ስለሰላም…

በሰላም ስለሰላም መነጋገርና መፍትሄ ማምጣት ምናልባትም ዘመናዊነትና ስልጣኔ ከተሸከፈባቸው ሽክፎች መሀል ዋነኛው ነው። ከዚህ ወግ በመነሳት ለሰው ልጅ መሰረታዊና እጅግ አስፈላጊ ሆነው ከተቀመጡ እውነታዎች መሀል ሰላም አንዱ ነው፤ ሰላም እሞግታለው።

ፈጣሪ ሕይወትን ሲፈጥር አብሮ ሰላምን ፈጥሯል። የሕይወትና የሰላም ቁርኝት እንደልደትና ሞት ያለ ክስተት ነው። ሰው ሕይወቱን በዋጋና በፍሬ፣ በራዕይና በጸጋ ለመኖር ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገዋል። ያለሰላም በተፈጥሮ በኩል የተቀበልናቸውም ሆኑ ከዓለም የወሰድናቸው ጸጋዎቻችን አይጠቅሙንም።

እንደ ሰላም ያሉ አንዳንድ ነገሮች በዚህ ምድር ላይ ያለእኩያና አቻ ብቻቸውን የተፈጠሩ ናቸው። ከሄዱ የማይመለሱ ካመለጡ የማይተኩ ናቸው። ሄደው ቢመለሱ እንኳን በበቀልና በጥላቻ ቆሽሸው፣ በእልህና በቁጣ ጨቅይተው ነው። በሀገራችን እየሆነ ያለው የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የትውልድ መቃቃር፣ የሕዝብ መፈራራት ትላንት ላይ ባመለጠን ሰላምና ሲመለስ በቀልና ጥላቻን ይዞ በተመለሰ ሰላም ነው።

ሰላምን አጥብቆ መያዝ አብሮነትን ማስቀጠል፣ ለጋራ ታሪክ፣ ለጋራ እሴት ዋጋ መስጠት ነው። የሚመጣውን ካለው ጋር አስተሳስሮ በኢትዮጵያዊነት ወግ ማዕረግ ማስቀጠል ነው። እንደሀገር ለመቀጠልና ከእኔነት ተላቆ ትውልዱን በኢትዮጵያዊነት ለማድመቅ ያለን አንድ አማራጭ ሰላም መር አስተሳሰብን መፍጠር ነው።

እንደ ሀገር ብዙ ችግሮችን ወርሰን የምንገዛገዝ ህዝቦች ነን። እንደማህበረሰብ ይዘናቸው የምንጓዛቸው ልምዶቻችን ስለሰላም ተግዳሮት የበዛባቸው ናቸው። በርግጥ ስለ ሰላም ብዙ በሚባልበት ሀገር ውስጥ ሰላም ዋንኛ ጥያቄ መሆኑ ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው።

ይህን ሀገራዊ ችግር ለመሻገር ትውልዱ ከአድማጭነት ወደተናጋሪነት መመለስ አለበት። ብዙዎች የፈለጉትን እየነገሩን እውነት ነው ብለን ስንቀበል የነበረው ማኅበራዊ ልምምድ ለምን? በሚል ምክንያት አዘል መጠይቅ መቀየር አለበት። ሰሚ ብቻ ሳንሆን እውነትን መርማሪ፣ ዋጋ ላለው ነገር ቅድሚያ ሰጪዎች ልንሆን ይገባል። ስለሰላም ዝም የማንል፣ ስለሀገር ግድ የሚለን፣ ስለትውልዱ የሚቆጨን ሆነን በአዲስ አእምሮና ልብ መሰራት መጪውን ግዜ መልካም የማድረጊያ ፍኖታችን ነው።

ለምንድነው ሰላም ያጣነው? ለምንድነው ለማንም በማይበጅ የወንድማማቾች ግፊያ ዋጋ እየከፈልን ያለነው? በእርቅና በምክክር መከራችንን መሻገር ለምን ተሳነን? የጋራ እሴቶቻችንና ማኅበራዊ ትውፊቶቻችን ለምን በምናምንቴ ተለወሱ? በብሄር ተቧድነን ኢትዮጶያዊነትን መከለል ምን ትርፍ ይሰጠናል? በላቀ ሀሳብ፣ በበላጭ እውነት ሰላማችንን መመለስስ ለምን አቃተን? በአንድ ሀገርና በአንድ ታሪክ ስር የብኩርና ግፊያ ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው? እኚህ ጥያቄዎች ለነበርንበትና ላለንበት ሀገራዊ ውጥንቅጥ መልስ የሚሰጡን መጪውንም ለመቃኘት እድል የሚሰጡን ናቸው።

መጠየቅ ካልቻልን መልሱ ላይ አልደረስንበትም። ትልቁ ችግራችን ተናጋሪና አድማጭ ሆነን መኖራችን ነው። ምንነቱን ሳናውቅ የጥቂቶች የዓላማ አስፈጻሚዎች ሆነን ቆይተናል። በራሳችን ላይ ካራና ሾተል አንስተን መታረጃችንን ስንስል፣ መውደቂያችንን ስንቆፍር ነበር። ስለሰላም መመካከር አቅቶን ዓላማችንን በጦርነት ለማሳካት ስንሞክር ግማሽ ክፍለ ዘመን ተሻግረናል። ስለአንድነት የጋራ መርህ ሳናበጅ ከብሄር ሽኩቻ ሳንወጣ በብዙ ዋጋ መክፈል ውስጥ ሰንብተናል።

ያቺ የሰላም እናት፣ ያቺ የፍቅር ክበድ፣ ያቺ ሰላምን አምጣ ለዓለም መከረኞች መጽናኛ የሰጠች ሀገር ዛሬ ሰላም አጥታ ወንድም ከወንድሙ ተሰጋግቶ የሚኖርባት፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ የሆነባት ሆናለች። ለምን ብንል ብዙ የምንለው አለ። እኔ ግን ለእርቅና ለምክክር ወገቡን ያሰረ ፖለቲከኛ ስለጠፋ፣ ለጊዜያዊ ጥቅም በለኮሱት እሳት ፍቅርም ጥላቻም የትውልድ ውርሶች ሆነዋል።

እንደ እውነቱና ሚዛን እንደሚደፋው ሀቃችን ከሆነ ውርሳችን ፍቅር ነበር። ውርሳችን አብሮነትና ወንድማማችነት ነበር። ከአባቶቻችን የወረስነው፣ ካለፈው የተቀበልነው ብዙ የኢትዮጵያዊነትና የአብሮነት ውርስ ነበርን። ከዛ ወደዚህ በመጣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ስርዐትና ማንነት ውስጥ ነበርን። ስልጥንና ይሁን ስይጥንና ባይታወቅም ወርቃችንን በፋንድያ ቀይረን፣ ሰላማችንን በጦርነት መንዝረን እዬዬ ባዮች ሆነናል። ይሄ በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ ላይ የመጨረሻው የሰብዐዊነት ዝቅጠትና የታላቅ ሀገር አሁናዊ ውርደት ነው።

መነሻውን የረሳ ትውልድ ምን መድረሻ ይኖረዋል? መጀመሪያውን የዘነጋ ፖለቲካ ምን በጎ ፍጻሜ አለው? እንደ ሀገር መነሻችን ኢትዮጵያዊነት ነበር። እንደ ትውልድ መጀመሪያችን ትስስብና ትቅቅፍ ነበር። በአንድነት ዳብረን፣ በኢትዮጵያዊነት ተሸልመን ከዛ ወደዚህ ስንመጣ በጋራ ታሪክና በጋራ እውነት ነበር። አሁን ላይ ወይበናል። ደማቅ ጸዳሎቻችን የብሄር ረኸጥ ጠብ ተደርጎባቸው ወይበዋል። አሁን ያለውን የእኔ እበልጥ እኔ ፖለቲካና የብሄር እሽቅድምድም በአንድ ቃል ብገልጸው በመርዝ እንደተለወሰ ዳቦ ነው።

ዳቦው በሕይወት ለመኖር ይጠቅመናል እንዳንበላው ግን መርዝ አለበት። እንዳንተወው ደግሞ ርሀብ ውስጥ ነን። በመኖርና ባለመኖር መሀል ያለ ሕላዊ ማለት እንዲያ ነው። የሀገራችንም ነባራዊ ሁኔታ እንደዛ ነው። በውስጧ የዘረኝነት፣ የእልህ፣ የጦርነት መርዝን ታቅፋ እንዳንኖርባት ስጋትን እንዳንተዋት እናት ሀገር ሆናብናለች። ዳቦውን ለመመገብ ሁለት አማራጭ ብቻ አለን።

መጀመሪያው መርዙን ከዳቦው ውስጥ ማውጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መርዙን የሚሽር መድሃኒት መፍጠር ነው። በሀገርም ላይ እንዲሁ ነው..ትውልዱን ለመታደግ የሀገር መርዝ ሆነው በእያንዳንዳችን መሀል የተሰገሰጉትን እንደብሄር፣ እንደጎጠኝነት፣ እንደ እልህና ይዋጣልን ያሉ አስተሳሰቦችን ማስወገድ አሊያም በምክክር መርዙን ማብረሻ የእርቅና የአብሮነት መላ መዘየድ ይኖርብናል።

እንዲህ ካልሆነ ሁሉም ነገር ውስብስብና አስቸጋሪ ነው። ብሔራዊ የእርቅና የምክክር መድረክ ብለን ስናወራ መነሻችን ይሄ እውነታ ነው። በበላጭ ሀሳብ በመካከላችን ያሉ ያለመግባባት ጽንሶችን ማስወረድ፣ የጦርነት ሽሎችን ማጨንገፍ ተቀዳሚ ሚናው ነው። ያለሕዝብ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክክር አቅመቢስ ነው።

ሰላሞቻችን ከእኛ መንጭተው ለእኛ የሚፈሱ የበረከት ወንዞቻችን ናቸው። ከእኛ ያልመጣ የትኛውም ነገር አያሽረንም። ሰላም ፈላጊዎች ነን ስለሰላም እንምከር ብለን በመንግስትም ሆነ በሌላ አካል በኩል ጥያቄ ሲነሳ ወደማንም የምንቀስረው ጣት የለንም። እኔ ስለን ከራሳችን ጀምረን በራሳችን የምንጨርሰው ነው።

በጋራ ሀሳብ ካልሆነ ሰላም እንዳይደረስ ሆኖ የተሸሸገ ነው። ለራሳችን አንሰን አናውቅም። በወንድማማችነት ስም ለብቻችን ተራምደን የወጣናቸው የበዙ አቀበቶች አሉ። በእኛ ካልሆኑ በማንም ያልተቻሉ የታሪክ ፋና ወጊዎች እኛንና ኢትዮጵያዊነትን ለብሰው ዛሬም ድረስ በክብር እየተጠሩ በዓለም አደባባይ አሉ። አቀበቱ የከበደን ለብቻችን ለመሻገር ስለተነሳን ነው። ሰላም የራቀን፣ ከእዬዬ ያልወጣነው አብሮነትን ሽረን በእኔነት ስለተጠመድን ነው።

መፍትሄው..ለገዘፈች ሀገር የሚመጥን የገዘፈ የሀሳብ መድረክ ማዘጋጀት፣ በዛ መድረክ ሁሉም ተናጋሪ፣ ሁሉም የመፍትሄ ሰው ሆኖ ስለሰላሙ ጠጠር ማዋጣት፣ ከጥላቻ ውርስ ወደፍቅር ውርስ የሚያሸጋገር የእርቅና የይቅርታ ድልድይ መገንባት፣ ድልድዩ በማንም መቼም የማይሰበር የኢትዮጵያዊነት አሻራ የታተመበት እንዲሆን፣ ብሔርና ዘረኝነት መልካቸው ወይቦ ሕብረብሄራዊነት እንዲያብብ ሁሉም በኃላፊነት እንዲቆም፣ ፖለቲካው በምክክር በእንዲሽር፣ ፖለቲከኞቻችን በውይይት እንዲታከሙ ማድረግ።

ትውልዱ ከመገፋፋት ወደተመተቃቀፍ እንዲመጣ ኢትዮጵያዊነትን ማስጠናት፣ በጠባቦች የጠበበውን የፖለቲካ ምህዳር ለኢትዮጵያዊነት እንዲመጥን በሀሳብ ማስፋት፣ ከጦርነት በፊት እርቅ በሚል መርህ ዋጋ መክፈልን የሚያስቀር የመነጋገር ባሕልን ማዳበር፣ ልጆች በቤተሰባቸው፣ በትምህርት ቤት ስለግብረገብነት እንዲያውቁ፣ ሰላም በዘር በቡዳኔ ሳይሆን በአብሮነት ቡዳኔ እንደሚመጣ መረዳት፣ ፖለቲከኞቻችን ከጥላቻ ስብከት ወደእርቅ ስብከት እንዲመለሱ፣ ወጣቱ ለእኩይ ዓላማ ከመሰለፍ ለአንድነት ዋጋ መክፈልን እንዲያውቅ በማድረግ ሰላማችንን መመለስ መቻል።

የጥላቻ ውርስ የደም ውርስ ነው። የቂም በቀል፣ የሰጣ ገባ ውርስ ነው። ይሄን ለበርካታ ጊዜ ኖረንበት አበባችንን ከማጠውለግና ፍሬአችንን ከማርገፍ ባለፈ ሀገራዊ ልምላሜ አልሰጠንም። እናም አቅጣጫ መቀየር ግድ በሚለን ጊዜ ላይ ነን። ስለፍቅር በምንዘምርበት፣ ስለኢትዮጵያዊነት በምንቧደንበት ጊዜ ላይ ነን። ጦርነት በቃን ስንል ስለሰላም ዋጋ የምንከፍልበት፣ ስለወንድማማችነት የምናወጋበት ዘመን ላይ ነን።

ለግጭትና ለጦርነት በተመቸ ስነልቦና ውስጥ ሰንብተናል። ይሄ አይነቱ ልምምድ ደግሞ ወትሮም በድህነት ስሟን ላላደሰችው ሀገራችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ ነው። ስለሰላም ዋጋ መክፈል እንጂ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ግንዛቤና ልምምድ ሀገር አይሰጠንም። እርቅና ፍቅር የመከናነባቸው ሀሳቦቻችን ጦርነትን እየወለዱ የነበረውን ከመሻር ባለፈ ባለው ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ መጪውን እንድንፈራ ሲያደርጉን እናውቃለን።

በመሸ ሰማይ ላይ ከዋክብት አጥተን፣ በገዘፈ ታሪክ ውስጥ አብሮነትን ገፍተን ጫፍ በሌለው ውንብድና ከወደቅን ሰነባብተናል። ስለፍቅር ዝም ብለን፣ ስለአብሮነት ተለጉመን ለክፉዎች ድንጋይ ስናቀብል ነበር። እኚህ ሁሉ ግን አልበጁንም። ስለፍቅር አፋችንን ከፍተን፣ ስለኢትዮጵያዊነት ልባችንን አስፍተን ለእርቅ፣ ቀመጥ አለብን።

ስልጣኔና ስይጥንና ሁለት መልክ ቢኖራቸው አንዱ ለሰላም ዋጋ መክፈል ሌላው ደግሞ ለጦርነት ዋጋ መክፈል ይሆናሉ። ከዚህ ውጪ በምንም ቢገለጹ ልክ አይመጡም። በማያሻማ መልኩ ጎራችን ከየት በኩል እንደሆነ አይጠፋንም። ለጦርነት ዋጋ ከፋዮች ሆነን የሰላምን መንገድ ዘግተን በራሳችን ላይ መከራን ስናውጅ ነበር።

ሰው ሀገርና ትውልድ በሰላም በኩል የሚያንጸባረቁ ጸሀዮች ናቸው። ጦርነት ደግሞ ይሄን ጸሀይ የሚሰውር የሞት ጥላ ነው። ለእኛም ሆነ ለመጪው ስንል ለሰላም ዋጋ በመክፈል ሀገራችንን ከመከራ መታደግ ይገባናል።

ሰላም የሰው ልጅ በተፈጥሮ በኩል የተሰጠው ተፈጥሮአዊ መልኩ ሲሆን እንደጦርነት ያሉ የመከራ መብቀያዎች ደግሞ ከአለም የቃረምናቸው የትዕቢት፣ የእልህ፣ የማንአለብኝነት፣ የራስወዳድነት፣ የእኔነት፣ ያለመነጋገር፣ ያለመደማመጥ፣ ያለመስከን፣ ያለመብሰል ነጸብራቆች ናቸው። ታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ ‹ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ› ብሎ ሲያዘን ሰላም ከህይወት ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት እየነገረን ነው።

ሰላም እኩያና አቻ የለውም። ሰው በፈጣሪ በኩል ለልዕለሰቡ የተሰጠው የሕይወት ስጦታው ነው። ልክ እንደሰው ሁሉ ዓለምም ከሰላም ውጪ ሁሉን አጥታ መኖር እንድትችል አቅም አላት። ምግብ መጠለያና ልብስ በሰው አምሳል ለተፈጠረ ለየትኛውም ፍጠር አስፈላጊ ሆነው በሳይንስ ሲረጋገጡ መነሻቸው ሰላም መሆኑ ሳይረሳ ነው።

የትኛውም ውብ ነገር፣ የትኛውም ውድ ነገር ሰላም በሌለበት የማይረባ ነው። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የትኛውም አስፈላጊና ጠቃሚ ነገር ርካሽ ነው። ፍቅርና አብሮነት በሌለበት ሁኔታ የትኛውም ምድራዊ እድል መርገምት ነው። ብዙ ኖሮን ያላተረፍነው ለምን ሆነና? እልፍ ተሰጥቶን ያረካነው በምን ሆነና?

ሀገር እንደሰላም የክብር ዘውድ የላትም። ትውልድ እንደአብሮነት ሸጋ ሽርጥ የለውም። እንደአንገት ላይ አልቦና ድሪ ሰላም የሀገርና ውበት የሕዝብ አሸክታብ ነው። በምንም ይጠራ፣ የቱንም ያክል በሕይወት ውስጥ ያለነገር ሁሉ በሰላም ስም ያማረ ነው። በጦርነት መታወቅና በሰላም መታውቅ እንደስልጥንናና ስይጥንና ሁለት የተራራቁ ማንነቶች ናቸው። ስለሰላም ዝም አልልም የሚል መንግስት፣ የሚል ፖለቲከኛ፣ የሚል ትውልድ ማፍራት አሁን ያሉብንን የወገንተኝነት እሳቤዎች የምናጸዳበት፣ ሀገራችንን ከዝቅታ የምንታደግበት እጅግ ምርጡ አማራጫችን ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You