ኛዋርጋ ቼንግ በጋምቤላ ከተማ ራስ ጎበና ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። እርሷ በምትኖርበት የጋምቤላ መንደር ያሉ አብሮአደጎቿ አብዛኛዎቹ የጋምቤላ ልጆች ናቸው። ነገርግን ቢያንስ ከአማራ እና ከትግራይ ክልል የመጡ ወዳጆች አሏት። ይሁን እንጂ ከሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ከመጡ ወገኖቿ ጋር አብራ የማደግ እድል አላጋጠማትም።
አሁን በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ስላመጣች 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ለማክበር አዲስ አበባ እንድትሄድ ተመርጣለች። ክልሉን ወክለው ለበዓሉ ከተመረጡ ተማሪዎች መካከል መሆኗ ሲነገራት በደስታ ዘላለች። አዲስ አበባን በስም ነው የምታውቃት። ከአራቱም የኢትዮጵያ ጫፎች ወደከተማዋ የሚነጉዱ ዜጎች በመዲናዋ በአብሮነት ስሜት እንደሚኖሩባት በመገናኛ ብዙሃን ስትሰማ ቆይታለች። አሁን ደግሞ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ብሎም ከምዕራብ እስከምስራቁ የአገሯ ክፍል ያሉ ወጣቶችን በምናቧ እየሳለች ነው። አዲስ የህይወት መነጸር የምትሞክርበት ወቅት መሆኑ ገብቷታል። ከተለያዩ ብሔርብሔረሰቦች ከመጡ የእድሜ እኩዮቿ ጋር ልትገናኝ ነው።
በመጀመሪያ የአዲስ አበባን ህንጻዎች እና የመንገድ ስፋት አይታ መገረሟን ታስታውሳለች። መስቀል አደባባይ ስትደርስ ደግሞ የከተማውን ባቡር ስትመለከት በግርምት መፍዘዟን ትናገራለች። ይህ ሁሉ ሁነት ካለፈ በኋላ ደግሞ ብሔራቸውን ወክለው የመጡ ልጆችን የምታገኝበት ሰዓት ደረሰ። የአካባቢዋን ባህል በሚያንጸባርቅ የጋምቤላን ሙቀት በሚያስታውስ አለባበስ አጊጣ በአዲስ አበባው መዘጋጃ አዳራሽ የመጀመሪያውን ትውውቅ ጀመረች። ከአዳራሹ ቆይታ በኋላ ደግሞ ጉዞ ወደ እንጦጦ ታሪካዊው ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ነበር።
እኛም በዛው ተገኝተን ”እንዴት ነው ጉብኝቱ” አልናት። ”የአንዱ ቀለም ቀይ የአንዱ ጥቁር የሌላው ደግሞ ጠይም ነው። አለባበሱም ሆነ አመጋገቡ እንደየ አካባቢው ይለያያል።
የታዘብኩት ግን ሁሉም በአንድነት በፍቅር ሲገኝ እንኳንም ኢትዮጵያዊ ሆንኩኝ የሚያስብል ስሜት ይፈጥራል። አንድ ጊዜ እጃችንን ተያይዘን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ሲያሰሙ የአብሮነት እጆች በጋራ እንደሚሰሩት ግንብ የጥንካሬ መንፈስ ይሰጣል።” የሚል መልስ ሰጠችኝ።
ተማሪ ኛዋርጋ እንደምትናገረው፤ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ተማሪዎች ሲገናኙ ልክ የተጠፋፋ ቤተሰብ ያህል ፍቅር ተለዋውጠዋል። ሁሉም ተማሪ ወደየመንደሩ መመለሱ ደግሞ ስለማይቀር የዛን ጊዜ አብሮነታችንን ለተቀሩት ልጆች ማስረዳት ያስፈልጋል። ”እኔም ጋምቤላ ስደርስ ለጓደኞቼም ሆነ ለአዛውንቶች ስለሱርማውም ሆነ ስለኦሮሞው ብሎም ስለሌላው በሔረሰብ ልጆች እያነሳሁ አንድነታችንን ይበልጥ እንዲያወቁት አደርጋለሁ። ሁሌም ተመልሶ ቢመጣ ያልኩትን ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፤ በቀጣይም የተለያዩ ተማሪዎች እየተገናኙ የቀጣዩን ትውልድ ግንኙነት እንዲያጠናክሩ መደረግ ይኖርበታል” ትላለች።
ተማሪ ሾማ አቻው ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዳሰነች የካብሲያ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። የብሔር ብሔረሰብ በዓሉን ለማክበር ነው አዲስ አበባ የተገኘችው። እርሷ እንደምትለው፤ ያልተዋወቁ ሰዎች በትልቅነት እድሜያቸው ሲገናኙ ልክ እንደወጣቶች በፍጥነት ሊግባቡ አይችሉም። ተማሪዎች ግን በልጅነታቸው ሲገናኙ በቶሎ ተግባብተው ለቀሪው ዘመናቸውም ስንቅ የሚሆን ፍቅር ይዘው ነው ወደየመጡበት የሚመለሱት። በመሆኑም በዓሉ ሲከበር ጭፈራ እና ሙዚቃው ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የተማሪዎችን ግንኙነት ማጠናከሩ ተገቢ አካሄድ ነው። በመሆኑም በዓሉ ቢያልፍም ከየእያንዳንዱ የገጠር አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎች ከሌላው አካባቢ ከመጡ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር የባህል እና የዕውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ ቀጣይነት ያለው አሰራር ያስፈልጋል።
እርሷ እንደምትለው፤ የደቡቡ ተማሪ የአፋሩ ተማሪ አኗኗር ሲያውቅ፣ አፋሩ ደግሞ የሶማሌውን ወይም የቤኒሻንጉሉን ሲተዋወቅ ሌላም ቦታ ወገኖች እንዳሉት ያስባል። ይህ ደግሞ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል። ትውውቁ ለሌሎች ተማሪዎችም የሚተርፍ ታሪክ ያለው በመሆኑ በደስታም ሆነ በችግር ወቅት የመረዳዳትን ባህል በኢትዮጵያ ልጆች ላይ ያጠናክራል።
ከ”አባቴ ለእኔ ሲነግረኝ” በማለት ትውስታዋን እነደምትናገረው፤ በጣሊያንም ሆነ በአድዋ ጦርነት ወቅት ማንም አካባቢውን ብቻ ያሰበ አልነበረም። የደቡብ ኦሞ ሰው ትግራይ ሄዶ ለአገሩ ክብር ተዋግቷል። ምክንያቱም ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ያለው አገር በሰላም ሲኖር ነው ሁሉም ወደትምህርቱ እና ወደስራው ተረጋግቶ ህይወቱን የሚቀጥለው። አሁንም የተለያዩ ብሔሮች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ መደረጉ ይበልጥ መረዳዳቱን ያጎላዋል።
”ዛሬ ያገኘሁት የአማራው ተማሪ ወይም የትግራዩ ልጅ ነገ ላይ ችግር ቢያጋጥመው ፈጥኜ የምደርሰው እኔ ነኝ። ምክንያቱም ወገን ማለት አንድ አካባቢ ላይ ያለ ዘመድ ብቻ እንዳልሆነ የአብሮነት ቆይታችን አስረድቶኛል። ወደመጣሁበት አካባቢ ስመለስም የኢትዮጵያ ልጆች ምን ያህል አንድነታችን ውበታችን መሆኑን ስሰብክ እኖራለሁ።” ትላለች ተማሪ ሾማ።
ሔኖክ አለማየሁ ደግሞ በባሌ ጊንር የመኩሪያ ተሰማ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እርሱ እንደሚለው፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ለበዓሉ የመጡ ተማሪዎች ሰሞኑን አንድ ላይ ውለዋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ እንዲቀራረቡ ረድቷቸዋል።ይህ ቅርርብ ከአምስት እና አስር ዓመታት በኋላ ፍሬ አፍርቶ እርስ በእርስ የሚጠያየቁበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል።
ተማሪ ሔኖክ እንደሚለው፤ ልጆች ምንጊዜም ያሳዩዋቸውን ነው የሚከተሉት። ጥላቻን ካስተማሩዋቸው መጥፎ ትውልድ ይሆናሉ። መልካሙንም ካሳዩዋቸው ህይወታቸው ንም ለጓደኞቻቸው አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ። የአሁኑ የተማሪዎች ግንኙነት በጥሩ ጎኑ የሚታይ ጅምር ነው። አሁን ላይ በሰማንያ እና ዘጠና ተማሪዎች የተጀመረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ነገ በአለት ላይ እንደተገነባ ቤት በአገር አንድነት ላይ ጠንካራ መሰረት መፍጠር የሚችል ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን በማስመል ከት ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ 140 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎችን ባለፈው ዓርብ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፤ ተማሪዎች ከመገለልና ልዩነትን ከማቀንቀን ይልቅ ሰፋ ያለ አመለካከትን፤ የእርቅን፤ የአንድነትን እና የትብብርን እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው ጥበብ፤ ቋንቋ፤ ማንነት እና አገር በቀል ዕውቀት ባለቤት መሆናቸውን ከግምት ማስገባት ታላቅ ትምህርት እና ግንዛቤ ለመውሰድ ዕድል እንደሚሰጥ በማሰብ ሰብዓዊነትን እንዲሹም ለተማሪዎች መክረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 1/2011
ጌትነት ተስፋማርያም