በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ:- በአፍሪካ የቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡናን ምርታማነት፣ ጥራትና የገበያ ተደራሽነት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቆሙ ።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ድርጅት 64ኛ ዓመት ስብሰባውን በስካይ ላይት ሆቴል ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ ዘላቂ እና ጥራት ያለው የቡና ምርት በማምረት የአፍሪካን የቡና የወጪ ንግድ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በተለይ በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር የዓለም አቀፍ ገበያ ዕድሎችን ማስፋት ይገባል፡፡

ለአፍሪካ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተጨማሪ ዕድሎችን ለመፍጠር እሴት መጨመር ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካ ቡና ከእርሻ እስከ ገበያ ያሉበትን የእሴት ሰንሰለት ተግዳሮቶች በመለየት መፍታት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡናን ምርታማነት፣ ጥራትና የገበያ ተደራሽነት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዋጋ ተለዋዋጭነት እና የቁጥጥር ማዕቀፎችንና መሰል የወደፊት ተግዳሮቶች እንገነዘባለን ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ጠቁመው፤ ይህም በአዳዲስ ምርምሮች፣ በኢንቨስትመንቶችና ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡናን ምርታማነት፣ ጥራትና የገበያ ተደራሽነት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቡና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ላይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች ነው፡፡ በዚህም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች ብለዋል።

ዘላቂ እና ጥራት ያለው ምርትን በማረጋገጥ የአፍሪካን የቡና ኤክስፖርት ለማሳደግ የተቀናጀ እና ግልፅ ተግባራት አስፈላጊ ናቸው ያሉት አዱኛ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ የቡና ምርት አሁንም ከፍተኛ የኤክስፖርት የገቢ ምንጭ መሆኑን አመልክተዋል ።

ግብርና የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የኤክስፖርት ገቢ በማስገኘት በአሕጉራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዘርፉን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በአፍሪካ ቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ስብሰባውም ቡና አምራች አገሮች በዘርፉ የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች ለመፍታትና ያሉትን ዕድሎች ለመጠቀም አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ የቡና አቅርቦት ሠንሠለትና የደን አያያዝን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ ይህም የኤክስፖርት አቅምን እና የንግድ ዕድሎችን እንደሚጨምር አብራርተዋል። የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ዕድገት ለማሳካት በመንግሥት እና በግሉ ሴክተሮች መካከል ትብብርን እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You