ለምክክራችን ሁለንተናዊ ውጤታማነት

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፣‹‹የአስተሳሰብ ልዩነት፣ ፉክክርና የሚጋጭ ፍላጎት ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ችግሮች በአንድ ፓርቲ፣ በአንድ ቡድን ወይንም በጥቂት ሰዎች አይፈቱም። ጥቂቶች በር ዘግተው ቢጨነቁና ቢጠበቡም መፍትሔ ሊሆኑና ሊያመጡም ፈፅሞ አይቻላቸውም። በመሆኑም ልዩነቶችን ለማጥበብ ሆነ ለማስታረቅ፣ ከተናጥል ይልቅ የጋራ ውይይት ባሕልና ልምድ የግድ ነው›› ይላሉ።

በተለይ ዓለም አንድ በሆነችበት በዚህ ዘመን ከአግላይ Exclusive ይልቅ አሳታፊ Inclusive መሆን የግድ እንደሚልና አንደኛው ሌላውን ከሚያገል ጠባብ አስተሳሰብ ነፃ ወጥቶ ‹‹የጋራ ውሳኔያችን ትክክል ነው፣ አንድ ስንሆን እንጂ ስንለያይ በቀላሉ እንወድቃለን›› ‹‹Divided we fail United we Stand›› ወደሚል መርህ መምጣት እንደሚያስፈልግም ያሰምሩበታል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቃጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም ሀገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስታቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች ሀገር ናት። ሀገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባሕልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።

ውይይት የሞት ያህል የሚከብድበት፣ በአመለካከት የሚለዩ በጠላትነት የሚፈረጁበት ሀገር ሆናም ዓመታትን አስቆጥራለች። ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ›› እኔ የማስበው ሁሌም ትክልል ነው›› የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግርም ረጅም ጊዜ ሲያደምት ከርሟል።

‹‹ችግር ካለም እኛው የሥርዓቱ ባለቤቶች እንናገር እንጂ ሌላው ምን ቆርጦትና ምንስ አግብቶት ነው በሥርዓቱ ላይ ተችት የሚሰነዝረው?›› የሚለው ከእኔ እና ከእኛ ውጭ ላሳር አመለካከትና ተግባርም ኢትዮጵያና ሕዝቦችን በሁሉ ረገድ ሊቀይሩ የሚችሉ የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችንና መፍትሔች ሳይቀር ከስመው እንዲቀሩ ምክንያት ሲሆን ታይቷል።

ይሁንና ከህልውና ባሻገር ስለ እንደ ሀገር ስለመፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለዚህ ስንክሳር መፍትሔ መስጠት የግድ ይላል። ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የሕዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖራት ነው።

ይህ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ምን ዓይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን ዓይነት የዲሞክራሲ፣ የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ ሀገራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ መምከር ግድ ይላል። ለበርካታ ዓመታት በተለይ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት የውይይት እሳቤ በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት ሲነሱ ቆይተዋል።

ጥያቄው አግባብ ነው፣ ይሁን የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ግን አልነበረም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በአንጻሩ ይህን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ከመምከር በሩን ክፍት አድርጓል። ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመላከት ርምጃዎችን እየተራመደም ይገኛል።

በአንድ ሀገር ማህበራዊ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ውይይት በሳል ውሳኔን በማመንጨት፤ መተማመንን በማዳበር፤ ህብረትን አንድነትን በማጠናከር፤ እንዲሁም አሰራርን ለማሻሻል እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ የሚያከራከር አይደለም። ፈፅሞ ሊቀራረቡና ሊታረቁ አይችሉም የተባሉ ሃሳቦችና ከግለሰብ አንስቶ እስከ ሀገራት የተቀራረቡት እንዲሁም ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ለጋራ አላማ የተሰለፉት በምክክር ነው።

የአንድ ሀገር ትላንት፣ አሁንና ነገ ታሪክ የተወሰነውና የሚወሰነው ማህበረሰብ ተነጋግሮ ለመግባባት ባለው ልምምድ ልክ ነው። የውይይት የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም ግብ ሰላም እንድነትና እድገት እውን ማድረግ ነው። በብዙ ጥያቄና ልዩነት ውስጥ በምትዳክር ሀገር ላይ የኃይል አስተሳሰብ የፍቅርን በር አይከፍትም። ይህን ማድረግ የሚቻለው በምክክር ነው።

የሰላም እጦት ባለመግባባት የሚመጣ እንደሆነ ሁሉ አብሮነትም በመግባባት የሚመጣ ነው። በመነጋገርና በመመካከር ልዩነቶችን መፍታት ያልተለማመደ ሀገርና ሕዝብ በልዩነቱ ከመጠቃት ባለፈ እርባና አይኖረውም። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሃሳብ ልውውጥ በኩል የዳመነ ማንነታችንን ለማጥራት ረጅም ርቀት ተጉዞ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ይታወቃል። ክልላዊ የምክክር ሂደቱ ግንቦት 21 ቀን በአዲስ አበባ ላይ ጅማሮውን አድርጓል።

ከሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ጥረት በኋላ እውን በሆነው የምክክር ሂደት ጅማሮ ላይ ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አካታች እንዲሆን ለማድረግ የሄደበት ርቀትና ያደረጋቸው ጥንቃቄዎች በግልፅ ታይቷል። እነዚህ አስደናቂ ተግባራትም አድናቆት የሚገባቸውና ኮሚሽኑንማ እጅጉን ሊያስመሰግኑት የሚገቡ ናቸው።

ለኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ መፍትሔዎችን የምናመጣበት የአብሮነት ከፍታ የምንሸጋገርበት የለውጥ ድልድይ ነው። የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተሻለ የፖለቲካ ባሕል ግንባታና ለሁለንተናዊ እድገትን እጅግ ወሳኝ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶቻችንን አርቀንና አጥበን በእርቅና በይሁንታ አዲሷን ኢትዮጵያ የምንፈጥርበት ነው።

በሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ታተርፋለች እንጂ አትከስርም። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለው ላይ ግልፅ አቅጣጫን ያስቀምጣል። የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የዳበረች ዲሞክራሲያዊት ሀገር ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው። ይሁንና ምክክሩ እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል ከማንስ ምን ይጠበቃል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

የተለያዩ የሥነ ልቦናም ሆነ የፖለቲካ ምሁራንም አንድን ውይይት ምክክር ውጤታማ ለማድረግ ይረዳሉ የሚባሉ መሰረታዊ ነጥቦችን ሲያስቀምጡ፣ ከወገናዊነት ነፃ በመሆን ሚዛናዊ አስተሳሰብን ማራመድ፣ ሁሉም እኩል የሚያሸንፈበት /Win-Win Resolution/ መንገድ መከተል፣ ግልጸኝነት፣ ትእግስት፣ መደማመጥና የሌሎችን ሃሳብ ማክበር የግድ እንደሚል አፅእኖት ይሰጡታል።

በውይይት በምክክር ወቅት በሰዎች መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። የሃሳብ ልዩነቶች ደግሞ አላማንና ግብን የማያስቱ እስከሆነ ድረስ ተፈጥሯዊ ሰውኛ /Humanistic/ ናቸው። የሃሳብ ልዩነቶችን አቻችሎ ለመቀጠል ከሁሉም በላይ ውይይትን ውጤታማ ለማድረግ ግን በተለይ የሰጥቶ መቀበል መርህ እጅግ ወሳኝ ነው።

ሚዛናዊ ሆኖ የሌሎችን ሃሳብ ለማዳመጥ የራስንም ለሌሎችም ለማስረዳት መዘጋጀት ይገባል። አንድ ጥግ ይዘን የሌሎችን ሃሳብ በጥርጣሬ መመልከት ለስህተት ይዳርጋል። ይልቁንም የሃሳብ ልዩነቶችን በቅንነት በመመልከት ሌላው የሚያስበውን በሌላው ጫማ ሆኖ መረዳት የግድ ይላል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ከሁሉ በላይ በሁሉ ረገድ አካታች መሆን ይኖርበታል። ስለኢትዮጵያ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ወይም ደግሞ ጥያቄ አለኝ የሚሉን በትምህርት ደረጃ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በጾታ ሳይገድቡ ማሳተፍና ሃሳቦችን መውሰድ ለውይይቱ ፍሬያማነት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የተለያዩ ሃሳቦች ሊነሱ ቢችሉም ለምክክሩ የሚቀረጹት አጀንዳዎች በዋናነት ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡ መሆን ይኖርባቸዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ከሁሉ በላይ ከግልና ከቡድን ይልቅ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም የግድ ይላል። በዚህ ረገድ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የሀገር ህልውና የገዢ ፓርቲ አሊያም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም። እንደ ዜጋ ወይም እንደ ፓርቲ መንቀሳቀስ የሚቻለውም ሀገር ስትኖር ብቻ ነው። ሀገርን አንድነት የሚጠብቁና የሀገርን ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልዩነት ሊኖረው አይገባም።

ለምክክሩ ውጤታማነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምሁራን ሚና የላቀ ነው። በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። እንደ ሀገር ሳያግባቡ የቆዩ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በመለየትና የሚፈቱበትን መንገድ በማመላከት ውይይቶቹ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ችለዋል። ይህን መንገድ የሀገራችን ምሁራንም ሊራመዱበት ይገባል። መገናኛ ብዙሃኑ መድረኩን የሚዘግቡበት መንገድ በራሱ በጥንቃቄና በአግባቡ ሊቃኝና ከወዲሁ ተገቢው ዝግጅት ሊደረግበት የሚገባው ነው።

ነፃና ገለልተኛ፣ የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለበት የምክክሩ መድረኩ፣ የምንፈልገውን እንዲሰጠን መድረኩ የሚፈልገውን ልንሰጠው ይገባል። ልባችንን ለፍቅርና ለይቅርታ፣ ለእርቅና ለአብሮነት አስገዝተን ከሆነ ለእርቅ የተቀመጥነው መድረኩ የሚሰጠን ብዙ ነገር አለው።

እኛም የራሳችንን ግዴታ በመወጣት ለሰላም በተከፈተው በር ውስጥ አልፈን ዐሻራችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል። ስለሰላምና ፍቅር እያሰማናቸው ያሉ የእርቅ ድምጾች ጎልተው መሰማታቸው አለባቸው። የብሔርና የዘረኝነት ካባዎች መውለቅ አለባቸው። ወንድማማችነታችንን ያደበዘዙ የቡዳኔና የጎጠኝነት መንፈሶች መሟሸሽ አለባቸው። ብዙሀነታችንን ያሳነሱ የእኔነትና የብቻነት ደዌዎች መሻር አለባቸው።

አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ሀገራዊ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ ሁሉም ጥያቄ ፈጣን መልስ ይኖረዋል ብሎ ማሰብም አግባብ አለመሆኑ ነው። የእያንዳንዱ ምክክር መልስ የሂደት ውጤት መሆኑን ጠንቆቆ መገንዘብ ያስፈልጋል። ‹‹ጥያቄው ላይ ዛሬ ተወያይተናል መልሱን ዛሬ ካልሆነም ነገ እንፈልጋለን›› ብሎ ማሰብም ግዙፍ ስህተት መሆኑን መረዳት ይገባል። ‹‹ሀገሬን እወዳለሁ›› ስንል ግን የእለት ተእለት ተግባራችንም ይህንኑ ቃላችን የሚያስታውስና የሚያስመሰክር ሊሆን ይገባዋል። ሀገሩን የሚወድ በሀገሩ ጉዳይ ዳር ተመልካች አይሆንም። ሀገሩን የሚወድ የሀገሩን ጥቅም ያስከብራል።

ሀገሩን የሚወድ ለሀገሩ ዘብ ይቆማል። ሀገሩን የሚወድ ፍላጐቱን ከሀገሩ ፍላጎት አያስበልጥም። በአጠቃላይ ሀገሩን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለሀገሩ ህልውና መሆኑ የሚያከርክር አይደለም። ከፊታችን እጅግ ብዙ ሥራዎች ይጠበቁናል። ዛሬ ላይ በጋራ የፈነጠቀናትን የእድገት ጭላንጭል ወደ ተንቆጠቆጠ ደመራ ለማሸጋገር እልህ አስጨራሽ ትግሉ ከፊታችን ተደቅኗል። ፍልሚያ በድል መወጣት ካለብን ደግሞ ቆሞ ቀርነት ማስወገድ ከንትርክ ይልቅ ውይይት ምክክር ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ የግድ ይላል።

ከፍታችንን ለማዝለቅ የነበርንበትን የኋሊት እያስታወስን፣ ከምናደንቀው ተምረን የቆሞ ቀርነት ታሪካችንንም አውግዘን በሌላ አነጋገር ከስኬታችንም ከጉድለታችንም እውቀት ቀስመን ወደፊት መሮጥ ይኖርብናል። ይህን ፍልሚያ አሸንፎ መውጣት ካለብን ጅማሪያችን እንዲህ ካሉ ተግባራት መሆን ይገባዋል። የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ መገንባት የምንችለው ይህም ሲሆን ነው ።

በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ እንደሌሎች የውይይት መድረኮች ተድበስብሶ የሚቀር ሳይሆን የሚዳሰስ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት መልክ ሊቃኝ ይገባል። ለዓመታት ስንጠይቅ የመጣን ከመሆናችን አንፃር በጣም በጥንቃቄና በጥሩ ዝግጅት መካሔድ ይኖርበታል። ለዚህ እጅግ ወሳኝ ታሪካዊ ሁነት ሁለንተናዊ መሳካትም ሁሉም የበኩሉን መወጣት የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባሩ መሆን አለበት።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You