የፖለቲካ ፓርቲዎች መመስረት አልፋና ኦሜጋ የሀገር ህልውና ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምስረታቸው ጀምሮ እስከ ስልጣን ድረስ ያሰቡትን አላማ ማሳካት የሚችሉት ሰላም ሲረጋገጥ እና የሀገር ህልውና ሲቀጥል ነው። ሰላም በሌለበት ፓርቲም ሆነ የፓርቲ ፖለቲካ አይታሰብም።
ሆኖም በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ተጀመረ ተብሎ ከሚታሰብበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ ከሀገር ይልቅ የራስን ጥቅም፣ክሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፣ከሀገር ህልውና የፓርቲ ህልውናን ማስቀደም ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ላልተገባ እሰጥ እገባና ግጭት አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትዘልቅ አድርጓታል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው። ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው። አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው። በጋራ ሠርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን በመፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ የፖለቲካ ታሪካችን ነው።
ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህልም ስለሌለን ችግሮች ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የሴረኝነት መነሻ ይሆናሉ። ቀላል የሚባሉ ችግሮች ሳይፈቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወሳሰቡ ስለሚሄዱ መፍትሔ ለመስጠት እንኳን አዳጋች እስከመሆን ይደርሳሉ።
በተለይም በርካቶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠራ አላማ ሳይኖራቸው በስሜት እና በግብታዊነት የፖለቲካ ምህዳሩን ስለሚቀላቀሉ በሂደት ማጣፊያው ሲያጥራቸው ይታያሉ። ድክመታቸውን ለመሸፋፈን ብሔርን ሽፋን አድርገው ጥላቻን ሲዘሩ መታየት አንዱ የፖለቲካ ባህላችን ስንክሳር ነው።
በብሔር ስም በየቦታው የሚቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቆሜለታለሁ ለሚሉት ወገን ፋይዳ ያለው ነገር ከመሥራት ይልቅ በተገላቢጦሹ ችግርና መከራ ሲቀፈቅፉ ማየት የተለመደ ነው። በእነሱ ምክንያት ንፁኃን ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና ሲሰደዱ ማየትም ያለፉት 50 ዓመታት የፖለቲካ ታሪካችን መጥፎ ዐሻራ ነው። በዚህም ምክንያት በፓርቲ ስም የሀገርና የሕዝብ ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ ወድቆ ቆይቷል።
ግላዊ ጥቅምን አስቀድመው የሚነሱት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈልጉትን ዓላማ ማሳካት የሚችሉት መጀመሪያ ሀገር ስትኖር መሆኑን ማመን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከራስ ፍላጎትና ከፓርቲ ህልውና የበለጠ ሀገራዊ ማንነት እና ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል። ልዩነታቸውን በተቻለ መጠን አቻችለው ለሀገር ሰላምና እድገት በጋራ መሥራትም ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ራስን ለውይይት፣ ለድርድርና ለመተማመን ማዘጋጀት የተሻለ ነው። ለሀገር ሰላም የሚበጀውም ይኸው ነው።
አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ለዚህ ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ነው። ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል። ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፣ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው።
ስለዚህም በዚህ ታሪካዊ የምክክር መድረክ መሳተፍ አዲስ ታሪክ የመጻፍ ያህል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር አንሳተፍም የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከግል ስሜትና ፍላጎት በመውጣት ኢትዮጵያን በምክክርና በውይይት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ዳር ተመልካች ሆኖ መተቸትና ማጥላላት ሀገርን ወደ አዘቅት ከመክተት በስተቀር ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚፈይደው አንዳችም ቁም ነገር አይኖርም።
አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው። ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል። በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንን ወደ መነጋገር፣መተባበርና መደጋገፍ መምጣት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ለዘመናት ሲንከባበሉ የመጡ ችግሮቻችን ይፈታሉ፤የጦርነት ታሪካችን ይዘጋል፤ሰላም ይሰፍናል፤ኢትዮጵያም የበለጸገችና የታፈረች ትሆናለች!
አዲስ ዘመን ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም