አንድን ታሪክ የጽሑፌ መግቢያ አድርጌያለሁ። ታሪኩም እንዲህ ነው። ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ፤ ጓደኛሞቹ በጣም የሚዋደዱና አብረውም በበረሀ መሄድ ያዘወትራሉ። ከዕለታት አንድ ቀን ይጋጩና አንደኛው ሌላኛው ላይ መሳሪያ ደግኖ እንዲህ ይለዋል። ምን ታመጣለህ? እዚሁ ብደፋህ! ሰው የለም፤ ማን ደምህን ያወጣዋል? ይለዋል።
ጓደኛው መቼም እግዚአብሔርና መንግሥት ደሜን ያወጡታል ይለዋል። ከዚያ ብዙ ነገር አብረው ያሳለፉትን ጓደኛውን እስቲ እንደሚያወጡልህ አያለሁ ብሎት ተኩሶ ይገለውና እዚያው ቀብሮት ይሄዳል።
ሰውዬው እንኳን ሰው ትንኝ የገደለ ሳይመስለው ዓመታት ተቆጠሩ። ከብዙ ዓመት በኋላ በዚያው በበረሃው መንገድ ይሄዳል። ገዳዩ ነገሩን ረስቶታል። ምክንያቱም ማንም አላየም፤ አልሰማም ብሎ ነበር የሚያስበው። ይህ ሰው አንድ በጣም ያፈራና ፍሬዎቹ ደስ የሚሉ የብርቱካን ዛፍ ያያል።
ይህማ ቆንጆ ነገር ለንጉስ ይገባል፤ ብሎ ብርቱካኑን ለቅሞ በስልቻ በማድረግ ይዞ ወደ ንጉሱ ቤት ይሄዳል። ከዚያም ጠባቂዎችን ለንጉስ የሚገባ ስጦታ ይዤ መጥቼያለሁ አስገቡኝ ይላቸዋል። ጠባቂዎችም አይሆንም ዞር በል ይሉታል። ከዚያም አስተዛዝኖ ሲለምናቸው፤ ጠባቂዎቹ ለንጉሱ ነገሩ። ንጉስ ሆይ! አንድ ሰውዬ ለእርስዎ ስጦታ አለኝ ይላል፤ እርስዎ ዘንድ መግባት ይፈልጋል ብለው ጠየቁ።
ንጉሱም፤ ‹‹ምን ጥጋበኛው ነው ለእኔ የሚሰጥ ብለው አስቲ አስገቡት›› አሉ። ከዚያ ጠባቂዎቹ በግራና በቀኝ በመሆን ይዘውት ገቡ። ሲገቡም ንጉሱ ደጅ ላይ ቁጭ ብለዋል።
ጌታዬ ለእርስዎ የሚገባ ስጦታ ይዤ መጥቼያለሁ ይላቸዋል። እስቲ በል እዚያው ሜዳ ላይ እንየው ይሉታል። ከዚያ የተሸከመውን መሬት ላይ ሲዘረግፈው የያዘው ብርቱካን ሳይሆን የሰው እጅ፣ እግር፣ ጭንቅላት፣ …የሚመስሉ ነገሮች ሆነ።
ሰውዬውም አልጠበቀም ነበር። ንጉሱም ደነገጡ። በሉ ይኸ ሰውዬ አንዳች የሰራው ነገር አለ፤ ጓሮ ወስዳችሁ ጠይቁት ብለው ጠባቂዎቹን አዘዙ። ጠባቂዎቹም እንደታዘዙት ሰውዬውን በተባለው ቦታ ወስደው ምን የሰራኸው ነገር አለ? ብለው ሲጠይቁት የነበረውን ታሪክ ተናገረ።
የገዛ ጓደኛዬን በረሀ ውስጥ ስንሄድ፤ መሳሪያ ደቅኜበት፤ እገልሀለሁ፤ ማነው ደምህን የሚመልሰው? ስለው መንግሥትና እግዚአብሔር ናቸው አለኝ። እኔም በትዕቢት እስኪ እንደሚመልሱልህ አያለሁ ብዬ ገድዬ ቀብሬው ነበር በማለት ተናገረ።
ጠባቂዎቹም ይኽንኑ ተመልሰው ለንጉሱ ነገሩት። ንጉሱም በሰውዬው ኑዛዜ መሠረት የእኛን ምረነዋል፤ ግን የእግዚአብሔርን አንምርም›› በማለት ሰውዬው እንዲገደል አዘዙ ይላል ታሪኩ።
እንግዲህ ተረቱ አስተማሪ ነው። ጥፋት ስንሰራ ሰው እንኳ ባያየን ፈጣሪ ያየናል ለማለት ነው። ንጉሱ ምድራዊውን መንግሥትም ሆነ የሰማዩን መንግሥት ማክበርና መፍራት ያስፈልጋል ብሎ የሚያምን ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየቀኑ በርካታ የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ከፖሊስ እና ከሌሎች የሕግ አካላት መረጃዎች እየተረዳን ነው። የወንጀሎቹ አይነትም በርካታ ነው፤ ከተራ ወንጀል እስከ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ይፈጸማል። አንዳንድ ወንጀል ፈጻሚዎች ወዲያው ሊያዙ የሚችሉበት ሁኔታ ቢኖርም አንዳንዶቹን ግን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ሲወስድ ይስተዋላል። እንዲያም ሆኖ በፖሊስና በኅብረተሰቡ ያላሰለሰ ጥረት የሚያዙበት ሁኔታ አለ። አንዳንዶች ግን የማይያዙበት ሁኔታ ያጋጥማል። አንዳንዶቹ ደግሞ ቆይቶም ቢሆን ቀን ይጥላቸውና በቁጥጥር ስር ይውላሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ ተደጋጋሚ ወንጀል ተብለው በፖሊስ ከሚገለፁት መካከል ጥቂቶችን እናውሳ። አንደኛው ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም እና ሀሰተኛ የሐኪም ማስረጃ በመያዝ ገንዘብ መሰብሰብ ነው። ይህም ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት ማሳያ ሲሆን፤ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚደረግ ኢ- ሞራላዊ ድርጊት ነው።
ሌላኛው የተሽከርካሪ ስርቆት ነው። ተሽከርካሪ ከቆመበት ይሰረቃል። የራይድ አሽከርካሪዎችን በማደናገር እና አግባብ ባልሆነ አቅጣጫ በመውሰድ እስከ ግድያ የሚደርስ ጉዳት ማድረስና ተሽርካሪውን መውሰድ ነው። ይህ ወንጀል ተሽከርካሪ በመውሰድ ብቻ አያቆምም። ተሽከርካሪውን ሌላ ወንጀል ይሰሩበታል። እነዚህ በተደጋጋሚ እየተመዘገቡ ካሉ የወንጀል ድርጊቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽን እየሆነ የመጣው ጉዳይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎችን መፈጸምና በማጭበርበር የግለሰቦችን ገንዘብ መስረቅ ነው። ለእዚህ ማስረጃ ይሆን ዘንድ በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተፈጸመውን ዘረፋ ማስታወስ በቂ ይሆናል። ሰሞኑንም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በተደጋጋሚ ጥንቃቄ አድርጉ የሚሉ አጫጭር መልዕክቶችን በእጅ ስልካችን ላይ ሲልክ ነበር። ይህም በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች
ምን ያህል አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ያመላክታል።
የሞባይል ንጥቂያ እንደ ወንጀል እየታየ አይደለም፤ ሞባይል በተደጋጋሚ ያልተሰረቀ የለም። ሌቦቹ እጅ ለእጅ ተይዘው እያለም እርምጃ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። አንድ ሞባይል የሰረቀ ሌባ ሲያዝና ኪሱ ሲበረበር አራት አምስት ሞባይሎች ይዞ የሚገኝበት ሁኔታ ስለመኖሩ ይሰማል። አንድ የሞባይል ሌባ ተይዞ ያለው ታወሰኝ። ይህ እኮ ዛሬ አራተኛዬ ነው ነበር ያለው።
የሞባይል ስርቆት ተለምዷል። የተሰረቀ ሞባይል ማግኘት እየተቻለ አይደለም፤ ሰዎች የተሰረቁትን ሞባይል ከማፈላለግ ይልቅ ስለመግዛት ነው የሚያስቡት። የጠፋ ሞባይል እንዳይገኝ ታውቋል። በሞባይል ስርቆት በእጅጉ የሚታወቁ ቦታዎች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ አይነቱ ስርቆት እንዲቆም ለማድረግ የሚደረግ ጥረት አለ ብዬም አልወስድም። በዚህ የተነሳም ይመስለኛል ወንጀሉ በእጅጉ እየተስፋፋ የመጣው።
የሕግ የበላይነትን ማስከበር የየትኛውም ሀገር ተቀዳሚ ተግባር እንደ ሆነ ይታወቃል፤ ይህ ሲሆን ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ሀገርን እንደ ሀገር ህልውናዋን አስጠብቆ ለማስቀጠል ይቻላል። ወንጀለኞች በፈጸሙት ወንጀል ልክ ለሌሎችም አስተማሪ ሊሆን በሚችል መልኩ፣ በተፈጸመው ወንጀል የተጎዱ ቤተሰቦችን ሊያጽናና በሚችል መልኩ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ይህ በአግባቡ እየተደረገ ነው ብለን ብንጠይቅ በአግባቡ አይደለም ነው መልሱ። የወንጀለኞች መበራከት፣ የወንጀል ድርጊቶች በተደጋጋሚ መፈጸም ሲታሰብ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ አይደለም ወደሚል መደምደሚያ ቢደረስ አይደንቅም።
በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየተበራከቱ፤ ተሽከርካሪን ያህል ቁስ ተሰርቆ የውሃ ሽታ ሆኖ እየቀረ፣ ተሽከርካሪ ለመስረቅ በሚል አሽከርካሪው በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደለ ያለበት ሁኔታ በጣም ሲደጋገም ቀደም ሲል ተመሳሳይ ወንጀል ፈጽመው ለሕግ በቀረቡ ወንጀለኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ አስተማሪ ነበር ለማለት አያሰኝም።
ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ለወንጀለኞች መራራትን ምን አመጣው ብሎ መጠየቅ ይገባል። ዜጎችን ኅብረተሰቡን አልፎም ተርፎ የሀገር ገጽታን በእጅጉ ያበላሹ ወንጀለኞችን ቀለል ባለ እርምጃ ማለፍ የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል። ቀላል እርምጃ መውሰድ ወይም በቂ መረጃ የለም በሚል ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰድ ወንጀለኞቹ የበለጠ ተጠናክረው በድርጊቱ እንዲቀጥሉ፣ ምናልባትም ሌሎችንም አይዟችሁ ብለው ወደ ድርጊቱ እንዲገቡ አያደርግም ተብሎ አይታሰብም።
እርምጃዎች ጨከን፤ ጫን ያሉ መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲህ አይነቶቹ የወንጀል ድርጊቶች ተፈጽመው ሲገኙ በወንጀለኞች ላይ በቃ ‹‹የእኛን ምረነዋል፤ ግን የእግዚአብሔርን አንምርም›› የሚል ጠንካራ አቋም መያዝ ይገባል።
ይህ ካልሆነ ግን ስሙንና አይነቱን እየቀያየረ የሚመጣውን የወንጀል ድርጊት መቆጣጠር አይቻልም፤ ኅብረተሰቡንም ሀገሪቱንም ከወንጀለኞች መጠበቅ ከእስከ አሁኑም በላይ የበለጠ አዳጋች እየሆነ ይመጣል የሚል ስጋት አለኝ።
የሕግ የበላይነት ከሌለ በትንሹ ሕዝብ እንደ ልብ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ይጠፋል፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ የሚኖረው እምነትም እየተሸረሸረ ይሄዳል። የሕግ የበላይነት እንዲጠበቅ የጠንካራ የፍትህ ተቋማት መኖር ወሳኝ ነው። ይህ ብቻውን ግን የትም አያደርስም። ተቋማቱ ጠንካራ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የሚችሉ መሆን አለባቸው። በተለይ ግላዊ በሆኑ ምክንያቶች ጠንካራ ውሳኔዎች የማይተላለፉ ከሆነ ችግሩ እየሰፋ ሄዶ የማህበረሰብ ጠንቅ እስከ መሆን ይደርሳል።
መኪና የሰረቀ፣ ይህ አንሶት ባለመኪናውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለ፣ በተደጋጋሚ ሞባይል ስልክ የሰረቀ፣ ብዙ ገንዘብ ሰርቶ ሊውል የሚችል መኪና ተኮናትሮ፣ ብዙ ሰውም አሰልፎ በሀሰተኛ የሕክምና መረጃ ገንዘብ ሲሰበስብ የተገኘ ሰውና ቡድን ላይ ምንም አይነት መለሳለስ መኖር የለበትም። ጠንካራ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ያ ሲሆን ነው ወንጀሉ እንዳይደጋገም፣ ጨርሶ እንዳይፈጸምም ማድረግ የሚቻለው።
ቆይቶም ቢሆን ተጠያቂነት ሊመጣ እንደሚችልም መገንዘብም ይገባል። በሕጉ ላይ የተቀመጠውን እርምጃ መውሰድ ራስንም ከተጠያቂነት ያወጣል። ከዚህ ሲያልፍም የሞራል ግዴታን መወጣትም ይገባል።
የሕግ የበላይነት አስፈላጊነት የሰው ልጅ፣ ማህበረሰቡ በሰላም እንዲኖር፣ ሕጉ ተጥሶ ሲገኝ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጸም ለማድረግ ወይም ሊፈጸም የሚችልበትን እድል ለማጥበብ ነው፤ ይህ ሊሆን የሚችለው በሥርዓትና ደንብ መዳኘት ሲኖር ነው።
ቅጣት የሚያቀሉ የሚያከብዱ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህን ማየት ችግር የለውም፤ የሕጉን መሠረት መሳት ግን አይገባም። በመሆኑም በመሰል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ እና ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴትን የሚፋልሱ አካላት ላይ እርምጃ ሲወሰድ ‹‹የእኛን ምረነዋል፤ ግን የእግዚአብሔርን አንምርም›› ማለት ተገቢ ይመስለኛል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም