ንግዳችንን ከሴራ ወደ ስራ

ከጥንት እስከዛሬ የሀገራችን የንግድ እንቅስቃሴ አስመጪዎችና ሻጮች የነገሱበት፣ ከውድድር ይልቅ በድርድርና ከመጠን በላይ ትርፍ መዛቅ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሸማቹን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው ነው። ሶስትና አራት እጥፍ ማትረፍ፤ ማጭበርበር እንደ ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ወይም መብት ተቆጥሮ የሚፈፅም ተግባር ከሆነ ቆይቷል፡፡

ፈጣሪያቸውን ፈርተው፣ ሕዝባቸውን ወደው፣ ስማቸውን አክብረው የሚሰሩ ነጋዴዎች ግን በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ አጭር ነው። በአድማ ወይም በክስረት ከፍ ሲልም በጉልበት ከገበያው እንዲወጡ ይደረጋል። ይህንን ሴራና አሻጥር ብዙ ጊዜ ሰምተነዋል፤ አይተነዋልም።

የሕዝቡ ጨዋነት፣ የመንግስትን ትእግስት ከመጤፍ ያልቆጠሩ ነጋዴዎችም እንደፈለጉ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትና ውጥረት ሲፈጥሩ ነበር። ትንሹ በመካከለኛው፣ መካከለኛው በትልቁ፣ ትልቁ በጠቅላይ አከፋፋዩ ከዚያም በብቸኛ አስመጪው እያሳበቡ ኑሯችን እንደሮኬት አስወነጨፉት። በመንግስት የሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችና ማስተካካዮችም ወደ እሳት እንደገባ ቅቤ ሕዝብ ጋር ሳይደርሱ ሲቀልጡ እየተመለከትን እንገኛለን ።

የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም በተለይም በከተሞች አካባቢ ብዙ ስራዎች ሲሰሩ እናያለን። ከመንግስት ካዝና ብዙ ቢሊዮኖች ፈሰስ መደረጉን እንሰማለን። ነገር ግን የኑሮ ሁኔታው ብዙም መሻሻል ሲታይበት አንመለከተውም። በሂሳብ ትምህርት ብቻ የምናውቃቸውና የምንማራቸው የነበሩ አንዳንድ በተግባር ግን የሌሉ ይመስሉን የነበሩ ቁጥሮች አሁን አሁን በቀላሉ የሚጠሩ የእቃዎች ዋጋ ሆነውም እያገናቸው ነው። የኑሮ ውድነት አልቀመስ ብሏል የሚሉ ድምፆችን መስማት ተለማምደነዋል። ወርሀዊ ደመወዝ የሚያገኝ ሰው ደመወዙን በቀዳዳ ኪስ ያስቀመጠው ያህል እየሆነበት አልበረክት ብሎት ተቸግሯል። የሌላውም ኑሮ እንደዚሁ ምግብ ለስራ ሆኖበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ በቀደመው ጊዜ የበሬ መግዣ በሆነ ብር አሁን ለአንድ ኪሎ ስጋ ሲከፍል ምንም የማይጨንቀው፤ በየስጋ ቤቱ እንደፈለገ የሚሆን እና ዓለም ጠባው የሚቸገር፤ ለራስ ምታት ወደ ዱባይ የሚሄደው ሰው ቁጥር እንደዚሁ ብዙ ነው። በከተማችን የሚነዱትን የተሽከርካሪ አይነትና ብዛት ስንመለከት፣ የሚገነቡ ቤቶችንም ስናይ አንዳችም ችግር የሌለብን ያህል እንመስላለን። እንደዚህ አይነቱ እድገትና የኑሮ ልዩነትን ኢኮኒሚስቶቹ ‹‹ዲስቶርትድ›› ወይም የተበላሸ እያሉ ይጠሩታል። በተለይ የኑሮ ልዩነት መስፋቱ አንድ ቀን ብዙሀኑ ጥቂት ቁጥር ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ እንዲነሳ ያደርጋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን መንግስት ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሌማት ትሩፋት ጀምሮ የሰንበት ገበያዎችን፣ የሸማች ማኅበራትን፣ ምግብ ማጋራትን፣ የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ብዙ ጥረቶች ሲደርግ ይታያል። በርካቶችም ተጠቃሚ እና ተመራጭ ሆነዋል። በተለይ የትምህርት ቤት ምገባ ሚሊዮን ብቁ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን ከማፍራት በዘለለ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና የፈጠረውን የኑሮ ውድነት በማገዝ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ነገር ግን በዚህ መልኩ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ፈሰሶች በተለያየ መንገድ ተመልሰው ሀብታሞችን የበለጠ ሀብታም እንዳያደርጉ ልዩ ጥንቃቄ ይሻሉ። በትክክልና ግልፅ በሆነ መስፈርት ድሀውን ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋም ማድረግ ያስፈልጋል። በእነዚህ ስፍራዎች ላይ የተሰጣቸውን አደራና ኃላፊነት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ኃላፊዎችን በመለየትና በማጣራት በተለየ መልኩ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

እንዲህ ካልሆነ የዜሮ ድምር/“ቪሺየስ ሰርክል” ጉዞ ወይም በቀዳዳ በርሜል ውሃ የመሙላት ያህል የመንግስትንም ጥረት ከንቱ ያደርገዋል። ሕዝቡንም ተስፋ ያስቆርጠዋል። እናም መንግስት ከሚሰራቸው ስራዎች እኩል ቁጥጥሩን በደንብ ሊያጠብቅ ይገባል።

በሌላ በኩል እንደማኅበረሰብ በእኛ ስም የመጣ ድጎማም ይሁን የኑሮ ውድነቱን ለማቃለልና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የተዘየደ መላ አላግባብ ተግባራት እየተከናወኑበት እያየን ዝም ማለት አይገባንም። ዋጋን በማናር ጥቂቶች የማይገባቸውን ቢሊዮኖችን እንዲያገኙ እንደመተባበር ይቆጠራል። የዋጋ መናር የማይመለከተው ሰው ስለማይኖር የኔ ጉዳይ ነው ብለን ልንከላከል ይገባል። እግረመንገዳችንም መብታችንን የማስጠበቅ ባህላችንን እናዳብራለን።

የዓለም ባንክና፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚያወጧቸው ዓመታዊ ሪፖርቶች ውስጥ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው ‹‹ኢንፍሌሽን ሬት›› ዋጋ ንረት የሚሉት ነው። እርግጥ የዋጋ ንረት መገለጫው ብዙ ነው። መኪና የተወደደበት እና ጫማ የተወደደበት እኩል አይደሉም፤ ውስኪ የተወደደበትና ነዳጅ የተወደደበትም እንደዚሁ። ሌላው ቀርቶ ልብስ የተወደደበት እና ዳቦ የተወደደበትም አይነፃፀሩም።

መሰረታዊ ፍላጎት የሚሏቸው ልብስና መጠለያ እንዳሉ ሆነው የመኖርና አለመኖር ጥያቄ የሆነው የምግብ መወደድ ግን ከሁሉም የከፋው እንደሆነ ሪፖርቱ ያትታል። የምግብም ይሁን የሌሎች ነገሮች መወደድ በሁሉም ዓለም በማንኛውም ጊዜ የሚከሰት ቢሆንም ሁልጊዜ ግን ጠንካራ ክንዱን የሚያሳርፈው እያደጉ በሚገኙ ሀገራት ላይ ነው። ሕዝባቸው ብዙ የሆነ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃቸው፣ በውጭ ጣልቃ ገብነትም ሆነ በውስጣዊ ምክንያቶች ግጭቶች በማያጧቸው ሀገራት ደግሞ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡

ሸቀጦች ሲበዛ ገበያው ላይ መወደድ በምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ የተሰሩ ስራዎች አናሳ አሊያም አሻጥር በበዛባቸው መንገዶች የተተበተበ መሆኑን ያመላክታል። በመፍትሄነትም በዘርፉ ላይ ያሉ አሳሪ ችግሮችን በመቅረፍ ምርትን በማሳደግ በቀጥታ ተጠቃሚው ጋር እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል።

በእርግጥ ይህን በአግባቡ የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ያለው ተግባር ለዜጎች ጭንቀት አፋጣኝ ምላሽ የሰጠ ነው። እየተስተዋለ ላለው የኑሮ ውድነት አይነተኛ ችግር ፈቺ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ስራ አስገብቷል። ፕሮጀክቱ ከ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ በጀት ተመድቦለት በመዲናይቱ በሚገኙ በኮልፌ፣ በንፋስ ስልክ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ላይ የግብርና ምርቶችን ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላት ተገንብተዋል። ማዕከላቱም ምርትን በቀጥታ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ እያደረሱ ይገኛሉ።

የኅብረተሰቡን የኑሮ ውድነት በማቃለሉ ረገድ ትልቅ እፎይታን የሚሰጡት እነዚህ የገበያ ማዕከላት የተለያየ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በገበያ ማዕከላቱ እየተገለገሉ ያሉ ሸማቾች መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ፍላጎት አቅርቦቶቻቸው ከመጠን፣ ከጥራትና ከዋጋ አንፃር ተመጣጣኝ መሆናቸውን ሲናገሩ ይሰማል። ማዕከላቱ ከሌሎች የገበያ አካባቢዎች 50 በመቶ ድረስ ዋጋ የሚቀንሱ አቅርቦቶች አሏቸው፡፡

የገበያ ማዕከላቱ የሕብረተሰቡን ኑሮ ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። የተለያዩ ምርቶቻቸውን በብዛትም በጥራትም ለማቅረብ እና ማዕከላቱን የሚያንቀሳቅሱ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሊሟሉላቸው የሚገቡ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዳሉ ይጠቀሳል። ውሃ፣ መብራት፣ የተስተካከለና የተሳለጠ መንገድ ያስፈልጋቸዋል። መብራት ባለመኖሩ አገልግሎት የሚሰጡበት ሰዓት የተገደበ እንዲሆን አድርጎታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ከመቅረፍ አኳያ እየሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም እነዚህ በመዲናችን በሚገኙ አምስት በሮች ላይ የተገነቡት ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላት የተቀላጠፈ ስራ እንዲሰሩ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል።

ለነጋዴውና ለሸማቹ ሕብረተሰብ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ በመንግስት በኩል የተመቻቸባቸው እነዚህ ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ጊዜውን በሚመጥን የቴክኖሎጂ ልኬት ዘመናዊነታቸውን ጠብቀው የተገነቡ ናቸው። በመደበኛ ወይም በባዕላት ቀናት የሚፈለጉ የምግብ ፍጆታዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ በአይነትና በጥራት የሚቀርብባቸው በመሆኑ የኑሮ ውድነት ጫናን እንደሚቀንሱ ጥርጥር የለውም።

የአደጉ ሀገራት መሰል ችግሮችን የሚያስወግዱበት የዳበረ ልምድና ጠንካራ ትከሻ አላቸው። በችግሩ እንደ እስፖንጅ ቢጨመቁም ተመልሰው መፍታታት ይችላሉ። የዳበረ ኢኮኖሚያቸው ብዙ አማራጮችን የመፈለግ ብቃት አለው፣ ቴክኖሎጂያቸው ብዙ መፍትሄን ያመጣላቸዋል፣ ተቋማቶቻቸውም ጠንካራ እና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሸማች ማሕበራትና ዩኒየኖቻቸው በተለየ የሚጠቀስ ስራ አላቸው። ማሕበራት ከማለት ይልቅ ጠበቆች፣ ተከራካሪዎች፣ መከታዎች፣ ቤዛዎች ቢባሉ ይቀላል፡፡

እነዚህ ማሕበራት ባሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ ዋጋ ጣሪያ ነካ፣ ኑሮ ተወደደ፣ ስግብግብ ነጋዴ የነቀዘ ስንዴ፣ ሙሰኛ፣ አሻጥረኛ የሚሉ የሰለቹን ቃላት የሉም። ከመንግስት በላይ መንግስት የሆኑ የሸማቹ መከታ ናቸው። ወይ ገዝተው መልሰው በመሸጥ አሊያም ነጋዴው ላይ ማዕቀብ በመጣል ገበያውን ፀጥ ኑሮውን ቀጥ ያደርጉታል።

በሕዝቡ፣ ከሕዝቡ፣ ለሕዝቡ የተቋቋሙ ናቸውና መነሻቸውም መድረሻቸውም የሕዝብ ጥቅም፣ የገበያ መረጋጋት ብቻ ነው። በዚህም ውጤታማ ናቸው። አሜሪካ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያና ሌሎችም ሀገራት ላይ አሉ።

በሀገራችንም እነዚህ ማሕበራት አሉ። ነገር ግን ገበያውን ማረጋጋት ላይ የሉበትም ማለት ይቻላል። አቅም ይሁን፣ ፍላጎት አልያም ልምድ ብቻ የሆነ ነገር ጎድሏቸዋል። ጥቂቶቹ ብቻ በጥቂት ነገሮች ውጤታማ ሲሆኑ ብዙሃኑ ግን ስማቸው ብቻ ነው የተረፈን። መንግስት እህልን ከአርሶ አደሩ ገዝታችሁ ለሸማቹ አቅርቡ ብሎ ቢፈቅድም፣ ብዙ ነገር ቢያመቻችላቸውም ይህንን ለማድረግ አልፈለጉም፣ ወይም አልቻሉም፣ አልያም ራሳቸው አሻጥሩ ውስጥ ተዘፍቀው የወንጀሉ ዋና ተዋናኝ ሆነዋል።

በጥርና በሀምሌ፣ በጥቅምትና በግንቦት መካከል የዋጋ ልዩነት የለም። ምርቱ ገብቷል በተባለበት ጥር ላይ ያልረከሰ መቼ ሊረክስ ነው? ማህበራት ወዴት ናችሁ እስኪ አቤት በሉ። ዓለም ለሚሳኤል ፅረ ሚሳኤል እንዳዘጋጀች ሁሉ ለማሕበራትም ሌላ ተቆጣጣሪ ማሕበራት ተቋቁመውም ቢሆን እህሉን ያቅርቡልን!

ለነገሩ አናቀርብም ቢሉ እንኳ መንግስት የንግድ ምህዳሩን በማስፋት የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡበት የወሰነው ውሳኔ መፍትሄ ይዞ መጥቷል። ውሳኔው ንግዳችንን ከሴራ ወደ ስራ፣ ከፉክክር ወደ ድርድር፣ ከነጋዴ ነጋሲነት ወደ ሸማች ንጉስነት ይለውጠዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

እነዚህ ታላለቅ ኩባንያዎች ለስማቸው ይጠነቀቃሉና፤ ቢያንስ ጥራት የጎደለው እቃ አምጥተው በገዛ ገንዘባችን በሽታ አያሸምቱንም ብለን እናምናለን። ለስራ ባህላችን መነቃቃትን፣ ለወጣቶቻችን የስራ እድልን፣ ንግድ ማለት ዘረፋ ለሚመስላቸው ብዙዎቹ ነጋዴዎቻችን የትርፍ ህዳግን፣ ለሚያመናጭቁን የደንበኛ አያያዝን ያስተምሩልናል።

በጥራትም፣ በአቅርቦትም፣ በመስተንግዶም የምንረካበት የንግድ ስርዓት እንዲመጣና የተመኘነው ምኞት እንዲሰምርልን መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ያፀደቀውን ውሳኔ በፍጥነት ወደ ተግባር ሊለውጠው ይገባል። ይህ ሲሆን የለም፣ ጠፍቷል፣ ተወዷል፣ ጨምሯል የሚሉ ከስግብግብነት ባህሪ የሚመነጩ ቃላት ከመስማት ማረፍ እንችላለን። ይሄ የሁሉም ችግራችን ብቸኛ መፍትሄ ባይሆንም ቢያንስ የጥጋብ ፊኛን የሚያስተነፍስ፣ የሟሸሸ ሸማችን የሚያንቀሳቅስ ተስፋ ነውና መንግስት ሆይ ፍጠን!

 አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You