ጅማ፡- የላቀ ችሎታና እውቀት ኖሯቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች፣ እውቀታቸውን በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ለማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡ ወላጆችና መምህራንም ስለ ሰላም የተገነዘበ፣ የተቃናና የተስተካከለ አመለካከት ያለው ትውልድን የማፍራት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋትና ግጭቶችን አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የተሻለ እውቀትና ችሎታ ኖሯቸው ነው፡፡ ይህ እውቀትና ክህሎታቸው ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ዳብሮ የተሻለ ዜጋ ሆነው መውጣት የሚችሉበትን እድል የሚፈጥርላቸው እንደመሆኑ፤ እነዚህ ተማሪዎች ያላቸውን እውቀት በየዩኒቨርሲቲ ዎቻቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ለማስቻል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ዩኒቨርሲቲዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ማህበረሰብም ለዚሁ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስፈን የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የላቀ እውቀት፣ የላቀ ችሎታ ኖሯቸው ነው፡፡ እናም ይሄንን እውቀትና ችሎታቸውን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የበለጠ ተግተው በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚስተዋሉ ጊዜያዊ ችግሮችንም በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት መዘጋጀት አለባቸው፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ልጆች የቤተሰብ ውጤቶች ናቸው፤ ልጆች የመምህራን ውጤቶች ናቸው፡፡ እናም የተማሪዎች ሃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ስለ ሰላም የተስተካከለና የተቃና እይታ እንዲኖራቸው አድርጎ ኮትኩቶ ማሳደግ፤ ስለ መከባበርና መቻቻልም ግንዛቤ መፍጠር ይጠይቃል፡፡ እናም በዚህ ረገድ ሁሉም የየራሱን ሚና ከተወጣ የተሻለ ትውልድ ይኖረናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ ወጣቶችን የመቅረጽ ሃላፊነት የመምህራን፣ የህብረተሰቡ በጥቅሉ የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻ ስለሆነ፤ በዚህ ረገድ ሁሉም የየራሱን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 1/2011
ወንድወሰን ሽመልስ