ከመስህብ ልማት ወደ መዳረሻ ልማት ያደገው የክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ

ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል፣ ታሪክና እና ሌሎችም መስህቦች ባለቤት ከሆኑ አገራት ተርታ በቀዳሚነት የምትሰለፍ ነች። ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ አገረ መንግስት፣ በአርኪዮሎጂ ጥናት ምድረ ቀደምት የሚል ስያሜን ያሰጣት የሰው ዘር መገኛ ነች። በተፈጥሮ የታደለች፣ የብዝሀ ህይወት መገኛና የልዩ ልዩ መልከዓ ምድሮች ስብጥርንም በጉያዋ ይዛለች። በሃይማኖት፣ በባህላዊ ምግብና መጠጥ፣ በአልባሳትና ውዝዋዜ ታድላለች። የእነዚህ ሁሉ ጸጋዎች ባለሀብት የሆነችው ይህች ሀገር እነዚህን ሀብቶች ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች ማጋራት የሚያስችል አቅምም አላት፤ እንግዳ ተቀባይነቷን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ ሁሉ ሃብቶች አንድ ስፍራ ወይም አካባቢ ላይ የሚገኙ አይደሉም። ይልቁኑም በሁሉም አቅጣጫና ክፍሎች የምናገኛቸው መስህቦች ናቸው። አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሶፍኡመር፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የሃረር ጀጎል ግንብ ጎንደር ፋሲለደስ፣ የባሌ፣ ስሜን እና ሌሎችም የተፈጥሮ ብሄራዊ ፓርኮች አንዲሁም ባህላዊ እሴቶች (የሸዋልኢድ፣ የፊቼ ጫምባላላ፣ የጊፋታ ሌሎችም ሀይማኖታዊ ትርጉም ያላቸው ትውፊታዊ የባህል እሴቶች) በመላው ኢትዮጵያ ብንጓዝ ህያው ሆነው የምናገኛቸው የመስህብ ሀብቶች ናቸው።

ይሁን እንጂ የታደልነውን ሀብት ያህል ወደ ቱሪዝም ኢኮኖሚ ምንጭነት የቀየርነው ሲሶውን አይሆንም። ያለንን የመስህብ ብዛት ያክል ወደ መዳረሻነት የቀየርነውና የቱሪስት መዳረሻ ያደረግነው እጅግ ጥቂት የሚባሉትን ነው።

በኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ ባህል፣ ታሪክና መሰል የቱሪዝም ሀብት ከታደሉ ስፍራዎች ውስጥ የሲዳማ ክልል አንዱ ነው። እነዚህን መስህቦች በማልማት፣ በማስተዋወቅና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ ግን አሁንም የሚቀሩ በርካታ ስራዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ‹‹በክልሉ የሚገኙ መስህቦችን ወደ መዳረሻነት ለመቀየርና ማህበረሰቡንና አገርን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው›› ስንል የሲዳማ ክልል የባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊ አበበ ማሬሞ ጋር አጭር ቀይታ አድርገናል።

እሳቸው እንደሚሉት የሲዳማ ክልል የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና ልዩ ልዩ መስህቦችን የያዘ ነው። ይሁን እንጂ ሀብቱ በራሱ በቂ የቱሪዝም ገበያ የሚፈጥር አለመሆኑን ይገልፃሉ። ሀብቶቹም ወደ ቱሪስት መዳረሻነት ተቀይረውና የልማት ስራዎች ተከናውነው ጎብኚዎችን ማስተናገድ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚገባ ይገልፃሉ።

‹‹ቱሪስቶች የተለያየ ፍላጎት ነው ያላቸው›› የሚሉት አቶ አበበ፤ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች እንዲሁም እያንዳንዱም በተናጠል ፍላጎታቸው እንደሚለያይ ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት የመዳረሻ ልማቶቹ ሲከናወኑ እነዚህን መሰረት ያደረጉና በጥናት ላይ የተመሰረቱ መሆን እንደሚገባቸው ይገልፃሉ። እንደ አገርም ኢንዱስትሪው ላይ የሚታየው ክፍተት ይህንን በተግባር መሬት ላይ ማውረድ ላይ እንደሆነም ይገልፃሉ። በተለይ ብዝሀ ፍላጎት ያላቸውን ጎብኚዎች እንደየ ፍላጎታቸው ማስተናገድና ከዚያ ከሚገኘው ሀብት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችል አደረጃጀት እስካሁን እንዳልተፈጠረ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እምቅ መስህብ ቢኖርም ሁሉም የበሰለና ለቱሪዝም ገበያ መቅረብ እንዲችል የተደረገ አለመሆኑን ያነሳሉ።

መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ (ሃላላ ኬላ) እና ሌሎችም የመዳረሻ ልማት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መስራቱንና እየሰራ አንደሆነም ጠቅሰው፣ የሲዳማ ክልልም ከላይ የተነሳውን የቱሪዝም ገበያ ክፍተት ለመሙላት በማሰብ በመዳረሻ ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ እንደሆነ የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊው ይገልፃሉ። የክልሉ መንግሥትም በእነዚህ የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ያስረዳሉ።

‹‹ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተደራጀ ወዲህ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማበልፀግ ላይ ነው›› የሚሉት አቶ አበበ፤ ቀደም ሲል በይርጋለም፣ ወንዶ ገነትና ሀዋሳ ላይ የተወሰነውን የቱሪዝም እንቅስቃሴና የመስህብ ስፍራዎችን ወደ መዳረሻነት የመቀየር ስራ አሁን ወደሌሎችም ቦታዎችም የማስፋፋት ተግባሩ መጠናከሩን ይጠቅሳሉ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከዘርፉ ያለው ተጠቃሚነት ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ገልፀው፣ አሁን ላይ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት የቱሪስቱን ቆይታ አራዝሞ የሚያወጣውን ወጪ ከፍ ለማድረግ፣ የቱሪስቱን እርካታ ለመጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

የመዳረሻ ልማት በባህሪው ጊዜ የሚወስድ ነው የሚሉት የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊው፣ ባሳለፍነው ዓመት ጋራምባ የማህበረሰብ አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ማልማት ውስጥ መገባቱን ይጠቅሳሉ። የመዳረሻ ልማቱ ሶስት ወረዳዎችን የሚያቅፍና ጋራምባ የሚባለውን ተራራ መሰረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማልማቱ ስራዎችም በታቀደው መሰረት እየሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሁን ሁለተኛው ክፍል /phase/ ላይ መድረሱንም ገልፀው፣ ከሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ውስጥም ኢኮ ቱሪዝም ሎጅ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል። ተራራውን መሰረት አድርጎ ለሚካሄድ ጉብኝትም የመወጣጫ ደረጃዎች ግንባታ አንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ ጎብኚዎች ድንን የሚተክሉባቸው ስፍራዎች /camping site/ በፕሮጀክቶቹ ከሚገነቡት መካከል ጥቀቶቹ እንደሆኑ ይናገራሉ።

በመዳረሻ ልማት በተገነባበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ማህበረሰብ ለቱሪስቶች አገልግሎት በመስጠት ገቢ ማግኘት እንዲችል የማደራጀት ስራ እንደሚሰራ የተናገሩት የቱሪዝም ዘርፍ የቢሮ ሀላፊው፤ ለዚህም ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ሰዎችን የማሰልጠን እንዲሁም በቁሳቁስና መሰል መሰረታዊ አገልግሎት መስጫዎችን በማሟላት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገልፃሉ። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በቱሪዝም ገበያ ልማቱ ላይ ለክልሉም ሆነ ለአገር ትልቅ አስተዋፆ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ማለት መስህብ ያለበት፣ ማህበረሰቡን ያቀፈና ለቱሪስቶች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ ሁኔታ የሚገኙበት እንደሆነ ያብራሩት አቶ አበበ ፣ ከዚህ ቀደም መስህብ ልማት ላይ ብቻ ትኩረት ይደረግ እንደነበር ይናገራሉ። ይህ ብቻውን በገበያ ልማቱ ላይ ውጤት አለማምጣቱንና መዳረሻ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ማስፈለጉን ይገልፃሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ስር ከሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶች አንዱ ሎክ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ነው። ይህንን ፓርክ ወደ መዳረሻነት ለመቀየር እና ማህበረሰቡንም የዚያው አካል ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። በልማቱም 29 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብር በመመደብ በፓርኩ ውስጥ ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሳፋሪ ሎጅ አባያ ሀይቅ ዳርቻ ጎን እየተገነባ ይገኛል። ይህንን የመዳረሻ ልማት ተከትሎ የግል ባለሃብቶችም በፓርኩ መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ልማቶች ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል።

‹‹የቱሪዝም የገበያ ድርሻው የተዳከመበት ምክንያት በመስህብ ስፍራዎቹ አካባቢ ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አሊያም የለማ መዳረሻ ባለመኖሩ ነው›› የሚሉት የቱሪዝም ዘርፍ የቢሮ ሀላፊው፤ ይህንን ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ባለሃብቱም ደፍሮ እንዲገባ ለማስቻል የክልሉ መንግሥት ምሳሌ በሚሆኑ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሆነ ይገልፃሉ። በሀዋሳና አካባቢው፣ በወንዶ ገነት፣ ይርጋለም እና መሰል ቀደም ሲል የሚታወቁ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይም እንዲሁ እሴት የመጨመር ተግባር እንደሚሰራም ያስረዳሉ።

በ2016 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ክልሉ ሶስት ሚሊዮን ቱሪስቶች እንደገቡ የሚናገሩት አቶ አበበ፤ ከእነዚህ ወስጥ 25 ሺህ የሚደርሱት የውጪ ዜጎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል። ቀሪዎቹ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መሆናቸውን ተናግረው፣ በቱሪዝም ዘርፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴም አንድ ነጥብ ስድስት በሊዮን ብር ከዘርፉ ገቢ መገኘቱን ይገልፃሉ። ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲነፃፀርም 20 በመቶ የሚሆን ጭማሪ ማሳየቱን ያስረዳሉ። የቱሪዝም ምርትና አገልግሎትን በጥራትና በብዛት ለቱሪስቱ ማዳረስ ከተቻለ ማህበረሰቡንም ሆነ አገርን የሚጠቅም የኢኮኖሚ አቅም መገንባት እንደሚቻልም አቶ አበበ አስታውቀዋል።

አቶ አበበ የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ባለሙያዎችን ጥራት ለማሻሻል ቢሮው ከትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ትብብርም ጥራት ያላቸው የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ያመለክታሉ። የሀዋሳ፣ ጎንደር፣ አርባ ምንጭ እንዲሁም የቱሪዝም ትምህርትን የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋርም አንዲሁ ባለሙያዎችን እያበቁ እንደሚገኙ ተናግረው፣ እነዚህ ባለሙያዎች በክልሉ መዳረሻዎች ላይ እንደሚሰማሩ ይናገራሉ። ይህም በዘርፉ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የቱሪስቱን እርካታ ለመጨመር መልካም ጅምር መሆኑንም አስታውቀዋል።

አቶ አበበ እንደገለጹት፤ በሲዳማ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብ በዲያስፖራ ኤጀንሲ በኩል በርካታ ስራዎች ይሰራሉ። በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በየአገሩ ያሉ ዲፕሎማቶችና ቆንፅላ ፅህፈት ቤቶች በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ አልሚዎችን ይጋብዛሉ፤ የሲዳማ ከልልም የዚህ አካል ነው። የክልሉ መንግሥትም እነዚህን አደረጃጀቶች በመጠቀም በክልሉ የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን፣ የመስህብ ስፍራዎችንና በዘርፉ ስለተመቻቸው እድል የሚገልፁ ማብራሪያዎችን በመስጠጥ የማስተዋወቅ ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

የአገር ውስጥ አልሚዎችም በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ፍላጎት እያሳዩና እየተሳተፉ ነው የሚሉት የቱሪዝም ዘርፍ ሀላፊው፣ ለአብነትም የስምጥ ሸለቆው ግዙፍ ሀይቅ በሆነው ሎክ አባያ አካባቢ በፓርክ ውስጥ በአባያ ሃይቅ ዳርቻ ለኢንቨስትመንት የሚሆን የሚለማ ቦታ በመሬት ባንክ መዘጋጀቱን ይናገራሉ። ይህ ስፍራ በርካታ ባለሀብቶችን ማስተናገድ እንደሚችል ገልፀው፣ ሰፊ ሃይቅ፣ ፍል ውሃ እና ሌሎች መስህቦችም እንዳሉትና ለአልሚዎች ምቹ መሆኑንም አመልክተዋል። የክልሉ መንግሥትም የባለሃብቶች ፍላጎት ከሆነ እና ለማልማት ዝግጁ ከሆኑ ይህንን ቦታ ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል። በሀዋሳ፣ በወንዶ ገነትና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ መስህቦች ላይ የኢንቨስትመንት ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

ሲዳማ ክልልን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከጎበኙት ሶስት ሚሊዮን ቱሪስቶች ውስጥ 25 ሺህ ብቻ የሚሆኑት የውጪ ዜጎች ናቸው ሲሉ ጠቅሰው፣ በንፅፅር ቁጥሩ አነስተኛ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል ብለዋል። የቱሪስት ፍሰቱ አነስተኛ የሆነው መዳረሻዎችን በበቂ ሁኔታ ካለማስተዋወቅ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነም ተናግረው፣ የቱሪስት ጉብኝት መርሀ ግብር የሚያሰናዱትና የሚሸጡት ዓለም አቀፍ ቱር ኦፕሬተሮች በሚሰጡት የተሳሳተ ምክረ ሀሳብና አገራት በየጊዜው በሚሰጡት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል።

በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሲዳማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅና ቱሪስቱን የመሳብ ጉዳይ አሁንም በቂ አለመሆኑን አቶ አበበ አስገንዝበዋል። ይህንን ተከትሎ የክልሉም ሆኑ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች በየዓመቱ በሚካሄዱ የሆቴልና ቱሪዝም ፌስቲቫሎች ላይ የዘርፉን መስህቦችና አገልግሎቶች እያስተዋወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ መድረኮችን እና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅም መዳረሻዎቹን የማስተዋወቁ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ከልሉ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You