የህልውና ስጋት ያንዣበበት ማህበር

አቶ አስተራየ እንየው የሚኖሩት አዲስ አበባ አብነት አካባቢ ነው። የተስፋ ለዓይነ ስውራንና የአካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ማህበር አባል ሲሆኑ የቤተሰብ ኃላፊና የሰባት ልጆች አባትም ናቸው። እይታቸውን ማጣታቸው ወፍራም ስጋጃ ጥንቅቅ አድርጎ ከመስራት አላገዳቸውም።

አቶ አስተራየ ዓይነ ስውራን እና ሌሎች የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከምንጣፍ በተጨማሪ ሌሎች ምርቶችን አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቋቋመው ማህበርን ከተቀላቀሉ አርባ ዓመት ደፍነዋል። ወትሮውም ቢሆን ትንሽ የነበረው ደመወዛቸው አሁን ጭራሹን ቆሟል። እርሳቸው እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ከተከፈላቸው ስድስት ወራት ተቆጥሯል። ‹‹ለምን?›› ቢባል ማህበሩ የሚያመርተውን ምርት የሚገዛው አካል ባለመኖሩ ነው። የግብአት እጥረት መኖርም የማህበሩን ህልውና ካደከሙ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል።

‹‹የኑሮ ውድነቱንና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው በእኛ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል›› የሚሉት አቶ አስተራየ፤ ደመወዝ እንደማይከፈላቸው እያወቁ እንኳን የማህበሩን ደጃፍ መርገጥ እንዳላቆሙ ይናገራሉ። ሥራ ከመፍታት እና ቤት ከመዋል ብለው ያገኙትን ሠርተው ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱም ያስረዳሉ። ‹‹እቤት ላለመዋል ብለን ስንገላታ ውለን ነው ወደ ቤት የምንሄደው፤ ችግር ላይ ወድቀናል›› ሲሉ የደረሰባቸውን ችግር ያስረዳሉ።

እርሳቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት ሁለገብ ባለሙያም ናቸው። አቶ አስተራየም ብሩሽ፣ መጥረጊያ፣ መወልወያ ምንጣፍ እና ሌሎችንም በሚገባ ይሠራሉ። ከአብነት ስድስት ኪሎ ድረስ በመመላለስ ‹‹ነገ የተሻለ ይሆናል፡፡›› በማለት በተስፋ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ ዘወትር ይመላለሳሉ፡፡

አቶ አስተራየ መንግሥት በጀት መድቦ ድጋፍ ቢያደርግ ችግሩን እንደሚያቃልል ይናገራሉ። የሚያመርቱትን ምርት የሚሸጡበት ቦታ እና ሁኔታ ቢያመቻች መልካም እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ግለሰቦች፣ የረድዔት ድርጅቶችና ሌሎችም ምርቶቻቸውን በመግዛት የቻሉትን ያህል ትብብር እንዲያደርጉም ይጠይቃሉ።

ማህበሩ ለአቶ አስተራየ ብዙ ነገራቸው ነው። በቂ የሚባል ገንዘብ ባያገኙበትም ሰው አትርፈውበታል። ከጓደኞቻቸው ጋር ያሻቸውን ተጫውተው ተደስተው እና የሆድ ሆዳቸውን እንዲያወጉ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ይሁንና በአንድ ነገር ቅር መሰኘታቸው አልቀረም። እርሱም ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ነው። በዚህ ችግር ሳቢያ በርካታ ማህበራት ለመዘጋት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ዛሬም ግን አልረፈደም፡፡

‹‹ አይዟችሁ የሚለን የለም። ቢቻል በገንዘብ ካልሆነም በሞራል አይዟችሁ ማለት ራሱ አንድ ድጋፍ ነው። በተጨማሪም የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር እና በቂ ትኩረት በመስጠት አደጋ ላይ ያሉትን ማህበራት መታደግ ይገባል፡፡›› ይላሉ አቶ አስተራየ።

ወይዘሮ አየሁሽ ብላታ እንደ አቶ አስተራየ ዓይነ ስውር ናቸው። ማህበሩን የተቀላቀሉት ገና በአፍላ ዕድሜያቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸውንም ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር ምንጣፍ ሲሰሩ ነበር ያገኘናቸው። የተቀጠሩበት ደመወዝ ክፍያው ትንሽ ቢሆንም ወቅቱ የኑሮ ውድነት ያልፈተነው ወቅት ነበርና በቂያቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። አራት ልጆቻቸውንም በሚገባ አሳድገውበታል፡፡

ዛሬ ግን ማህበሩ ችግር ላይ በመሆኑ ደመወዝ እየከፈላቸው አይደለም። ቤት ከመዋል ብለው በማህበሩ ያገኙትን ሰርተው ወደ ቤታቸው ያቀናሉ። የጥሬ ዕቃ አለመኖር እና የገበያ እጥረት መኖር ማህበሩ ችግር ውስጥ እንዲዘፈቅ ማስገደዱንም አያይዘው ይገልጻሉ፡፡

ወይዘሮ አየሁሽ መንግሥት ቢደርስልን፤ እንዲሁም ድርጅቱ የጥሬ ዕቃ ድጋፍ ቢያገኝ እና በሙያ የሚያግዝ ሰው ቢገኝ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ይገልፃሉ። መጪው ትውልድ ምን ችግር እንደሚገጥመው አይታወቅም ያሉት ወይዘሮዋ፤ ማህበሩ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ሊሆን ይችላልና ሁሉም ለራሱ ሲል የቻለውን ድጋፍ ቢያደርግ መልካም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ ግደይ የተስፋ ለዓይነ ስውራንና የአካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ማኅበሩ የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅና መብታቸውን ለማስከበር ዓላማ ይዞ በ1972 ዓ.ም በድጋሚ ደግሞ በ1992 ዓ.ም ነበር የተቋቋመው። በዚህ ማህበር ዓይነ ሥውራን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ጉዳት ያለባቸውም እንዲካተቱ ተደርጓል። ይህ ማህበር 153 አባላት የነበሩት ሲሆን፤ እንደልብ እየተንቀሳቀሰ ባለመሆኑ ዛሬ ላይ ወደ ድርጅቱ የሚያቀኑ አባላት ቁጥር በእጅጉ እየተመናመነ መጥቷል።

እንደ ምንጣፍ ፣ የተለያዩ የስጋጃ አይነቶች፣ መጥረጊያ፣ ብሩሽ፣ መወልወያ እና ሌሎች ምርቶችን ዓይነ ስውራኑ እና ሌሎች አካል ጉዳት ያላቸው አባላት የአቅማቸውን እንዲሁም የፍላጎታቸውን ያህል እንዳይሠሩ የጥሬ ዕቃ እጥረት እንዲሁም የገበያ ትስስር ትልቅ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። አባላቱ ደመወዝ ከተከፈላቸው አምስት ወራት ማለፉን የሚገልፁት፤ አቶ ዮሐንስ አሁን ላይ ለትራንስፖርት ብቻ ተብሎ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ውጪ ምንም የሚያገኙት ገቢ የለም። እንደውም አንዳንዶቹ አካል ጉዳተኞች ከሥራ ገሸሽ እንዲሉ ተገደዋል።

ከዚህ ቀደም ድጋፎችን ከውጭ ድርጅቶች ፣ ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች ያገኝ ነበር ። አሁን ግን ሁሉም ነገር ቀርቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያሉት አባላት እንዲቆዩ የሄዱትም ዳግም ተሰባስበው ምርቶችን በስፋት ለማምረት ሁሉም በቻለው መጠን ድጋፍ ቢያደርግ የተሻለ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት በኩል የተለያዩ በጎ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሥራው የሚበረታታ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ሞዴል የነበሩ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ዛሬ ላይ ፈተና ውስጥ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ እነርሱን ማጠናከር ይገባል። ‹‹የጎደላቸው ነገር ምንድ ነው?›› ብሎ በመጠየቅ ከመንግሥት በኩል መረዳት እና የገበያ ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል።

አቶ ዮሐንስ እንደሚያስረዱት፣ ችግሩን ለመፍታት በተቻለው መጠን የተለያዩ ባለሙያዎችን እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ በእነርሱ ታግዞ የበለጠ ለመሥራት ታቅዷል። በተለይም ምርቶችን በማስተዋወቅ በኩል ብዙ መሥራት ይገባል። የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለመሥራት ታስቧል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ በትምህርት ብዙም ያልገፉ በመሆናቸው ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው። እንዲህ በሚሆንበት ወቅት ወደ ልመና ለመሄድ ይገደዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ማበረታታት ይኖርበታል። የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለሚተዳደሩ ማህበራትም ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ወይም በቴክኖሎጂ የታገዘ አመራረት እንዲከተሉ ማገዝ ብሎም ድጋፍ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።

እየሩስ ተስፋዬ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You