ከቃልም በላይ በተግባር

ተግባር ከቃላት በላይ ትርጉም አለው። በቃላት ያልነበረው እንደነበረ ሊነገር፣ ያልሆነው እንደሆነ ሊሞካሸ እና ሊሞገስ ይችል ይሆናል፤ ይህ ግን ለተወሰነ ጊዜ እንጂ ሊዘልቅ የሚችል አይደለም። ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ተግባር ብቻ ነው። ለእዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል ዋናዎቹ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ናቸው።

ተግባር ከቃል በላይ ኃያል ሆኖ የሚታይበት ይህ የኢትዮጵያ ልጆች የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ መርሀ ግብር ከዓመት ዓመት ባህል እየሆነ እና እያደገ መጥቷል። ይህ ደግሞ በየአመቱ በተተከሉ ብዙ ቢሊዮን ችግኞች ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የችግኝ ተከላው እያመጣ ባለው ተፈላጊ ለውጥም ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ፣ የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አካባቢዎችም ወደ ቀድሞ ገጽታቸው እንዲመለሱ እያስቻለ ይገኛል። ይህንንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት ተሰጥቷል። ሂደቱም እየተመናመኑ እና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ አስተዋጽኦም እያበረከተ ይገኛል። ለብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ ትልቅ እድል የሰጠ በመሆኑም፣ የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋት እንዲያንሰራሩ በማድረግ በኩል የጎላ ሚና ይጫወታል።

የተፈጥሮ ስነ ምህዳሩም እንዲስተካከል በማድረግ ተኪ የሌለው ሚና ይጫወታል። የተረጋጋ ስነ ምህዳር መፈጠሩን ተከትሎም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖር መናገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆናል።

የአረንጓዴ አሻራ ጠቀሜታ ከዚህ ሁሉም ይሻገራል። የደን ሽፋንን በመጨመር ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን የመቀነስ አቅም እንዲያድግ ያግዛል። ይህ ደግሞ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል። በሌላ በኩልም ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረትም ያግዛል፤

ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምሯል። ለእዚህም የአቮካዶ ተክል ልማቱ በአብነት ይጠቀሳል። በመርሃ ግብሩ የተተከሉ የአቮካዶ ችግኞች ፍሬ መስጠት ከመጀመራቸውም በላይ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ስለመሆናቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ናቸው።

በየአመቱ በመርሃ ግብሩ እየተተከሉ የሚገኙት ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችም ደርሰው ፍሬ መስጠት ሲጀምሩ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። አምና በስፋት ከተተከሉት ችግኞች መካከልም ማንጎ እና አቮካዶ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ችግኞች ማፍራት ሲጀምሩ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የራሳቸውን ፋይዳ ያበረክታሉ።

በአምስተኛው ዙር የተተከለውን ሳይጨምር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ባካሄደችው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተተከለው የችግኝ ብዛት 25 ቢሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የሚውሉ ችግኞች የማዘጋጀቱ ስራ ተጀምሯል። 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል። እስካሁንም ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን አካባቢ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ይህም ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከታቀደው በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የሚያመለክት ሲሆን፤ ስራውም ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ መመልከት የሚቻልበት ነው።

ችግኞቹን በአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ላይ ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታሩን ዝግጁ ማድረግ ተችሏል። ቀሪውም በቀጣዮቹ ጊዜያት ዝግጁ ማድረግ እንደሚቻል በዝግጅት ምዕራፉ የተከናወነውን በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል።

ዘንድሮ 2016/17 በ132 ሺ 144 ችግኝ ጣቢያዎች ችግኝ በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። በመንግሥት፣ በግልና በህብረት ስራ ማህበራት ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ችግኝ የማዘጋጀቱ ስራ እየተካሄደ ሲሆን፣ ከችግኞቹ መካከልም 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚሆኑት ተቆጥረው ለተከላ እየተዘጋጁ ይገኛሉ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በአንድ በኩል ስነምህዳሩን ማስተካከልን ታሳቢ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጓል። ዘንድሮ ሊተከል ከታሰበው መካከል 60 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ለፍራፍሬ፣ ለደን ልማት፣ ለመኖ እና ለአፈር ለምነት ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንዲተከሉ ታሳቢ በማድረግ በስፋት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። 40 በመቶ የችግኝ ዝግጅቱም ለውበት እና ለደን ልማት አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች ላይ አተኩሯል።

የደን ልማት በጣም ወሳኝም አስፈላጊም መሆኑን መገንዘብም ይጠቅማል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ 80 በመቶ የአለም እፅዋት በደን ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ እጽዋት ኑሯቸውን በጫካ ውስጥ ላደረጉ እንስሳት መኖሪያ ናቸው። ለመድሃኒትነትም በግብአትነት ያገለግላሉ።

በአለም አቀፍ ደረጃም ከአምስት ሰዎች አንዱ ኑሮው በደን ላይ የተመሰረተ ነው። በከባቢ አየር ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጨመር አንዱ ምክንያት የደን ውድመት ነው።

ችግኞችን በመትከል 500 ቢሊዮን ዛፎችን ማድረስ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የካርበን መጠን በ25 በመቶ ለመቀነስ ይረዳል። በዚህም የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ ይቀንሳል። ዛፎች ለውሃ መጎልበትም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ይህ ሁሉ ሲታሰብ ኢትዮጵያ የያዘችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው። ተግባሩ አርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት አማራጭ በመሆኑም ገበያን ያረጋጋል፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛል፤ ወደስርዓተ ምግብ ሽግግር የተጀመረውን ተግባርም ይደግፋል፣ ምርቱን ወደውጭ ልኮ ምንዛሬ ለማስገኘትም ያስችላል።

አምና በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ብቻ የተተከለው የችግኝ ብዛት 560 ሚሊዮን ነበር። ዘንድሮ ከዚህ በላይ ችግኝ በመትከል በአለም ታሪክ እንደሚመዘገብ ይጠበቃል። ለዚህም ከወዲሁ ስራዎች ተጀምረዋል። እቅዱን እውን ለማድረግ ዘንድሮም በብዛት በአንድ ጀምበር የሚተከሉ ችግኞች የሚካሄድበት ወቅት በእቅዱ ተካትቷል። ይህም ነሐሴ ወር እንደሚከናወን ይጠበቃል።

ተግባሩ በአለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ታሪክ ሆኖ እንዲመዘገብ ለማድረግም ከወዲሁ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በአንድ ጀምበር በሚተከሉ ችግኞች መርሃ ግብር የሚሳተፈው የህዝብ ብዛት በሚሸፈነው ተሳታፊነት ከኢትዮጵያውያን የበለጠ የሰራ ሀገር የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።

ሆኖም በአንድ ጀምበር ታሪኩ በተከለው የችግኝ ብዛት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ማስመዝገብ የተቻለ አልሆነም። ዘንድሮ ግን ይህንንም እውን ለማድረግ ስራዎች መጀመራቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በዚህ ታሪካዊ ሂደት አሻራውን ለማሳረፍ ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል።

ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤ በዘርፉ ሙያተኞች በተደረገው ክትትልም ከተተከሉት ችግኞች መካከልም 90 በመቶው ጸድቀዋል። ውጤቱን ለማስመዝገብም የአመራር እና የባለሙያ ድጋፍና ክትትል ሥራ ከፍተኛ እንደነበር ማንሳት ይቻላል። ትግበራው በአጭር ጊዜ ውጤት የታየበት፣ በተግባር ታጅቦ በየአመቱ ችግኞች እየተተከሉ የዘለቁበት መርሃ ግብር ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልትን ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ የተወሰደው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የቃላት ሳይሆን፣ በተግባር የታየ ነው ሲባል የሚነገር ብቻ ሳይሆን የሚታይ፣ ተሞክሮውም ለጎረቤት ሀገራት፣ ለአህጉርና ለአለምም የሚተርፍ፣ ከቃልም በላይ በተግባር መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።

ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You