179ሺ 119 ስኴር ኪሎ ሜትር ስፋት አላት:: የሕዝብ ብዛቷም 4ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በመቶ ማይልስ ርዝምት ከገልፍ ኦ ኤደን ጋር ጠረፍ ትጋራለች:: በስተደቡብ ከኢትዮጵያ ጋር በስተምዕራብ ደግሞ ከጅቡቲ ጋር ትዋሰናለች:: በስተምስራቅ ደግሞ ከፊል ነጻነቷን ካወጀችው ከፑንትላንድ ጋር ትጎራበታለች:: ሶማሊላንድ::
ዋናዋ ሶማሊ ሪፐብሊክ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ የቆየች ስትሆን፤ ሶማሊ ላንድ በበኩሏ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆና እስከ 1960 ድረስ ዘልቃለች:: ሁለቱም ከቅኝ ግዛት ከወጡ በኋላ ውህደት ለመፈጸም ጥረት የተደረገ ቢሆንም ይህነኑ አካሄድ ሶማሊላንድ ስትቃወም ቆይታለች::
በተለይም የዚያድ ባሬ አስተዳደር ከመጣ በኋላ ይህንኑ በጉልበት የመዋሃድ እንቅስቃሴ በመቃወም ሰፊ ንቅናቄ ተደርጓል:: ይህን ተከትሎም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት በመግባት በሁለቱም ወገኖች ላይ በርካታ ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራ ደርሷል:: በወቅቱም አምባገነኑ የዚያድ ባሬ መንግስትም በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ተቃዋሚዎችን ገድሏል::
ሶማሊላንድ እኤአ ከ1991 ጀምሮ ነጻነቷን ያወጀችና ላለፉት 33 ዓመታትም እራሷን በራሷ ስታስተዳድር ቆይታለች:: የራሷ የሆነ መከላከያ ኃይል፤ መገበያያ ገንዘብና የውጭ ሀገራት የመጓጓዣ ሰነድ ያላት ነች:: ከዓለም ሀገራት ዕውቅና ባታገኝም በርካታ ሀገራት ግን ነጻ ሀገር ትታሰባለች::
ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ጭምር በየጊዜው በምታደርገው ምርጫ ላይ በመገኘት በታዛቢነት ሲገኙ ቆይተዋል:: ካላት ሰላምና አካባቢያዊ አቀማመጥ አኳያ የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ ትስባለች:: በርካታ ባለሃብቶችም በዚህች ሀገር ላይ መዋዕለነዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው::
በወደብ ልማትና ተያያዥ ዘርፎች አንቱታን ያተረፈው የተባበሩት ኢምሬትስ ንብረት የሆነው ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን ለማልማት ፍላጎት ማሳደሩና ወደ ስራ መግባቱ ለሶማሊላንድ ትልቅ ተስፋን ፈንጥቋል:: የዲፒወርልድ ውሳኔም በፋይናነስ እጥረት ለምትስቃየው ሶማሊላንድም ከፍተኛ እፎይታ አስገኝቷል::
ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያም በበርበራ ወደብ ላይ የባለቤትነት መብት ወስዳ ወደ ልማት መግባቷ በአካባቢው መነቃቃትን ፈጥሯል:: የበርበራ ወደብን የኢምሬትስ መንግስት 51በመቶ፤ የሶማሊላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግስት 19 በመቶውን በመውሰድ ወደቡን በጋራ በማልማት ላይ ይገኛሉ:: ይህም በሶማሊላንዶች በኩል እንደትልቅ ተስፋ የሚወሰድ ነው::
ሶማሊላንድ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ ተደጋጋሚ ምርጫዎችን አካሂዳለች:: ምርጫዎቹ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጭምር በዲሞክራሲዊነታቸውና በሰላማዊነታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው:: ለአብነትም እኤአ በ2003 እና በ2010 በሶማሊላንድ የተደረገው ምርጫ ሰላማዊ ከመሆኑም በላይ ገዢው ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲ ያለምንም ኮሽታ ስልጣኑን ያስረከበበትና በሰላማዊነቱም በአፍሪካ ተጠቃሽ ምርጫ ነው::
በ2107 በተደረገው ምርጫም የአውሮፓ ሕብረት፤ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ አሜሪካ ሉኡኮቻቸውን በመላክ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነትና ሰላማዊነት ታዝበው ተመልሰዋል:: ስለምርጫው ዴሞክራሲያዊነትና ሰላማዊነትም ዕውቅና ሰጥተዋል::
ሶማሊላንድ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ወሳኝ ስፍራ ናት:: በገልኦፍኤደን ዳርቻ የምትገኝ እና 1/3ኛው የሚሆኑ መርከቦች የሚጓጓዙበት የባቤል መንደብ መዳረሻ ናት:: ሶማሊለንድ ያለችበት አካባቢ በዓለም ላይ ያሉ ኃያላን ሀገራት የሚራኮቱበት ከፍተኛ የስህበት ማዕከል ነው::
በአሁኑ ወቀት አሜሪካ፤ ፈረንሳይ፤ ቻይና፤ ሩስያ፤ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፤ ጣሊያን፤ ጃፓን የመሳሰሉ ሀገራት የጦር ሰፈር መስርተው የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ትንቅንቅ ውስጥ የገቡበት አካባቢ ነው:: በዚሁ አካባቢ ጅቡቲ ወሳኙን ድርሻ የያዘች ቢሆንም በቀጣይ ሶማሊላንድ የማይናቅ ድርሻ እንደሚኖራት ይገመታል::
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የቀረበ ግንነት አላት:: በ2004 ዓ.ም አካባቢ አገናኝ ጽህፈት ቤት ከፍታ ግንኙነቷን ከማጠናከር ባሻገር በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ ያሉ የሶማሊ ተወላጆች ያላቸውን የሃይማኖትና የባህል አንድነት እንዲጠናከር ስትሰራ ቆይታለች:: ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ደግሞ ግንኙነቱ ወዳ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል::
ከሶማሊላንድ ጋር በተፈጸመው መግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባህር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል:: ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው:: ቀጠናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል::
ለሶማሊላንድም ቢሆን ትሩፋቱ የበዛ ነው:: በዓለም ላይ ካሉት 18 ድሃ ሀገራት ተርታ የምትቆጠረው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ የወድብና የባህር በር ጥያቄ መቀበሏ ዝቅተኛ የሆነውን ኢኮኖሚዋን ለመደገፍና ከፍተኛ የሆነውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ዕድል ይሰጣታል:: ዓመታዊ ጥቅል ገቢዋ ከ2ቢሊዮን ዶላር ላልዘዘለው ለዚቹ ሀገር ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈጥር ነው::
በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በሁለቱም ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል:: የኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጠኛ በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ተገኝቶ እንዳረጋገጠው ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ያደረጉትን ስምምነት ሕዝቡ በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበለው::
ሶማሊላንድ ነጻነቷን ያወጀችበትን ዕለት በማስመልከት አደባባይ የተገኙ የሀርጌሳ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ሁለቱን ሀገራት የሚጠቅምና ግንኙነታቸውንም የሚጠናክር ነው:: ይህንን የመግባቢያ ሰነድ የሚቃወሙ አካላትም የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድን ግንኙኘት የማይሹና የጋራ ዕድገትን የማይመኙ ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል:: እነዚህን አካላት ወደ ጎን በመተው የተጀመረው ስምምነት ወደ መሬት እንዲወርድ አበክረው መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል::
ዋዳኒ ናሽናል ፓርቲ የተሰኘውም የሶማሊላንድ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የተደረሰውን ስምምነት በአድናቆት ነው የተመለከተው:: የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሀመድ ጂማ አዳም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ላይ መድረሷ ሁለቱንም ተጠቃሚ ያደርጋል:: ኢትዮጵያም የባሕር በር እና ወደብ ተጠቃሚ እንድትሆን ዕድሉን ይሰጣል፤ ለሶማሊላንድም ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን ይዞ ይመጣል::
የሶማሊላንድ የኢንቨሰትመንት ሚኒስትር አብዱረዛቅ ኢብራሂም በበኩላቸው እንደገለጹት በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ሁለቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው:: ሶማሊላንድ በባሕር የተከከበች ከመሆኗ አንጻር የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በአሳ ልማትና ተያያዥ ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አድርገዋል::
በተለይም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችውን ውጤት የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በሶማሊላንድ እንዲደግሙት ፍላጎቱ እንዳላቸው ተናግረዋል:: ኢትዮጵያ ለዘመናት ተቆጣጥራ ከኖረችው የቀይባሕር አካባቢ በበርካታ ሴራዎች ምክንያት ከአካባቢው ገለል እንድትል ተደርጋለች:: በዚህም ዝናና ክብሯ ዝቅ ብሎ ተሰሚነቷ አሽቆልቁሏል:: የኢትዮጵያዊነት ስነልቦናም ክፉኛ ተጎድቶ ኖሯል::
የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከስነልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል:: የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል::
ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል::
በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትጵያ ሚና አሽቆልቁሏል:: ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ በዓለም እጅግ ተፈላጊ ከሆኑትና የሃያላን ሀገራትንም ቀልብ የሚስብ በመሆኑ እድገቷን የማይፈልጉ አካላት በተቀነባበረ ሴራ ከቀይ ባሕር እስኪያርቋት ድረስ ገናና እና በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆና ቆይታለች:: ሆኖም ሀገሪቱ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮ ተፈላጊነቷ አሽቆልቁሏል::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል:: በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል::
ይህንን ሕዝብ ቁጥር ያህል ይዞ ደግሞ ባሕር እና ወደብ አልባ የሆነ አንዳችም ሀገር የለም:: ስለዚህም ኢትዮጵያ በባሕር እና ወደብ አልባነት የተጋረጡባትን ችግሮች ለመፍታት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በርካታ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች:: ይኼው ጥረቷ ፍሬ አፍርቷል:: ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደተግባር ገብተዋል::
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ያደረጉት ስምምነት ለኢትዮጵያም ጥቅሙ የጎላ ነው:: ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጭ የሚያሰፋ መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል ከተፈረመ በኋላ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ተስፋ ፈንጥቋል:: ስምምነቱ ለኢትዮጵያም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከማስገኘቱም በሻገር መረጋጋት ለራቀው አፍሪካ ቀንድ አካባቢ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ የሚመጣ ነው ::
ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው:: ቀጠናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍቷል::
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ፣ በቀይ ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ እየተከሠቱ በሚገኙ የጸጥታና የደኅንነት ፈተናዎች የተነሣ የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ አደጋ እየተጋረጠበት ይገኛል:: በቅርቡ እንኳን የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረሳላጤ አካባቢ በመርከቦች ላይ እየፈጸሙት ባለው ጥቃት ከአካባቢው አልፎ በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ መገንዘብ ይቻላል::
ስለሆነም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ደኅንነቱና አስተማማኝነቱ የተጠበቀ የባሕር በር እንድታገኝና በቀይ ባሕር አካባቢ አጥታው የነበረውን ስፍራ መልሳ እንድታገኝ ከማድረጉም ባሻገር በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ማንንም የሚጎዳ አይደለም:: ይልቁንም አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው::
ከሁሉም በላይ ዓለም አቀፍ ሕጉና ተቋማት ጭምር ፍትሃዊ የሆነ የባሕር በር ተደራሽነት እንዲኖር ስለሚፈልጉ በኢትዮጵያና በሶማሊ ላንድ መካከል የተደረሰ የመግባቢያ ስምምነትን የሚደግፉት እና ተቀባይነትም ያለው ነው:: በተለያዩ ጊዜያትም ከሀገራትና ዓለምአቀፍ ተቋማትም የሚወጡት መግለጫዎች ይህንኑ የሚያንጻበርቁ ናቸው::
መንግስት እራሱ ተነሳሽነቱን ወስዶ የኢትዮጵያውያንን የባሕር በር የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ነው:: ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈረመውም የመግባቢያ ሰነድ የዚሁ ጥረቱ ማሳያ ነው:: ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም:: ሌሎችም የቀጣናው ሀገራት በዚሁ መንገድ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም