
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀጣይ ዓመት ለሚያከብረው 60ኛ ዓመት በማስመልከት ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ መጽሐፍት በማሰባሰብ ለቤተ መጽሐፍት ሊያበረክት መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ 24ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀው የመጽሐፍት ዓውደ ርዕይና የፓናል ውይይቶች ማጠቃለያ ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በ2017 ዓ.ም ለሚያከብረው 60ኛ ዓመቱ ስድስት ሺህ መጻሕፍት ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የማሰባሰብ ሥራ ይጀምራል።
የኢቢሲ ስጦታ ተብሎ የሚሰበሰቡትን መጽሐፍት በክልሎችና አዲስ አበባ በሚገኙ ቤተ-መጻሕፍት እንዲሁም የኮንደሚኒየም ቤቶች ላይ በሚገኙ የንባብ ማዕከላት ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን አመላክተዋል፡፡
ታዳጊና ወጣቶች ክረምቱን እንዲያነቡ ዕድል ለመፍጠር መላው የድርጅቱ መገናኛ ብዙኃን አድማጭና ተመልካች መጽሐፍትን በማሰባሰብ ሂደት አብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ሬድዮ ጣቢያ ለሌሎች ሚዲያዎች አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢቢሲ የዕውቀትና የመረጃ ቤት እንደመሆኑ ለሀገር ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሆነ ታዳጊዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ታቅዶ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ አምስት የቴሌቪዥን ቻናሎችና ሦስት የሬድዮ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፤እነዚህን ከሳይበር ሚዲያዎች ጋር በማስተሳሰር የይዘት ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ ጥቂት ቀናት በመዝናኛና በአፋን ኦሮሞ ቻናሎች አዳዲስ የይዘትና የአቀራረብ ስልቶች የተከተሉ ለውጦች እንደሚደረጉም አስታውቀዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም