አዲስ አበባ፡- የጤና መድኅን ምዝገባዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መጀመሩን የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ገለጸ።
ዘንድሮ ከአንዳንድ በሲስተም ከማይገናኙ ወረዳዎች በስተቀር ሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቆመ።
በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው ሞቲ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የጤና መድኅን ምዝገባዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ተጀምሯል። በዚህም አንድ የጤና መድኅን አባል ከየትኛውም አካባቢ ሲመዘገብ ሙሉ መረጃው እስከ ዋና መሥሪያ ቤት ድረስ እንዲመጣ የማድረግና ከሆስፒታሎች ጋር የሚተሳሰርበትን አሠራር የሚፈጠርበት ነው።
ከተጀመረባቸው አካባቢዎች ቦረና ዞንና አዲስ አበባ ከተማን እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ቦረና ዞን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጅታል ሥርዓት (ሲስተም) የማስገባት ሥራ እንደተከናወነ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ወደ ዌብሳይት መቀየሩን ጠቁመው፤ ዘንድሮ ከአንዳንድ በሲስተም ከማይገናኙ ወረዳዎች በስተቀር ሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ እንደሚገቡም አመላክተዋል።
እንደእርሳቸው ገለፃ በ2016 በጀት ዓመት የጤና መድኅን ተጠቃሚውን ማኅበረሰብ ወደ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጋ ማድረስ ተችሏል። በ2017 በጀት ዓመትም ደግሞ ይህን ቁጥር በ10 በመቶ ለመጨመር ታቅዷል።
በመዋጮን በተመለከተም በ2016 በጀት ዓመት ከኅብረተሰቡ የተሰበሰበው 12 ቢሊዮን እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንንም 10 በመቶ ለመጨመር መታቀዱን ገልፀዋል።
የመዋጮ አሰባሰባችን በየወረዳው የተበታተነ ሲሆን አቅም አይኖረውም ያሉት ሥራ አስፈፃሚው በዞንና በክልል ደረጃ ከፍ አርገን በመሰብሰብ ወደ ጋራ ቋት ለማምጣት እየሠራን ነው ብለዋል። ዞኖች በዞን ደረጃ፣ ክልሎች ደግሞ በክልል ደረጃ ቋት እንዲመሠርቱ ለማድረግ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በዚህ ዓመት ለየት ያለ የመዋጮ አሰባሰብ እንደሚኖር ገልፀው፤ ኅብረተሰቡ በየአቅሙ እንዲከፍል የሚያስችል ሦስት ደረጃ እንደተቀመጠ ጠቅሰዋል። ዝቅተኛው የከፍያ መጠን 720 መሆኑንና ይህን የሚከፍሉት የመክፈል አቅማቸው ዝቅ ያለ ዜጎች በመሆናቸው ወጪውን መንግሥት እንደሚሸፍን ገልፀዋል።
በሁለተኛ ደረጃ አንድ ሺህ 200 አካባቢ እንደሚከፍል እንዲሁም ከፍተኛው በገጠር አንድ ሺህ 730 በከተማ አንድ ሺህ 750 መሆኑንም አብራርተዋል። ይህም እንደየገቢ ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ የጤና መድኅን ጠቀሜታን ተረድቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ አስተማማኝ ሠላም የሌለባቸው የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች ጭምር አፈፃፀሙ ጥሩ መሆኑን አንስተዋል። ባለፈው በጀት ዓመትም በኦሮሚያ ክልል 90 በመቶ በአማራ ክልል ደግሞ 65 በመቶ አፈፃፀም እንደተመዘገበም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል በሰሜኑ ጦርነቱ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰው፤ አገልግሎቱን በ2016 ዓ.ም ማስጀመራቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን አብዛኛው በክልሉ የሚገኝ ማኅበረሰብ የገቢ ሁኔታ ዝቅተኛ ከመሆኑ አኳያ ወጪቸው በመንግሥት ወይስ በአጋር ድርጅቶች ይሸፈን በሚለው ዙሪያ እየተወያዩ እንዳሉ አስረድተዋል።
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም