ለታዳጊዎች ዓለም አቀፍ በር የሚከፍተው የአካዳሚዎቹ ስምምነት

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ኢንዱስትሪ በርካታ አስርት ዓመታት ወደ ኋላ የዘለቀ ታሪክ ያለው፤ አገሪቱም ተሰጦ ባላቸው ታዳጊዎች የተሞላች ብትሆንም ዛሬም ድረስ በሚፈለገው ልክ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ መፍጠር አልተቻለም። በካፍ ምስረታና በአፍሪካ እግርኳስ እድገት ላይ ጠንካራ መሰረት የጣለችው ኢትዮጵያ በዘላቂነት ይህ ነው የሚባል ስም መትከል ሳትችል ቀርታለች። በተለይ እምቅ አቅም ያላቸው ታዳጊዎችን ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ እግር ኳስ መድረኮች ላይ በበቂ መልኩ ስታሳትፍ አይስተዋልም። ይህ እውነታ እግር ኳስን ልክ እንደ ባህላዊ ስፖርት ለሚወደው ደጋፊ እና ታዳጊ እግር ኳስ አፍቃሪያን ስሜት የሚጎዳ ነው።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ይህንን አሉታዊ ታሪክ የሚቀይሩ ኢትዮጵያውያን ባለተሰጦ ታዳጊዎች ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት እንዲያተርፉ መንገድ የሚጠርጉ ፕሮጀክቶች እየተመለከትን ነው። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ የቡና ስፖርት ክለብ ተጫዋች የነበረው አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ የሚመራው እድሉ አካዳሚ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

አካዳሚው ታዳጊዎችን በመመልመል ስልጠና መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል። ከዛ በፊትም ግን በተቆራረጠ ሁኔታም ቢሆን ስልጠና ይሰጥ እንደነበር መስራቹ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ ይናገራል። በዘንድሮው ዓመት በሀገር ውስጥ ክለብ በምድብ አንድ በኢትዮጵያ ቡናና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የገቡ ተጫዋቾች እንዳፈሩም ይገልፃል። በቀጣይም ፕሮፌሽናል ተጫዋች ለማፍራት ጠንካራ የውጪ ግንኙነት መመስረቱንም ለአዲስ ዘመን በሰጠው ቃለ ምልልስ ነግሮናል።

‹‹በኢትዮጵያ እምቅ ችሎታ ያላቸው ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በማብቃት የሚገኝ ነገር የለም። ውጤት ላይ ለማድረስም ከባድ ፈተናዎች አሉት›› የሚለው አሰልጣኝ እድሉ፤ በተለይ የስፖርት ማዘውተሪያ የማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል። በውጪ ሀገር በዚህ ረገድ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከመሬት ጀምሮ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹም ይገልፃል። ይህ ደግሞ ሰልጣኞችን ውጤታማ ለማድረግና ዓለም አቀፍ እውቅናና እድል እንዲያገኙ ለማስቻል ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይናገራል።

ስፔን እአአ የ2010 የዓለም ዋንጫ ስታሸንፍ የሀገራቸው እድገት በስድስት በመቶ መጨመሩን የሚናገረው አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ፤ ለታዳጊዎች ትኩረት ሰጥቶ ከስር መሰረቱ መስራት እግር ኳስን ከማሳደግ ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ አንዳለው ያስረዳል። በመሆኑም አካዳሚዎች ላይ መስራትና ቲኤፍ ኤ ኢሊትን ከመሰሉ ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች ጋር አጋር መሆን ትክክለኛው አማራጭ መሆኑን ያነሳል። በመሆኑም የመንግስት ኃላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ያሳስባል።

ኢዲዋይ አካዳሚ ከሰሞኑ አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት አድርጓል። ይህ ስምምነት ቲኤፍ ኤ ኢሊት ከሚባል በዱባይ የሚገኝ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ክለብ ጋር ነው። ቲኤፍ ኤ በዱባይ ሊግ በሶስተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደራል። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾችን እየመለመለ ስልጠናም እየሰጠ ወደ አውሮፓ መላክ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። ይህ አካሄድ ለተስፈኛ ተጫዋቾች መልካም እድል ሲሆን ፕሮጀክቱን ለሚያንቀሳቅሱት ደግሞ የእግር ኳስ ኢኮኖሚያዊ እድል ተደርጎ ይቆጠራል።

ቲኤፍ ኤ ኢሊት ምስራቅ አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ ልዩ ችሎታ /talent/ ያላቸው ታዳጊ ተማሪዎች ከመመልመል ባሻገር የአካዳሚውን ደረጃ /standard/ እንዲያሟሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ አውሮፓ ክለቦች ይልካል። አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ታዳጊዎች አዙሯል።

የኢዲዋይ አካዳሚ መስራች አሰልጣኝ እድሉ ከቲኤፍ ኤ ኢሊት ጋር ባደረገው ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ምልመላ ስምምነት መሰረት ታዳጊ ናትናኤል አረጋዊ የሚባል ተጫዋች መመልመል ችለዋል። የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ ታዳጊው ወደ ቲኤፍ ኤ አካዳሚ ገብቶ ከሰለጠነ በኋላ ከመላው ዓለም ከአስር ሀገራት ከመጡ ተጫዋቾች አንደኛ ወጥቶ ለመፈራረም በቅቷል። ይህንን መነሻ በማድረግ ሌሎች ልዩ ችሎታ በቃት ያላቸው ልጆች ለማፍራት የሁለቱ አካዳሚዎች ግንኙነት መመስረቱን አሰልጣኝ እድሉ ይናገራል።

የቲኤፍ ኤፍ ኢሊት አካዳሚ ቴክኒካል ዳይሬክተር የሆኑት አሊ ኢል ጂኢሽ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ አካዳሚያቸው ተሰጦ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል መንገድ ለማመቻቸትና የብቃታቸው ጥግ እንዲደርሱ ይሰራሉ። ለዚህ እንዲያግዛቸውም በቅርቡ በአጋርነት ለመስራት ከተስማሙት እድሉ አካዳሚ /ኢዲዋይ/ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

‹‹ታዳጊዎች እንደየ እድሜ እርከናቸው አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ እንሰራለን የሚሉት›› ቴክኒካል ዳይሬክተሩ፤ ይህ አካሄድም ብቃት ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች ትክክለኛውን ፕሮፌሽናል ደረጃ እንዲያሟሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው ይናገራሉ። በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ የጀመሩት ፕሮጀክት ይህንን አካሄድ የተከተለ መሆኑን ይገልፃሉ።

የቲኤፍ ኤ ኢሊት ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ፉአድ ሀፊድ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ታዳጊዎች ላይ የተመለከቱት ተሰጦ እና የእግር ኳስ ፍቅር በእጅጉ አስደንቋቸዋል። በዚህም ታዳጊዎች የብቃታቸው ጫፍ ደርሰው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ለመርዳት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ እግር ኳስ እድገት ላይ ጠንካራ መሰረት ለመጣል ፍላጎት አሳድሮባቸዋል። ከተመለከቱት እምቅ አቅም አንፃር ታዳጊዎቹ የራሳቸውንም ሆነ የአገራቸውን የእግር ኳስ ደረጃ ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ሙሉ እምነት እንዲያገኙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

ቲኤፍ ኤ ኢሊት ከእድሉ አካዳሚ ጋር ስምምነት ካደረገ በኋላ ታዳጊዎችን ለመመልመልና ለማሰልጠን ተግባራዊ ስራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ባሳለፍነው ሳምንትም ከአካዳሚው ከፍተኛ አሰልጣኝ ከሚባሉት መካከል አሰልጣኝ ሰሚር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። አሰልጣኙ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታና ስልጠና ሲሰጥ በነበረበት ቀናቶች ወላጆችና ወጣቶች የነበራቸው ደስታ ከፍተኛ እንደነበር ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በሂደቱ የአሰልጣኝ እድሉ ደረጄ አካዳሚ ለታዳጊዎቹ ግንዛቤ በመስጠት እንዲሁም ለአሰልጣኙ የታዳጊዎቹን ብቃት በሚገባ እንዲረዱት ለማስቻል በጋራ መስራታቸውን የዝግጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You