የፍትሃዊነትና የተደራሽነት ማሳያ

ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆን ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም። አካል ጉዳተኛነት በማንኛውም ሁኔታ፣ ጊዜና ስፍራ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ከጽንሰት እስከ ህልፈት ሊደርስ የሚችል አንዱ የህይወት አጋጣሚ ነው። የአካል ጉዳትን ለመተርጎምና ለመረዳት የሚጠቅሙን ሁለት ቁልፍ ፅንሰ ሀሳቦች ያሉ ሲሆን እነሱም ስነት እና አካል ጉዳት ናቸው።

እነዚህ ሁለት ፅንሰ ሀሳቦች መካከል ጉልህ ልዩነት አለ። ስነት ሥር በሰደደ የጤንነት ጉድለት ለምሣሌ የስኳር በሽታ፣ በምግብ እጥረት፣ በህመም ምክንያት የሚከሰቱ የአካል ጉዳት ችግሮችን የሚያመላክት ነው። የልጅነት ልምሻ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።

በቤት ውስጥ አደጋ፣ በተሽከርካሪ አደጋ፣ በፀብ ወይም በግጭት፣ በቦምብ ፍንዳታ የሚከሰት የአካል መደበኛ ተግባር መሰተጓጐልን ወይንም የአካል መዋቅር መዛባትን ያስከትላል። ስነት በጽንስ/በወሊድ ግዜ ወይም ከውልደት በኋላ በሂደት የሚፈጠር ነው። የአካል ጉዳት የምንለው ደግሞ ከአንድ በላይ የስነት አይነት በአንድ ሰው ላይ ሲከሰት ነው።

ከዓመታት በፊት በወጣው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ሪፖርት መሠረት፤ በዓለም ላይ ካሉት አንድ ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል 15 በመቶዎቹ በታዳጊ ሃገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ይገኛሉ። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።

የተዛባ አመለካከት ባልተገራበትና ትክክለኛ ግንዛቤ ባልያዘበት፣ አድልዖና መገለል ባልተወገደበት እንዲሁም የመረጃ ተደራሽነትና ትኩረት ባልሰፈነበት ማኅበራዊ አውድ ውስጥ አካል ጉዳተኞች ከድህነት አዙሪትና ከጎስቋላ አኗኗር ይወጣሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው።

በተለያዩ ጊዜያት የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ያላማከለ እና የእለት ተዕለት ኑሯቸውን አዳጋች የሚያደርግ ሆኖ እንመለከታለን። አንዳንድ ጊዜ የእግር መንገዶችን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስቸግሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለብዙዎች፣ ትምህርት ቤቶችም ሆኑ የጤና ተቋማት የሚገኙባቸው ቦታዎች በጣም ሊርቁ፣ የንፅህና አገልግሎት መስጫዎች ጨርሶ ላይኖሩ ወይም ሊቆለፉ አሊያም አገልግሎት ሊሰጡ በማይችሉበት ደረጃ የንጽህና ጉድለት ሊኖርባቸው ይችላል።

የሚገነቡ ህንፃዎች አሰራራቸው አካል ጉዳተኞችን ያላማከሉ በመሆናቸው መሰናክል ሲሆኑ ይስተዋላል። ለአብነትም፤ ከፍ ያሉ የደረጃ መርገጫዎች፣ ጠባብ በሮች፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ መግቢያዎች አለመኖር፣ ጠባብ ክፍሎች፣ በቂ ብርሃን ያለመኖር፣ የደረጃ መደገፊያ ያለመኖር እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

ለሰው ልጆች የአዕምሮ እድገት እጅግ ወሳኝ በሆነው የትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው ትምህርታቸውን መከታተል እንዳይችሉ አካል ጉዳተኞችን የሚያደናቅፉ ነገሮችም በርካታ ናቸው። በርካታ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆች ውሃና የንፅህና መጠበቂያ አገልግሎት መስጫዎች ባለመኖራቸው ወይም ለመጠቀም የሚያስቸግሩ በመሆኑ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ይገለላሉ።

ከትምህርት ቤቶች የመፀዳጃ አገልግሎት መስጫዎች ጋር በተያያዘ እንደመሰናክል ሊቆጠሩ የሚችሉት ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ የመፀዳጃ ቤቶች ጨርሶ አለመኖርና፣ ወደ መፀዳጃ ቤቶቹ የሚወስዱ መንገዶች አመቺ አለመሆን፣ አጋዥ ወይም መሪ/ደጋፊ ነገሮች አለመኖር ወይም የክፍል መጥበብ ሊሆኑ ይችላሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ የመስጠት፣ የማስተማር እና ሌሎች ኃላፊነቶች የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት፣ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን በየአገሮቻቸው ሕገ-መንግሥት አካተውና አፅድቀው፣ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ የመማር መብት እንዳለው እና መንግሥት፣ ማኅበረሰቡ፣ ሲቪክ ማኅበራትና ወላጆች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ወይም የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እንቅፋት የሆኑ ክፍተቶችን በመሙላት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞች የመማር ዕድል እንዲያገኙ ማስቻል ግድ ይላቸዋል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዞ እጅግ አበረታች ነው። በተለይም በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ፅህፈት ቤቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እየተመራ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ሲገነባ ቆይቷል።

ከመደመር የመፅሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ በሚደረገው የትምህር ቤቶች ግንባታ እስካሁን ድረስ 34 ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል። በባህርዳር ከተማ በተገነባ ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ ማቋቋሚያ ተቋም 500 ሴተኛ አዳሪዎችን በማሰልጠን በሚፈልጉት የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረግ ህይወታቸው እንዲለወጥ ተደርጓል።

አሁን ደግሞ ትምህርት ቤቶችን መገንባቱ እንዳለ ሆኖ የሚገነባው ትምህርት ቤት አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ስራዎች እየተሰሩ ነው። በተለይም አይነስውራን ያለሃሳብ በተሟላ መሰረተ ልማት የተገነባ ትምህርት ቤት ውስጥ እየኖሩ መማር እንዲችሉ በማሰብ የተገነባው ክብርት ሼይካ ቢንት ሙባረክ የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ተመርቋል። ይህም ትምህርት ቤት በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት መሪነት ከተገነቡ ትምህርት ቤቶች መካከል ነው።

ይህ ትምህርት ቤት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ከ300 በላይ አይነ ስውራን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ምርቃት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ “የምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ሰዎችን እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው። ለከፍተኞች ብቻ ሳይሆን ዝቅተኞችንም ማገልገል እና ማቀፍ ተገቢ ነው በሚል እሳቤ ሁሉንም ያማከለ መሰረተ ልማት እየገነባን ነው።” ብለዋል።

ይህ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ለአይነ ስውራን ምቹ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባ ነው። በውስጡም በርካታ ጥራታቸውን የጠበቁ መኝታዎችን፣ ምቹ መመገቢያ ክፍሎችን እና ሰፋፊ መናፈሻዎችን ያካተተ ነው። ቤተ-መጽሃፉም ለአይነ ስውራን ምቹ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባ ነው። አካል ጉዳተኞችን ያላማከለ ልማት የእውነት ልማት ሊሆን አይችልም እና አሁን የተገነባው የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ለሌሎች ዘርፎችም ምሳሌ የሚሆን ነውና ሊበረታታ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በንግግራቸው ያሉት ይህንኑ ነው። “በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተገንብተዋል። ቀዳዊት እመቤት ፅህፈት ቤት 34 ትምህርት ቤቶችን ገንብቷል። ነገር ግን አንድ የአይነስውራን ትምህርት ባይካተትበት የሙሉ ግማሽ ይሆናል። ግማሹን አካል የዘነጋ ይሆን ነበር” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ ተናግረዋል። በዚህ ረገድም የክብርት ሼይካ ቢንት ሙባረክ የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ለአይነ ስውራን የደረሰ የፍትሃዊነትና የተደራሽነት ማሳያ ሆኖ አቃቂ ክፍለ ከተማ ላይ ተከስቷል።

ቲሻ ልዑል

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You