የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ንግዱን ያነቃቃው ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ

ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ‘ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ 2024’ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ የንግድ አውደ ርዕይ ማካሄዷ ይታወቃል። ለአምስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚሁ አውደ ርዕይ ላይ እንደተገለፀው፤ አውደ ርዕዩ የሃገር ውስጥ ግንባታ እና መሰረተ ልማት ችግሮችንና መፍትሄዎችን ማመላከት እንዲሁም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን አንድ በማድረግ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገትን፣ ተግዳሮቶችን እና እድሎችን እንዲገነዘቡ የማድረግ ዓላማ አለው። የኢንዱስትሪውን አቅም ለመገንዘብ የዲዛይንና ግንባታ እንዲሁም የግንባታ ጥገና እና ፋሲሊቲ አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ውሳኔ ሰጪዎች ሃሳቦችን ማሰባሰብንም ያለመ ነው።

ከግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2016 በተካሄደው በዚሁ አውደ ርዕይ ላይ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የግንባታ አገልግሎቶችና የስማርት ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ቀርበውበታል። በመድረኩ 156 ዓለም አቀፍ እና ሃገር በቀል ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 115ቱ ዓለም አቀፍ ፣ 41ዱ ደግሞ ሃገር በቀል መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣም ዓውደ ርዕዩን አጠቃላይ እንቅስቀሴ ምልከታ ያደረገ ሲሆን፣ በዓውደ ርዕዩ የተሳተፉ አካላትንም አነጋግሯል። ተሳታፊዎቹ አንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት የቢግ 5 አውደ ርእዮች ከተለያዩ ሀገሮች ጋር በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚካሄዱ ግንኙነቶች እያደጉ እንዲመጡ አስችሏል።

አቶ ታሪኩ ተክሉ ከርቢ ስቲል ስትራክቸር የተባለ ድርጅትን ወክለው ነው በአውደ ርእዩ የተሳተፉት። ድርጅታቸው በዋናነት የሚያመርተው ተገጣጣሚ ህንፃ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ለመገንባት እና ለመጋዘን፤ ለሞል፤ ለመጋዘን /ዌር ሃውስ/ና ለፋብሪካዎች መስሪያ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ። የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ዱባይ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥም እነዚህን ምርቶች በማቅረብ ከ16 ዓመታት በላይ ይታወቃል። በዋናነትም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጀምሮ ከ600 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ለሃገር እድገት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ቢግ ፋይፍ ከተጀመረ አንስቶ በአምስቱም ዓውደ ርዕዮች ላይ ድርጅታቸው መሳተፉን አቶ ተክሉ ይናገራሉ። ድርጅታቸው በግንባታው ዓለም ትልቅ ስም ያለው ቢሆንም፣ በዓውደ ርዕዩ ላይ መሳተፉ ተጨማሪ የገበያ እድሎችን ለማግኘትና ደንበኞችን ለማፍራት እያገዘ ነው ይላሉ። ‹‹ባለፉት አምስት ዓውደ ርዕዮች ላይ መሳተፋችን ይበልጥ እንድንታወቅና ገበያችንንም ለማስፋፋት ጠቅሞናል›› ሲሉም ነው ያስታወቁት።

በተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማወቅም እድል እንደተፈጠረለት ተናግረው፤ ድርጅቱ ባለው ምርት ላይ ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ አሻሽሎ በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን መነሳሳት የፈጠረለት መሆኑንም ያስረዳሉ። ዘንድሮ ደግሞ ከሌላው ጊዜ በተለየ ትልልቅ እና በዘርፉ የካበተ ተሞክሮና አቅም ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሳተፋቸውን አመልክተው፣ ይህም የበለጠ የልምድና የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠር እንዳስቻለው ይናገራሉ። ከብዙዎቹ ጋርም ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ከኮቪድ መከሰት ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መቀዛቀዙ የእቃ አቅራቢ ነጋዴዎችም የንግድ እንቅስቃሴ ተዳክሞ እንዲቆይ አርጎታል። ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ ትላልቅ ሃገር አቀፍ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን ተከትሎ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ሥራ መልሶ እያንሰራራ መምጣቱ የእነሱም የንግድ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ተመልሷል። ከዚህ ባሻገር ደግሞ እንዲህ አይነት ትላልቅ ዓለምአቀፍ አውደርዕዮች እየተስፋፉ በመምጣታቸው የሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ሃገራት ጋር የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እየጎለበተ መጥቷል።

በንግድ አውደ ርዕዩ ላይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሳተፋቸው በሃገሪቱ ያለውን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢ ለማየት እድል እንደሚሰጥ ተናግረው፣ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የገፅታ ግንባታ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም አቶ ታሪኩ ያስገነዝባሉ።

የሃገር ውስጥ የንግዱ ዘርፍ ተዋናዮችም ያንን በሚመጥን መልኩ ራሳቸውን ማዘጋጀትና ማዘመን ይገባቸዋል ሲሉም ይናገራሉ። በሌላ በኩል በአውደ ርዕዩ ላይ የተገኙ ጎብኚዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ የመግዛት አቅሙ ግን ውስን መሆኑን አስታውቀዋል፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር እንደሚያያዝ ገልጸዋል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የእቃዎች ዋጋ የናረበት ሁኔታ መታየቱን ጠቁመዋል።

የሚመለከተው አካል ዘርፉን ለሚያንቀሳቅሱ አካላት የተለየ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልከተዋል። ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የኮንስትራክሽን ዘርፍ የማደግ ተስፋ እንዳለው ጠቅሰው፣ ካለው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በአካባቢዎቹ በሚፈለገው ልክ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያዳግታል ብለዋል። ዘርፉ እንደሃገር እንዲያድግና ሃገርም በዛው ልክ እንድትበለፅግ ለማድረግ የፀጥታው ችግር እንዲፈታ ሁሉም መረባረብ አንዳለበት አስታውቀዋል።

ወይዘሪት ሌሊሴ ወርቅነህ ደግሞ ኢንጪኒ ሜንቴናስ ኢንጅነሪንግን ወክላ ነው በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፈችው። ሌሊሲ እንደምትናገረው፤ ድርጅታቸው በዋናነት ስካፍሆልዲንግ የተባሉ ለሕንፃ ግንባታና የማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) ሥራዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ መሳሪያዎችን እያመረተ ይሸጣል፤ ያከራያል፤ የዲናሞና መሰል ማሽኖች ጥገና ሥራዎችንም ይሰራል።

ድርጅታቸው በአውደ ርዕዩ ላይ ሲሳተፍ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁማ፤ በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎችን እንዲሁም የላቀና የረቀቀ የኮንስትራክሽን ዘርፉ መሳሪያዎችን ከሚያመርቱ ስም ያላቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ የመስራት እድል እንደተፈጠረላቸው ታስረዳለች። ያለምንም ወጪና ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ እዚሁ ድረስ በዘርፉ ትልቅ ደረጃ ከደረሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ልምድ መቅሰም መቻላቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ታብራራለች። ‹‹ትራንስፖርት ሳናወጣና ሌላ ሃገር መሄድ ሳይጠበቅብን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማግኘትና ልምድ ለመቅሰም አስችሎናል›› ትላለች።

በእነዚህ ሶስት ዓመታት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻላቸውን ተናግራ፤ ወደፊትም ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ትገልፃለች። መንግስት መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለትና ሶስት ጊዜ በማዘጋጀት ዘርፉ ይበልጥ እንዲጎለብት እንዲያደርግ ነው ወይዘሪት ሌሊሴ ያስገነዘበችው።

አቶ ጆባኒ ባፍራንቾኒ ቫልፒንት የተባለ የጣሊያን ቅንጡ ቤቶች ቀለም አምራች ኩባንያ አስተባባሪ ናቸው። አንኮላ በተሰኘ የጣሊያን ከተማ ውስጥ ያለው ድርጅቱ በተለይም ውድና ዘመነኛ የሆኑ ቀለሞችን በማምረትና በተለያዩ ዲዛይን ቅቦቹ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ይታወቃል።

‹‹ምርቶቻችንን በዋናነት ቅንጡ ሆቴሎችና ሪልስቴቶች ናቸው የሚጠቀሙት›› የሚሉት አቶ ጆባኒ ፣ ድርጅቱ በተለይ በአውሮፓ ገበያ ከፍ ያለ ስም እንዳለው ያስረዳሉ። ቢግ ፋይፍ የኮንስትራክሽን ባዛር ላይ ሲሳተፍ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜው መሆኑን ጠቅሰው፤ በእነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆንዋ የአፍሪካን ገበያ ለመቀላቀል ሰፊ እድል እንደተፈጠረላት ያብራራሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥራት ያለውን ምርት ያውቃል፤ ይመርጣልም›› የሚሉት አቶ ጆቫኒ፣ በመጀመሪያው የባዛሩ ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ ነገር መታየቱን ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ከተለያዩ ሃገራት ከመጡ ተሳታፊዎች ጋር በመቀራረብ ቀጣይነት ያለው የንግድ ትስስር ለመፍጠርም ሆነ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዳስቻላቸው ያመለክታሉ። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዘርፉ ተዋናዮች የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ለማወቅም ሆነ ሽግግር ለማድረግ ያግዛል የሚል እምነት አላቸው።

‹‹እርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ታዲጊ በሆኑ ሃገራት ላይ መሰራትም ሆነ የንግድ ልውውጥ ማድረግ ከመሰረተ ልማትም ሆነ ከውስብስብ አሰራር ጋር ተያይዞ ፈታኝ ነው፤ በተለይ የጉምሩክ አሰራሩ ምቹ ካለመሆኑ የተነሳ የውጭ ኩባንያዎች በስፋት ዘልቀው ለመግባት ብዙ አይጋብዛቸውም›› ይላሉ።

በመሆኑም የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመጋበዝም ሆነ ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስሩ እንዲያድግ ከተፈለገ እንደ ኬኒያና ኡጋንዳ ካሉ ሃገራት ተሞክሮ በመውሰድ የጉምሩክ አሰራሩን ማሻሻል ወሳኝ እንደሆነም ያስገነዝባሉ። ‹‹በጎረቤት ሃገራት መዋለንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚመጡ የውጭ ባለሃብቶች የተለየ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል፤ በኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ዘርፍ እንደመሆኑ ለተዋናዮቹ ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል›› ብለዋል።

አቶ ጆቫኒ እንደሚሉት፤ ከውጭ በርካሽ ገንዘብ የተገዛ ማንኛውም ቁስ እዚህ ሲመጣ የሚጣልበት ቀረጥ ከተገዛበት ዋጋ በብዙ እጥፍ ከሆነ በተለይ በወጭ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች አያበረታታም። በሌላ በኩል አስመጪው ቀረጡ በጨመረበት ቁጥር ተጠቃሚው ላይ ያልተገባ ዋጋ የሚጭንበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ጥቂት የማይባሉ አስመጪ ድርጅቶች ቀረጡን ስለሚፈሩ ብቻ በዝቅተኛ ዋጋ ጥራቱ በጣም የወረደ እቃ የሚያስገቡበት ሁኔታ ይስተዋላል።.

አሰራሩ ከተሻሻለ ከውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ በተለይ ለቀጠናው ሃገራት ማዕከል እንደሆነች ጠቅሰው፣ ኩባንያው ያለውን የንግድ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ማቀዱን ያስረዳሉ። ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መንግስትም በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚታየውን ማነቆ እንዲፈታ ጠይቀዋል።

አባይ ቀለም ፋብሪካም በዓአለም አቀፍ የንግድ አውደ ርዕዩ ላይ ከተሳተፉ ድርጅቶች አንዱ ነው። በድርጅቱ በሽያጭ ሰራተኝነት ላይ የምትሰራው ወይዘሪት ቤተልሄም አለኸኝ እንደምትለው፤ ፋብሪካው የብረት፤ የእንጨት፤ የመኪና፤ የመስታወት፣ ለስነ ጥበብ ሥራዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ዘመኑን የሚዋጁ ቀለሞችንና ኮርቲዞችን ያመርታል። በተጨማሪም ባክቴሪያ የሚከላከል ለሆስፒታሎች የሚያገለግል ቀለምም በማምረት ለተጠቃሚዎች ያቀርባል።

‹‹ድርጅታችን ቢግ ፋይፍ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄድ ከጀመረ አንስቶ በመሳተፍ ብቻ ሳይሆን አጋርም በመሆን የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል›› የምትለው ወይዘሪት ቤተልሄም፤ እነዚህ ዓመታት በአውደ ርዕዮ ላይ የተሳተፉ የተለያየ አይነት ባህሪና አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን የማግኘት እድል ገጥሞታል›› ትላለች። ይህም በዚያው ልክ የንግድ ዕይታውንም ሆነ መዳረሻውን እንዲያሰፋ አድርጎታል ባይ ነች።

የእነሱ ድርጅት በአውደ ርዕዩ ላይ የሚያቀርባቸውን ምርቶች የተመለከቱ ብዙዎቹ የውጭ ድርጅቶችም ሆነ ከውጭ የሚያስመጡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተዋናዮች ምርቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታሉ ብለው እንዳልገመቱም ጠቅሳ፣ አብረው ለመስራት ፍላጎት ያሳዩበት ሁኔታ እንዳለም ታስረዳለች።

‹‹በተለይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከተለያዩ ሃገራት ያስገቡ የነበሩ ኮንትራክተሮችና የአርክቴክቸር ሰዎች አብረውን ለመስራትም ሆነ ምርቶቻችንን ለማግኘት ፍላጎት አሳድረዋል›› ስትል ትገልፃለች። መሰል አውደ ርዕዮች መዘጋጀታቸው አምራች፤ አቅራቢና ሸማችን ለማገናኘት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ በመሆናቸው በላቀ ሁኔታ ሊስፋፉና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገነዘባለች።

አውደ ርእዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተጎብኝቷል።

ማህሌት አብዱል

 አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You