ዜጎችን ከሀሰተኛ መረጃዎች ለመታደግ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ በዩ ቲዩብ እና ቲክቶክ ከሕዝብ ባህል እና ሞራል ውጭ የሆነ ሀሰተኛ የፈጠራ ታሪኮችን እንደ እውነተኛ ታሪክ እያደረጉ ሲያቀርቡ አገኘኋቸው ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሏል:: እነዚህ ወጣቶች ቢሮ ተከራይተው፣ ካሜራ ገዝተው፣ ስክሪፕት አርቅቀው፣ ቃለመጠይቅ ተለማምደው ነው ይህን የሚሠሩት:: ይህ የሚያሳየን ብዙ ነገር አለ::

በዋነኝነት ይህ የሚያሳየው የርዕይ መንጠፍ ወይም በተለምዶ ፈረንጆቹ ‹‹ፌለር ኦፍ ኢማጂኔሽን›› የሚሉት ነው:: በሲኒማው ዘርፍ ብዙ ርቀት የተጓዙት ሀገራት የፊልም ኢንዱስትሪውን የሚጠቀሙበት በእውነተኛው ዓለም የሌለ ነገር ግን ቢኖር ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማሳየት ነው:: ለዚያም ነው በእውነተኛው ዓለም የሌሉ ነገሮችን በፊልም የምናያቸው:: ስናያቸው “ይሄማ ውሸት ነው፣ ይሄ ተጋነነ፣ ይሄ የማይመስል ነገር ነው” እንላለን:: ያልናቸው ነገሮች ግን ብዙውን ጊዜ ዘግይቶም ቢሆን የቴክኖሎጂ ሰዎች እውን ሲያረጓቸው እናያለን::

ሞባይል ስልክን ዛሬ ሁላችንም ከመያዛችን በፊት መጀመሪያ ላይ የፊልም ሃሳብ ነበር:: አሁን ዓለምን ካጥለቀለቀው ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) አንስቶ አብዛኞቹ ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂዎች በአንድ ወቅት የልብወለድ እና የፊልም ሃሳብ ነበሩ:: ዛሬስ እኛ የምንሠራቸው የዩቲዩብ እና ቲክቶክ ቪዲዮዎች ወደፊት ምን አይነት ኢንዱስትሪን ይፈጥሩ ይሆን? ምን አይነት ቴክኖሎጂንስ ያዋልዱ ይሆን? አሁን በሚሠሩት ይዘት መሠረት ከሆነ ቀጥሎ የሚመጣው ውጤት ጥሩ እንደማይሆን ግልጽ ነው:: እስኪ አስቡት ሰዎች ስራዬ ብለው እስኪርቢቶ ይዘው ወረቀት ገልጠው የሚጽፉት የፊልም ሃሳብ “ለባእድ አምልኮ መስዋእት ሊያደርጉ ልጃቸውን ስላረዱ ቤተሰቦች” “ስለ ግብረ ሰዶም” “በዘመዷ ስለተደፈረች ታዳጊ” እና መሰል አይነት ይዘቶች ነው:: ያሳፍራል:: ጭንቅላታችንን ጨምቀን የምናፈልቀው ሃሳብ ይህ ከሆነ ጭንቅላታችን ነጥፏል ማለት ነው::

ይህ ዛሬ ለዩቲዩብ ገበያ ተብሎ የሚፈበረክ ልብ ወለድ ነገ ይለመድና ሕዝባዊ ባህል ይሆናል:: ሌሎች በፊልማቸው ያዩትን ቴክኖሎጂ በሳይንስ እውን ሲያደርጉት እኛ ደግሞ በፊልማችን የምናሳየው መላሸቅ በቀጣይ በሕይወታችንም ላይ ይተገበራል ማለት ነው::

እርግጥ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ይህ ችግር የርዕይ መንጠፍ ችግር ሳይሆን ርዕያችን ዝና እና ገንዘብን ማዕከል ያደረገ መሆኑ ነው ይላሉ:: ለምሳሌ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ቁጣ ቀስቅሶ የነበረ አንድ አስነዋሪ የዩቲዩብ ትወና ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንዲት ሴት እና አንድ ታዳጊ ህጻን ይቅርታ በጠየቁበት ሌላ ቪዲዮ ላይ እንደተናገሩት ከሆነ ወደዚህ አይነት ተሳትፎ የገቡበት ምክንያት ‘ታዋቂ ለመሆን’ በማሰብ ነው:: በእርግጥም በተሳሳተ መንገድም ቢሆን ታዋቂ ሆነውበታል:: እነሱን ከጀርባ ሆነው የሚያሠሩት ሰዎች ደግሞ ቪዲዮው ብዙ ጊዜ በመታየቱ ገንዘብ አትርፈውበታል:: ስለዚህም ዓላማቸው ተሳክቷል ማለት ይቻላል:: ያለንበት የኢኮኖሚ ችግር ሰዎች ማንኛውንም ነገር እንዲያደርጉ በር የሚከፍት ሊሆን ይችላል:: ዝናውም ቢሆን የሚፈለገው ገንዘብ አስከትሎ ስለሚያመጣ ነው:: ስለዚህም ሃሳባቸውን እንረዳለን:: ነገር ግን ካልጠፋ ሃሳብ እንዲህ አይነት ሰንካላ ሃሳቦችን አዕምሮአቸው እንዴት አመነጨላቸው? የሚለው ሃሳብ ነው የሚያስጨንቀው::

እርግጥ እንዲህ አይነት ነገር በኛ ሀገር ብቻ ያለ አይደለም:: ባደጉትም ሀገራት እንዲህ አይነት የላሸቁ ሃሳቦች አሉ:: ነገር ግን እንዲህ አይነት ሰዎች የሚስተናገዱበት ሥርዓትም አለ:: በምንም መንገድ ግን ዋነኛ የትኩረት መስህብ እንዲሆኑ አይፈለግም:: ለምሳሌ ከላይ እንደጠቀስናቸው አይነት ከባህል እና ወግ ያፈነገጡ ሃሳቦችን የሚያስተናገዱት የወሲብ ቻናሎች ሲሆኑ መንግሥታትም እነዚህ ቻናሎች እና ድርጅቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋሉ:: በተቃራኒው ለሀገር እና ለሕዝብ ፋይዳ አላቸው በሚባሉ እና ሀገራዊ ርዕይ (national vision) በሚሰበክባቸው የፊልም እና የሚዲያ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረጋል:: ለዚያ ነው አሜሪካ እና አውሮፓ የራሳቸውን ራዕይ እና እሴት የሚሰብኩበት የሆሊውድ ስቱዲዮዎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያፈስሱት:: እኛ ጋ ሁለቱም ቀስ በቀስ እየተደባለቁ ነው:: እንዲያውም ይሄ ብዙ ኢንቨስትመንት የማይፈልገው እና ቁጥጥር የማይሻው የዩቲዩብ እና ቲክቶክ ዘርፍ ዋናውን የሲኒማ እና የሚዲያ ኢንዱስትሪ እየተጋፋና እያዳከመው ነው:: ስለዚህም በቅርብ ጊዜ ዩቲዩቡ እና ቲክቶኩ ደካማ እና የላሸቀ ሃሳብ ካላቸው ባለቤቶች ጋር ሆነው ዋነኛ ሚዲያ (mainstream media) ሊሆኑ ይችላሉ:: ስለዚህም ዜጎችን ከሀሰተኛ መረጃዎች ለመታደግ እንዲሁም የማህበረሰብን ባህልና ወግ ከሚሸረሽሩ ከውሸት ታሪኮች መጠበቅ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: በዚህ እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን እርማት መስጠት ካስፈለገን ከአሁኑ ነው:: ከአሁኑ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታዩ የአስተሳሰብ ውድቀቶችን በጠንካራ ሂስ ማረም እልፍ ካለም በሕግ አግባብ መቆጣጠር የግድ የሚሆነውም ለዚህ ነው:: አልያም ዛሬ በእንቁላሉ ጊዜ በቸልታ ያለፍነው ውድቀት ነገ በበሬው ጊዜ ለማረም ያስቸግራልና ይታሰብበት::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You