‹‹የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሁሉም አካላት ትኩረትና ርብርብ ያስፈልጋል›› -ብርሃነመስቀል ጠና (ዶክተር) የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ መምህራን ኮሌጅ ሆኖ በርካታ መምህራንን ለኢትዮጵያ አበርክቷል። የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ። በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስያሜ አግኝቶ በርካቶችን አሰልጥኖ አስመርቋል። ጉዞው በዚህ አላበቃም። ኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በሚል ስያሜ በከተሞች ዙሪያ ዕውቀት ለመገብየት የሚስችል ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ተቋቋመ።

ይሁን እንጂ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፈልግ አመላክቶ ነበርና በ2013 ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሚል እንደገና እንዲደራጅ ተደርጓል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ዩኒቨርሲቲው ብቁ መምህራን ለማፍራት፣ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ከመሥራት በአጠቃላይም የትምህርት ዘርፉ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ከመቅረፍ አንጻር እያከናወናቸው ባሉ ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ:-

 አዲስ ዘመን፡- ውይይታችንን ተቋሙ ዛሬ ላይ ለመድረስ ያለፈባቸው ሂደቶች ምን ይመስላሉ ከሚለው ብንጀምር ጥሩ ይመስለኛል።

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ወደኋላ ዳራውን ተመልሰን ስናይ እንደ ተቋም ካየነው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የትምህርት ዓይን ከፋች ተቋም ነው። እንደነጸጋዬ ገብረመድህን፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤልን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የተማሩበት የመደበኛ ትምህርት ዓይን ከፋች ተቋም ነው። በ1935 የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ መደበኛ ትምህርት ማስተማር የጀመረ ነው።

ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ መምህራን ኮሌጅ ሆኖ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ለኢትዮጵያ ያበረከተ አንቱ ሊባል የሚገባው ትልቅ ተቋም ነው። የዚህ ተቋም ዐሻራ የሌለበት ኢትዮጵያዊ የለም።

ተቋሙ እንደዚህ አንጋፋ፣ ብዙዎችን ያፈራና በብዙሃኑ ሕዝብ ላይ ዐሻራውን ያሳረፈ ከሆነ ለምን እንደስሙ ሳያድግ ቆየ የሚለው ደግሞ ያነጋግራል።

ተቋሙ እንደስሙ ሳያድግ የቆየበት ምክንያት የነበሩት ሥርዓተ መንግሥታት ባሳረፉበት ጫና ነው። ሰውና ተቋምን ለይቶ ባለማየት በሰዎች ላይ ባላቸው ግላዊ ግጭትና ጥላቻ ተቋሙ ወደኋላ እንዲቀር ተደርጓል።

በ2006 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ስያሜ ተሰጥቶት በአዲስ አበባ ስር እንዲደራጅ ተደረገ። ለሦስት ዓመታት በዚህ ስያሜ እንደቆየ በ2009 እኔ ፕሬዚዳንት ሆኜ መጣሁ። ፕሬዚዳንት ሆኜ ስመጣ የመጀመሪያ ሥራዬ የነበረው ተቋሙን ወደ ትልቁ ቁመናው መመለስ ነው።

በዚህም ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በሚል ስያሜ የከተማ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ተቋቋመ። በዚህም ብዙ ነገሮች እንዲስተካከሉና የዩኒቨርሲቲ ቁመና እንዲይዝ ተደረገ። ለአምስት ዓመታት በሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲነት በርካታ ዜጎችን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል። ያም ብቻ አይደለም። ፕሮግራሞቻችንን ወደ ዶክትሬት ዲግሪ እያሳደግን መጣን። በዚህም ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ሆነ። ለውጥ ሲመጣ ግን በመንግሥት ለውጥ ያስፈልገዋል ተብሎ ከታስቡት ተቋማት አንዱ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት 100 ዓመታት አንድም የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይኖራት ትምህርትን ስትመራ የኖረች ሀገር ናት። ላለፉት 100 ዓመታት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አልነበረንም። ነገር ግን ሌሎች ዩኒቨርሲዎች ነበሩን። ለትምህርት ግን ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አለ፤ በየክልሎችም መምህራን ኮሌጆች ነበሩ። በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም አንዳንድ የትምህርት ኮሌጆች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ግን መምህራን ኮሌጆች ናቸው እንጂ የትምህርት ኮሌጆች አይደሉም። የትምህርት ኮሌጅ በባህሪው ይለያል።

ስለሆነም በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ደረጃ ስለዩኒቨርሲቲው ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርበን ባስረዳንበት ወቅት ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ነው ወይ የሚያስፈልገው ለኢትዮጵያ? ከእርሱ ይልቅ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አይደለም ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ተደረገ። ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የከተማ ምህንድስና አለው፣ የቢዝነስ ፋካሊቲ አለው፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅም አለው።

የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ አልያም ጳውሎስ መሄድ ይችላል። የቢዝነስ ፋካልቲውም ስድስት ኪሎ አልያም ኮሜርስ መሄድ ይችላል። የከተማ ምህንድስናው ደግሞ ልደታ እንዲሁም አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሄድ ይችላል። ለምንድነው ባለን ላይ ተጨማሪ የምናደርገው የሚለው ነገር ትልቅ አጀንዳ ነበር። የሚያስፈልገን ግን የሚጎድለንን የሚሞላ ተቋም መሆን አለበት የሚለው ሃሳብ ሁላችንንም ያስማማ ነበር። በዚህም በመልሶ ማደራጀቱ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ተወሰነ።

ይህ ውሳኔ ሲተላለፍ ለእኔ የተሰጠኝ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 በተቋማት መልሶ ማደራጀት ሂደት ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል የሚል ደብዳቤ ብቻ ነበር።

ከባዱ ሥራ የመጣው ከዚህ በኋላ ነበር። የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በምን ፍልስፍና ነው የሚመራው፣ ከሌላው ዩኒቨርሲቲ የሚለየው በምንድነው? ማንንስ ነው የሚያሰለጥነው በምንስ ሥርዓተ ትምህርት ነው የሚያሰለጥነው የሚሉና ሌሎችም ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ነበሩ።

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በዓለም ላይ ያሉ የትምህርት ዩኒቨርሲቲዎችን ልምድ ማሰስ ጀመርን። በዚህም በብዙ ድካም ዩኒቨርሲቲውን እውን ማድረግ ችለናል። አሁን ላይ ሲታይ በቀላሉ የተቋቋመ ቢመስልም ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው።

በዚህ ሂደትም የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን ፍኖተ ካርታ መቅረጽ ችለናል። በፍኖተ ካርታውም ተቋሙ ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት መበየን ነበረብን። ፍኖተ ካርታውን ተሠርቶ በባለሙያዎች እንዲገመገም ተደርጓል።

በ2010 የተሠራው የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፈልግ አመላክቶ ነበር። ዩኒቨርሲቲው የፍኖተ ካርታው የጥናት ውጤትም ነው።

ይህን መነሻ በማድረግም የዩኒቨርሲቲውን ፍኖተ ካርታ ሠራን። በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ 800ሺህ በላይ መምህራን አሉ። ከ40 ሺህ የማያንሱ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም ይገኛሉ። ለምንድነው ይህንን ሁሉ መምህር ይዘን ትምህርት ወደቀ የምንለው። ስለውድቀት ለምንድነው የምናወራ? ውድቀቱስ ይህን ያህል ስር የሰደደ መሆን ነበረበት ወይ? ይህ ከሆነ የልጆቻችንን እጣ ፋንታ ምንድነው? ይህን ስብራት መጠገን ያለበትስ ማነው የሚለው ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።

ለዚህም ፍኖተ ካርታውን መነሻ በማድረግ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት በዳይሬክተር የሚመሩ አምስት ማዕከላትን አቋቁሟል። በእነዚህ ማዕከላትም ፈተና አዘገጃጀትና ምዘና አሰጣጥ፣ የጥናትና ምርምር አካሄድ፣ የሥራ ላይ ስልጠና መስጠትን ጨምሮ በሌሎችም የትምህርት ሥራዎች ላይ ተገቢውን እውቀት ለማስጨበጥ የሚያግዙ ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ ዩኒቨርሲቲው ብቁ መምህራንን ለማፍራት ምን እየሠራ ነው? ተማሪዎችንስ የሚቀበለው በምን መልኩ ነው?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- አዳዲስ መምህራንን ከማሰልጠን ባለፈ በከፈተው የሥራ ላይ ስልጠና መስጫ ማዕከል አማካኝነት በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀው በማስተማር ላይ ላሉ ዜጎች የሥራ ላይ ስልጠና ይሰጣል። የዚህም ስልጠና ዓላማም መምህር ሳይሆኑ መምህር የሆኑ ዜጎችን መምህር ማድረግ ነው። ይህም በክረምት ስልጠናና በተለያዩ ሁኔታዎች ይሰጣል።

ዛሬ ላይ ወደ አንድ የግል ትምህርት ቤት ብትሄዱ ከሚያስተምሩት መምህራን ውስጥ አብዛኞቹ በማስተማር ሙያ የተመረቁ አይደሉም። የሆነ ጊዜ ምን አጋጠመኝ ሃይድሮሊክ ኢንጅነሪንግ ተመርቃ ልጆች እያስተማረች አገኘኋትና እዚህ ምን ትሰሪያለሽ ብዬ ስጠይቃት ሥራ ስላጣሁ ነው የሚል ምላሽ ሰጠችኝ። ይህ የብዙ ትምህርት ቤቶች እውነት ነው። እነዚህ ሰዎች የእኛን ልጆች ነው የሚያስተምሩት። በተሳሳተ ሰው ስለሆነ እየተማሩ ያሉት ይጠፋሉ። ስለሆነም እነዚህን ሰዎች የሥራ ላይ ስልጠና መስጠትና ማብቃት ያስፈልጋል።

ማስተማርን መቆያ ሳይሆን ወደውት እንዲያስተምሩና የማስተማር ሥነ ዘዴውን ለማስተማር ነው ማዕከሉን የከፈትነው።

እስከ ባለፈው ዓመት የነበረው የቅበላ ሥርዓት ጥሩ አልነበረም። ከመቶ ሀምሳ እንኳን ማምጣት ያልቻሉ ተማሪዎች በመልሶ ቅበላ ሥርዓት እንዲመደቡ የሚደረግበት ሁኔታ ነበር። አሁን ላይ ግን ትምህርት ሚኒስቴር ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ይመድባል። ዩኒቨርሲቲው በራሱ የመምህርነት ስልጠና መውሰድ የሚፈልጉ ተማሪዎችን የመቀበል ነፃነት ተሰጥቶታል። በዚህም መስፈርቱን የሚያሟሉና ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ተመዝግበው ስልጠና እንዲወስዱ እያደረግን ነው። በዋናነት ግን እንደ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስደው የተሻለ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ይመደባሉ። ይህ አንድ ተስፋ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ልክ እንደ ሕክምናና ሌሎችም መስኮች ለመምህርነት ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች እንዲመደቡ ማድረጉ ትልቅ ነገር ነው። ተጠናክሮ መቀጠልም ይኖርበታል።

ዩኒቨርሲቲው የተቀበላቸውን ተማሪዎች በእውቀትና በክህሎት ለማብቃት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።

ይሁን እንጂ በየዓመቱ እየተቀበለ ያለው ከ600 እስከ 700 የሚሆኑ ተማሪዎችን ብቻ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በቂ የተማሪዎች ማደሪያ ባለመኖሩ ነው። በመሆኑም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መገንባት ይኖርበታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር 17 ሺህ ሄክታር ቦታ ሰጥቶናል እዛ ላይ የምንገነባ ነው የሚሆነው። ይሁን እንጂ እንደ ሀገር ካለው የትምህርት ጥራት ችግር አንጻር መምህራን ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት የሚጠይቅ ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ምክንያቱም ዛሬ ጥሩ ዘር ካልዘራን ነገ ጥሩ አዝመራ አንሰበስብም። ነገ ላይ የሰለጠኑ ሰዎችን የምናፈራው ዛሬ በምንዘራው ዘር ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ያለበትን የተማሪዎች ማደሪያ እጥረት መቅረፍ ይኖርበታል። አይሲቲን ጨምሮ የመሠረተ ልማትና የላብራቶሪም ችግር አለበት። ይህ ትልቅ በጀት የሚጠይቅ ነው።

መንግሥት በጀት መድቦ እያገዘን ነው። አሁንም ይህንን ድጋፍ አጠናክሮ ከቀጠለ የተሻለ ሥራ መሥራት እንችላለን።

በምቀበላቸው ጥቂት ተማሪዎች ብቻ የኢትዮጵያን ትምህርት ችግር ልንፈታ አንችልም። አሁን ላይ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንትና የቦርድ አባላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው። የባለድርሻ አካላት ትብብር ከታከለበት ችግሩ ይቀረፋል ብየ አምናለሁ።

አንድ መሀንዲስ ተበላሽቶ ቢወጣ ሕንፃ አልያም መንገድ ነው የሚያበላሸው። የተበላሸውን ሕንፃም ሆነ መንገድ ማስተካከል ይቻላል።

አንድ መምህር ከተሳሳተ ግን ትውልድ ነው የሚያጠፋው። የተበላሸው ቡሉኬት አልያም ግንባታ ተመልሶ ይጠገናል። ቢፈርስም ሌላ ይሠራል ምንም ችግር የለውም። ትውልድ ከተሰበረ በምን ይጠገናል? ትውልድ ከተሰበረ በምንም ስለማይጠገን ትውልድ የማይሰበር ይልቁንም የሚገነባ መምህር እንዲፈጠር ነው መሥራት ያለብን።

ዛሬ ከዚህ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የሚወጣው ልጅ ነገ የልጆቻችን አስተማሪ ስለሚሆን ተሰብሮ ወጥቶ ነገ ልጆቻችንን እንዳይሰብርብን በእውቀትና በክህሎት በቅቶ እንዲወጣ እናደርገዋለን። ይህን ለማድረግ ደግሞ ምሁራንን እያሰባሰብን ከተማሪዎች ጋር እንዲመክሩና ልምድ እንዲቀስሙ እናደርጋለን። በዚህም ሰልጣኖች ውስጥ መነሳሳት እንዲፈጠርና ተስፋ ያላቸው መምህራን እንዲፈጠሩ እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፦ ለረጅም ዓመታት በትምህርት ዘርፉ አገልግለዋል። አሁንም በሀገሪቱ የመጀመሪያና ብቸኛ የሆነውን የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይመራሉ። በእርስዎ እይታ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ዋነኛ ችግር ምንድነው ይላሉ?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ እኔ ሕይወቴም ኑሮዬም ትምህርት ነው። ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ያለውን ትምህርቴን የተከታተልኩትም በትምህርት ዙሪያ ነው። በእኔ እይታ የኢትዮጵያ ትምህርት ዋንኛ ችግሮች ሁለት ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ችግር ባለፉት ዓመታት ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ከመፍታት ይልቅ በጨበጣ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ነው። ችግሩን በጥናት ለይቶና መፍትሔዎችን አስቀምጦ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ችግርን በስብሰባ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ይስተዋል ነበር። ሁለተኛው ችግር ደግሞ ጥናት ተብለው የሚቀርቡ ጥናቶችም በረጂ ድርጅቶች ላይ የተንጠለጠሉ መሆን ነው። ጥናቱ በርዳታ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ የሆነ ሀገር የተሠራውን ጥናት አምጥተው የስም ለውጥ ብቻ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠና አስመስለው ያቀርቡ ነበር። ይህም የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል።

እነዚህ ጥናቶች በርካታ የሀገር ሀብት ቢፈስባቸውም መሠረታዊ ችግሩን የለዩ ባለመሆናቸው ችግሩን ሊፈቱት አልቻሉም።

ትምህርት ተሰብሮ ብልጽግና አይረጋገጥም፤ ትምህርት ተሰብሮ ልማት ሊለማ ይችላል ግን ያልተማሩ ሰዎች መጥተው ያፈርሱታል።

ልማታችን ሰው ተኮር ካልሆነ ከባድ ነው። መሰል ችግሮችን ለማስቀረት ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ላይ የሠራነው በሀገራችን ምሁራን የተዘጋጀ ሀገር በቀል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ነው። በዚህም የእኛን ችግር ማዕከል ያደረገና ራዕያችንን የሰነቀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ነው ያዘጋጀነው።

ችግሩ ሰፊ ስለሆነ በቀላሉ ለመውጣት ሊከብደን ይችላል። ግን ያለ ሀገራዊ አቅሞቻችን አስተባብረን ከተጠቀምን ለውጥ የማናመጣበት ምክንያት አይኖርም።

አዲስ ዘመን:- ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባለፈ በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየትና የመፍትሔ ሃሳቦችን ማመላከት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከመሥራት አንጻር እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማን አንኳር ችግሮች ለመፍታት በግምባር ቀደምትነት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለው ይህ ዩኒቨርሲቲ ነው። አሁን ላይም በርካታ ጥናቶችን ለከተማ አስተዳደሩ በመሥራት ላይ እንገኛለን። የምንሠራቸው ጥናቶች መሬት የሚያርፉ እንዲሆኑ አንፈቅድም። ጥናቱ ወርዶ አንድም ሰው ችግር ቢሆን መፍታት መቻል አለበት። ምክንያቱም ያ ጥናት የሚሠራው በደሃ ሕዝብ ገንዘብ ነው። አንድ ተቋም ላይ ጥናት ስንሠራ የችግሩ ትክክለኛ ቦታ የቱ ጋር እንደሆነ እናመላክታለን። ያ ተቋም ደግሞ ያን ወደ መሬት አውርዶ ችግሩን መቅረፍ ይኖርበታል።

ወደ ትምህርት ስንመጣ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያን ትምህርት ችግር ሊፈቱ የሚችሉ አራት ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ጥናት እያካሄድን እንገኛለን። እነዚህ ጥናቶች ለትምህርት ሚኒስቴር ግብዓት ይሆናሉ። ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ያንን ወስዶ ወደ ትግበራ የሚገባውን ወደ ትግበራ ያስገባል። እውቀት የሚያገኝበትን እውቀት ያገኝበታል። የት ላይ ማተኮር እንዳለበት ይረዳበታል።

አዲስ ዘመን፡- የመምህርነት ሙያ የተከበረና የሁሉም ሙያዎች ምንጭ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ከሙያው ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተዛቡ አመለካከቶች ይስተዋላሉ። ይህን የተሳሳሰተ አመለካከት ከመቅረፍ አንጻር ምን መሠራት አለበት ይላሉ?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ እዚህ ላይ ሁለት ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። የመጀመሪያው ሙያ ከገንዘብ ጋር ከተገናኘ ዋጋ የለውም። አንድ ሐኪም ቀዶ ጥገና እየሠራ ስለደመወዝ ካሰበ ታካሚውን ይገድላል ማለት ነው። ማንኛውም ሰው የገባበትን ሙያ ማክበር አለበት። ከዛ ባለፈ ደግሞ አንድ ሙያተኛ መኖር መቻል አለበት። መንግሥትና ሕዝብ ስለመምህራን ማሰብ አለበት። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የመምህራንን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። መምህራን ደግሞ ዕለታዊ ችግሩን በትውልድ ላይ ላለመመንዘር መጣር ይጠበቅባቸዋል። ጥናት ምርምር ማድረግን ጨምሮ ያሉ አማራጮችን ሁሉ መመልክት ይኖርባቸዋል። በዚህ ሂደት እነሱም ይጠቀማሉ የሕዝብንም ችግር ይፈታሉ።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ሃሳብና የሚያስተላልፉትም መልእክት ካለ እድሉን ልስጥዎት።

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ የኢትዮጵያ የትምህርት ችግር እንዲፈታ የመንግሥት ትኩረትና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል። ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲም መንግሥት ሙሉ ትኩረት መስጠትና ሊሟሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዲሟሉ ከማድረግ አንጻር እንዲያግዘን እንፈልጋለን። ዩኒቨርሲቲውም ዘር ላይ የሚስተዋለውን ችግር ከመቅረፍ አንጻር የበኩሉን ሚና ለመወጣት በቁርጠኝነት የምንሠራ ይሆናል። ሕዝቡ ደግሞ በየአካባቢው ልጆቹን ለማስተማር የሚሄዱለትን መምህራን ማክበርና ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚል መልእክት ነው ማስተላለፍ የምፈልገው።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን።

ዶክተር ብርሃነመስቀል፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You