አዲስ አበባ፡- ብዝኃነትን የሚያከብር ትውልድ ለማፍራት በትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መርሕ የሚከበረውን 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በሚገኙ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች መሐከል የጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ልዩነት መቀበልና ማክበር የሚችሉ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጸኑ ሆነው እንዲያድጉ በትምህርት ቤቶች ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው፣ ስለ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትና መልካም ሥነምግባር ያላቸውን ግንዛቤ የሚፈትሽ የጥያቄና መልስ ውድድር በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ ሲካሄድ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ውድድሩ ተማሪዎች ስለ ኅብረብሔራዊነት ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድር በበኩላቸው፤ የሀገር ፍቅር ያለውና ብዝኃነትን አውቆ የሚያከብር ትውልድ ለማፍራት ተማሪዎች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል። በትምህርት ቤቶች በየጊዜው የሚካሄዱ መሰል መርሐ ግብሮች ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው ያላቸው ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል ብለዋል።
ኅዳር 29 ሀገሪቷ ብዝኃነቶች የሚያስተናግድ ኅብረብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓት የፀደቀበት፤ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በእኩልነት የሚያከብሩት በዓል መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም እንደሀገር መግባባት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል ።
በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ ባሕልና እሴት ያላቸው ናቸው ያሉት አፈ ጉባዔዋ፤ ሁሉንም በእኩልነት መልማት ያስፈልጋል፤ ለዚህም አንዱ የአንዱን ቋንቋ፣ ባሕል እና እሴት ማክበር ይኖርበታል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታትም እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፖሊሲ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አውስተው፤ የሀገር ፍቅር ያለውና ብዝኃነትን አውቆ የሚያከብር ትውልድ እንዲፈራም ተማሪዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ውድድሩ ከትናንት በስቲያ በከተማ አቀፍ ደረጃ የተጠናቀቀ ሲሆን ተማሪዎች ስለ ኅብረብሔራዊነት ያላቸው ግንዛቤ እንዲያዳብሩ የሚያግዛቸው መሆኑ ተገልጿል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም