ለአምራችና ሸማቹ መፍትሔ ይዞ የመጣው ተንቀሳቃሽ የቲማቲም ማቀነባበሪያ

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚያዘጋጃቸው ኤግዚቢሽኖች ዋና የትውውቅና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ ስፍራ መሆን እየቻሉ ናቸው:: በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የንቅናቄው ኢግዚቢሽን ላይ ከተሳተፉት የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ፣ የግንባታ ግብዓት አምራቾች፤ ማሽነሪ አምራቾች የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች፣ የግብርና ምርቶች አቀነባባሪዎች፣ ወዘተ መረዳት እንደተቻለውም መድረኩ የዘርፉን አምራች ኢንዱስትሪዎችና ምርቶቻቸውን ፈላጊዎችን ማስተዋወቅና ማስተሳሰር ችሏል::

ከመድረኩ ጉብኝትና ከተሳታፊዎች መረዳት እንደቻልነውም መድረኩ የትውውቅና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ መሆን መቻሉን አረጋግጠናል:: ቴክኖሎጂ በማላመድ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችንም አመላክቷል:: ወደ ኢግዚቢሽኑ አዳራሽ ሳይገባ በስተቀኝ ውጪ ላይ የቀረቡ የሀገር ልጆች አሻራ ያረፈባቸው የማሽንና የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ምርቶችም ይህንን ያመላከቱ ናቸው::

በዚህ ስፍራም አንድ ግዙፉ ተሳቢ ተሽከርካሪ ላይ የቲማቲም ማቀነባበሪያ የሚል መረጃ በትልቁ ተለጥፎበት ተመለክተን:: የተሽከርካሪውን ዙሪያ በሚገባ ከቃኘን በኋላም የተሳቢውን መወጣጫ ተጠቀምን በራፉ ደርሰን፤ ሆድ እቃውንም ቃኘን:: የኢትዮ ኢንጂነሪግ ግሩፕ አንዱ አካል በሆነው በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተመረተ የቲማቲም ማቀነባበሪያ ስለመሆኑ የማቀነባበሪያው አስገብኚ ገለጸልን::

ማቀነባበሪያውን እያስጎበኘ ማብራሪያ የሰጠን የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የጥራት ቁጥጥርና ማረጋገጫ ክፍል ኃላፊ አቶ ግርማዬ ልዑል ሰገድ እንዳብራራው፤ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በስሩ ያቀፈው የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አካል ነው::

ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ማምረቻ፣፣ ሜክሲኮ ላይ የሚገኘው አዲስ ማሽን ቱልስ፣ ትራንስፎርመር የሚያመርተው ፓወር ኢንጂነሪንግ በዚህ ግሩፕ ስር ከሚገኙት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ:: በደብረ ብርሃንም ማሽነሪዎችን የሚያመርት ድርጅት አለው::

ይህ የቲማቲም ማቀነባበሪያ የተሰራው በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ነው:: በኛ ተቋም ውስጥ ሶስት አይነት ተንቀሳቃሽ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፕላንቶች ሰርተናል የሚለው አቶ ግርማዬ፣ እነዚህም የጥራጥሬና ቅመማ ቅመም፤ የድንች ማቀነባበሪያ እና ይህ የቲማቲም ማቀነባበሪያ መሆናቸውን ይገልጻል::

ለኢትዮ ኢንጂነሪግን ግሩፕ ከመንግስት ከተሰጡት ዋና ዋና ተልእኮዎች መካከል አንደኛው ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ ማልመድ /አዳብት ማድረግ /ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ገበያን ማረጋጋት ነው ሲል ጠቅሶ፣ የቲማቲም ማቀነባበሪያው ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስታውቋል::

አቶ ግርማይ እንዳብራራው፤ የቲማቲም አግሮ ፕሮሰሲንግ ፕላንቱ ዋና ዓላማ ገበሬው ያለበት ቦታ ድረስ ተንቀሳቅሶ የቲማቲም ሳልሳና ሌሎች የቲማቲም ውጤቶችን ማቀነባበር ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ አርሶ አደሩ አካባቢ ያለው የቲማቲም ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ ምርት በዝቶ የሚያነሳው አጥቶ የሚጣልበት ሁኔታ እንደነበረም ይጠቅሳል:: በዚህ ማሽን የቲማቲሙን የቆይታ ጊዜ /ላይፍ ታይም/ በመጨመር የአርሶ አደሩንም የሸማቹንም ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል::

በዚህ ማሽን አራት አካላት ይጠቀማሉ ተብሎ ታስቧል:: አንደኛ አርሶ አደሩ፣ ሁለተኛው ሸማቹ፣ ሶስተኛው መንግስት ሲሆኑ፣ አራተኛው ደግሞ በአነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝነት ተደራጅተው ከልማት ባንክ ፋይናንስ አግኝተው የሚሰሩ አካላት ናቸው::

ይህን ማሽን ገዝቶ መስራት የሚፈልግ ባለሀብት ካለም ባለሀብቱ ተጠቃሚ ይሆናል ሲል ጠቅሶ፣ ይህን ሲያደርግ እሱ ብቻ አይደለም ተጠቃሚው፤ የሚቀጥራቸው ሰራተኞችም ይጠቀማሉ ብሏል::

ይህንንም ሲያብራራ እንዳለው፤ አርሶ አደሩ ምርቱ ሲባዛና ተቀባይ ሲያጣ ሲደርስበት ከኖረው ችግር ይታደገዋል:: የአርሶ አደሩ ምርት ገበያ ያገኛል:: እንደሚታወቀው ማኅበረሰቡ ቲማቲም ሲረክስ በዝቅተኛ ዋጋ እየገዛ ቢጠቀምም፣ ሲወደድ ደግሞ 120፣ 100 ብር የሚገዛበት ሁኔታ ታይቷል::

የቲማቲሙን የቆይታ ጊዜ /ላይፍ ታይም/ በማራዘም ሸማቹ በተመሳሳይ ዋጋ ሁሌም ቲማቱሙን የሚያገኝበትን ሁኔታ እንፈጥራለን ማለት ነው ይላል:: ዋጋው ዝቅ ባለ ጊዜ ትኩሱን፣ ዋጋው ወደድ ሲል ደግሞ የተቀነባበረውን በ20ና 25 ብር እየገዛ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያለው::

ስለ ማቀነባበሪያው የማምረት አቅም ተጠይቆ ሲያብራራም፣ ማቀነባበሪያውን /ፕላንቱን/ ወደ መስራት ሲገባ የተያዘው እቅድ በሰዓት 250 ኪሎ ግራም ቲማቲም እንዲፈጭ አርገን ነው ይላል:: የቦይለሮቹንና ሌሎች የማሽኑን ክፍሎች አቅም ጨምረን በሰዓት 500 ኪሎ ግራም ቲማቲም እንዲፈጭ አርገን ሰርተነዋልም ነው ያለው::

ማቀነባበሪያው በተለያዩ የኃይል አማራጮች እንዲሰራ ተደርጎ ስለተሰራ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሊገጥመው የሚችል ችግር አይኖርበትም:: በገጠር አካባቢ መቶ በመቶ መብራት የለም፤ ማቀነባበሪያው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለበት አካባቢ የሚገባ ከሆነ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሶስት ፌዝ መስመር ጋር ተያይዞ እንዲሰራ ይደረጋል:: የኤሌክትሪክ ኃይል ርካሹ ስለሆነ በእዚህ መገልገል ያዋጣል::

ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ሌላ የኢነርጂ አማራጭ ተዘጋጅቶለታል:: 25 ኪሎ ዋት ጀነሬተር መጠቀም ይችላል:: ይህም የኃይል አቅርቦት ሁሉም የማሽኑን ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ ያስችላል:: ኢነርጂ ለማምረት የሚያስችል ቦይለርም ተገጥሞለታል:: ከ22 እስከ 23 ሊትር ነዳጅ ተጠቅሞ አንድ ሺ ሊትር ውሃ ወደ እንፋሎት /ኢነርጂ መቀየር ይችላል:: በእዚህም አንድ ቀን ሙሉ መስራት ይችላል::

የማቀነባበሩ ስራ እንዴት እንደሚፈጸም ሲያብራራም ከሁለት ቦታዎች በስተቀር አጠቃላይ ስራው አውቶሜትድ ነው፤ በቅድሚያ ቲማቲም ወደ ማሽኑ እንዲገባ ከመደረጉ በፊት የተበላሸ ቲማቲም እንዲወገድ ይደረጋል፤ ከፍተኛ ግፊት ያለው ውሃ በመጠቀም ይታጠባል::

ማቀነባበሪያው ፓስቸራይዝ በማድረግ፣ ማሸግ የሚችልም ነው:: የመጠቀሚያ ጊዜ ቆይታን ማሳጠርና ማስረዘም በዚህ ማቀነባበሪያ ተጠቀሞ ማምረት የሚፈልገው ድርጅት ውሳኔ ይሆናል:: አምራቹ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ማድረግ ከፈለገ ለዚህ የሚያስፈልገውን ፓስቸራይዝድ ማድረጊያ ኬሚካል መጠቀም አለበት:: ለስድስት ወር ለሶስት ወር ወዘተ ካለም እንዲሁ የኬሚካል መጠኑ ይወስነዋል::

እጅ ከጀርሞች ንክኪ ነጻ አይደለም የሚሉት አቶ ግርማዬ፣ ይህን ለማስወገድ ስራዎች በማሽን ቢሰሩም ለጀርሞች ምንም አይነት እድል ላለመስጠት በሚል ስራው የሚከናወንባቸው የማሽን ክፍሎች ስተራላይዝድ ይደረጋሉ ሲል ያብራራል:: አጠቃላይ ስራው አውቶሜትድ ቢሆንም በሰውም ክትትልና ቁጥር ይደረግበታል ነው ያለው::

ማቀነባሪያው የጤና ሚኒስቴር ስታንዳርድ ያሟላ ማሸጊያንም ያካተተ መሆኑን ጠቅሷል:: የአንድ ምርት ዋጋ በአብዛኛው ማሸጊያው ላይ ይወሰናል ያለው አቶ ግርማይ፣ ለሌሎች የምንመክረውም ይህን አይነት ማሸጊያ እንዲኖር ነው፤ ከውጪ የሚመጡት የተቀነባበሩ የቲማቲም ውጤቶችም የሚታሸጉት ይህ ማቀነባበሪያ በሚያሽግበት መንገድ መሆኑን ያስገነዝባል::

ሳልሳው የሚታሸግበት ቁስ እንደ አምራቹ ፍላጎት አንደሚወሰንም ተናግሯል:: ማቀነባበሪያውን የሚፈልጉ አካላት ማሸግ የምንፈልገው በብርጭቆ ነው፣ በፕላስቲክ ነው፣ በጀሪካን ነው የሚል ከሆነም በጥያቄያቸው መሰረት ማስተናገድ እንደሚቻልም ጠቁሟል:: በታሸገው ምርት ማሸጊያ ላይ ምርቱ የተመረተበት ቀንና ዓመተ ምህረት፣ የአገልግሎት ቆይታውን የሚመለከቱ መረጃዎች ይታተማሉ::

አቶ ግርማዬ እንዳብራራው፤ ምግብ መቶ በመቶ ከጀርም ነጸ መሆን አለበት:: ,ምክንያቱም 10ሺ አምርተን አንድ ሰው ከታመመ መጀመሪያ ተጠቃሚው አካል ይጎዳል፤ ሁለተኛ አምራቹ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል:: ተጠቃሚው የዚህን ኩባንያ ምርት ተጠቅሜ ታምሜያለሁ ካለ መደርደሪያ ላይ ያለው ምርት ብቻ ሳይሆን እየተመረተ ያለው ምርት እንዲሁም አምራች ድርጅቱ ስም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል::

ስለዚህ በቲማቲም ማቀነባበሪያው ተመርቶ የታሸገው ምርትም እንዲሁ መቶ በመቶ ሰቴራላይዝድ ተደርጎ እንዲወጣ ይደረጋል ሲል ጠቅሶ፣ የታሸገው ምርት በስቲም ስቴራላይዝድ ከተደረገ በኋላ ነው ወደ ፓኪንግ እንዲሄድ የሚደረገው ብሏል::

እኛ መንግስታዊ የልማት ድርጅት ነን፤ ዋናው ተልእኮዋችን ወደ ሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂን በማምጣት ማላመድ ነው:: በተለይ ደግሞ ባለሀብቱ የማይደፍራቸውን፣ በገባባቸው እከስርባቸዋለሁ የሚላቸውን ቴከኖሎጂዎች በማምጣት የማላመድ ስራ እንሰራለን ያለው አቶ ግርማዬ፣ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ሀገራዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነም አስገንዘቧል:: መንግስት ያንን ተልእኮ ለኛ ይሰጣል፤ እኛ እንሰራለን፤ እኛ ይህን ስንሰራ የጣልነው ያነሳነው ብዙ ነገር አለ በማለት ማቀነባበሪያውን በማምረት ሂደት ውጣ ውረዶች መታለፋቸውን ጠቅሷል::

አቶ ግርማዬ ‹‹ማቀነባበሪያው የድርጅቱ የመጀመሪያ ምርት/ፕሮቶታይፕ/ ነው:: አሁን የማሽን ስራውን ከልማት ባንክ ጋር ለማያያዝ እየተመከረ ነው:: ኢንዲስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ጎብኝተውት ከልማት ባንክ ጋር መተሳሰር አለበት ብለዋል፤ ለወጣቶች የስራ እድል ይከፍታል የሚል አቅጣጫም ሰጥተዋል ሲሉም አብራርቷል:: የመንግስት ተቋማት ይህን ማመቻቸት ከቻሉ፣ እኛ ሰርተን ብቻ ሳይሆን ሞክረንም፣ ለሀገር ያለውን ፋይዳ ማሳየት ችለናል ብሏል::

ስራው የቅብብሎሽ እንደሆነም ጠቅሶ፣ ከዚያ በኋላም ስራው ውስብስብ መሆኑን ጠቅሶ ተቀናጅተን ሌሎች የመንግስትና የግል ተቋማት እጃቸውን አስገብተው በግል የሚወስዱም ሆኑ የተደራጁ አካላት ሊወስዱት እንደሚችሉ ጠቁሟል::

እሱ እንዳለው፤ የድርጅቱ ዓላማ የቲማቲም ማቀነባበሪያ ማሽን መስራት ብቻ አይደለም፤ ይህን ማሽን እኔም መስራት እፈልጋለሁ የሚል አካል ካለ/ የግልም ሆነ የመንግስት/ ለማቀነባበሪያው /ለፕላንቱ/ ያወጣውን ወጪ ሸፍኖ እንዲወሰድ ተደርጎ ድርጅቱ ሌላ ለሀገር የሚያስፈልግ ፕላንት ወደ መስራት ይገባል::

እነሱ የሰሩትን ማሽን የሚፈልጉ አካላት እየተበራከቱ መምጣቸውንም ጠቅሷል:: ‹‹ ይህ ማሽን ጎብኝቶ ያልተደነቀ የለም:: ከመቶ በላይ የቢዝነስ ካርዶችን ይዘን መጥተን ነበር፤ ሁሉም በጎብኚዎች ተወስደዋል፤ ሌሎች እጅ ላይ የነበሩ ቢዝነስ ካርዶችን ጭምር ተቀብለን ሰጥተናል:: ተቋማችን ድረስ ለመምጣት በመፈለግ ስልክ ቁጥር የወሰዱም አሉ:: የመንግሰትም ጽኑ ፍላጎት እንዳለ አስተውለናል ሲል ለማሽኑ በጎብኚዎችና መንግስት ዘንድ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ስለመሆኑ አመልከቷል::

እነ አቶ ግርማዬ አሁን ከገኙት ግብረ መልስ በመነሳሳት ማቀነባበሪያውን ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመስራት ማሰብ ጀምረዋል:: ሌሎች ማሽኖችን እንዲሰሩም መነሳሳት ፈጥሮባቸዋል:: ከዚህ ባለነሰ እቃና የማምረት ፍጥነትን ከፍ በሚያደርግ መልኩ አንዴት መስራት ይኖርብናል ብለን እንድናስብ አርጎናል ሲል አቶ ግርማዬ ተናግሯል::

ይህ እንዲሆን ግን ለማሽኑ የሚያስፈልጉ ከውጪ የሚመጡ እቃዎች በሀገር ውስጥ አንዲመረቱ ያስፈልጋል:: ማንኛውም ሀገር በቀል ድርጅት እነዚህን አካላት ማምረት እችላለሁ ካለ ማምረት ይችላል፤ ለእዚህ ግን የምግብና የመድህኒት ማምረቻና መጠቀሚያ እቃዎችን ማምረት ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም ፈቃድ መውሰድ ይኖርበታል::

በመጀመሪያ የሚፈለገው ራስን መቻል ነው፤ እንዱ የውጪ ድርጅት ጥቅሜ ተነካብኝ ባለ ቁጥር ከሚጥለው ማእቅብ ለማውጣት የሀገር ውስጥ የማምረት እቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል ሲል አቶ ግርማዬ አስገንዝቧል::

የማቀነባበሪያውን ዋጋ አስመልክቶ ሲያብራራም ሁሌም የመጀመሪያ ምርት ውድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ቴክኖሎጂ እየተስፋፈ ሲመጣ የማምረቻ ጊዜና ወጪ እየቀነሰ ስለሚመጣ ዋጋው እየቀነሰ ይመጣል ብሏል::

ብዙ ማሽኖችን ብትታዘዙ ማምረት ትችላላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረብንለት አቶ ግርማዬ፣ መጀመሪያው የኢንጂነሪግ ስራውን ልታፈርስ ትችላለህ፤ ትገነባለህ፤ ብዙ ጊዜ ሊወሰድ ይችላል፤ ፕሮቶ ታይፑን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት አካባቢ ሊወስድም ይችላል ሲል ጠቅሶ፣ ብዙ ማምረት /ማስ ፕሮዳክሽን/ ውስጥ ለመግባት ለኛ ብዙ ችግር የለብንም ሲል አስታውቋል::

ኢትዮ ኢንጂነሪግ ሚሊኔየም ፓርክን የሚያካክሉ ትላልቅ ወደ አምስት የሚደርሱ ፋብሪካዎች እንዳሉት ገልጾ፣ ብዙ ማምረት /ማስ ፕሮዳከሽን/ መቶም አንድም ብንታዘዝ አንድ አይነት ነው ብሏል፤ አንድ ታዞ የሚወጣው አንድ ወር የሚወስድ ከሆነ ለኛ መቶ ብንታዘዝም ያው ነው የሚሆነው›› ሲል አብራርቷል::

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You