስ አብዮት ተብሎ ጥቂት ያመጣቸው ለውጦች ቢኖሩም፣ በርካታ ውጥንቅጦችንም ማስከተሉ ይታወቃል። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግስት/ ደርግ/ መላ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲጠይቁ የኖሩትን የሀገሪቱን ስር የሰደዱ ችግሮች ፈትተዋል ከተባሉት መካከል የገጠር መሬት እንዲሁም የከተማ ቦታንና ትርፍ ቤትን የመንግስት ያደረጉ አዋጆችን በማውጣቱ በደግ ይጠቀሳል። እነዚህ አዋጆች የመላ ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች ነበሩ፤ ለእነዚህ የተሰጡት መልሶች ትልቅ እርምጃ የሚባሉ ናቸው።
የገጠር መሬት አዋጁ አርሶ አደሩን ከጭቆና ቀንበር አውጥቷል። ከባላባታዊው ስርዓት መዳፍ ውስጥ አውጥቶ የመሬቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ዘርግቷል። የከተማ መሬትና ትርፍ ቤት አዋጅም በከተማ ነዋሪዎችና ከተማ ልማት ላይ የነበረውን ጫና አቃሏል። እነዚህ አዋጆች ያኔ ባይወጡና ሕዝቡን ባይታደጉ ኖሮ ዛሬ በሀገራዊ ምክክሩ የሚነሱ ከአብይም አብይ የሚባሉ ሀሳቦች እንደሚሆኑ ጥርጥር አልነበረውም።
ደርግ በእነዚህ አዋጆች አርሶ አደሩንና ከተሜውን ቢታደግም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ደም ሲቃባም ነው የኖረው። በአንድ በኩል ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደምን ዜማ፣ በሌላ በኩል ‹‹የፍየል ወጠጤ…. ››ን ቀረርቶ እያሰማ ነጋ ጠባ እያሰማ ያላደረገው ያልደፈረው የግፍ አይነት አልነበረም።
በንጉሱ ዘመን በሀገሪቱ ለተፈጸመው ግፍና በደል ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የሀገሪቱን 60 ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ወህኒ ቤት እያሉ ረሽኗል። ስርዓቱን ተቃውሞው ጫካ የገቡትን፣ አኩርፈዋል ያላቸውን ሁሉ እያሳደደ በወረንጦ እየለቀመ ጨርሷቸዋል። በዚህ ሁሉ የሕግ የበላይነትን ጥሷል።
መግደል የተጠናወተው ያ መንግስት አብዮት ልጆቿን ትበላለች እያለ አብረውት ብዙ ርቀት የተጓዙ ጓዶቹን በሀሳብ ልዩነት፣ በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳቢያ ቅርጥፍ እያረገ በልቷቸዋል። ለእዚህ ይሆን አብዮት ልጆቿን ትበላለች መባሉ? የእነ ኮሎኔል አጥናፉ፣ የእነ ጀነራል ተፈሪ በንቲ፣ የእነ ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም መገደል ከዚህ ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል።
በዚያ የጠመንጃ ዘመን ሰው የበላውና በሰው የተበላው ብዙ ነው። በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር የዚህች ሀገር ውድ ልጆች /አንድ ትውልድ/ እንደ ቅጠል ረግፈዋል፤ በወጡበት ቀርተዋል። ጓዳዎች በጥይት በተፈረከሱ ወጣቶች ደም ጨቅይተዋል፤ አስከሬን መንገድ ላይ ማየት ተለምዶም ነበር። ከአንድ ቤት ሁለት ሶስት ወጣት የታጣበት ሁኔታም ተከስቷል። የእነዚህ ዜጎች ቤተሰቦች ይህ መጥፎ ጠባሳ ትቶባቸው ባለፈው ቀውስ ከቆሙት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው እድሜያቸውን ለመግፋት ተዳርገዋል።
አያሌ ዜጎች ለአያሌ ዓመታት በወህኒ ቤት ተሰቃይተዋል፤ የተረፉትም ባወጣ ያዋጣው ብለው ሀገራቸውን ወደ ሁዋላ ጥለው እግራቸው ወደ መራቸው ባእድ ሀገር ተሰደዋል፤ ጥቂት የማይባሉትም በረሃ ቀርተዋል፤ የአሸዋና የባህር ሲሳይ ሆነዋል። አንዳንዶቹም መሳሪያ ይዘው ጫካ ገብተዋል።
የከሸፉት መፈንቀለ መንግስቶች በ1953 ዓ.ም በ1982 ዓ.ም የመንግስት ባለስልጣናትን በልተዋል፤ በመክሸፋቸው ደግሞ ራሳቸው መፈንቀለ መንግስት አድራጊዎቹ በወረንጦ ተለቅመው ተብልተዋል፤ በ1953ቱ የመንግስቱ ነዋይ ግርግር በገነተ ልኡል ቤተመንግስት የተረሸኑት፣ ሁሉም መፈንቅለ መንግስቱ ከሽፎ በመንግስት ኃይሎች የመፈንቅለ መንግስቱ ተዋንያን እየታደኑ የተገደሉበት ሁኔታ፣ በ1982ቱ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስትም እንዲሁ ከመንግስት ወገን የነበሩ ጥቂት የመፈንቅለ መንግስቱ ተቃዋሚዎች አስቀድሞ የተበሉበት ሁኔታ ቢኖርም፣ መፈንቅለ መንግስቱ መክሸፉን ተከትሎ በአዲስ አበባና በአስመራ ያለቁት ጀነራል መኮንኖችና በሌላ ማእረጎች ቁጥር አያሌ ነው፤ በመፈንቅለ መንግስቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ጀነራሎችና በሌላ ማእረጎች እየታደኑ ወህኒ ከወረዱ በሁዋላ ያለምንም ፍርድ የተረሸኑበትን ሁኔታ ታሪክ አይረሳውም።
በኃይል ስልጣን ለመያዝም ሆነ በኃይል ስልጣን ላይ ለመቆየት በተደረጉ ጥረቶች ሀገሪቱ ብዙ ያወጣችባቸው ልጆች ከዚህም ከዚያም ወገን ተበልተዋል። በዚህ ሂደት ወስጥ የገደለው ሲያቅራራ፣ የተገደለበት ደግሞ ቀን እስኪያልፍ … እንዲሉ ዞር ብሎም ይሁን አድብቶ ሲያሴር ነው የኖረው። ችግሩ ‹‹ለሀገር ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትም አልወጣ፤ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ›› የሚባል ነበር።
በጦርነት ድል አድርጎ መንግስታዊ ስልጣን የተቆጣጠረው አካል/ኢሕአዴግ/ ወደ ሶስት አስርት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ስልጣን ላይ ቢቆይም፣ መሰረቱ ጦር መሳሪያ ስለነበር ለውይይት በር ከፍቶም አያውቅም። በተቀነባበረ ምርጫ፣ በይስሙላ ዴሞክራሲ ስልጣን ላይ የቆየው ያ መንግስት፣ በውስጡ በተፈጠረ ልዩነት ተፈረካከሰ።
ኢህአዴግን ሲመራ የነበረው ኃይልም እንዲሁ በወታደራዊ ኃይል ባይወገድም ለሕዝብና ለሀገር መስራት ካለበት ብዙ አጉድሏል ተብሎ በሕዝባዊ አመጽና በፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ የለውጥ ኃይል ስልጣኑን በተለሳለሰ መልኩ እንዲለቅ ተደርጓል።
ሁሉም መንግስታት የንግግር ጠረን ያልዞረባቸው መሆናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብና የሀገሪቱ መሻት የነበረውን ሀገራዊ ምክክር አውን እንዲያደርጉ ቢጠየቁም አልሞከሩትም። በእዚህ በኩል ተጠያቂ ከመሆናቸውም በዘለለ ተቆጣጥረውት ከቆዩት ቤተመንግስት በኃይልም ይሁን በስልት ለመወገድ ተገደዋል።
መንግስታት ወደ ስልጣን ሲመጡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ቃል ቢገቡም፣ የሕዝቡን የዘመናት ችግር አብሮ መክሮ ዘክሮ በመፍታት ሀገረን የመምራት ጉዳይ እውን ለማድረግ ቢምሉ ቢገዘቱም፣ ከምርጫ ማግስት በሁዋላ ወይም ስልጣኑን እንደያዙት ካረጋገጡ በኋላ ቃላቸውን ሲያጥፉ ነው የኖሩት። ለእዚህም ነው በሀገሪቱ መንግስት ሲቀየር አንጻራዊ ሰላም ብቅ ይልና ብዙም ሳይቆይ የሚጠፋውና በምትኩ ጦርነት ግጭት እስርና ግድያ ማሳደድ የሚንሰራፋው። ሀገሪቱ በእዚህ አዙሪት ውስጥ ነው ስትዳክር የኖረችው።
ይህ ዘመናት ተሻግሮ እዚህ የደረሰ በየተራ አሸናፊ የመሆን መጥፎ እሳቤ ለሀገርና ሕዝብ የበጀው አንድም ነገር የለም። ይልቁንም ሀገርና ሕዝብ መንግስታትን እንዳያምኑ የሚያደርግ እሳቤ ፈጥሯል። በተረኛ እሳቤ እንዲሰላቹ አድርጓቸዋል።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ይህን የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት በገባው ቃል መሰረት እየሰራ ይገኛል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ይህን ችግር ለመፍታት የተጀመረው ጥረትና አሁን የደረሰበት ምዕራፍም ይህንኑ ያመለክታል። ለምክክሩ የሚያስፈልጉ በርካታ ሂደቶች ታልፈው አሁን ወደ መምከሩ ምዕራፍ ተገብቷል። በዚህም የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች በውይይት ለመፍታት፣ መፍታት ያልተቻሉትን ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ ለመፍታት እየተሰራ ነው።
የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት አጥብቆ ሲሰራበት የቆየው ዜጎች፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ወዘተ ለዘመናት ሲጠይቁ የኖሩት በሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ችግሮችን የመፍታት እሳቤ እነሆ ወሳኝ ሊባል በሚችል ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያውያን በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳያቸው ላይ መምከር ጀምረዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው የአጀንዳ ሀሳቦችን የመስጠት፣ አጀንዳዎችን የማንሸራሸርና የማደራጀት ስራ በአዲስ አበባ ባለፈው እሮብ መጀመሩ ይታወቃል። ይህ ምክክር በይፋ በተጀመረበት ባለፈው ቅዳሜም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን /ዶ/ር/ ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተገኝተዋል።
እናም ከሀገራዊ ምክክር ውጪ ባሉት አማራጮች ዘመናትን ሞክረናል፤ የተጠበቀው አልሆነም፤ ከሰሞን የዘለለ ሊባል የሚችል ድል አልተገኘም። አርባም፣ ሰላሳም፣ አስራ ሰባት ዓመትም ይሁን የቀናት እድሜ ከመተላለቅ፣ ከሴራ፣ የጎሪጥ ከመተያየት ውጪ የተገኘ የኢትዮጵያውያንን መሰረታዊ ችግር በመፍታት ሊታደግ የሚችል ጠብ የሚል ነገር አልመጣም።
ይህ መንገድ በራሱ የከሸፈ ነው። ለእዚህ ደግሞ ከኛው ሀገር ውጪ ሌላ መጥቀስም አያስፈልግም፤ ይበቃዋል፤ ተሞከረ ተሞከረ። ያልሞከርነው እንዳማረን ቀርቶ የኖረውን ሀገራዊ ምክክር እንስራበት ተብሎ ወደ ስራ ተገብቷል። ለምምክሩ ስኬት ማድረግ ያለብንን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ አይነት እድል ተመላልሶ አይመጣም፤ ይህ ታላቅ እድል እጃችን ውስጥ ገብቷልና ሀገርን ሕዝቧን ለመታደጊያ ለመዋል እንረባረብ።
ወቅቱን የምክክር እናድርገው፤ ምክክር የጨዋ ነው እንዳልኩት እኛም በጨዋነት አንታማምና ከልብ ጨዋ ሆነን ይህን ታላቅ አጋጣሚ እንጠቀምበት።
ዘካርያስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም