በቅርቡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት“ ማንይጠየቅ?” በሚል ርዕስ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የአሠራር ጥሰቶችን የሚያስመለክት የምርመራ ዘገባ ሠርቷል። የዘጋቢ ፊልሙ ማጠንጠኛ በዩኒቨርሲቲው የተፈጸመን የሕግ ፣ የአሠራር ጥሰትን እና የሙስና ድርጊትን ይመለከታል። ዩኒቨርሲቲው የተማረ ዜጋ የሚፈራበት ተቋም ከመሆን ይልቅ ግለሰቦች ሀብት የሚያፈሩበት ወደመሆን እንደተሸጋገረ ያስመለክተናል።
ኢትዮጵያ ለሙስና ወንጀሎች ያላት ተጋላጭነት በየጊዜው እየጨመረ እንደመጣ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል። ከሁሉም በላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እጅጉን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱም አብሮ ይነሳል። ይህ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ላይ የተሠራው ዘጋቢ ፊልም ብዙ ነገሮችን በግልጽ እንድንመለከት አድርጎናል ማለት ይቻላል።
በዩኒቨርሲቲው የሕዝብና የመንግሥት ሀብትና ንብረት ከሚመዘበርበት መንገድ አንዱ የአበል ጣሪያን በማብዛት የሚፈጸም ክፍያ አንዱ ነው። በተቋሙ በወንበር ላይ የሚገኙ አመራሮች ከሕግ ውጪ የተጋነነ አበል እየወሰዱ ስለመሆናቸው ለመታዘብ ተችሏል ። ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ቡድን መሪ የሆኑ ሁለት ግለሰቦች በስድስት ወራት ብቻ የሁለት ሺህ 430 ቀን ወደ አንድ ሺህ 490 ቀን ማለትም ከአንድ ሚሊዮን 600 ሺህ ብር በላይ አበል እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
ሌላው አስደንጋጩ መረጃ ከ1 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በዩኒቨርሲቲው እየተሠራ ያለው የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከል የመስሪያ ገንዘብ ከፋይናንስ እውቅና እና ከሕግ ውጪ ሲንቀሳቀስ ነበር። የግንባታው ሥራ የተሰጠው ድርጅትም በኮንስትራክሽን ዘርፍ እውቅና የሌለው ስለመሆኑ በምርመራ ዘገባው ተመላክቷል። በአንድ ተቋም ብቻ በዚህ ደረጃ የሕዝብና የመንግሥትን ሀብት ሲመዘበር ማየት ልብን ያደማል።
ይህ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ቅሌት በሀገራችን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸም የሙስና ወንጀል ወደ አሳሳቢነት ደረጃ እየተንደረደረ እንደሆነ እንደመስታወት ያስመለክተናል። በየዓመቱ የሚቀርቡ የበጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ውጤቶችም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሆነ የበጀት ምዝበራና ብክነት የሚፈጸምባቸው ቀዳሚ ተቋማት መሆናቸውን ያሳያሉ።
ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ እውቀትን ከመልካም ሥነ ምግባራዊ ቁመና ጋር ያዋሃደ ወጣት ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ቁልፉና አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል። በሥነ – ምግባር የታነፀ ትውልድ አስተምረው በማስመረቅ ሀገር ከድህነት ቀንበር እንዲያወጡ ይጠበቃል። መንግሥትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ዘርፉን ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ ለገንዘብ ምዝበራው እንደ ዋነኛ መደላድል ሆነው እያገለገሉ ነው።
የማህበረሰብን ችግር ይፈታሉ ተብለው ሲጠበቁ የጥቂት ግለሰቦች የሀብት ምንጭ ሲሆኑ ታዝበናል።የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱን በአካባቢያዊነት ፣ በዘመድ አዝማድ የሚፈጸመው ቅጥር ፤ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎቹን ወደ ሌብነት መንደርነት አውርዷቸዋል። በተቋማቱ ተጠያቂነት ያለ እስከማይመስል ድረስ የሕዝብ ሀብት ያለአግባብ እየባከነ እና እየተበዘበዘ ይገኛል። ጥቂት በማይባሉ የመንግሥት ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ የኦዲት ሪፖርቶች ይሄንኑ የሚጠቁሙ ናቸው።
እንደ ማሳያ በኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት እርምጃ ያልወሰደበት ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጀት ጉድለት መኖሩን፣ ማስተካከያ የተደረገበት የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ እንደማይሆን ከመጠቆም ውጪ ተጠያቂ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ኢምንት ነው ። ይህ አይነቱ አካሄድ በተቋማቱ ችግሩ እንዲባባስ፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በማናለብኝነት እንዲዘረፍ ትልቅ ምክንያት ሆኗል ለማለት ያስደፍራል።
በመንግሥት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እንዳሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፤ በተለያዩ መድረኮች ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት ማዕከሎች ፣ የብዙ ደሃ ሕዝብ ሀብት የሚፈስባቸው ቦታዎች ናቸው። ከምንም ነገር በላይ የዚህ ሕዝብ ሀብት የሆነ ተቋም በሌብነት እና በሙሰኝነት የተጨማለቀ አስተዳደር ሊኖረው እንደማይገባ ሲናገሩ ይደመጣል።
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አመራረጥ በሚመለከት አዲስ መመሪያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነ፤ ከዚህ ባሻገር የገንዘብ ሚኒስቴር ሦስት ጊዜ መጥፎ የተባለ ኦዲት ካለው ዩኒቨርሲቲውን የሚመሩ ሰዎች ከቦታቸው እንደሚነሱ ፤ በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታም ካለ በሕግ እንደሚጠየቁ ሲናገሩም ተሰምተዋል።
በመንግሥት ደረጃ ችግሩን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ቢሆንም፤ በየዓመቱ የሚወጣው የኦዲት ሪፖርት ግን የሕጉን ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። የሀገርን ሁለንተናዊ ቁመና ይበይናሉ ተብለው ተስፋ የሚደረግባቸው ዩኒቨርሲቲዎቻችን፤ በዚህን መጠን ወደሚገለጽ የዝቅጠት ደረጃ መግባታቸው በተቋማቱ ዙሪያ ያለውን የቤት ሥራ ክብደት የሚያመላክት ነው።
አሁን ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚታዩት ብልሹ አሰራሮችን በፍጥነት መንገድ ለማስያዝ ካልተሞከረና እና ልጓም ካልተበጀላቸው ችግሩን መልክ ለማስያዝ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በተቋማቱ በሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተጠያቂነት መስፈን አለበት ።
ሪፖርቶችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሌቦቹንም ወደ ተጠያቂነቱ ማምጣት ይገባል ። በዋናው ኦዲተር ሪፖርት የበጀት ብክነት ያስከተለ ምዝበራ ስለመፈጸማቸው የሚያመለክቱ መረጃና ማስረጃ የቀረበባቸውን የዩኒቨርሲቲዎቹ ባለድርሻ አካላት ሕግ ፊት በማቅረብ ለጥፋታቸው የሚመጥን ቅጣት እንዲሰጣቸው የማድረግ ጉዳይ ይዋል ይደር የሚባል አይደለም።
“ እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ ብትቀጪኝ ፤ በሬ አልሰርቅም ….” እንዳለው በየተቋማቱ ያሉ ሌቦች ነገ በሬ ከመስረቃቸው በፊት ዛሬ በእንቁላሉ ጊዜ ቆንጠጥ ማድረግ ይገባል። መንግሥትም ሕግን ማስከበር ሕዝብ አደራ የሰጠው የውዴታ ግዴታው ነው። በየ ተቋማቱ የምዝበራ መሪ ተዋንያን የሆኑትን አካላት ለሕግ በማቅረብ የተጠያቂነት አሠራር መኖሩን ወይም አለመኖሩን ለሕዝቡ ማረጋገጥ ጭምር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።
ስለሆነም መንግሥት ከታሪክ ተወቃሽነት የሚያድነውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ፤ ተቋማቱን ለሀገር አለኝታ የሆነ ቁመና እንዲላበሱ ማድረግ ይገባል። በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ኦዲተር መስሪያ ቤት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን አስተዳደራዊ ንቅዘት ይፋ በማውጣት ረገድ በየጊዜው የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
በአጠቃላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገሪቱን ከሚፈታተኗት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እንዲሁም የማህበራዊ ችግር መገለጫ ድክመቶች መፍትሔ እንዲያመጡ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን አጠቃላይ ቁመና ለስማቸው በሚመጥን አስተዳደራዊ ብቃትና የመልካም ሥነ ምግባር እሴት ላይ እንዳልሆነ መናገር ያስደፍራል።
አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሙሰኞች መፈንጫ በመሆን፤ ለሀገር እድገት ሳይሆን ስጋትን እየፈጠሩ ናቸው። ስለዚህ በአብዛኛዎቹ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ክፉኛ የተባባሰውን የሞራል ኪሳራና የሥነ-ምግባር ዝቅጠት በቅጡ የመፈተሽ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል!!
ዳንሮባ ከባሌ ጎባ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም